ከሞት ፍርድ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣው የውንብድና ወንጀል

ሠርቶ ማግኘት አግኝቶ የተሻለ ሕይወት መኖር የብዙ ሰዎች ሕልም ነው። ሰዎች መኖር ለሚፈልጉት የምቾት ኑሮ ሲሉ ያዋጣኛል ያሉትን መንገድ በሙሉ ይከተላሉ። ገሚሱ ጥሮ ግሮ በላቡ ያፈራውን ሀብት ለመጠቀም ሲነሳ ገሚሱ ደግሞ ያለፋበትን ሀብት ለማጋበስ ሲጥር ይታያል። ይህን ሀሳብ ያነሳነው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተዘጋ ዶሴ አገላብጠን ያገኘነውን ታሪክ ልናካፍላችሁ ስለወደደን ነው።

ወጣቶች ናቸው። ያለፉበትን ጥሪት መሰብሰብ ሕልማቸው የሆኑ ቀማኞች ናቸው በአንድ ላይ የተሰበሰቡት። ሁሉም ያለድካምና ልፋት የገንዘብ ቁልል ውስጥ መዋልና ማደርን ነው ዓላማ ያደረጉት። ሕልማቸውን እውን ለማደረግ ከማስፈራራት እስከ መግደል የሚደርስ የዱርዬዎች ቡድን ነው። እንደ ጣሊያኖቹ ማፊያዎች የሚፈሩ፤ ሁሉን ነገር በጉልበት የሚያደርጉ የጭካኔ ጥግ ድረስ ሲሄዱ ምንም የማይጎረብጣቸው ናቸው።

ሁሉም በጠዋቱ የወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በባዶ ጉራ እራሳቸውን ወጥረው በውድ ልብሶች መድመቅ፤ ውድ ጌጦችን ከማድረግ አንስቶ ውድ መኪናዎችን ለመንዳት በመመኘት ያገኙትን ሁሉ መንጠቅና መዝረፍ ተቀዳሚ ሥራቸው ሆነ።

አንድ አይነት ክንፍ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበራሉ እንደሚባለው የተለያየ አካባቢ ተወልደው ቢያድጉም፤ ከተለያየ አይነት የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች ቢፈጠሩም ሕልምና ፍላጎታቸው አንድ አይነት ሊያውም በሰው ላብ መክበር ነውና ማንም ነጋሪ ሳያስፈልጋቸው ተስማምተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

የተገናኙት ሁሉም ተሰብስበው የሚቅሙበት ጫት ቤት ውስጥ ነው። በተለያየ አጋጣሚ ወደ ጫት ቤቱ የመጡት እነዚህ ወጣቶች ስሜትና ፍላጎታቸውን እየለዩ በአንድ ተሰባስበው ደርዘን ሞልተዋል። የነጠቁትንም ፤የቀሙትንም በሙሉ ይዘው እዛው በመምጣት የሚሸጠው ተሽጦ እንደ ሀብታም መኖርን ይለማመዱበታል።

የምቾት ሕይወት ልምምዳቸውን በዘረፉት ገንዘብ አጠናክረው የቀጠሉት ወጣቶች ሠርቶ ለማግኘት ማቀዳቸው ትተው የሰውን ሀብት እንዴት የራሳቸው ማድረግ እንደሚችሉ በማሰብ ጭንቅላታቸውን ወጥረው ይውላሉ።

አቤል ኢሳያስ ተስፋዬ፣ አቤል አዋየው አሊ፣ አቤል ግደይ በረኸ፣ ሀብታሙ ወንድሙ ገብረየስ፣ ዳንኤል ጎይቶም ተስፋዬ ፣ ናትናኤል ግደይ በረኸ፣ ዳንኤል ዮሐንስ ገብረ መድን፣ ዮናስ ፍፁም ከበደ፣ ናትናኤል ረዳኢ ኪሮስና ሌሎች አንድ ላይ በመሆን ውድ ሆቴሎች ሀብታሞች የሚውሉበት መዋል ያዘወትሩ ነበር። ይህን ማድረጋቸው ደግሞ የተሻለ ገንዘብ ያለው ተዘራፊ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም እንደ ጓደኛ የቀረቡትን የመኪና መለዋወጫ ባለቤት አጭበርብረውና አደንዝዘው ጥሪቱን በሙሉ ወስደዋል። ማንም ሳይደርስባቸው የተለያዩ ጥበቦችን እየተጠቀሙ የሰው ገንዘብን ማራቆት የለመዱት እነዚህ ቀማኞች ውሎ እያደር ፍላጎታቸው በመጨመሩ የተነሳ ጠንከር ያለ የዘረፋ አቅድ በማውጣት ሕይወትን ሊቀይር የሚችል ስርቆትን ለመስረቅ አቀዱ።

ለዘረፋው ሥራ አመች እንዲሆን ባለፀጋዎች የሚውሉበትን ቦታ በማዘወተር ማንን ቢዘርፉ የተሻለ ገቢ ሊያገኙ እንደሚችሉ ማቀድ ጀመሩ። በላባቸው ያላመጡትን ገንዘብ በመበተን ሀብታም መስሎ በመታየት፤ ከሰዎች ጋር በመቀራረብ የተለያዩ መረጃዎችን ማሰባሰብ ጀመሩ። በዚህም ከባለፀጋዎቹ መካከል አምስቱን ለይተው ብዙም ዋጋ ሳያስከፍል ሊዘረፍ የሚችል ሰው ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። በቀላሉ እጅ ውስጥ ለማስገባትም አለኝ የሚሉትን ምርጥ አማራጭ ሁሉ ለመጠቀም ወሰኑ።

የተጠናው የዘረፋ እቅድ

አቶ ኪዳነ ማሪያም ወልዱ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ተሠማርተው ሀብት ያካበቱ ሀብትን በሀብት ላይ ለመደረብ ሥራን አማራጫቸው ያደረጉ ታታሪ ግለሰብ ናቸው። እኝህ ሰው ለመዝናናት ፀጥ ያሉ ውስኪ ቤቶችን ምርጫቸው ያደርጉ ነበር።

ሁካታ የበዛበት ቤት ምቾት ስለማይሰጣቸው በዝግ የሚያስጠቅሙ ትልልቅ ውስኪ ቤቶች ውስጥ ያጠመደ አያጣቸውም ነበር። ያኔ ለዘረፋ እቅዳቸው ምቹ ሰው ሲፈልጉ የነበሩት የዘረፋ ቡድን አባላት ወደ ውስኪ ቤቱ ሲመላለሱ ነበር ያገኟቸው። ወዳጅ መስለው ቀርበው የሀብታቸውን ልክ ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ ለዘረፋ ምቹ እቅድ ያወጡላቸው ጀመር።

ለቀናት አቶ ኪዳነ ማሪያም ቤት አካባቢ የመሸገው የዘረፋ ቡድን በምን ሰዓት ጥበቃ እንደሚላላ በማጥናት ለዘረፋ ምቹ የሆነውን ሰዓት አጥንተው ጨረሱ። ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ለጉዳዩ ማስፈፀሚያ የሚሆን ግብዓት ለማሟላት መዘጋጀት ጀመሩ።

የዘረፋ ቡድኑ አባላት የተጠናውን እቅድ አዘጋጅተው ከጨረሱ በኋላ ነበር አልባሳትን። የጦር መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪን ማዘጋጀት የጀመሩት። ዛሬ ላይ ዝግጅቱ ተጠናቆ ለዘረፋ የሚሆን ሙሉ ትጥቅ ያሟላ የማፊያ ቡድን ተፈጠረ። ይህ ቡድን ሕልሙን እውን ለማድረግ በጊዜ ተኝቶ በሌሊት ለመንቃት ተዘጋጅቷል።

ዘረፋ

ሙሉ ትጥቁን ያሟላው የዘረፋ ቡድን በደንብ የተዘጋጀ እራት በልቶ መጠጥ ብጤም ቀማምሶ ሙሉ ትጥቁን አሟልቶ ግዳዩን ወደ ሚጥልበት ቦታ ተንቀሳቀሰ። እለቱ ታኅሣሥ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር። በግምት ከሌሊቱ 9፡30 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 መሪ 20 ሜትር ጎላጉል አጠና ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የተገኘው ይህ ቡድን የሥራ ክፍፍል አድርጎ ዘረፋ ለመፈፀም ወደ አቀደው ቤት ተጠጋ።

የዘራፊው ቡድን የማይገባ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ሽጉጥ፣ ጩቤ፣ እና ገጀራ ይዘው የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ግቢ በር ገንጥለው ገቡ። በቡድንና በኃይልና በብዛት ጥቁር ልብስ ለብሰው ነበር በር ገንጥለው ወደ ግቢው ውስጥ የገቡት። በኃይልና በብዛት የገቡትን ዘራፊዎች የተመለከቱት ተበዳዮች በድንጋጤ ከመቆም በስተቀር እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል ምንም ጥረት ማድረግ አልቻሉም ነበር።

በኃይል ወደ ቤቱ ውስጥ የገቡት ዘራፊዎች ውስጥ የነበሩትን ሰዎች በማስፈራራት ያለውን ንብረት በሙሉ በመለቃቀም ቀድመው ባዘጋጁት ተሽከርካሪ ላይ መጫን ጀመሩ። በዘረፋቸውም አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 365 ሺ ብር የሚያወጣ የተለያዩ ንብረቶችን በመውሰድ ከአካባቢው ለመሰወር መታተር ጀመሩ።

ከዚህም በተጨማሪ ከላይ በተገለፀው ቀንና ቦታ ከሌላኛው የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ውስጥ የግቢውን የአጥር ሽቦ በከተር ቆርጠው በመግባትና በማስፈራራት አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 1 ሚሊዮን 13 ሺ 200 ብር የሚያወጣ የተለያዩ አይነት ንብረቶችን በመውሰድ ከአካባቢው ተሰወሩ።

ዘረፋው እንደተፈፀመባቸው ከድንጋጤ ያቸው መለስ ያሉት ተበዳዮች ለፖሊስ ጉዳዩን ያመለከታሉ። ፖሊስም ጥቆማው ከደረሰው ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ዘራፊዎች ዱካ መከታተል ጀመረ። እልህ አስጨራሽ ከሆነ ክትል በኋላ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

የፖሊስ ምርመራ

1ኛ አቤል ኢሳያስ ተስፋዬ፣ 2ኛ አቤል አዋየው አሊ፣ 3ኛ አቤል ግደይ በረኸ፣ 4ኛ ሀብታሙ ወንድሙ ገብረየስ፣ 5ኛ ዳንኤል ጎይቶም ተስፋዬ፣ 6ኛ ናትናኤል ግደይ በረኸ፣ 7ኛ ዳንኤል ዮሐንስ ገ/መድን፣ 8ኛ ዮናስ ፍፁም ከበደ፣ 9ኛ ናትናኤል ረዳኢ ኪሮስ የተባሉ ዘጠኝ ተከሳሾች በሁለት ክሶች የተከሰሱ ሲሆን፣ በ1ኛ ክሳቸው ላይ ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ታኅሣሥ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 መሪ 20 ሜትር ጎላጉል አጠና ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን ሽጉጥ፣ ጩቤ፣ እና ገጀራ ይዘው የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ግቢ በር ገንጥለው ገብተዋል።

ከዛም ወደ ውስጥ በመግባት ተበዳዮችን በማስፈራራት አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሺ ብር የሚያወጡ የተለያዩ ንብረቶችን ወስደዋል። ከዚህም በተጨማሪ በ2ኛ ክስ ላይ ከላይ በ1ኛ ክስ በተገለፀው ቀንና ቦታ ከሌላኛው የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ውስጥ የግቢውን የአጥር ሽቦ በከተር ቆርጠው በመግባትና በማስፈራራት አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 1 ሚሊዮን 13 ሺ 200 ብር የሚያወጣ የተለያዩ አይነት ንብረቶችን በመውሰድ ከአካባቢው ተሰውረው ፖሊስ ባደረገው ክትትል የተያዙ በመሆናቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

የክርክር ሂደቱ የታየውም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ሲሆን በችሎቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው እንዲያሰሙ ቀጠሮ ቢሰጣቸውም የመከላከያ ምስክር ባለማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ የመከላከል መብታቸው ታልፎ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል።

 

ውሳኔ

በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ መሠረትም 1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ፣ 2ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በሌሉበት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት፣ 9ኛ ተከሳሽ በሌለበት በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት፣ 3ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች በሌሉበት በ16 ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ቀርበው በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

አስመረት ብሥራት

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You