የአንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፡- የተወዳጁና አንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፡፡

የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የሙያ አጋሮች እንዲሁም የሙያ አድናቂዎች በተገኙበት ትናንት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ተፈጽሟል፡፡

አርቲስት ጌታቸው ካሳ ከአባቱ አቶ ጸጋዬ መኮንንና ከእናቱ ከወይዘሮ ሳንካምየለሽ ደጀኔ ጥር 3 ቀን 1939 ዓ.ም በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል አካባቢ መወለዱን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

ወላጅ አባቱ ሙዚቃ ውስጥ እንዳይገባ ከገባም በስማቸው እንዳይጠራ በመከልከላቸው፤ አርቲስት ጌታቸው ለሙዚቃ ካለው ፍቅር የተነሳ የአባቱ ስም በባለቤቱ አባት ስም ቀይሮ ወደ ሙዚቃው ዓለም በይፋ የተቀላቀለ አርቲስት ነበረ።

አርቲስት ጌታቸው ካሳ፤ ሀገሬን አትንኳት፣ አዲስ አበባ፣ ሳይሽ እሳሳለሁ፣ ልውሰድሽ አንድ ቀን፣ የከረመ ፍቅር፣ እመኛለሁ፣ ትዝ ባለኝ ጊዜ በሚሉት ዘፈኖቹ ይታወቃል፡፡

ድምጻዊ ጌታቸው በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የሐረር ፖሊስ ኦርኬስትራ የተቀላቀለ ሲሆን፤ አሃዱ ያለበት አዝመሪኖ የኤርትራ ትግሪኛ ሙዚቃ ለሙዚቃ የተሻለ ዝንባሌ እንዲኖረው አስችሎታል።

ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የራሱ የሙዚቃ ፈጠራ የታየበትን «ሳይሽ እሳሳለሁ» የተሰኘ ሙዚቃው በጊዜው የነበሩ ሸክላ ሙዚቃ አሳታሚዎች ቀልብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎት እንደነበርም ይነገራል፡፡

ከመድረክ ሥራዎቹ በተጨማሪ በበርካታ ምሽት ክበብ ሙዚቃን የተጫወተው አርቲስቱ፤ ከሙዚቃ ጎን ለጎን ክራርና ፒያኖ ይጫወት እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

ለ28 ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካን ሀገር ቢያደርግም ለሀገሩ ከነበረው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ዜግነቱን ሳይለውጥ ወደ እናት ሀገሩ መመለስ መቻሉ የሙያ አጋሮቹ በነበረው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ ተናግረዋል።

በተጨማሪም አርቲስቱ ለ50 ዓመታት በመዚቃ ውስጥ ማሳለፉንና ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ማደግ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ማደግ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት አርቲስት ጌታቸው ካሳ፤ የመጀመሪያውን በጥበቡ በለጠ የተገጠመው እመኛለሁ የተሰኘውን ዜማ ለመድረክ አብቅቶ በሕዝብም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡

ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለደ በ77 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You