ቅድመ ምርመራ- የማህፀን በር ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል

ወይዘሮ ለምለም ካሣሁን (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ታማሚ ናቸው፡፡ ሕመሙ ሲበረታባቸው ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ለተሻለ ሕክምና ከመጡ አንድ ዓመት ሊሞላቸው ነው፡፡ በአሁን ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ አሁን ደግሞ በጤናቸው ላይ መሻሻል እያዩ መጥተዋል፡፡

የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ለምለም፤ በበሽታው ምክንያት መገለል ደርሶባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያየ ሕክምና አድርገዋል፡፡ በአሁን ወቅትም የጨረር ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ ከትናንት ዛሬ የተሻለ እንደሆነ አምነው ከሕመማቸው ለመፈወስ ሕክምናቸውን አጥብቀው እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከ600ሺህ በላይ ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ተጠቅተዋል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት፣ በክትባት እጥረትና አስቀድሞ ምርመራ ለማድረግ በቂ ግብዓት ባለመኖር ምክንያት ከፍተኛ የሞት መጠን እንደሚመዘገብም ይኸው መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህ መረጃ መነሻነት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሴቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ በሽታዎች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡

በበሽታው በአብዛኛው እድሜያቸው ከ23 እስከ 49 ዓመት የሚሆኑ ሴቶች እንደሚያጠቃም ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ጥናቶች የሚያመለክቱት፡፡ በአፍሪካም ከጡት ካንሰር ቀጥሎ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የብዙ ሴቶችን ሕይወት በመቅጠፍ በሁለተኛ ደረጃ መቀመጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዶክተር ማለደ ቢራራ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከማህፀን የታችኛው ክፍል የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ካንሰር 99 በመቶ የሚመጣው ‹‹ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ›› (Hpv) በተባለ ቫይረስ አማካኝነት ነው፡፡ ቫይረሱ እንዲመጣ የሚያደርጉ የተለያዩ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ከነዚህም ውስጥ አንዱ ከዚህ በፊት የአባላዘር በሽታ መኖር ነው፡፡ ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ መኖርና ግንኙነት ማድረግ እንዲሁም በለጋነት እድሜ ቶሎ ወሲብ መጀመርም ሌላው አጋላጭ ምክንያት ነው፡፡ በሌላ በኩል ብዙ ልጅ መውለድም ለቫይረሱ አጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

ዶክተር ማለደ እንደሚናገሩት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ሕመም ሲጀምር ምንም አይነት ምልክቶችን ላያሳይ ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ገብቶ ምልክቶች ለማሳየት እስከ አስር ዓመታት ስለሚፈጅበት ምልክቶቹን በቶሎ አውቆ ወደ ሕክምና ለመሄድ አዳጋች ይሆናል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ የሚኖረው ሥርጭት እየበዛ እና እየተስፋፋ ሲሄድ ምልክቶቹ መታየት ይጀምራሉ፡፡

በሽታው ሳይታወቅ በቅድመ ካንሰርነት ደረጃ የሚታይ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰተው ግን በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ምልክትም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ስለዚህ ማንኛውም ለአቅመ ወሊድ የደረሰች ሴት ወደ ጤና ተቋማት በማምራት እና ምርመራ በማድረግ ራሷን ማወቅ እንደሚኖርባት በጤና ባለሙያዎች ይመከራል፡፡

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይገደብ በተለያዩ ቦታዎች ምርመራ ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ተፈጥሯል፡፡ በሽታው በቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ ከተገኘ በሀገር ውስጥ ሕክምናውን መከታተል ይቻላል፡፡ የሕክምና ክትትል በሚገባ ከተደረገም በሽታው የሚድን እና የሚጠፋ ነው፡፡

ነገር ግን በሽታው በቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ እያለ ሳይታወቅ በዛው ከቀጠለ እና ወደሙሉ ካንሰርነት ከተቀየረ ምልክት ማሳየት ይጀምራል። ምልክቶቹም በማህፀን አካባቢ የመድማት፣ እብጠት፣ የሕመም ስሜት እንዲሁም በሰገራ እና በሽንት ላይ የተለዩ እና ያልተለመደ ፈሳሽ መታየት ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ከካንሰር ጋር የተያያዘ የተጠናከረ የምዝገባ ሥርዓት ባለመኖሩ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ከሕዝብ ቁጥር አንፃር ይህን ያህል ነው ብሎ ደፍሮ ለመግለፅ ያስቸግራል። በአጠቃላይ ግን በየዓመቱ ከአምስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ታማሚዎች እየተገኙ መሆኑን ከሆስፒታሎች ከሚገኙ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በሽታው ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ የሚከሰት ሁለተኛ ደረጃን የያዘ የካንሰር ዓይነት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ዶክተር ማለደ እንደሚያስረዱት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ብዙ ሴቶችን ለሞት ከሚዳርጉ የካንሰር ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ከሌሎች የካንሰር አይነቶች ለየት የሚያደርገው ግን አስቀድሞ መከላከል የሚቻል መሆኑ ነው፡፡ ጤናማ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ አንደኛው መከላከያ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው እና በጣም የሚከረው ደግሞ ቫይረሱን የሚከላከል የኤች.ፒ.ቪ (HPV) ክትባት መውሰድ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ በተለይም ግብረ ስጋ ግንኙነት ያልጀመሩ እድሜያቸው ከ9 ዓመት ጀምሮ እስከ 15 ዓመት ድረስ ላሉ ልጃገረዶች የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ በሽታውን በሚገባ ለመከላከል ያግዛል፡፡

ምናልባትም መከላከያ መንገዶች ሳይተገበሩ ቀርተው በሽታው በቅድመ ካንሰርነት ደረጃ ከታወቀ ማከም ይቻላል፡፡ በሽታው ታውቆ መከላከል እንዲቻል ግን ማኅበረሰቡን ለማስተማር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡

እድሜያቸው ለአቅመ ወሊድ የደረሱ ሴቶችም ወደ ሕክምና ተቋማት በማቅናት ራሳቸውን ማወቅ ከበሽታው ራሳቸውን መከላከል ይኖርባቸዋል። በመንግሥት በኩልም ውጤታማ የሆኑ ሀገራት ልምድን በመቅሰም ክትባቱን ማስፋፋት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የተገኘባቸውን ሴቶችን ማከም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግም የሕክምና ተቋማት ዝግጁ ናቸው። ለአብነትም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ጥቁር አንበሳ እና ሌሎች ሆስፒታሎች የቀዶ ህክምና በማድረግ፣ የጨረር ሕክምና በመስጠት ሕክምና የሚሰጡ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ ግን መለመድ እንዲሁም መተግበር ያለበት አስቀድሞ መከላከል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የመከላከያ ዘዴዎችን በማስተማርና ግንዛቤውን ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ በማስፋፋት በበሽታው የሚያዙ ሴቶች ቁጥር ለመቀነስ ብዙ መሥራት ይገባል፡፡ ምንም እንኳን በአዲስ አበባ እና በክልሎች መከላከል እንዲቻል የሕክምና ተቋማት ዝግጁነት ይኑር እንጂ በግንዛቤ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶችም ወደነዚህ ጤና ተቋማት ሄዶ ቅድመ ምርመራ የማድረጉ ልምድ በሴቶች በኩል እምብዛም አይታይም፡፡ ስለዚህ የቅድመ ማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ ልምድን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡

የሚሰጠው ክትባት በዋጋ ደረጃ ውድ የሚባል በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው በእርዳታ መልክ ነው፡፡ መንግሥትም ወጪን በመጋራት ከሌሎች ክትባቶች ጋር በማዛመድ ፕሮግራሙ ውስጥ በማካተት ቀጣይነት ባለው መልኩ ያለማቋረጥ እንዲቀጥል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸው በማድረግ ክትባቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሰጥ ለማድረግ የድርሻቸውን ቢወጡ በበሽታው የሚያዙ ሴቶችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ላይ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፤ ከካንሰር ጋር የተጀመረው ርብርብ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም በርካታ ርቀቶች መጓዝ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ርብርቡ አንድም ማኅበረሰቡ ስለ ካንሰር በደንብ እንዲያውቅ፤ አውቆም በቅርብ ወዳለው ጤና ተቋም በመምጣት አገልግሎት እንዲያገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ28 በላይ ጤና ተቋማት የካንሰር ታማሚዎች የኬሞ ቴራፒ ሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱንና በእነዚህ 28 ተቋማት ላይ ተጨማሪ መድኃኒቶችን፣ የሰው ኃይልን በማሰማራት ሕክምና እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የጨረር ሕክምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑንም የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቀደም ሲል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረው የጨረር ሕክምና አሁን ላይ ወደ ሰባት ማዕከላት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ግዜ የጨረር ሕክምናውን ሀረማያ፣ ጅማ እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች እየሠሩ መሆናቸውንና አራቱ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ከሌሎች የካንሰር አይነቶች በጣም አንገብጋቢና እናቶችን እየነጠቀ ያለው የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር (cervical cancer) ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጤና ተቋማት በሽታውን የመለየት አቅም አላቸው ብለዋል፡፡ ተቋማቱ የመለየት አቅም እንዲያጎለብቱ የተደረገ መሆኑንና በሁሉም ወረዳዎች ቢያንስ አንድ ጤና ተቋም የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን መለየት እንደሚችል እንዲሁም ለይቶም እዛው ሕክምና መስጠት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ገና በጅምር ያለ ከሆነ ማከም፤ ካልሆነ ደግሞ ወደሚቀጥለው ጤና ተቋም ሪፈር ማድረግ የሚችልበት አግባብ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ስድስት ወር ብቻ ከ264 ሺህ በላይ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከመለየት ባሻገር ተጨማሪ ሕክምና የሚፈልጉትን ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡

የብዙ ሴቶችን ሕይወት እየነጠቀ ያለውን የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ለመከላከል ክትባቱን መውሰድ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ የአባላዘር በሽታ ካለ መታከም፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከል እና መታከም እንዲሁም የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You