በቢሾፍቱ ከተማ ዲጂታል የአድራሻ  ሥርዓት ተተገበረ

ቢሾፍቱ:- በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ፕሮጀክት ተጠናቆ በቢሾፍቱ ከተማ ተግባራዊ መደረጉን የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ትናንት አስታወቀ።

የዲጂታል ሥርዓቱን ያስጀመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በመርሐግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ የአድራሻ ሥርዓት ሳይኖር ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የማይታሰብ ነው።

ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ማንኛውንም አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

በ73 ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ የቢሾፍቱ ከተማ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት በዚህ መሠረት የተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው፤ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓቱ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ኢንስቲትዩቱ ከሚተገብራቸው ለውጥ አምጪ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።

የአድራሻ ሥርዓቱ ከፍተኛ በጀት፣ የከተማ መስተዳድሮችን ቁርጠኝነትና የነዋሪዎችን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ሌሎች ከተሞች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓቱ የቱሪዝም ከተማ ለሆነችው ቢሾፍቱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ነው። ለከተሞች እድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርና እንገነባለን ለምንለው ስማርት ሲቲ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩቱ የዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ሥራ አስኪያጅ አድማሴ ገበየሁ፣ የቢሾፍቱ ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ከ 10 ሺህ በላይ ቤቶች ማካተቱን አመላክተዋል፡፡

ሀገርኛ ቋንቋዎችን መሠረት አድርጎ የተሠራ በመሆኑ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ትናንት ተመርቆ ሥራ የጀመረው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በከተማዋ የሚገኙ ተቋማትን እና የመኖሪያ ቤቶችን ትክክለኛ መገኛ ሥፍራ በማመላከት ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማቅለልና ለማቀላጠፍ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የተቀላጠፈ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ጥገና አገልግሎት ለመስጠት፣ ፈጣን የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለማድረስ፤ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማዘመን እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ግብይትን እና ማኅበራዊ አገልግሎትን ለማሳለጥ መሠረት ይሆናል ተብሏል።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በቢሾፍቱ ከተማ የጀመረውን ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ ሁሉንም ከተሞችና ገጠሮች ለመሸፈን ውጥን ይዟል።

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አመራሮች፣ ከንቲባዎች፣ አባገዳዎች እና የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን  የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You