የአንጋፋዎቹ ምክር ለልጆች

ሰላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁልን? ትምህርት፣ ጥናት እንዴት ነው? እየበረታችሁልን ነው? ጎበዞች በርቱ እሺ። ልጆችዬ፣ እናንተ ነገ ጥሩ ሰው እንድትሆኑ፤ እንዲሁም በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት እንድታስመዘግቡ እና ሀገራችሁን የምታኮሩ ዜጎች እንድትሆኑ ሁሉም ሰው መልካሙን ሁሉ እንደሚመኝላችሁ ትገነዘባላችሁ ብለን እናስባለን። መመኘት ብቻ አይደለም፤ ስትጎብዙ ‹‹ቀጥሉበት›› ስታጠፉ እና ስትሰንፉ ደግሞ ከስህተታችሁ እንድትማሩ የሚመክሯችሁ እና የሚቆጧችሁ ለእናንተ ብለው እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? በጣም ጥሩ።

ስለዚህም ልጆችዬ ከዚህ ቀደም ልጆችን በተመለከተ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ ለእናንተ መልካም ምኞታቸውን እና ምክራቸውን ካስተላለፉ አንጋፋ እና ታዋቂ ሰዎች መካከል ውስጥ ያስተላለፉላችሁን መልዕክት እናቀርብላችኋለን። በተጨማሪም ስለ እነርሱ በጥቂቱ እንነግራችኋለን።

ልጆችዬ፣ የክብር ዶክተር ዳዊት ይፍሩን ታውቋችኋላችሁ? ለማታውቋቸው እንግዲያውስ እናስተዋውቃችሁ። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ ዐሻራ የጣሉ ናቸው። የሙዚቃ ባለሞያው የክብር ዶክተር ዳዊት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የሙዚቀኞች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ። የእርሳቸው ምክርም፡-

«በተለያዩ መድረኮች ላይ ጥሩ ሥራ በመሥራት የሚሸለሙ ልጆች አሉ አይደል? ስለዚህም ልጆች እንደ እነርሱ ጎበዝ መሆን አለባችሁ።»

የሚል ነው። ለወደፊት የምትመኙት እና መሆን የምትፈልጉት ደረጃ ላይ ለመድረስም ከፍተኛ ጥረት እና ከፍተኛ የሆነ ልምምድ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

‹‹የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ጥረት እና ብዙ መሥራት እንዳለባችሁ እንድትገነዘቡ አደራ እላለሁ፡››

ሲሉም ነው ለእናንተ መልካሙን ምክራቸውን የለገሱት።

አርቲስት፣ መምህር እና ሠዓሊ ጋሽ አክሊሉ መንግሥቱ ብዙዎች አርቲስት እና ሠዓሊ በሚለው ስያሜ ያውቋቸዋል። እርሳቸው እንደሚናገሩት ልጆች ዓይናቸው ሁልጊዜ ንጹህ ነው። ሁሌም ንጹህ ሆነው በጥሩ መንገድ እንዲያድጉ ወላጆች በአግባቡ ማሳደግ፣ መንከባከብ እና ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ ማድረግ ላይ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።

ልጆችዬ፣ ጥሩ መልዕክት ነው አይደል? ታዲያ እናንተም ጥሩ ልጅ ለመሆን ወላጆች የሚሏችሁን እንደምታዳምጡ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ወደ ጠንካራዋ ሴት እንለፍ አይደል? ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ «የሜሪጆይ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት» መሥራች ናቸው። በበጎ አድራጎት ሥራቸው ይታወቃሉ። ሴቶችን፣ አረጋውያን እና ሕፃናትን በመርዳት ከ20 ዓመት በላይ ተሻግረዋል። እርሳቸውም ለእናንተ ጥሩ መልዕክት አላቸው።

ሲስተር ዘቢደር በመጀመሪያ ደረጃ ልጆች ፈጣሪን መፍራት እንዳለባቸው ነው የሚመክሩት። ሁለተኛው ምክራቸው እናት እና አባቶቻችሁን (አሳዳጊዎቻችሁን) እንድታከብሩ በጣም አደራ ብለዋል። ሦስተኛው ምክራቸው ደግሞ ምን መሰላችሁ፣ ጎዳና ላይ ብዙ ሕፃናት ታያላችሁ አይደል? በጣም የተቸገሩ እናቶች፣ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉ ታዳጊዎች፣ ሕክምና የማያገኙ በጣም የሚያሳዝኑ ልጆች ስላሉ፤ ለእነርሱ ልብስ በመስጠት እና የተለያዩ ድጋፎችን እንድታደርጉላቸው፤ እንዲሁም የተቸገረን ሰው መርዳት እንዳለባችሁ የሚያሳስብ ነው። ‹‹ይህንን በማድረጋችሁ ፈጣሪን ታስደስታላችሁ።›› ሲሉም መልካሙ ምክራቸውን እንካችሁ ብለዋል።

ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም መልዕክት አላቸው። ‹‹ልጆች ስለ ሀገራቸው ጠንቅቀው እንዲያውቁ በታሪክ ዙሪያ የሚጻፉ መጽሐፍትን ማንበብ ይኖርባቸዋል። ስለሀገራቸው ያላቸው ግንዛቤ ከፍ ማለት ይኖርበታል።›› በማለት ልጆች ላይ ብዙ ነገር መሥራት እንደሚገባም ጥቆማ አድርገዋል።

ልጆችዬ አንጋፋ አርቲስቶች፣ እንዲሁም በጎ አድራጊ ሰዎች እናንተ ትልቅ ቦታ እንድትደርሱ በመመኘት እና ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ያስተላለፉላችሁን ምክር ወደዳችሁት አይደል? ‹‹በሚገባ ወደነዋል።›› የሚል መልስ እንደሰጣችሁኝ ምንም ጥርጥር የለኝም። መውደድ ብቻ ሳይሆን ምክራቸውን ተግባራዊ ታደርጋላችሁ ብለን እናምናለን። ልጆችዬ፣ ምክሩ ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ወላጆች የሚጠቅም ነው ብለን እናስባለን።

ልጆችዬ፣ እንደምታውቁት በየሳምንቱ ለእናንተ የሚሆን፣ እናንተ ብታነቡት ትጠቀሙበታላችሁ ብለን ያመናቸውን ነገሮች ወደ እናንተ እናቀርባለን። እናንተም ይህን በመረዳት እንደምታነቧቸው ተስፋ እናደርጋለን። ልጆችዬ፣ በቀጣይ ሳምንት ለእናንተ የሚሆን ቆንጆ ነገር ይዘን ለመቅረብ ቃል በመግባት በዚሁ እንሰነባበት አይደል? ከመሰነባበታችን በፊት ግን የምንላችሁ አለን። ትምህርታችሁን በርትታችሁ አጥኑ። ከትምህርት ቤት ላለማርፈድ በሰዓታችሁ ተነሱ። ለትምህርት የሚሆናችሁን እንደ ደብተር፣ እርሳስ፣ ቦርሳ፣ ላጲስ እና የመሳሰሉትን የትምህርት ቁሳቁሶች አስቀድማችሁ አዘጋጁ። በእቅድ ተመሩ። በትምህርት ቤት ቆይታችሁ ደግሞ አትረብሹ። ትኩረታችሁንም ትምህርት ላይ ብቻ አድርጉ፣ እሺ ልጆች። በሉ ልጆችዬ፣ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You