የአፍሪካን ብልጽግና ለማረጋገጥ …

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት አንግቦት ከነበረው አባል ሀገራቱን ከቅኝ ገዥዎች ነፃ የማውጣት ተልዕኮ አንስቶ እስከ ወቅታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር በርካታ ስኬቶች አስመዝግቧል፡፡

ኅብረቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም የዓለም ኢኮኖሚንና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ አንድ አቋም መያዙ ከኅብረቱ ታሪክ ተጠቃሽ ስኬቶች አንዱ ነው፡፡ የአየር ንብረት ተፅዕኖውን ለመላመድና ለመቋቋም የሚረዳትን ተገቢውን ክፍያ እንድታገኝ ኅብረቱ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት እንዲሁም የአፍሪካ ድምጽ የሚጎላበት ሚዲያ እንዲኖር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችም በአዎንታዊ የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ኅብረቱ ከስድስት አስርተ ዓመታት በላይ ጉዞው ሊሻገራቸው ያልቻሉ በርካታ ፈተናዎች እንዲሁም መመለስ ያልቻላቸው የጎሉ የቤት ሥራዎች እንዳሉም መካድ አይቻልም፡፡

በበርካቶች ዘንድ ኅብረቱ ተደጋግሞ ከሚወቀስባቸው ጉዳዮች አንዱ የማስፈፀም አቅሙ ያን ያህል የተጠናከረ አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ አንደኛው ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ከአባል ሀገራት የሚጠበቀውን ገንዘብ በአግባቡ መሰብሰብ አለመቻሉ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የኅብረቱ የ2023 በጀት 654 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን በዛምቢያ በተደረገ ጉባኤ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ60 በመቶ የሚልቀው በጀት ከለጋሾች እንደሚሰበሰብ በወቅቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህም ኅብረቱ ከራሱ አቅም ይልቅ የሌሎችን እጅ ጠባቂ እንዳደረገው በርካቶች ያምናሉ፡፡

ኅብረቱን ለዚህ ከዳረጉት ዋነኛው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ጥቂት የማይባሉት አባል ሀገራቱ ከዓመታዊ የሀገር ውስጥ ገቢያቸው ከአንድ በመቶ ያነሰውን እንኳን ማዋጣት አለመቻላቸው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አፍሪካ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር በሙስና እንደምታጣ ጥናቶች ያሳያሉ ፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 በመቶ የሚሆነውን እንኳን ማዳን ቢቻል የኅብረቱን የ2 ዓመት ወጪ መሸፈን ይቻላል ብለው የሚቆጩ አፍሪካውያን ብዙ ናቸው፡፡

አህጉሪቱ ዛሬም ሙስናን መሻገር አለመቻሏ፣ የእርስ በርስ ግጭቶች በሚፈለገው ደረጃ ማስቆም አለመቻሉ፣ ድህነት አሁንም የአህጉሪቱ ቀንደኛ ጠላት መሆኑ፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ተደራሽ አለመሆንና ጥራቱም የተጓደለ መሆን፣ በኅብረቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች አፈጻጸም የተለያየና የሚፈለገውን ውጤት ከማስመዝገብ አኳያ ውስንነት ያለበት መሆኑ የኅብረቱና አባል ሀገራት ጉድለት ሆነው ቀጥለዋል።

ዛሬ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ከስኬቱም ሆነ ከልምዱ ለመማር የሚያስችለው ከግማሽ ክፍለ ዘመን የበለጠ የዕድሜ ባለፀጋ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም የወደፊት አቅጣጫውን ሲተልም ያለፈውን ጉዞ ዞር ብሎ ማየት፤ የቆመበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቆ መረዳትና መጪውን አቅርቦ ማሰብ ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት፣ ተሳትፎን ማሳደግ፣ የገቢ አቅምን ማጎልበት ወሳኝ ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ከነጉድለቶቹም ቢሆን ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተሻለ አደረጃጀትና አሠራር እንዳለው ይታመናል፡፡ ካለንበት ዘመን አኳያም ሊኖረው ይገባል፡፡ ግን በቂ ነው ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ሁሌም ዘመኑን የዋጀ የተሻለ አሠራርና አደረጃጀት መዘርጋት እንዳለበት መካሪ አያሻም፡፡

ለምሳሌ በሀገሮች ጣልቃ ያለመግባት መርህን በማሻሻል ኅብረቱ በመፈንቅለ መንግሥት የመጡ ቡድኖችን በአባልነት አይቀበልም፣ ነገር ግን በአፍሪካ አሁንም ድረስ የእርስ በርስ ግጭት የሚታይባቸው ሀገሮች ጥቂት እንዳልሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ችግር ሊቀርፍ የሚችልና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አደረጃጀትና አሠራር ሊኖረው ግድ ይላል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ አውትሉክ መረጃ እንደሚያስቀምጠው፤ በአፍሪካ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት ያሉ ወጣቶች ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ከ70 ከመቶ በላይ ይሸፍናሉ፡፡ ከአፍሪካ ሕዝቦች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ወጣቶች መሆናቸውን የበርካታ ጥናቶች ውጤትን ማጣቀስ ይቻላል፡፡

የዓለም ባንክ ከዓመት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 25 የሚጠጋ ወጣቶች አሉ። ከነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚጠጉት ሥራ ፈላጊ መሆናቸው ኅብረቱ የሚጠብቀውን ከባድ ሥራ ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በዚህ ረገድ ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገ እድገትን ማበረታታት ግድ የሚለው ወቅት አሁን ነው፡፡

በአህጉሪቱ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ እሙን ነው። በተለይም ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች በአግባቡ አለመሰራታቸው ለማንም የተሸሸገ አይደለም፡፡

የአፍሪካ ኅብረትም በየሀገሮቹ ለወጣቶች ምን ያህል የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ መጠየቅን የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊያደርገው ይገባል፡፡

ኅብረቱ ሊያሳካ ያሰባቸውን ግቦች እውን ማድረግ የሚቻለው በሁሉም የነቃ ተሳትፎ መሆኑ አያጠያይቅም። በመሆኑም አባል ሀገራት ችግሮችን ከመለየት ጀምሮ እስከ ክትትልና ግምገማ ሥርዓት ኅብረተሰቡን በሁለንተናዊ መርሃ ግብሮች ማሳተፍ ይገባቸዋል፡፡

ይህ ሲደረግም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ በርካታ የፈጠራ ችሎታዎችን ማውጣትና እንደ አህጉር ችግር ፈቺ ዜጎችን መፍጠር ይቻላል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ፡፡

በአፍሪካ በየቦታው የሚታዩ የእርስ በርስ ግጭቶች መንስኤ በዋነኛነት የሕዝብ ፍላጎት አለመሟላት ነው። በተለይም የአናሳዎች መብት አለመከበር የግጭት መንስኤ ሲሆን ይታያል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየአካባቢው አስተዳደር ሕዝቡን በየጊዜው ማማከር ያስፈልጋል፡፡

አፍሪካ በእርዳታና በብድር ከምታገኘው ይልቅ በታክስ ማጭበርበርና ስወራ የምታጣው ከ10 እጥፍ እንደሚልቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የታክስ ሕጎች ክፍተት መኖርና በሙስና የተጨማለቁ ባለሥልጣናት እንዲሁም ብቃት ያለው የሰው ኃይል አለመኖር አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማሻሻል የአፍሪካን ነፃነት ማረጋገጥ እንደሚቻል የዘርፉ ምሁራን ደጋግመው ያነሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካን የእርስ በርስ ንግድ ማስፋፋት፤ የታሪፍና ቀረጥ ምጣኔን ማሻሻል፤ የወጪ ገበያ የምርት ዓይነቶችን ማስፋትና ሀገራቱን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር የየሀገራቱን የተናጠል ጥረትና የኅብረቱን አመራሮች የጋራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ጥራት ያለው ትምህርት ማስፋፋት፤ ለዚህ የሚሆን የትምህርት መሠረተ ልማት ግንባታና የግብአቶች አቅርቦት ማሟላትን ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ፤ ለዚህ የሚሆን አህጉራዊ ቁርጠኝነት መፈጠር ከአህጉሪቱ ሀገራት ሆነ ከኅብረቱ የሚጠበቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራቱን በማስተባበር ካለፉት 60 ዓመታት በላይ ያለፈበትን የውጣ ውረድ ጉዞ በማጤን የተሻለ ነገን ለመገንባትና የአፍሪካን ብልጽግና ለማረጋገጥ የአፍሪካ ሀገራት ሆነ ተቋማቸው አፍሪካ ኅብረት ከትናንቱ በበለጠ መትጋት ይኖርባቸዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016

Recommended For You