ሕጋዊ የፖለቲካ ሥርዓት ተከትሎ ስልጣን መያዝ ለፖለቲካ ስብራቶቻችን ፈውስ ነው

ሰላም ሉአላዊነቱ የተረጋገጠ ሀገር ሕዝባዊ ህልውናው ይቀጥል ዘንድ መሰረቱን ሊያፀናበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለሰላም ረብ የለሽ ዋጋ ሲሰጡ የተመለከትናቸው የትኞቹም ሀገራት ሲፈርሱ እንጂ ሲፀኑ አልሰማንም፤ ደግሞም አላየንም። በታሪክ ግን ውስጣዊ የሰላም ያለመረጋጋት ጉዳዮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ሲጥሩ የታዘብናቸው ሀገራት ከፈተናዎቻቸው በላይ ሆነው ህልውናቸው ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለሰላም ስናወራ፣ የሰላምን አስፈላጊነት በትምህርት ቤት ስለተማርነው፣ ሰዎች ስለነገሩን ወይም ቃሉን ብቻ ስላወቅነው አይደለም፤ የሰላምን አስፈላጊነት ከየትኛውም ሀገር ሕዝቦች ይልቅ በተግባር ስለምናውቀው ነው፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንድ ሃሳቦች በቀጥታ ከሚተረጎሙ ይልቅ በተቃርኖ ሲተረጎሙ ትርጉማቸው በቀላሉ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ሰላም ማለት ምን ማለት ነው? ከማለት ይልቅ ሰላም ማለት ምን ማለት አይደለም? ቢባል የበለጠ ይገባናል፡፡

ከታሪኳ ከግማሽ በላይ የጦርነት ታሪክ በሆነባት ሀገር፣ ጀግና ሲባል እንኳ የጦር ሜዳ ጀብዱ ብቻ የሚታሰብባት ሀገር፣ የውጪው ሲለቃት የእርስ በርሱ፣ ይህም ጋብ ሲል የውጪው የሚፈራረቁባት ሀገር፣ ጦርነት ከስልጣኔ ማማ አውርዶ ወደ ድህነት አዘቅት ለወረወራት ሀገር ስለ ሰላም መካሪም አስተማሪም አያስፈልገውም፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንኳ ይህንን ይነግረናል፡፡ የአርባና የሃምሳ ዓመታት ታሪካችንን መለስ ብለን ብንቃኝ ከአራትና አምስት ታላላቅ ጦርነቶች በላይ አካሂደናል፡፡

ጦርነቱ የእርስበርስ ሲሆን ደግሞ ክፋቱም ጥፋቱም እጅግ የከፋ ነው፡፡ በዚህም በዚያም ወገን የሚጎዳው የሚሞተውም የራስ ወገን ነው፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ከዩክሬኑ ጦርነት እጅግ የከፋ ውድመትና እልቂት የደረሰበት ነው ያሉት የሰሜኑ ጦርነት በመቶ ሺህዎችን አሳጥቶን ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ አውድሞብን ገፅታችንን አጠልሽቶት የዘወትር ጠላቶቻችንን አሰባስቦብን በመጨረሻ የተቋጨው ግን በንግግር፣ በድርድር፣ በሰላም ስምምነት/በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ነው፡፡

መጨረሻው ይሄ ሊሆን ካወደመው በላይ ቅራኔ ፈጥሮ ፤ቁርሾን ተክሎ ባይሄድ ምን ነበረበት ያስብላል። በዚያ ጦርነት የሞተው ራሱ ብቻ ሳይሆን የተጎዳው ቤተሰቡ ቢቆጠር ለማገገም ዓመታት ያስፈልገዋል፡፡ የተተከለው እሾህ፣ የተረጨው መርዝ፣ የቆሰለው ልብ ለማገገም ዓመታት ያስፈልጉታል፡፡

እንደነአውጎስጢኒዎስ ያሉ ሊቃውንት ተገቢ የሆነ ጦርነትና ተገቢ ያልሆነ ጦርነት /ጀስቲስ ዋር እና አንጀስቲስ ዋር/ እያሉ ለሁለቱም ተገቢውን ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ በሀገር ህልውና በህዝብ የመኖርና ያለመኖር ላይ የሚነሳ ጦርነትን መከላከል አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምሩበታልና ግቡና አላማው ግን መጠፋፋት እንዳልሆነ ጦርነት አንሺውም ይሁን ተከላካዩ ክፍል እስከገባቸውና ለመነጋገር ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ ለሰላም ቦታ መስጠት አስፈላጊነቱን ላይ ይደመድማሉ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በግጭት እና የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ማለፍን ምርጫው ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ጉዞ በሀገራችን ታሪክ ውስጥም በርካታ ጊዜያት ተደጋግሞ ተመልክተነዋል። አሁን በምንገኝበት የዘመናዊ የፖለቲካ ሂደታችን ውስጥም ካለፈው ባልተማረ መልኩ ግጭት ላይ ሙጥኝ እንዳለ አለ፡፡

ለጉዞው በዚህ ደረጃ መውረድ ባለሙያዎች የፖለቲካው መንገድ አለመቀየሩን እንደችግር ሲያነሱ ፤ሌሎች ደግሞ ለአካሄዱ በተዋንያኖች በኩል የሚሰጠው ቦታ ራስን ብቻ የተመለከተ ሆኖ መዝለቅን ምክንያት ያደርጋሉ፤ ዞሮ ዞሮ ኃይልን/ ጠበመንጃን መፍትሄ አድርገው መሄዳቸው ሀገርና ሕዝብም ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡

በርግጥ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኃይልና በጦር መሳሪያ ስልጣን ለመያዝ ማሰብም ሆነ መመኘትም ዘመኑን የሚዋጅ እሳቤ እንዳልሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። በጦር መሳሪያ ወይም በኃይል የሚደረግ የስልጣን መሻት ወይም ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ተገቢ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ በዋናነት መቀየር ያለበት የራስ አስተሳሰብ ነው ፤ እዚህ ላይ መስራት ደግሞ ከፖለቲካ ከተዋንያኖቻችን የሚጠበቅ ትልቁ ኃላፊነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ አንፃር መንግሥታቸው ለሰላማዊ የሀገር ጉዞና ለዜጎች መስተጋብር በጋራ ለመስራት ከተቃራኒ ኃይላት ጋር ዝግጁ መሆናቸውን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ አፈሙዞቻቸውን ካነሱ አካላት ጋር የተጀመሩ ንግግሮች እንዲቀጥሉ ዛሬም በመንግስት በኩል ተነሳሽነቱ እንዳለ ገልጸዋል።

ግጭትና ጦርነት የሕዝብ ሀብትና ንብረት ከማውደም ባለፈ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ የሚያመጣው ትሩፋት የለም። ያለፍንባቸው የግጭት ዓመታትም ይህን በሚገባ አሳይተውናል፡፡ ብዙ ወንድሞቻችንን አሳጥተውናል ፣ አካለ ጎዶሎ አድርገውብናል፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት አውድመውብናል።

መነጋገር የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫው ሲሆን፤ የተፈጠሩ ቁርሾዎችም በቀላሉ የሚፈቱበት መንገድ ቀና ሲሆኑ ተመልክተናል። ሰላም የሁሉ መሰረት ነው። በእያንዳንዱ የሀገር ጉዞ ውስጥ ከቃል በላይ የሆነው የሰላም ሂደት ቁልፉን ሚና ይጫወታል፡፡ እኛም ብንሆን ተግባርና አካሄዳችንን መዳረሻ አድርገን ካስቀመጥነው ግብ ጋር ማስላት ይኖርብናል። ለመደራደር የመነጋገሪያ ነጥቦቻችን ሁሉንም ማህበረሰብ የሚወክሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ተዋናይ አካላት የኢትዮጵያ ህዝብ የጦርነት፣የመፈናቀል፣የሰቆቃ ህይወት ይበቃዋል ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ከራሳቸው የጥቅም ፍላጎት ይልቅ የህዝባቸውን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መንከራተት፣ መሞት ከግምት በማስገባት ህዝባቸውን ይቅርታ በመጠየቅ፣ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው በማሰብ በተረጋጋ መንፈስ በመደራደር በመነጋገር ህጋዊ የሆነ የፖለቲካ ስርአትን በመከተል ስልጣን መያዝ እንደሚቻል ማመን ይኖርባቸዋል፡፡

ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ ሰላምንና መረጋጋትን የማያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን በዚች ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያብብበትን፣ የውይይት ባህል የሚለመድበትን መንገድ መከተል ይገባል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ዘላቂ ሰላም ማምጣትና የሕዝባችንን የልማት መሻት ማሟላት የሚታሰብ አይሆንም፡፡

በእርግጥ በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑንና ግማሽ መንገድ ሄዶ ለሰላም እንደሚሠራ እየተነገረ ይገኛል። ትጥቅ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ጉዳዮችን በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል። ከሰሞኑ የብልፅግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ይሄንኑ የሰላም አማራጭ እንደሚገፉበት መግለፁም ይታወሳል፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ የታጠቁ ኃይሎች ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት እንደሀገር ከገባችበት የሰላም መደፍረስ ችግር ለመውጣት መንግሥት ቀዳሚውን ተነሳሽነት በሰላም ዙሪያ ሲወስድ እየተመለከትን ነው። መንግሥት ወደ ንግግር መምጣቱ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል የሚገኝ ድል አይኖርም፡፡ ይገኛል ብሎ ማሰብ ሀገርና ሕዝብን ወደ ከፋ እልቂት ከመምራት ባለፈ ትርጉም አይኖረውም።

የሰላምን ዋጋ የተረዳ ማህበረሰብ ለቅፅበት አንድነቱን የሚያጠናክርለትን ይህንን የተረጋጋ ስነምህዳር ከእጁ እንዲወጣበት አይሻም፡፡ በዚህ ረገድ ውስጣዊ ችግራችንን በራሳችን አቅም ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜም ሆነ ቀደም ባሉት ጊዜያት እየተደረጉ ያሉት የሰላም አማራጭ መድረኮች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መልካም መንገዶች ናቸው፡፡

መንግሥት እየሄደበት ያለው የሰላም አማራጭ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊያጤኑትና ሊከተሉት የሚገባ ነው፡፡ ሀገርን ከማስቀጠል አንፃር ቅድሚያውን ወስዶ ለውይይት የሚቀርብ የትኛውም አካል ይበረታታል፡፡ አብዛኞቹ ችግሮቻችን የመነጩት በቅርብ ጊዜ ሳይሆን ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም በቀላሉ የሚፈቱ ባለመሆናቸው ቁጭ ብሎ መወያየትን፣መነጋገርን ይጠይቃሉ፡፡

ማንኛውም ኃላፊነት ያለበት አካል ስለሀገሪቱ የሚመለከተው የተሻለችና ለሁሉም ዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህንን ለማሳካት የሚደረግ ውይይት ከአስፈላጊ በላይ ነው፡፡ ትርጉሙም የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የመወሰን ያህል አቅም ያለው ነው።ይህ የሰላም አማራጭ ውጤታማ የሚሆነው ግን በሰላም መድረኩ ላይ የሚገኙት አካላት ተገቢውን ፍላጎትና ጥረት ሲያደርጉ ነው፡፡

ዛሬም ቢሆን ነገ ሀገራችን ሰላሟ ተረጋግጦ እንዲቀጥል፤ ሰላምን መሰረት ያደረጉ የውይይት መድረኮች መተኪያ የማይገኝላቸው አማራጮቻችን ናቸው፡፡ ጡንቻ መፈታተን በየዘመኑ ካስከፈለን ዋጋ አንጻር በችግሮቻችን ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለን መነጋገር ግዴታችን ነው።

በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮች ላይ ነዳጅ በመጨመር የሚያቀጣጥሉ በዙሪያችን ባሉ ጠላቶቿ ሁኔታ ሁላችንም ብልህ ካልሆንን ጦርነቱ ግጭቱ ሁሉንም ይዞ የሚጠፋ ነው፡፡በብዙ መስዋእትነት አባቶቻችን ያስረከቡንን ውዲቷን ሀገራችንን ሊያሳጣን እንደሚችል መዘንጋት የዋህነት ነው፤ጥልቅ አለማወቅ ጭምር።

በቀደመው የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የምንሻገረው ችግር የለም፤ ከዚህ ይልቅ የተዘረጉ የሰላም እጆችን ተቀብሎ፣ የተነሱለትን አላማ በድርድርና በንግግር ማሳካት ብልህነት ብቻ ሳይሆን ቅድስናም ጭምር ነው፡፡ ነባር ቁስልንም የሚሽር ነው፡፡

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You