የህዝብ ሮሮ አሁንም የሚሰማበት ተቋም

ፓስፖርት ፈልገው ወይም በሥራ ምክንያት ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጎራ ካሉ ረዥም ሰልፍ እና መጨናነቅ ማየት የተለመደ ነው። የሰልፍ አሰላፊዎች ዱላም ሊያጋጥም ይችላል።

ወጣት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ልጅ ያዘሉ እናቶች እንዲሁም «ፓስፖርት ፈልገው ነው?» እያሉ እግር በእግር የሚከተሉ ሕገወጥ ደላሎችም በአካባቢው ውር ውር ይላሉ። የፓስፖርት አሰጣጥ ሂደቱን ለመመልከት በመሥሪያ ቤቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎችም ይህንን መመልከት ችለዋል፣ ሆኖም በወቅቱ መረጃ ለመሰብሰብ ያደረጉት ሙከራ በፖሊሶች ክልከላ ምክንያት አልተሳካም።

አገልግሎቱ 24 ሰዓት የፓስፖርት ህትመትና በበይነ መረብ ምዝገባ አሠራር ዘርግቻለሁ ቢልም አሁንም በርካታ ተገልጋዮችን አገልግሎቱ ደጃፍ ላይ መመልከት አልቀረም።

ተገልጋዮች ዐሻራ ለመስጠት እና ፎቶ ለመነሳት በመሥሪያ ቤቱ መገኘት ግዴታቸው በመሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በወረፋው ምክንያት ላልተፈለገ እንግልት ይዳረጋሉ። እንግልቱ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከጥሩ እንቅልፍ ተነስቶ ረዥም ሰልፍ ከመሰለፍ ይጀምራል። በሌቦች መዘረፍም የሚያጋጥም ክስተት መሆኑን ተገልጋዮች በምሬት ይናገራሉ።

ለአላስፈላጊ እንግልት እና ወጪ ተዳርገናል የሚሉ ተገልጋዮች ሃሳባቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲገልጹ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት በበይነ መረብ አማካኝነት ከተመዘገቡ ወራት እንዳለፋቸው ይገልጻሉ።

ተገልጋዮቹ አገልግሎቱ አካባቢ ወረፋ ለመያዝ ስንሞክር «እኔ ቅድሚያ ወረፋ ልያዝላችሁ ክፈሉኝ» በሚሉ ደላሎች እንዋከባለን ይላሉ። እነሱ እንደሚሉት የመሥሪያ ቤቱን ሰልፍ አሰላፊዎች ወከባና ዱላ አልፎ ውስጥ መግባት መቻል መታደል ነው።

ተገልጋዮቹ በሌሊት ለመነሳት ሲሉ በአካባቢው ለአልጋ ኪራይ ከፍለው እንደሚያድሩና ለአላስፈላጊ ወጪም እንደሚዳረጉም ይገልጻሉ። ሰልፉ ረዝሞ ወረፋ ሳይደርሳቸው ከቀረም ቅጣት እንደማይቀርላቸው ይናገራሉ።

የፓስፖርት አሰጣጥ ሂደቱ ተስተካክሏል ይባል እንጂ አሁንም ችግሮቹ እንደነበሩ ናቸው የሚሉት ፎቶ ለመነሳት በተሰጣቸው ቀጠሮ በአገልግሎቱ እንደተገኙ የሚናገሩት አቶ ቀለሙ ተረፈ (ስማቸው የተቀየረ) ናቸው።

አሠራሩ ዘመናዊ ሆኗል የሚባል መረጃ በመስማታቸው የተቀላጠፈ መስተንግዶ ጠብቀው ወደ አገልግሎቱ እንደሄዱ የሚናገሩት ተገልጋዩ፤ በአገልግሎቱ የተመለከቱት ግን በአካባቢው ያለውን በርካታ አገልግሎት ፈላጊ ሕዝብ በተገቢው መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ በዱላ በመደብደብ ሥርዓት ለማስያዝ ሲሞከር መሆኑን ይገልጻሉ።

ወደ መግቢያ በሩ ተጠግቶ መረጃ ማግኘት የማይታሰብ እንደሆነም ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በዱላ ከምደበደብ አገልግሎቱ ይቅርብኝ ብለው ተመልሰዋል። የፓስፖርት አሰጣጥ ሂደቱ ሳይዘምን እንደዘመነ አድርጎ ማስተዋወቅም ፍጹም ተገቢነት እንደሌለውና ሕዝብ በለውጥ እንዳያምን እንደሚያደርግም ይናገራሉ።

ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ጌታቸው መኩሪያ (ስማቸው የተቀየረ) በአገልግሎቱ መግቢያ በር ላይ ያለውን ረጅም ሰልፍ እና እንግልት በትዕግስት አልፈው ወደ ውስጥ ቢገቡም መልካም መስተንግዶ እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የአገልግሎቱ ሠራተኞች ቁጣ ትዕግስትን የሚፈታተን ነው።

ከጉዳያቸው ጋር ግንኙነት የሌለው ጥያቄ መጠየቃቸውን እና እናትና አባታቸው በሕይወት እንደሌሉ በመናገራቸው ከአባታቸው ወይም ከእናታቸው የትውልድ ስፍራ የቅርብ ዘመድ መታወቂያ ኮፒ ካላመጡ እንደማይስተናገዱ እንደተነገራቸው ይገልጻሉ። መታወቂያ ኮፒ የማመጣበት ምንም የስጋ ዘመድ ስለሌለኝ ከከፈልኩ በኋላ ፓስፖርት እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ ይላሉ አቶ ጌታቸው። በአገልግሎቱ ቅሬታ የሚቀርብበት አሠራርም በግልጽ እንደሌለ በምሬት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም አጠቃላይ የቀረቡትን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ የተቋሙን የሥራ ኃላፊ ለማነጋገርና ለተገልጋዮች በቂ መረጃ ለመስጠት በስልክ፤ በአካልና በደብዳቤ ጭምር ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም የተቋሙ ኃላፊ ስለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም። በመጨረሻ ግን የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳሬክተር ወይዘሮ ማስተዋል ገዳ ምላሽ ሰጥተውናል።

ወይዘሮ ማስተዋል ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት በክብር መስተናገድ እንዳለባቸው ያምናሉ። ተገልጋዮችን በአግባቡ ባለማስተናገድ የዲሲፕሊን ችግር ያለባቸው ሠራተኞች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ይገልጻሉ። በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ተገልጋዮች ቅሬታ ሲኖራቸው ቅሬታ ለተቋሙ ማቅረብ አለባቸው ይላሉ። ለተቋሙ ሠራተኞች ደንበኞችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ሥልጠናም እንሰጣለን ይላሉ ወይዘሮ ማስተዋል።

ዳይሬክተሯ ተገልጋዮች አዲስ ፓስፖርት ፈልገው በድረ ገጽ ሲያመለክቱ ፎቶግራፍ የሚነሱበትን እና ዐሻራ የሚሰጡበትን ቀንና ሰዓት የሚያሳውቅ በመሆኑ ተገልጋዮች በሰዓቱ ብቻ ቢመጡ ሰልፉ ሊቀንስ እንደሚችል እንዲሁም የተቀጠሩ ተገልጋዮች ሳይስተናገዱ እንደማይቀሩም ይናገራሉ።

በአካባቢው መጨናነቅ የሚፈጠረው ቀጠሮ ባላቸው ተገልጋዮች ብቻ ሳይሆን «ፓስፖርት ዘግይቶብናል» ብለው ለመጠየቅ በሚመጡ ተገልጋዮች እና አንድ ጉዳይ ለመጨረስ ከአንድ በላይ ሰው ስለሚመጣ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ተገልጋዮች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተሰልፈው ለዘራፊዎች እንዳይጋለጡ ሰልፉ በሥራ ሰዓት ብቻ እንዲሆን በአገልግሎቱ በኩል የታሰበ ነገር ካለ የተጠየቁት ዳይሬክተሯ የሌሊት ሰልፉ ከአገልግሎቱ እውቅና ውጪ መሆኑንና ለሰልፉ ሰዓት የመገደቡን ጉዳይ በቀጣይ በጋራ የሚታይ ነገር እንደሚሆን ነው ምላሻቸውን የሚሰጡት።

በመሀል ጉዳይ አስፈጻሚ ደላሎች አሉ ስለሚባለው የተጠየቁት ዳይሬክተሯ አንዳንዴ በውጭ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ያሉ ደላሎች አስቸኳይ ፓስፖርት እናሰጣለን በሚል ኅብረተሰቡ ለተለያየ ወጪ እየተዳረገ እንደሆነ ጥቆማዎች ለተቋሙ ይደርሳሉ ይላሉ። ይህንንም የተቋሙ የጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት የሚያጣራበት ሥርዓት እንዳለውም ይናገራሉ።

ተገልጋዮች ለአስቸኳይ ፓስፖርት በሕገ ወጥ ደላሎች በኩል ለማስጨረስ ከመሞከር ይልቅ እራሳቸው በጥቂት ቀናት መጨረስ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሯ የሚናገሩት።

ተገልጋዮች እንግልቱን ለመቀነስ ለአስቸኳይ ፓስፖርት ካልሆነ በስተቀር አቅራቢያቸው ባለው የአገልግሎቱ ጽሕፈት ቤት በኩል ቢያመለክቱ ሰልፍና መጨናነቁ ይቀንሳል ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

እሳቸው ይህንን ቢሉም በተቋሙ በር ላይ ያለው ሰልፍም ሆነ የተገልጋዩ ምሬት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ዘላቂ መፍትሔም ይሻል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You