የምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ለስኬት እንዲበቃ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ በመንግሥት በኩል የተወሰዱ መልካም እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አለመግባባቶች፣ የፖለቲካ ልዩነቶች፣ የእርስበርስ ግጭቶች፣ ሌሎችም ሀገርን የሚያናጉ የፀጥታ ችግሮች ተከስተዋል። ችግሮቹ አድገውና ጎልብተው የኋላ ኋላ ሀገሪቷን ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ከትተዋል፡፡

በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ሀገሪቷን ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል። ይኸው ጦርነት ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ፣ መፈናቀልና ስደት ብሎም ለተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ሆኗል። በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም እንዲሁ በተዛቡ ትርክቶች እና ጀብደኝነት በተፈጠሩ ምክንያቶች የሰላም ማጣቶች ተከስተዋል።

እነዚህን ችግሮች ጨምሮ እንደሀገር ይዘናቸው የምጓዛቸውን የአለመግባባትና የግጭት ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለዘለቄታው በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋቁሟል። ኮሚሽኑ እስካሁን በተጓዝንባቸው የታሪክ ጅረት ውስጥ በዜጎች መካከል በልዩ ልዩ መልኩ የተፈጠሩ ቅራኔዎችንም ጭምር ለመፍታት ዓላማ የሰነቀ ስለመሆኑም ተነግሯል።

አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ሁለት አመት አገባዶ ወደ ሦስተኝ አመቱ እየተጓዘ ነው። በእነዚህ አመታት ውስጥ ከምስረታው ጀምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራና ለምክክሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዚህም ቀደም ሲል በሌሎች ሀገራት ተሞክረው ውጤት ያመጡና በዚያው ልክ ደግሞ ባለመስማማት የተጠናቀቁ ሀገራዊ ምክክሮች በምን ምክንያት ሊከሽፉ እንደቻሉና ያለውጤት ሊጠናቀቁ እንደቻሉ ተሞክሮ ወስዷል።

ምክክሩ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በተከተለና ሁሉንም ዜጋ ባሳተፈ፤ ሁሉንም አካል ሊያረካ በሚችል መልኩ እንዲካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ ሁኔታ ሥራዎች (ከትግራይና ከአማራ ክልል ውጪ) በመላው ሀገሪቱ እያከናወነ ነው። በዚህም ዋናውን ሀገር አቀፍ ምክክር ለማካሄድ የሚያስችሉ ጠቃሚ ግብአቶችን ለመሰብሰብ እንደቻለ ይታመናል።

በዚህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፤ ሴቶች፣ ወጣቶች የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ መምህራንና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ለዚህም የሚሆን የተሳታፊነት መስፈርቶችን ኮሚሽኑ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

በምክክር ሂደቱም የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ተባባሪ አካላት ሆነው እንደሚሠሩም ተገልጿል፡፡

በፌዴራል ደረጃ በተመሳሳይ የአጀንዳ መሰብሰብ ሥራ እንደሚከናወን፤ በተመሳሳይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን በዚሁ የምክክር አጀንዳ ውስጥ እንዲካተቱ የማድረግ ሥራ እየሠራም ነው ፡፡

ኮሚሽኑ ሥራው ከአንዱ ምዕራፍ ወደሌላኛው ምዕራፍ እየተሸጋገረ አሁን ላይ፤ የአጀንዳ ማስባሰብ ጀምሯል፤ በዚህም ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ምክንያት የሆኑ አሁናዊ እና የአደሩ ችግሮችን አንጥሮ በማውጣት በውይይት መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በተለያዩ ጊዜያት ኅብረተሰቡን ወደ ግጭት የመሩ አለመግባባቶች፣ ቅራኔዎችና ሌሎችም የፀጥታና የሰላም መድፍረሶች ምክንያት ጉዳዮችን ነቅሶ ለሀገራዊ ምክክሩ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ይጠበቃል፡፡

ኮሚሽኑ ባለው አቅም በብዙ ቁርጠኝነት እስካሁን ባለው ሂደት የሚያስመሰግን ሥራ እየሠራ ቢሆንም፤ በሀገሪቱ እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች ለሥራው ፈተና ሆነዋል። ለዚህ ደግሞ በሰላም ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት በግጭትና ሰላም ማደፍረስ ሥራ ተጠምደው ያሉ አካላት እጃቸውን መሰብሰብ፤ ሕዝቡ በየጊዜው ለሚያነሳቸው የሰላም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በቅርቡ ከተሳታፊዎች ልየታ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ መሸጋገሩ እንደ አዎንታዊ እርምጃ የሚታይ ቢሆንም፤ ወደ ዋንኛው የውይይት ምዕራፍ ገብቶ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመፍታትና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ጥርጊያ መንገድ ማመቻቸት እንዲችል የመላውን ኅብረተሰብ ተሳትፎና የፖለቲካ ቡድኖች ይሁንታና ትብብርን ይሻል፤ ከብዙዎችም ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ቢያንስ ቢያንስ ሕዝቡ በችግሮቹ ዙሪያ እንዲወያይ ዕድል ይፈጥራል የፖለቲካ ቡድኖችና ቅር የተሰኙ አካላት በችግሮቻቸው ዙሪያ እንዲያወሩና ለችግሩም ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጁ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሀገሪቱ በልዩ ልዩ መልኩ ለተፈጠሩ አለመግባባቶችና መቋሰሎች ማከሚያ ይሆናል ተብሎም ይገመታል፡፡ ለዚህ ታዲያ መፍትሔው በሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል እጅ ላይ ነው፡፡ ሁሉም አካል ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን ሠርቶ በሀገሪቱ የሚፈለገው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ከራሱ ከኮሚሽኑ፣ ከመንግሥት፣ ከልዩ ልዩ የፖለቲካ ቡድኖችና ከሕዝቡ ብዙ ይጠበቃል። የኃይል አማራጭን ወስደው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች በዚህ ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁነታቸውን ከወዲሁ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ሕዝቡም ቢሆን ይህን ሀገራዊ ምክክር በእጅጉ የሚፈልገው ነውና ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የራሱን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል።

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You