የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሳትፎ ከእነ ግለቱ እንዲቀጥል

 

ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብቷን መሠረት ከግብርና ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራዕይ ሰንቃ ለተግባራዊነቱ መሥራት ከጀመረች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዘመናት የተጀመረውን ይህን እቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ በሚያስችሉ ተግባሮች ላይ በስፋት ሠርታለች፤ እየሠራችም ትገኛለች፡፡

ለእዚህም በመንግሥት ደረጃ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሠማራት የተከናወነውን ተግባር በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የስኳር ኢንዱስትሪዎች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በርካታ የኃይል ማመንጫዎች ላይ ለመሥራት ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱ ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ የማዳበሪያ ፋብሪካው ጉዳይ የሀገር አንጡራ ሀብት ይዞ ቢጠፋም፣ የስኳር ፋብሪካዎቹም እንደታሰበው ባይሆኑም፣ የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታውም የሆነ ርቀት ተጉዞ ቢቆምም፣ ለእነዚህ ሁሉ ዋና መሠረት እንደሚሆን የሚጠበቀውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በመገንባት በኩል ጥሩ ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ሀገሪቱ የዘርፉን አስፈላጊነት በማመን በዘርፍ መሥራቷን ግን አጠናክራ ከመቀጠል ውጪ ወደሁዋላ ያለችበት ጊዜ የለም፡፡ እንደ ሀገር የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውም በዘርፉ የመሠራቱ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ማድረግ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሚፈጸም ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል። በእዚህም አንዳንድ ለውጦች መታየት መጀመራቸውም እየተገለጸ ነው።

አንዳንድ የግብርናው ዘርፍ ኃላፊዎች እንዳሉትም፤ ግብርናው በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አሁንም የመሪነቱን ስፍራ ቢይዝም፣ ቀደም ሲል ይይዝ ከነበረው ስፍራ እየቀነሰ መምጣቱን ይገልጻሉ፤ የአገልግሎቱና ኢንዱስትሪው ዘርፎች የግብርናውን ሸክም መቀነስ ጀምረዋል ነው የሚሉት ኃላፊዎቹ፤ ይህም እንደ ሀገር የተያዘው እቅድ ለውጥ ማሳየት መጀመሩን ያመለክታል። የሜካናይዜሽን እየተስፋፋ መምጣትም ሌላው ሲጠቀስ የሚሰማ ነው፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈልገውን የመሬት፣ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች ለማሟላት፣ ለዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግና ለመሳሰሉት ተግባሮች ትኩረት በመስጠት ብዙ ተሠርቷል። ይሁንና ባለሀብቱ ወደ ዘርፉ ሲመጣ እነዚህን ፍላጎቶቹን መመለስ ላይ ግን ችግር ይስተዋል ነበር፡፡ በብዙ ሥራ የመጣን ባለሀብት በአሠራር ችግር ማጣት ወይም ማስደንገጥ ዘርፉን ማድረስ በሚፈለግበት ደረጃ ላይ ለማድረስ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳርፍም ተብሎ አይወሰድም፡፡

መንግሥት ቆይቶም ቢሆን ይህን ችግር ለመፍታት ተንቀሳቀሷል፡፡ እነዚህን አቅርቦቶች በማዘጋጀት በኩል እንደ ሀገር ይታይ የነበረውን ችግር ለመፍታት በተከናወኑ ተግባሮች የሚታዩ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት በተለይ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ የተከናወነው ተግባር በዘርፉ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባሮች የሚጠቀሰው ነው ማለት ይቻላል፡፡

በግሉ ዘርፍ ተገንብተዋል የሚባሉትን ሳይጨምር በሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተገንብተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱ በተለይ የውጭ ባለሀብቶች መሬትና መሠረተ ልማት ለማግኘት ወዘተ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር ቀንሶታል።

የውጭ ባለሀብቶች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ፈጽመው የለማ ሼድ በመረከብ ማሸነሪዎቻቸውን አምጥተው በመትከል በቀጥታ ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ፈጥሯል፤ አለበዚያም የለማ መሬት ባለበት በዚህ ስፍራ ገብተው ኢንዱስትሪያቸው የሚፈልገውን አይነት መሠረተ ልማት ገንብተው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የለማ መሬትና ሼድ ብቻ አይደለም ያላቸው፡፡ እንደ ባንክ፣ ጉሙሩክና የመሳሰሉት ተቋማት ቅርንጫፎችም በዚያ የሚገኙባቸው በመሆናቸው አገልግሎቶችን ፍለጋ ባለሀብቶቹ ሊባክንባቸው የሚችለውን ጊዜና ሀብት የሚያስቀር አሠራር ያላቸውም ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ይሰማ የነበረውን ቅሬታም መፍታት አስችሏል፡፡

በእነዚህ መሠረተ ልማቶች በሚገባ በተሟላላቸው ስፍራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆኑ የአልባሳት አምራቾች ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ በተጣለው ማዕቀብ የተነሳ አንዳንዶች ልማቱን በሚፈለገው መልኩ ማስኬድ ባይችሉም አንዳንዶቹ ትተው የወጡበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ዛሬም ድረስ ፓርኮቹ በእጅጉ ተፈላጊ ሆነዋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፓርኮቹ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ለሚመጡና ምርቶቻቸውንም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ገበያም አቅምም ያላቸውን የውጭ ባለሀብቶች እንዲያስተናግዱ ለማድረግ ነበር የሚሠራው፡ ሀገር ከእነዚህ ባለሀብቶች የምትጠቀመው ይዘው ከሚመጡትና በቀጣይም ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ ብቻ አይደለም፡ እውቀታቸው፣ ልምዳቸውና ይዘው የሚመጡት ቴክኖሎጂም እንደ ሀገር የሚፈለግና የኛን የዘርፉን ባለሙያዎች እንዲሁም ባለሀብቶች ለማፍራት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለውጭ ባለሀብቶች ቅድሚያ መሰጠቱ ትክክልም ተገቢም ነው፡፡

ይህ ሀሳብ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአጎዋ እስከ ታገደችበት ጊዜ ድረስም በርካታ ስመ ጥር የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ገብተው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስችለዋል። ሌሎች በርካቶችም ሼዶችን በመያዝ ወደ ሥራ ለመሠማራት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ በስፋት ገብተው የሚሠሩበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶቹ ወደ ፓርኮቹ እየገቡ ናቸው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽንን መረጃ ዋቢ ያደረገው ይህ ጋዜጣ ይዞት የወጣ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ኮርፖሬሽኑ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ሥራዎች ላይ የሚሠማሩ ባለሃብቶችን ቁጥር ለመጨመርና ከኢንቨስተሮች ጋር ያለውን ትስስር ለማሻሻል አዳዲስ የሪፎርም ተግባራትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተግባራትም ብዙ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹና ወደ ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲገቡ ማድረግ ችለዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን የማነቃቃት፣ የማበረታታትና ወደ አምራች ዘርፉ ገብቶ ውጤታማ ሥራዎችን እንዲሠራ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ አምራች ዘርፉ እንዳይገቡ መሰናክል የነበሩ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በቅርቡ ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለመሥራት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት ካደረጉት አስራ አንድ ኩባንያዎች መካከል አብዛኞቹ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ በ2016 ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ አምራቾች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው፡፡

በ2015 እና 2016 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲነቃቁ፣ ባለሃብቶቹ ያሉባቸውን የፋይናንስና ሌሎች ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባራት ተከናውነዋል። በመሆኑም በ2015 እና ዘንድሮ ከተመዘገቡት ባለሃብቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ መረጃዎች ሲታሰቡ የሀገር ውስጥ አምራቾች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ የተሰጠው ትኩረት ውጤት እያሳየ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የግሉ ዘርፍ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ባሉት የአምራች ኢንዱስትሪው ሼዶች እንዲሁም ራሱ በየክልሉ በሚገነባቸው ፋብሪካዎች የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሳታፊነቱ እየጨመረ ለመምጣቱ ከየክልሎቹና ከተሞቻቸው፣ ዞኖቻቸው የሚመጡ መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣቸው በርካታ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ካሉበት ሁኔታም መረዳት የሚቻለው የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እያሳየ ያለው ተሳትፎና እያከናወነ ያለው እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡

የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ እዚህ ደረጃ ለማድረስ ሀገሪቱ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በወታደራዊው አገዛዝ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በአጠቃላይ ክፉኛ መመታቱ ይታወቃል፤ በኢሕአዴግ መንግሥት የማንሰራራት ሁኔታ ቢታይበትም፣ በመሬትና በመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳቢያ በእጅጉ ተፈትኗል፡፡

በወቅቱ የነበረው መንግሥት የግሉ ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እንዲሠማራ ጽኑ ፍላጎት ቢኖረውም፣ የግሉ ዘርፍ ከለተመደው የንግድና ሕንጻ ልማት ውጪ በኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ በኩል የሚታየው አልነበረውም፡፡ የቆየባቸው የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች ዘርፎች በቀላሉ የሚከበርባቸው መሆናቸው፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የዘርፉ እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ልምድ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑ በወቅቱ ለነበረው የግል ዘርፍ በዚህ ዘርፍ መሰማራት አስፈሪ ነበር፡፡

ይህን አመለካከት ለመቀየርና ስጋቱን ለማስወገድም ሀገሪቱ ብዙ ሠርታለች፡፡ የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው ቢሰማራ ራሱንም ሀገርንም እንደሚጠቅም በማመን፣ የግሉ ዘርፍም እንዲያምን በማድረግ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ብዙ ሠርቷል፤ ለሀገርም ለባለሀብቱም በዘላቂነት የሚጠቅመው የአምራች ዘርፉ መሆኑን ብቻ አልነበረም ሲያስገነዝብ የነበረው፤ ማበረታቻዎችንም በማድረግ ባለሀብቱን ከንግድ ወደ አምራች ዘርፉ ለማሳብ ተሞክሯል፡፡

በመንግሥት እጅ ውስጥ የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ለግሉ ዘርፍ በማዞር የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት ተሠርቷል፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ አይደፍራቸውም ተብለው በሚታሰቡት እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ባሉት ላይ በማተኮር የግሉ ዘርፍ እንዲነቃቃ ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህም ለግሉ ዘርፍ መነቃቃት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው የሚሠማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መጠን እየጨመረ መምጣት የቻለው ሀገሪቱ ለዘርፉ የሰጠችውን ይህን ሁሉ ትኩረት ተከትሎ በተከናወኑ በእነዚህ ሁሉ በርካታ ሥራዎች ነው፡፡ ይህ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የአምራች ዘርፉ ተሳትፎ እየተጠናከረ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

እነዚህ በአምራች ኢንዱስትሪው ተሠማርተው እየሠሩ ያሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ምርታማ በሚሆኑበት ላይ በትኩረት መሠራት ይኖርበታል፤ እነዚህ ባለሀብቶች በቀጣይ በአምራች ኢንዱስትሪው ለሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ፈር ቀዳጅ እንደመሆናቸው፣ ለእነሱ የሚደረገው ድጋፍ ከእነሱ የሚገኘው ውጤት ባለሀብቶቹ በዘርፉ እንዲቆዩ፣ ሌሎችን ባለሀብቶችንም እንዲከተሏቸው በማድረግ በኩል ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡

ባለሀብቶቹ ብዙዎች የሚፈሩትን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ደፍረው የገቡ እንደመሆናቸው እንደ ዓይን ብሌን መታየት ያለባቸውና ገና በዙ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባም ናቸው፡፡ ዘርፉ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በኃይል አቅርቦት፣ በገበያ ችግር ተደናግጦ ከዘርፉ እንዳይወጣ ማድረግ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ብዙ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው፡፡ ንቅናቄው ከጦርነትና ግጭት ከውጭ ጫና ጋር በተያያዘ ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ያስቻለ ነው፡፡ ይህ የንቅናቄው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ተኪ ምርትን ዋና ጉዳይዋ አርጋ አተኩራ የምትሠራ ሀገር፣ ለውጭ ገበያ ማምረትን ሌላው ዋና ጉዳይዋ አርጋ የምትሠራ ሀገር ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ትኩረት መሰጠቷን አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል። ይህን በብዙ ዓመታት ድካም የመጣ የአምራች ዘርፉን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ የመጨመር ውጤት ይበልጥ እንዲጨምር ማድረግ ላይ መሠራት ይኖርበታል፡፡

በዚህ ተሳትፎ መጨመር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችል አንድም አይነት ተግዳሮት እንዳይኖር፣ ቢኖሮም ፈጥኖ ለማቃለል መሠራት ይኖርበታል፡፡ እስከ አሁን የተደረገውም ይሄው ነው። መንግሥት ዘርፉ በታሰበው ልክ አልሆነም ብሎ አልተወውም፤ ከዚህም ይልቅ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ዘርፉን መደገፉን ነው የቀጠለው፡፡

አሁንም ይሄው ሥራ መጠናከር ይኖርበታል። የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለግሉ ዘርፍ ለማቅረብ የተከናወነው ተግባር አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ሆኖ፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የባለሀብቶች ፍሰት ታሳቢ ያደረገ ግንባታም ሆነ ዝግጅት አለመኖሩ ያሳስባል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ባላውቅም፣ የኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የሼዶች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እያመለከቱ ናቸው፡፡ ይህ ፍላጎት ከእስከ አሁኑም በላይ ሊጨመር እንደሚችል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመግባት ሁኔታ ይህን ፍሰት ታሳቢ አርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለሀብቶቹ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየመጡ ያሉት ሀገር በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በሆነችበት በአሁኑ ወቅት ነው። በግብዓት በውጭ ምንዛሪ እንዲሁም ከሠላምና ደህንነት ጋር ተያይዞ በርካታ ፈተናዎች በሀገሪቱ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

ሀገር በእዚህ ፈተና ውስጥ አትቀጥልም፤ መንግሥት እያከናወነ ባላቸው ተግባሮች ተግዳሮቶቹ ሊወገዱ የሠላምና ፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሠላም ደኅንነት ሊሰፍን ይችላል፡፡ ያኔ ደግሞ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው በተለይም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመጡት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በእጅጉ ሊጨምር ይችላል፡፡

ይህን ጥያቄ የሚመልስ ሥራ ከወዲሁ መሠራት ይኖርበታል፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለው ቦታ ውስን እየሆነ ባለበት ሁኔታ የባለሀብቶችን ጥያቄ መመለስና ዘርፉን አጠናክሮ ማስቀጠል ይከብዳል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መረጃ እንደጠቆመው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ 177 ሼዶች መካከል አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን እየጠበቁ ያሉት 20 ብቻ ናቸው፤ 157ቱ ሼዶች በባለሃብቶች ተይዘዋል፡፡ አምስት ፓርኮች (አዳማ፣ ቦሌ ለሚ፣ አዲስ፣ ሰመራ እና ድሬዳዋ (የማኑፋክቸሪንግ ክፍሉ) በመሙላታቸው አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ አይችሉም፡፡

የኮርፖሬሽኑ ሼዶች በባለሀብቶች መያዛቸው አንድ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብተው ባለሀብት ሳያገኙ የቀሩ ሀገሮች እንዳሉ ከሚገለጸው አኳያ ሲታይ ይህ አፈጻጸም ከፍተኛ ተብሎ የሚያዝ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣይ የሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል ሼድ የሌላቸው መሆኑ በኢንዱስትሪ ልማቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳርፍም ተብሎ አይወሰድም፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከወራት በፊት በወጣው መረጃ መሠረት በርካታ ሼዶችን እንደሚገነባ ጠቁሞ ነበር፡፡ ሼዶቹን ለመገንባት አሁን መንቀሳቀስ ቢጀምር እንኳ በቅርቡ ፓርኮቹን ሊፈልጉ የሚችሉ ባለሀብቶችን ማስናገድ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በሌላ መረጃ መንግሥት ፓርኮችን ለመገንባት ሀሳቡ እንደሌለው እየተገለጸ ነው፡፡ በቀጣይ ሊሆን የሚችለው የግሉ ዘርፍ ፓርኮቹን እየገነባ ለባለሀብቶች የሚያቀርብበት መንገድ መሆኑም ተመልክቷል። በግሉ ዘርፍ በኩል ግንባታዎች እንደሚካሄዱ የሚወጡ መረጃዎች የነበሩ ከመሆናቸው ውጪ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የቻይና ኩባንያ በዱከም ከገነባው ውጪ የኢንዱስትሪ ፓርክ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡

መንግሥት ፓርኮቹ በግሉ ዘርፍ እንዲገነቡ አቅጣጫ አስቀምጦ ከሆነ ጥሩ ነው፤ የግል ዘርፉ ይገነባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የወደፊቱን እንጂ በቅርቡ ሊከሰት የሚችለውን ፍላጎት ይመልሱታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለሀብቶች ለፓርኮቹ ያላቸው ፍላጎት ሲታይ ፓርኮቹ ልማት ላይ ፈጥኖ መሥራትን የግድ ይላል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ብዙ ሀብት ሊፈልግ ይችላል፡፡ እንደ ሀገር ይህን ማድረግ የሚቻል ላይሆን ቢችልም፣ ሊኖር ከሚችለው ፍላጎት አኳያ ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቀው እንዳለ ሆኖ የኢንዱስትሪ ልማቱ የሚጠይቀውን ይህን መሰረተ ልማት ለመገንባቱ ሥራ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ የግሉን ዘርፍ የአምራች ዘርፍ ተሳትፎና ውጤታማነት ከእነግለቱ መጠበቅ ይቻላል፡፡

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You