ወስኖ ራስን መለወጥ!

እናቱ ማርገዟን ስታውቀው ለማስወረድ ተጣድፋ ወደ ሀኪም ቤት ሄደች፡፡ ሀኪሞች አይሆንም አሉ። ካለችበት የኑሮ ሁኔታ አንፃር ሌላ ልጅ መውለድ ለእርሷ የማይታሰብ ነው፡፡ ሀኪሞች እምቢ ቢሏትም እርሷ ግን ተደብቃ የአልኮል መጠጥ እየጠጣች ፅንሱን ልታጨናግፈው ሞከረች፡፡ ይሁንና ይህን ሁሉ ውጣውረድ አልፎ ልጁ ተወለደ፡፡ የሕፃኑ ቤተሰቦች ለፍቶ አዳሪ ናቸው፡፡

ልጁ አድጎ ጫማ የሚገዛለት ሰው እንኳን አልነበረም፡፡ ዘመዶቹ የጣሉትን አሮጌ ጫማዎች አድርጎ እግርኳስ ይጫወት ነበር፡፡ ጓደኞቹ በአባቱ የፅዳት ሥራ እያሾፉ ልቡን ይሰብሩት ነበር፡፡ አስተማሪው እንኳን ተማሪዎች በተሰበሰቡበት በአባቱ ድህነት ቀልዶበት ያውቃል፡፡ አባቱ ሰካራም ወንድሙ ሱሰኛ ነበሩ፡፡ እርሱም ትምህርት ይከብደው ነበር፡፡

ልጁ ግን እግር ኳስ ላይ በረታ፡፡ ምን ያደርጋል! የልብ ህመም ያዘው፡፡ መሮጥ፣ መራመድ ቁጭ ማለት እንኳን አቃተው፡፡ ትንፋሽ አጣ፡፡ ዶክተሩ እግር ኳስ መጫወቱን ያቁም፤ ወይም የልብ ቀዶ ህክምና ይደረግለት አለ፡፡ ቀዶ ህክምናው ካልተሳካ ሊሞት እንደሚችል በዶክተሩ ተነገረው፡፡ ያኔ ደግሞ እድሜው አስራ አምስት ዓመት ነበር፡፡ ለታላቅ ህልሙ ሲል ቆራጥ መሆን ነበረበት፡፡ ምንም ሳያመነታ የልብ ቀዶ ህክምናውን አደረገ፡፡

አስገራሚው ነገር ከቀዶ ህክምናው በኋላ እንደውም ፍጥነቱ ጨመረ፡፡ ታላቅ የመሆን ምኞቱ፣ ጥረቱ፣ ፅናቱ ተጨምሮ ዓለም የሚያከብረው የእግር ኳስ ተጫዋች ሆነ፡፡ የጎል ማሽን ይሉታል፡፡ ሚሊየኖች የእርሱን ማልያ በፍቅር ይለብሳሉ፡፡ በዓለም ላይ እጅግ አውቅናን ካተረፉ ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ታውቁታላችሁ! የምድራችን ታላቁ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው፡፡

አሁን ላይ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የመጀመሪያው ቢሊየነር የእግር ኳስ ተጫዋች ነው፡፡ ተጫዋቹ ቆራጥ ሆኖ ያን ቀዶ ህክምና ባያደርግ ኖሮ ዛሬ ስለእርሱ አይወራም ነበር፡፡ ቆራጥ መሆን እንደሚያስከብር ከዚህ ሰው በላይ ምስክር የለም፡፡ አንተም የተሻለ ሰው ለመሆን መወሰን አለብህ፡፡ አንድ ውሳኔ ህይወትህን እስከመጨረሻው ሊለውጠው ይችላል፡፡ የምትፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ ከፍርሃትህ ጀርባ ቁጭ ብለዋል፡፡ ቆራጥ ካልሆንክ ማንም አይፍልግህም፡፡ ለራስህ አትሆን፤ ወይ ለቤተሰብህ አትሆን አልያ ደግሞ ለምትወዳቸው አትሆንም፡፡ የሚያመነታ ሰው ሲባክን ይኖራል፡፡ ስለዚህ ቆራጥ መሆን አለብህ ወዳጄ!

የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ዶክተር ፍሬድ ለስኪን አዕምሯችን በቀን ውስጥ ከ60 ሺ በላይ ሃሳቦችን ያስባል ይለናል፡፡ አብዛኛው ደግሞ ተደጋጋሚ ነው፡፡ ግማሹ ስለትናንት ነው፡፡ ቁጭት ነው፡፡ ብሶት ነው፡፡ ‹‹ወይኔ! እንዲህ ባላደርግ ኖሮ፣ አበላሸሁት፣ አጠፋው›› እያልን ነው የምናስበው፡፡ ግማሹ ደግሞ ስለነገ ነው፡፡ ‹‹እንዲህ ቢሆን ፣ እንዲህ ባገኝ የሚል›› ምኞት ነው፡፡ ለውጥ የሚጀምረው ደግሞ አሁን ላይ ትኩረት አድርገህ በመወሰን ነው፡፡

ከዚህ በፊት የወሰንካቸው ውሳኔዎች ያሳጠሁ ደስታ አለ፡፡ የአእምሮ ሰላም አለ፡፡ እንደውም ሰዎች መጥተው ‹‹አንተ ጀግና ነህ፡፡ እንዲህ በማድረግህ አደንቅሃለው›› ያሉህ ጊዜ አለ፡፡ ‹‹እህቴ አንቺ በጣም ጎበዝ ነሽ፣ እንዲህ በማድረግሽ ገርሞኛል›› ብለው ያደነቁሽ ወቅት አለ፡፡ ያ ወቅት በጣም ቆራጥ ሆነሽ የወሰንሽበት ነው፡፡ በዚሁ ቅፅበት ሱሱን ለማቆም መወሰን አለብሽ፡፡ ፈርተህ ያቋረጥከውን ትምህርት ለመቀጠል መወሰን አለብህ፡፡ እጀምራለሁ ብለህ እያመነታህ ያለኸውን ያን ሥራ ለመጀመር አሁን መወሰን አለብህ፡፡

በትምህርቴ፣ በስራዬ፣ በፍቅር ግንኙነቴ፣ በትዳሬ ወዘተ ለውጥ እፈልጋለሁ ብለህ ካሰብክ መጀመሪያ መወሰን አለብህ፡፡ ከዛ ወደ ተግባር መግባት አለብህ። ግን ‹‹እንዴት አድርጌ ልወስን፤ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ቁረጥ! ወስን ማለት ማን ያቅተዋል›› ካላችሁ ልክ ናችሁ፡፡ ለዚህ መንገድ ያስፈልጋል፡፡ መንገዱ ደግሞ እንሆ……

መወሰን ለምን ይጠቅማል?

አንድን ነገር ለምን እንደምታደርገው ካወክ ጀምረህ አታቆመውም፡፡ አንዳንድ ሰው ይነቃቃል፡፡ የሚገርም ኃይልና ደስታ ይሰማውና ስፖርት መስራት ይጀምራል፡፡ አንድ ሰሞን ሰርቶ ሰልችቶት ያቆማል፡፡ በጠዋት መነሳት ይጀምራል፡፡ ከዛ ይሰለቸውና ‹‹እንዴ! ለነብሴ ነው ወይስ ለስጋዬ በጠዋት እየተነሳው ስፖርት የምሰራው›› ብሎ መነሳቱን ያቆማል፡፡ አየህ! የአንድን ነገር አላማ ስታውቅ ጀምረህ አታቆምም። ከወሰንክ ወሰንክ ነው፡፡ ስለዚህ ለምንድን ነው የምትወስነው? ባትወስን ምን ታጣለህ? ምን ትጎዳለህ? ህመሙን እወቀው፡፡ ካልወሰንክ ባለህበት ቆመህ ልትቀር ነው። ያ የምትፈልገው ህልም በቁምህ እያየኸው አፈር ሊበላው ነው፡፡ ስለዚህ መወሰን አለብህ፡፡

እንዳታፈገፍግ የምታጣውን ነገር ቀድመህ አስበው፡፡ ከዛ ደግሞ ብትወስን ምን ታገኛለህ? ደስታው ምንድን ነው? ብትወስን ራስህን በአስተሳሰብና በስብእና መገንባት ትጀምራለህ። ከዚህ በፊትም ቢሆን ብዙ ነገሮችን መቀየር የቻልከው በወሰንክባቸው ወቅቶች ነው፡፡ ህይወትህ በራስህ ቁጥጥር ውስጥ ይገባል፡፡ የህይወትህ ካፒቴን አንተ ራስህ ትሆናለህ፡፡ እስከምትችለው ማደግ ትጀምራለህ፡፡

በነገራችን ላይ አሁን አንተ ያለህበት ደረጃ ላይ ያደረሰህ ከዛሬ አምስትና አስር ዓመት በፊት አብረሃቸው ትውላቸው የነበሩ ሰዎች፣ ጓደኞችህ፣ ታነበው የነበረው መጽሐፍ፣ ታየው የነበረው ፊልም…. ወዘተ ብቻ ውሎህ ዛሬ ላይ አድርሶሃል፡፡ ነገ የምትርስበትንም የሚወስነው ዛሬ የምትወስናቸው ውሳኔዎች ናቸው፡፡ አየህ! ለመለወጥ ስትወስን ለምንድን ነው የምለወጠው? ምንድን ነው የሚጠቅመኝ ? ባልለወጥ ምን አጣለሁ? ባልወስን ምን እጎዳለሁ ማለት አለብህ፡፡

መጠበቅ አቁም!

ብዙ ሰው የሆነ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ጥበቃ ላይ ነው፡፡ በህይወቱ የሆኑ ነገሮችና ክስተቶች እስኪመጡ፣ የሆነ ሰው መጥቶ እስኪረዳው እየጠበቀ ነው፡፡ እንዳትወስን ያደረገህ፣ እንዳትጠነክር ያደረገህ፣ ልፍስፍስ ያደረገህ ከሰው መጠበቅ ነው። ሁኔታዎች እስኪቀየሩ መጠበቅ ነው እንዳትወስን ያደረገህ፡፡

ማን እንዲመጣ ነው የምጠብቀው? ማንም አይመጣም፡፡ ማንንም አጠብቅ፡፡ የሆነ ሥራ ለመሥራት ሙድ ውስጥ ልግባ አትበል፡፡ ስራው ራሱ ያነቃቃህ፡፡ መርፌ የሚፈውስህ እያሳመመህ ነው፡፡ እድሎች እንኳን የሚመጡት በራስህ የምትችለውን ያህል ስትጀምር ነው፡፡ ቆመህ ስትጠብቅ ያልመጡ እድሎች መንቀሳቀስ ስትጀምር ግን በላይ በላይ ይደራረባሉ፡፡ ፍቅረኛ ሳይኖርህ ዞር ብለው ያላዩህ ሰዎች ፍቅረኛ ስትይዝ አላስቆም አላስቀምጥ ይሉሃል። ቆመህ ስትጠብቅ ያልመጣው ታክሲ እንኳን በእግር መንገድ ስትጀምር ‹‹የሞላ አንድ ሰው!›› ይልሃል፡፡

ይህች ዓለም የምታደላው ቁጭ ለሚል ሳይሆን ለሚሮጥ ነው፡፡ ከሰው ለሚጠብቅ አይደለም ለራሴ አላንስም ብሎ ለሚታገል ነው፡፡ ከሰው መጠበቅ ልብህን ይሰብረዋል፡፡ እድል እስኪመጣ ቁጭ ማለት ብኩን ያደርግሃል፡፡ መሮጥ አለብህ፡፡ መታገል አለብህ፡፡ እድል የሚመጣው ቁጭ ለሚል ሳይሆን ለሚዘጋጅ ነው፡፡ ካልተዘጋጀህ እድሉ ቢመጣ ራሱ ታባክነዋለህ፡፡ ተዘጋጅ! መጠበቁን አቁምና ጊዜህ እንዳይባክን አሁኑኑ ወስን፡፡

ወደኋላ መመለስ የለም!

ወደኋላ የሚመልሱህን ነገሮች አስወግድ፡፡ እንዳትለወጥ፣ ቆመህ እንድትቀር፣ እንድትፈዝ … ሰዎች እየተለወጡ ነው፡፡ አንተ ግን ቆመሃል፡፡ እንደዛ እንድትሆን ያደረገህ ምንድን ነው? እስቲ ቁጭ በልና አስበው፡፡ ውሎህ ነው፣ ጓደኞችህ ናቸው፣ በዙሪያህ ያለ ሰው ነው፣ ማን ነው? አንዳንድ ጊዜ የተመረዘ እጅ የሚቆረጠው ባለቤቱ ስለማይፈልገው አይደለም፡፡ ሌሎቹን የሰውነት ክፍሎች ስለሚመርዛቸው ነው፡፡

ውሎህን የምትቀይረው፤ አትችልም፣ አትርረባም፣ የትም አትደርስም ከሚሉ ሰዎች የምትሸሸው ስለማትወዳቸው አይደለም፡፡ ግን ቆራጥ እንዳትሆን፣ የውሳኔ ሰው እንዳትሆን እያደረጉህ ስለሆነ ነው፡፡ ህልምህን ቆፍረው እየቀበሩት ስለሆነ ነው፡፡ ውሎህን ለመቀየር ምንድን ነው የያዘህ? ምንስ ነው የጎተተህ? አስቲ ይህን አስብ፡፡ ቆራጥ ስትሆን ሰዎች እንኳን ያከብሩሃል፡፡ እሱ እኮ ከወሰነ ወሰነ ነው ይሉሃል፡፡

እንዳንድ ሰው ያቆመውን ሱስና መጥፎ ልማድ የሚጀምረው ከነዛ ሰዎች ጋር ሲገናኝ ነው፡፡ ወይ የሆነ የለመደው ቦታ መልሶ ሲውል ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ከህይወትህ አስወግድ፡፡ የማይጠቅሙህን ሰዎች ከህይወትህ ቆርጠህ አውጣ፡፡ ለውጥ መጀመር ቀላል ነው፡፡ እስከ ፍፃሜው መጓዝና መጨረስ ነው ከባዱ፡፡ ከፍፃሜው ላይ ለመድረስ ግን ወደኋላ ማየት የለብህም፡፡ ወደኋላ እንድታይ የሚያደርጉህን ሁኔታዎች፣ ሰዎች እንደሆኑ ለይተህ አውጣና ከህይወትህ ቆርጠህ ጣላቸው፡፡

ኃላፊነት ውሰድ

ሰበበኛውን ቅበረው፤ ያለበለዚያ አንተኑ ይቀብርሃል፡፡ በህይወት ውስጥ አንዳንዱን ሰው ከፍ የሚያደርገው፤ ሌላውን ደግሞ ዝቅ የሚያደርገው ችግሮች አይደሉም፡፡ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ እንጂማ! አንተን የገጠመህ ችግር እኮ ሁሉንም ይገጥመዋል፡፡ ትምህርት ናላውን ያዞርበታል፡፡ ሥራ ይከብደዋል፡፡ ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ይውላል፡፡ አብዛኛው ሰው እንደዛ ነው፡፡ በትዳሩ ደስተኛ አይደለም፡፡ አንተን የገጠመህ ችግር ሁሉም ይገጥመዋል፡፡ ልዩነቱ ችግሩ አይደለም፡፡ ለችግሩ የምትሰጠው ምላሽ ነው፡፡ የምተሰጠው ምላሽ ደግሞ ኃላፊነት መውሰድ መሆን አለበት፡፡

ኃላፊነት መውሰድ ማለት ከፈጣሪ ቀጥሎ ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ ብሎ ለውጡን መጀመር ነው፡፡ ከማንም አለመጠበቅ ነው፡፡ ሁኔታዎች እስኪቀየሩ አለመጠበቅ ነው ኃላፊነት መውሰድ፡፡ ከእኛ የባሰ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ህይወታቸውን የቀየሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አንተ እድለ ቢስ ስለሆንክ አይደለም። ሰነፍ ስለሆንክ አይደለም፡፡ በተፈጥሮ ያልታደልክ ሰው ስለሆንክም አይደለም፡፡ ኃላፊነቱን ስላልወሰድክ ነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነቱን ውሰድ፡፡ ወዳጄ! በምድራዊ ችግር ተስፋ መቁረጥ የለብህም፡፡ ምክንያቱም አንዱ በር ሲዘጋ ሌላው ይከፈታልና፡፡

ከወሰንክ አድርገው!

ልብህ አምኖበት ከወሰንክ ወደተግባር ግባ፡፡ አእምሮህ ካሰበ፤ ልብህ ከወሰነ ድርጊት ያስፈልጋል። ለመብላት መወሰን አያጠግብም፡፡ በተግባር መብላት አለብህ፡፡ ባለህበት የምትቀረው ወስነህ ወደ ድርጊት ካልገባህ ነው፡፡ መወሰን ሌላ ነገር ነው፤ ወደ ተግባር መግባት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ መድኃኒቱ አለኝ ብትል ምን ዋጋ አለው! ካልዋጥክ አትድንም። ከወሰንክ ወደ ተግባር መግባት አለብህ፡፡ ውሳኔ አቅጣጫህን ይቀይረዋል፡፡ ድርጊት ደግሞ መንገዱን ያስጀምርሃል፡፡ የማይቆም ጥረት ከፍፃሜ ያደርስሃል። ዋናው ግን መጀመርህ ነው፡፡

ለአንተ ለመለወጥና ለመወሰን ወሳኙ ጊዜ የባነንክበትና የነቃህበት ሰአት ነው፡፡ እሱም አሁን ነው፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You