ያልገባን የዓድዋ ትምህርት

በዓድዋ ድል ላይ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ምሁራን የተደረጉ ጥናቶች ፣ ምርምሮች፣ ድርሳናት፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎች፣ ተረኮች እና አካዳሚያዊ ሙግቶች፤ ዓድዋ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን ከፍ ሲልም የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን የሚተርኩ ናቸው። የዓድዋን ድል ከዚህ አንፃር ብቻ መመልከት የአሸናፊዎች ታሪክ ብቻ እንዳያደርገው እሰጋለሁ። ዳሩ ግን ታሪኩ የተሸናፊዎች፣ የቅኝ ገዥዎች፣ የተስፋፊዎች ፣ የወራሪዎች ፣ የነጮች ጭምር አድርገን ስናየው የዓድዋ ድል ከጥቁር ሕዝቦች ድል አልፎ የሰው ልጆች ታሪክ፣ ገድል ይሆናል።

ፀሐፍት የዓድዋ ዘመቻ ከወሰደው ጊዜና ከሚያካልለው የቦታ ስፋት እንዲሁም በድል ከመደምደሙ አንፃር ሲታይ የ19ኛው መ. ክ .ዘ ታላቁ ጦርነት እንደሆነ ያወሳሉ። ዓድዋን አንድ እርከን ከፍ በማድረጉ ላይ ከተግባባን፤ ይሄን የሰው ልጅ ታላቅ ታሪክ የነበሩትን መግፍኤዎች፣ መነሻዎች ፣ ውጤቶችን አክለን ትምህርቱን የዘመናዊ ኢትዮጵያ እርሾነቱንም ለጋዜጣው እንዲመጥን ቀንጨብ አድርገን እንመልከታለን።

የፈረንሳይ ቱኒዚያን የመያዝ፣ የናፒየር ዘመቻ፣ የቤልጅየሙ ንጉሥ ኮንጎን የመቆጣጠር፣ የአውሮፓውያን የተስፋፊነት ሕልም፣ የስዊዝ ካናል መገንባትን ተከትሎ የቀይ ባሕር ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከፍ ማለቱና በወቅቱ የነበረው የዘውድ ሽኩቻ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ ለመቋመጧ በመግፍኤነት ከሚጠቀሱት ሰበቦች ዋነኞቹ ናቸው። በጊዜው የንጉሥ ምኒልክ ወደዙፋኑ መቃረብ ያስደሰተው የጣሊያን ወኪል ፔትሮ ኢንቶኔል ግንኙነቱን በፊርማ ለማረጋገጥ ሚያዝያ መገባደጃ ላይ በ1881 ዓ.ም ውጫሌ ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም በቃ።

ስምምነቱ ስውር ደባ ያለው ቢሆንም ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው የባሪያ ንግድን ለማስቀረትና ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ላሰበችው የንግድ ልውውጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያገለግል ነበር። ዳሩ ግን ውሎ ሳያድር የስምምነቱ አንቀፅ 17 ውዝግብ አስነሳ። በዚህ አንቀፅ የጣሊያንኛ ቅጅ መሠረት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታደርገው በጣሊያን በኩል እንደሆነ የሚያስገድድ መሆኑ በተዘዋዋሪ ሀገሪቱን በጣሊያን ሞግዚትነት የምትተዳደር ያደርጋታል። የአማርኛው ቅጅ ግን የውጭ ግንኙነት ማድረግ ትችላለች ይላል። በስምምነቱ አንቀፅ 19 ላይ የአማርኛና የጣሊያንኛ ቅጅዎች እኩል ተቀባይነት እንዳላቸው መደንገጉ አለመግባባቱን አካረረው።

በ1887 ዓ.ም በወርሐ መስከረም በገበያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒልክ ታሪካዊውን የ “ወረ ኢሉን ” ክተት አዋጅ አስነገሩ። « …ሀገርንና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል። እኔም የሀገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም፤ እያለፍ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ፤ …» አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት፣ ከመላው ሀገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100ሺህ በላይ ወዶ ገብ የገበሬ ጦር እና 29ሺ ፈረሰኞች በኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ አልበገር ባይነት ፤ ዳርድንበሩን፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመመ። ጄነራል ባራቲየሪም ሠራዊቱን ወደ መሀል ትግሬ እንዲንቀሳቀስ ትዕዛዝ ሰጠ።

አፄ ምኒልክ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ፋሽስታዊውና ወራሪው የጣሊያን ጦር ከግዛታቸው ለቆ እንዲወጣ ቢጠይቁም፤ ጄኔራሉ አሻፈረኝ ከማለቱ ባሻገር በዕብሪት የማይሆን ቅድመ ሁኔታ ይደረድር ጀመር፤ የአፄው ጦር ትጥቅ እንዲፈታ፣ ራስ መንገሻ እንዲታሰሩ፣ መላውን ትግሬን እንዲያስረክብ እና የጣሊያንን የበላይነት እንዲቀበል ጠየቀ። በዚህም ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ እርግጥ ሆነ። ወራሪው ጣሊያን የመጀመሪያውን የሽንፈት ኩታውን በሁለት ሰዓት ውጊያ አምባላጌ ላይ ተከናነበ።

የአምባላጌው አኩሪ ድል ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው ታላቅ ፋና ወጊ ድል ቢሆንም ፤ ከወታደራዊ ስኬቱ በላይ ሥነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነበር። ኢትዮጵያውያን የአውሮፓን ጦር ድል መንሳት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት፤ የአፄ ምኒልክን ጦር የውጊያ ሞራል ያነቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭም የንጉሡን ክብር ፣ ተቀባይነት ከፍ አደረገ ። የአፄ ምኒልክ ጦር ግስጋሴውን ቀጥሎ መቀሌን ተቆጣጠረ። ይሄን ተከትሎ ስብሀትና ሀጎስ የተባሉ ለጣሊያን ያደሩ ባንዳዎች ከድተው ለንጉሡ መግባታቸው ለወራሪው አስደንጋጭ መርዶ ነበር።

የንጉሡ ጦር በወርሐ የካቲት እኩሌታ ለዓድዋ ጥቃት ዝግጁ ሆነ። የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦር ወዲና ማዶ ተፋጠጠ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደ ጦርነት የጀኔራል ባራቲየርና የሌሎች ጄኔራሎች ጦር ተሸነፈ። ሸሸ። ተፈታ። ወደ 10ሺህ የሚጠጋ የጣሊያን ጦር ሙት፣ ቁስለኛ፣ ምርኮኛ መሆኑን አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ሲያትቱ ፤ ሌሎች ደግሞ የሟቹን ቁጥር 11ሺህ ፣ የተማረከውን 4ሺህ ያደርሱታል ።

ከጄኔራሎች አርሞንዲና ዳቦርሚዳ ሲሞቱ ፤ በ1850ዎቹ የሀገራቸውን ነፃነትና አንድነት በማስከበሩ ብሔራዊ ጀግና ከነበረው ጁሴፔ ጋሪባልዲ ጋር ይነፃፀር የነበረው የጄኔራል አርቤርቶኔ መማረክ ለጣሊያናውያን ሌላው አስደንጋጭና በሀፍረት አንገት ያስደፋ መርዶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ከጦር መሣሪያም መድፍ ፣ 11ሺህ ጠመንጃ ፣ በርከት ያለ ጥይትና ቁሳቁስ ተማርኳል። ከኢትዮጵያ የጦር አበጋዞችና የንጉሡ የቅርብ ባለሟሎች ጀግናውን ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ልዑል ዳምጠው፣ ደጃዝማች መሸሻ፣ ደጃዝማች ጫጫ፣ ቀኛዝማች ገነሜና ሌሎች ለሀገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት መውደቃቸውን፤ በተጨማሪም 4ሺህ ሲሞቱ 6ሺህ ኢትዮጵያውያን መቁሰላቸውን የተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ቢያትቱም ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገመታል።

ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስከአፍንጫው የታጠቀው የጣሊያን ጦር አፍሪካዊና ኋላቀር በሆነ የገበሬ ጦር የኢትዮጵያ ሕዝብ መረታቱ ለማመን የሚቸግር መነጋገሪያ ሆነ። አንዳንድ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች የኢትዮጵያውያንን ጥቁርነት እስከ መካድ ደርሰው ነበር። የታላቁ የዓድዋ ድል የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱ (ብርሃነ ዘኢትዮጵያ) ዝና በመላው ዓለም እንዲናኝ ከማድረጉ ባሻገር ሀገሪቱን በዓለምአቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ መነጋገሪያ አደረጋት።

ከአፅናፍ አፅናፍ የዓለምን ትኩረት እንድትሰብ አደረጋት። ድሉ ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉ በማሳየቱ ፤ በቅኝ ግዛት፣ በጭቆና ለሚገኙ የዓለም ሕዝቦች በተለይ ለአሜሪካ ጥቁሮች መነቃቃትን ፈጥሯል። ለማርከስ ጋርቬ ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለኔልሰን ማንዴላ ፣ ለኩዋሚ ንኩሩማህ፣ ለስቲቭ ቢኮ እና ሌሎች ንቅናቄዎች እርሾ በመሆን አገልግሏል፡፡ ለደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት ሆኖ አገልግሏል። የአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራችን ከ20 በላይ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት ሰንደቅ በተለያየ ቅርፅ የመገኘቱ ምስጢርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነትም የራሳቸው ጥረት እንዳለ ሆኖ መነሻው አንፀባራቂው የዓድዋ ድል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። አንዳንድ የፖለቲካና የታሪክ ልሂቃን የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ሆነ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት (አ ህ) የምስረታ ሃሳብ የዓድዋ መንፈስ የበኩር ልጅ የሆነው የፓን አፍሪካኒዝም የመንፈስ ክፋይ ነው ይሉታል።

የዓድዋ ትምህርት

በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ የዓድዋን ድል ትምህርት ፣ አንድምታ፣ ጥልቀት ፣ ከፍታ ፣ ንዑድነትና ትርጉም በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ይገልፀዋል ፦ «…ምኒልክ እና ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ሥልጣናቸውን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ብቻ አልነበረም ። …የትግራይ ፣ የሸዋ ፣ የኦሮሞ ፣ የወላይታ እና የሌሎች ሕዝቦችን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ ሀገር ለመገንባት እንጂ፤ የሕዝቦች ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ሃይማኖት ፣ ማንነት ብሔር ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የጋራ ነፃነትን ለመቀዳጀት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው።

ይህ ዓይነቱ መተሳሰር ብቻ ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ፤ የዓድዋ ትምህርትም ይኸው ነው። ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ መሆን እንዳለበት ዓድዋ ያስታውሰናል። የዓድዋ ድል ያስገኘው ነፃነት ብቻ ሳይሆን የተገኘበትን መንገድ ብናጤነው የዘመናችንም ታላቅ ወታደራዊ ድል እንድሆነ እንረዳለን። በጠመንጃ ብቻ በመታገዝ የተገኘ ድል አይደለም። የበርካቶችን ልብ በማሸነፍ እንጂ ፤ …»

ይህ የሬይሞንድ ጥልቅ ፣ ምጡቅ የዓድዋ ትምህርት፣ ፍልስፍና ዳጎስ ዳጎስ ያሉ መፅሐፍት የሚወጣው ከመሆኑ ባሻገር አዲስ አተያይን ንጻሬን የገላለጠ ነው ማለት ይቻላል። የዓድዋን ትምህርት ሀገራችንና ሕዝባችን ከሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሊተረጎም ፣ ሊተነተን ፣ ሊመከርበት የሚገባ ከቡድ ሃሳብ ነው። በአንድ በኩል የምንገኝበትን ዘመንና ትውልድ የዋጀ፤ ከፍ ሲልም እኛን እንደ ዜጋ ተከሳሽ ሳጥን ላይ አቁሞ በመስቀለኛ ጥያቄዎች የሚሞግት፣ የሚዳኝ ሆኖ ይሰማኛል። በሌላ በኩል በአግባቡ ተንትነን ከተረዳነው መሻገሪያ ይሆነናል።

አዎ ! በጀግኖች አባቶቻችን ከ128 ዓመታት በፊት የተቀዳጀነውን ታላቁ የዓድዋ ድልም ሆነ፤ ከጣሊያን የአምስት ዓመቱ ቆይታ፤ ከንጉሣዊ አገዛዙ፤ ከጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነፃ የወጣንባቸውን ድሎች ልንከላከላቸውና ልንጠብቃቸው ባለመቻላችን ለአንድ ምዕተ ዓመት ከሩብ ለዘለቀ አሳር እንደዳረገን ውድ ዋጋ እንዳስከፈሉን በጥሞና ልናንሰላስለው ይገባል። የሚያሳዝነው ከእነዚህ ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያዎች ዛሬም አለመማራችን ነው። ብልጥ ብንሆን ከሌሎች የሰው ልጆች ታሪክ መማር በቻልን።

እኛ ግን ከራሳችን ታሪክ መማር ባለመቻላችን ዛሬ ለምንገኝበት ቅርቃር ዳርጎናል። ከትናንቱ የ27 ዓመታት ግፍ ፣ መከራና አሳር እንኳ መማር አልቻልንም። አይደለም የዓድዋውን፣ የአምስት ዓመት የጣሊያን ወረራ ፣ የደርግና የትህነግ / ኢህአዴግ ነፃነቶችን ባለፉት አምስት አመት በአደራ የተረከብነውን የነፃነት ቀብድ እንደቀደሙት ባክኖ፣ ትርጉም አጥቶ እንዳይቀር በአግባቡ ለመጠቀም፣ ከቅልበሳ ለመከላከልና ለመጠበቅ የተዘጋጀን አይመስልም።

ሬይሞንድ ከላይ አፄ ምኒልክ ፣ እቴጌ ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ወራሪውን ፋሽስት ጣሊያን ድል ለመንሳት ብቻ አልነበረም። የሀገሪቱን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ ሀገር ለመገንባት እንጂ ይለናል። ይሁንና ዛሬ ሀገራችን ድንበርን ተሻግሮ የሚወር ጠላት ባይኖራትም ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞም ሆነ በሌሎች ፈተናዎች በብሔራዊ ጥቅሟ ጉሮሮ ላይ ለመቆም የጦር ዕቃውን ታጥቆ፣ የራስ ቁሩን ደፍቶ፣ ጡሩሩን ለብሶ፣ ጦሩን እየሰበቀና ዘገሩን እየነቀነቀ ግዳይ ለመጣል አጋጣሚውን በንቃት የሚጠብቅ ኃይል መኖሩን ልብ ያልን አይመስልም። በቅጡ ተረድተናቸዋል የሚል እምነት ግን የለኝም። ለሥልጣን ጥም ማርኪያ ብሔራዊ ጥቅሟን ፣ ሀገራዊ አንድነቷን ያለምንም ማቅማማት አሳልፎ ለመስጠት በጥፍሩ የቆመ ኃይል መኖሩን አናንቀነዋል።

የሰላማችን፣ የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችንና የተስፋችን ስጋት የሆኑ ኃይሎችን ልናስቆማቸው የምንችለው አያት ቅድመ አያቶቻችን የዓድዋ ድል ለመቀናጀት በአንድነት እንደቆሙት ሁሉ እኛም ልዩነቶቻችንን አቆይተን ይሄን ክፉ ቀን ለማለፍ ዳር እስከ ዳር እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መቆም ስንችል ነው። በታላቅ መስዋዕትነት እጃችን የገባ የጋራ ነፃነትን ለመከላከልና ለመጠበቅ ሌት ተቀን በንቃት መቆም አለብን። የዓድዋ አንጸባራቂ ድል የተመዘገበው ሰው ተከፍሎለት አጥንት ተከስክሶለት፣ ደም እንደጎርፍ ፈሶለት እንጂ ዳር ቆሞ አይዞህ በማለት አይደለም።

በሀገራችን ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአለት ላይ እንዲመሠረት መተኪያ የሌላት የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ጣት መጠቋቆሙን፣ መጠላለፉን ፣ ልዩነትን፣ ወንዜነትን፣ አቃቂር ማውጣቱን፣ አቅላይነትን ፣ አሉባልታውን ፣ ወዘተ. ትተን የመፍትሔው አካል በመሆን የዜግነት ግዴታን መወጣት ይጠይቃል። የዓድዋ ትምህርት ሀ ሁ …. ይህ ነው። ለአለፉት 128 ዓመታት ብንቆጥረው ብንቆጥረው አልገባን፣ አልገባው ያለን የታሪክ ፊደል።

ለእነ ማዲባ ፣ ኦሊቨር፣ ንኩሩማህ ፣ ማርከስ ፣ ስቲቭ ቢኮ፣ ጆሞ፣ ሙጋቤ፣ ቦብ፣ ለመላው አፍሪካ ፣ ለዩናይትድ ስቴትስ መብት ተሟጋቾች ለእነ ማርቲን፣ ሮዛ ፣ ጄሲ ጃክሰን፣ ማልኮም ኤክስ ፣ ሉዊስ ፋራካህ፣ ኤሊጃህ ሞሀመድ፣ ኦባማ የተቆጠረው የፊደል ገበታ እኛ በአጥንት፣ በማንነት ፖለቲካ፣ በታሪክ ምርኮኝነት፣ በታሪክ ሽሚያ ተጋርዶብን፣ ዛሬም ቅኔ፣ ምስጢር እንደሆነ አለ። በዚህ የተነሳ የጋራ ህልም፣ ርዕይ፣ የታሪክ ብያኔ ፣ የጋራ ጀግና፣ የጋራ ድል፣ የጋራ ሀገር፣ የጋራ መሪ፣ የጋራ መነሻና መዳረሻ ፣ …፤ እንዳይኖረን አድርጓል ።

ግርዶሹን ለማንሳትና ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን ማንነቶችን መመልከት እንድንችል በአያት ቅድመ አያቶቻችን ሰው የመሆን ኢትዮጵያዊ ንስር ዓይን እንመልከት። እንኳን ታላቁ የሰው ልጆች ሁሉ የነፃነት የድል በዓል የሆነው ዓድዋ 128ኛ አመት ደረሰባችሁ። ደረሰብን። እኛ እዚያ ከፍታ ላይ መድረስ አይደለም ከማንነት ፌርማታችን ገና አልተንቀሳቀስንም።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You