በዓለማችን የሚገኙ ሀገራት ፈርጀ ብዙ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማድረግ የጋራ ጉዳዮቻቸውን ይከውናሉ፤ አለመግባባት ሲፈጠርም በውይይትና በድርድር ይፈቱታል፡፡ ሁልጊዜ የዲፕሎማሲ ሥራ ስኬታማ ላይሆን ስለሚችል ወደ ጦርነትም የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከጦርነት በኋላ የሰላም መፍጠሪያው ደግሞ ያው ዲፕሎማሲ ነው። ዲፕሎማሲ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ቅርጽ ሊኖረው የሚችል ሲሆን መንግሥታት እንደየፈርጁ ይጠቀሙታል፡፡
የዲፕሎማሲ ሥራ መደበኛ ከሆነው በተጨማሪ በበርካታ አካላት ሊከናወን ይችላል፡፡ ለአብነት ያክል በሃይማኖት ተቋማት፤በአሰላሳይ ተቋማት (Think tank)፤ በሲቪክ ማህበራት፤በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የንግዱ ሴክተር ውጭ ሀገር ከሚገኙ አቻ ተቋማት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር የጋራ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡
አንዳንድ ተመራማሪዎች የዲፕሎማሲ ተግባር የሚያከናውኑትን እስከ ዘጠኝ መደድ (track) ያደርሱታል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚያከናውኑትን አካላት በሁለት ብቻ እየከፈሉ የሚተነትኑትን ምሁራን ጥናት የምጠቀም ሲሆን እነዚህም በመንግሥት የሚከናወነውን መደድ አንድ በማለት፤ መንግሥታዊ አካላት ባልሆኑት የሚከናወነውን ዲፕሎማሲ መደድ ሁለት በማለት ይሆናል፡፡
መንግሥታት የዲፕሎማሲን ሥራ የሚመሩበት ዋናው ተቋም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው። በመሆኑም መንግሥት ከሌላ መንግሥት ጋር የሚያከናውነው ዲፕሎማሲ መደድ አንድ ዲፕሎማሲ ሲሆን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የሚያከናውኑት ዲፕሎማሲ መደድ ሁለት ዲፕሎማሲ (Track 2 Diplomacy) ይባላል፡፡
እነዚህ ሁለት የዲፕሎማሲ መደዶች(Track1 and Track2 ) በየራሳቸው መቆምና ተነጣጥለው መስራት የሚችሉ ሲሆን፤ በሁለቱ መካከል የቅንጅት ሥራ የሚያከናውኑ ከሆነ ደግሞ መደደ አንድ ነጥብ አምስት ዲፕሎማሲ (Track 1.5 Diplomacy) ይባላል:: የዚህም ጽሁፍ ትኩረት መደድ አንድ ነጥብ አምስት ዲፕሎማሲ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ 1.5 ዲፕሎማሲ በሚል ይጠቀሳል።
የ1.5 ዲፕሎማሲ ፅንሰ ሃሳብ በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ዲፕሎማሲ ብዙ ክፍተቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ በመሆኑም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የዲፕሎማሲ ሥራ ቢታገዝ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚል መነሻና እሳቤ የያዘ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በሁሉም የዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መግባት አለባቸው ማለት ሳይሆን በተመረጡ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የመንግሥትን የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲያግዙ ሊደረግ እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጣል፡፡
ለአብነት ያክል የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ግንባታ፣ በዘላቂ ልማት እና በዓለም አቀፍ ጤና ጉዳዮች ላይ ያሉ ብዙ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የትብብር እና አካታች አካሄድ ስለሚፈልጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የአካባቢ ማህበረሰቦች፣ የአካባቢው ተወላጆች እና ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ተዋናዮች ብዙ ጊዜ ጠቃሚ እውቀት እና አመለካከቶች ስላላቸው ለተወሳሰቡ ዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ።
በዚህ የዲፕሎማሲ አሰራር የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ባለሙያዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች በተለያዩ መንገዶች ማለትም በምክክር፣ኮንፈረንስ እና ወርክሾፖች ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት እና ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያገለግል ነው። ይህ አካሄድ ከመደበኛው የመንግሥት የዲፕሎማሲ ተዋናዮች ባሻገር የተለያዩ ድምፆችን እና አመለካከቶችን በማካተት የዲፕሎማሲያዊ ሂደቶችን ውጤታማነት እና አካታችነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ግንዛቤያቸውን፣ ምርምሮችን እና ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን ለመደበኛዎቹ ዲፕሎማቶች የሚያካፍሉበት መድረክ ይፈጥራል። ይህ የእውቀት ልውውጥ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን የሚያበለጽግ እና የበለጠ በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ ለማድረግ ያስችላል።
በጋራ ተግዳሮቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ተሳትፎን በማድረግ የትብብር እና የጋራ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል። የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ይሰሩ እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአካባቢ ጥበቃ፤ በሳይንስ፤ ስደት እና ወዘተ የሥራ መስኮች ውስጥ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ እውቀትና ተሞክሮ ስለሚኖር ለዲፕሎማሲ ግብአት እውቀታቸውን መጠቀሙ መልካም ነው፡፡
በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ቅንጅት የሚከናወን ዲፕሎማሲ የአካባቢ ማህበረሰቦች ድምጽ እና ስጋቶች ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ ከታች ወደ ላይ (Bottom-Up Approach) ያለውን አካሄድ ትኩረት ይሰጣል። መንግሥት ከመንግሥት ጋር የሚያደርገው ዲፕሎማሲ በአብዛኛው ከላይ ወደታች የሚፈስ ነው (Top-Down Approach)::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ውሳኔዎች በአካባቢው ማህበረሰቦች ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው እና የእነሱ ተሳትፎ ውጤታማ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማግኘት ወሳኝ ሊሆን ይችላል። መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር 1.5 ዲፕሎማሲ የእነዚህን ማህበረሰቦች ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ለማስገባት ያስችላል፡፡ ይህ አሰራር በመደበኛው የዲፕሎማሲ መስመሮች ውስጥ ላይገኙ የሚችሉ የፈጠራ አስተሳሰብን፣ ሙከራዎችን እና አማራጭ አመለካከቶችን ለማየት ያግዛል።
መደድ 1.5 ዲፕሎማሲ በሀገሮች መሀከል የሚከሰትን ግጭት ለማስቆም ይረዳል፡፡ በተለይ መንግሥታዊ የዲፕሎማሲ መስመሮች በፖለቲካ ውጥረቶችና ግጭቶች እንዳይደናቀፍ ሊያግዝ ይችላል። ይህ ዲፕሎማሲ የግጭት አፈታት ጥረቶች አማራጭ የውይይት እና የድርድር መንገዶችን በማቅረብ ሚና ይጫወታል።
ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር በፖለቲካ ማነቆዎች ወይም መተማመን ማጣት ሊደናቀፍ በሚችልበት ሁኔታ፣መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በ1.5 ዲፕሎማሲ ማሳተፍ መደበኛ ላልሆኑ ውይይቶች፣የመተማመን ግንባታ እርምጃዎች እና የሽምግልና ጥረቶች እድልን የመፍጠር እና የመግባባት መድረኮችን ማመቻቸት ይችላል። ይህ የሰላም ግንባታ ሂደቶችን ለማከናወን እና ግጭቶችን ለመፍታት አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ቅንጅት የሚከናወን ዲፕሎማሲ የዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችንና ክፍተቶችን ለመከታተልና ለመገምገም አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ውጤታማነት ለመገምገም እና መሻሻል ያለባቸውን ቦታዎች ለመለየት አመለካከቶችን፣ መለኪያዎችን እና የግምገማ ማዕቀፎችን መጠቀምን ይጠይቃል። ክትትል እና ግምገማ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት፣ ካለፉት ተሞክሮዎች መማር እና ዲፕሎማሲያዊ ስልቶችን በማጣጣም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያስችላል።
የመደድ 1.5 ዲፕሎማሲ አሰራር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ውስጥ ሊከወን የሚችል እንደሆነ ከላይ ተጠቅሷል፡፡ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማሳያ ከሆነው ውስጥ አንዱ የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ የሚከሰትን አደጋ ለመከላከል የፓሪሱ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡ ይህ ዲፕሎማሲ ከስር ወደ ላይ (Bottom-Up Approach) ያለውን አካሄድ የተከተለ ነው፡፡
በመሆኑም የ1.5 ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 12 ቀን በ2015 ከአንድ መቶ ዘጠና ሀገሮች በላይ በሚሆኑ መንግሥታት የፀደቀው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ነው። የፓሪሱ ስምምነት የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በማሳተፍ ዲፕሎማሲያዊ ሂደቱ ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ፈተና ለመቅረፍ ጥረት የተደረገበት ነው።
በዚህ ስምምነት ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉ በካይ ጋዞችን እንዲቀንሱና የዓለም ሙቀት መጨመርን እንዲቆጣጠሩ የተስማሙበት ነው፡፡ ይህም የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እቅድ (Sustainable Development Goals) ስኬት ለማምጣት አንዱ የአየር ንብረት ቀውስን መከላከል በመሆኑ ነው፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ 1.5 ዲፕሎማሲ በተለይ ከሀገር አቀፍ ድንበሮች ባሻገር ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጠቃሚ ነው። እንደ ፍልሰትና ስደት፣ ሽብርተኝነት፣ የሳይበር አደጋዎች እና ወረርሽኞች ያሉ ጉዳዮች በበርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል የትብብር ጥረቶችን ይፈልጋሉ። 1.5 ዲፕሎማሲ የመንግሥት ያልሆኑ ተዋናዮች በእውቀታቸው እና በኔትወርኩ አማካኝነት እነዚህን ውስብስብ ፈተናዎች በብቃት ለመወጣት ጠቃሚ ግንዛቤዎችን እና ግብአቶችን ማበርከት ይችላል።
በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ቅንጅት የሚከናወን ዲፕሎማሲ ተጠያቂነትን እና ግልጸኝነትን በዓለም አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲኖር ያግዛል። ሰፋ ያሉ ተዋናዮችን በማሳተፍ የዲፕሎማሲያዊ ሂደቶችን መመርመር እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋናዮች ብዙውን ጊዜ የተለያዩ አመለካከቶችን በማምጣት ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነት እና ለሰብአዊ መብቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ደረጃዎች መጠበቅ ያግዛሉ።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መደበኛውን ዲፕሎማሲ በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በማቴሪያል፣ በቴክኖሎጂ፣ አጋርነትን በማስፋት፣ የሕዝብን ድጋፍ በማሰባሰብ፣ ተጽእኖ በመፍጠር እና ወዘተ ድጋፎችን በመስጠት የተሳካ ዲፕሎማሲ ለማከናወን ያግዛሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሁሉም የዲፕሎማሲ ተግባራት ላይ እንዲገቡ ሳይሆን በተጠኑና በተመረጡ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ።የዲፕሎማሲ ሥራም ምስጢራዊነት ከሚጠይቁ የሥራ መስኮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው እንደመሆኑ መጠን 1.5 ዲፕሎማሲ ሲከናወን የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማግኘትና በምስጢራዊነት መካከል ያለውን ሚዛን በጥንቃቄ መጠበቅና መምራት ያስፈልጋል፡፡
መደድ 1.5 ዲፕሎማሲ ለኢትዮጵያ ያለው ጥቅም በርካታ ነው፡፡ በተለይ የሀገራችን ወጣቶች በየአረብ ሀገር ለሚደርስባቸው ችግር መፍትሄ በመስጠት በኩል መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአየር ንብረት ጥበቃ፤ በሰላምና ጸጥታ ተግባር፤ በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች፣ በሳይንስ ዲፕሎማሲ፤ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፤ በኢኮኖሚና ፐብሊክ ዲፕሎማሲና ወዘተ ዙሪያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሳተፉ ማድረጉ በመንግሥት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም መደድ 1.5 ዲፕሎማሲ ሥራ የሚያስፈልጉባቸው የዲፕሎማሲ መስከች በጥናትና ምርምር በመለየትና ስትራቴጂ በማዘጋጀት መተግበር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ አሰራር አንዱ በሥራ ጫና ሲደክም ሌላው ተመልካች የማይሆንበት በመሆኑ የትብብር መንፈስ መፍጠር፤ የባለቤትነትን እና ያገባኛል ስሜትንም መፍጠር የሚችል በመሆኑ ፈርጀ ብዙ ዲፕሎማሲ (holistic diplomacy) ለማከናወን ያግዛል፡፡
ለማጠቃለል ያህል 1.5 ዲፕሎማሲ ኦፊሴላዊ ዲፕሎማሲ ክፍተት ለመሙላት እና ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ያግዛል እንጂ የመንግሥት ለመንግሥት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን አይተካም፡፡ ሆኖም ግን በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ትብብርን፣ ውይይትን እና የጋራ መግባባትን ለማስፋፋት፣ ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ለመፍታት፣ ሕዝባዊ ድጋፍን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ለማሰባሰብ ፣ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ይጠቅማል።
የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ሬሚታንስን ለመጨመር፣ የአደጉ ሀገራትን የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም፣ የዲፕሎማሲ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሕዝብ ግፊትን ለመፍጠር፣ የእውቀት አቅርቦትን ለመፍጠር፣ አካታችነትን ለማሳደግ፣ የፈጠራ ዘዴዎችን ለዲፕሎማሲ ለመጠቀም፣ በዲፕሎማሲ ዘርፍ አቅም ግንባታ ለማስፋት ይረዳል።
መንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት መካከል ድልድይ በመገንባት የሥራ ቅንጅትንና ትብብርን ለመፍጠር፣የመረጃ ልውውጥን ለማስፋት፣ የሀብት ማሰባሰብ ለማገዝ፣አዳዲስ መፍትሄዎችን ለመቃኘትና ለመጠቀም፣ የሀገር በቀል የዕውቀት ሥርዓቶችን ለዲፕሎማሲ ሥራ እንደግብአት ለመጠቀም እና ወዘተ ያግዛል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ 1.5 ዲፕሎማሲ አሰራርን በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ መተግበር የሀገራችንን የዲፕሎማሲ ተግባር አንድ እርምጃ ወደፊት ይወስደዋል የሚል እምነት አለኝ ፡፡
በመላኩ ሙሉዓለም ቀ.
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስልጠና ዳይሬክተር ጄኔራል
melakumulu@yahoo.com
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016