የወላይታና አካባቢዋ ሠላም – ለኢንቨስትመንት ምቹነት

ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ሠላም ካለ ወጥቶ መግባት፤ ዘርቶ መቃምና ወልዶ መሳም ይቻላል። አለፍ ሲልም ለኢንቨስትመንት እድገት ሠላም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በነበረው ቆይታ የአካባቢው ሠላም ለኢንቨስትመንት ዕድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ መታዘብ ችሏል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በአካባቢው ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ሲገልጹ፤ ሥራ አጥነትን ከመቀነስ አኳያ የግሉ ዘርፍ ሰፊ ድርሻ አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢንቨስትመንትን መሳብ ትክክለኛው አማራጭ ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያም የተለያዩ ዘርፍ ያላቸውን ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ላይ ትገኛለች፡፡

እንደ ወላይታ ዞንም ያለው ሁኔታ ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 53 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘት ችለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ያስመዘገቡት ጠቅላላ ካፒታልም ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን፣ 680 ሚሊዮን 185 ሺ 901 ብር ሲሆን፤ እነዚህ ባለሀብቶች ከመካከልም ወደ ሥራ የገቡና በሂደት ላይ ያሉ ይገኙበታል፡፡

በዞኑ እየተከናወነ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት የኢንቨስትመንት ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ጨምሯል፡፡ ለአብነት ያህል በገጠር እርሻም፣ በከተማ አገልግሎት ዘርፍ፤ እንዲሁም በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጭምር መሻሻል አሳይቷል፡፡ እንደዞን ሲታይ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ለዚህም የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ይናገራሉ፡፡ ከክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ወላይታ ሶዶ የአስተዳደርና የፖለቲካ ማዕከል ሆናለች፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ የተረጋጋ ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ በአካባቢው የተፈጠረው ሠላም አስተማማኝና ለኢንቨስትመንት ዕድገት ምቹ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይም ለዲያስፖራው፣ ለሀገር ውስጡና ለውጭ አገር ባለሀብት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከተመዘገበው ካፒታልም ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘው የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ነው፡፡ ዲያስፖራው ከተሠማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ የሆቴል ቱሪዝም፣ የማኅበራዊ አገልግሎትና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በማኑፋክቸሪንግ አግሮፕሮሰሲንግ ላይ እንዲሠማሩም ዘርፎች ተለይተውና የቢዝነስ አዋጭነታቸው ታይቶ እንዲገባባቸው እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፤ ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ መሬት ወስደው አጥረው የተቀመጡ አካላት ተለይተው 19 በሚደርሱ ፕሮጀክቶች ላይ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ በቀጣይም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማያለሙ ከሆነ የመቀማት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡ መሬትን ለኢንቨስትመንት ልማት መስጠት ብቻ ሳይሆን ውጤታማ መሆናቸውም በአግባቡ የሚገመገም እንደሆነና የገበያው ሁኔታ ምን ያህል ነው የሚለው እንደሚታይ አመላክተዋል፡፡

ሌሎች ባለሀብቶችም በተረከቡት ቦታ በአፋጣኝ ማልማት እንደሚጠበቅባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው፤ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መሠረተ ልማት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዞኑ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በዞኑ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር ስለመኖሩ ያነሱት አቶ ሳሙኤል፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ኢንቨስትመንት ወደ ዞኑ መሳብ ወሳኝ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ደግሞ ሠላምና መልካም አስተዳደር ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹ከሠላምና ጸጥታ እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር አኳያ የወላይታ ዞን ለሌሎች አካባቢዎች አንጻር ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ በዞኑ የሚገኙ ቀበሌዎች ከወንጀል ስጋት ነፃ በመሆናቸው፤ የትኛውም አካል ከአንድ ስፍራ ወደሌላ ስፍራ በሠላም መንቀሳቀስና መሥራት ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ በዞኑ ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢኬድ ዝርፊያም ሆነ ንጥቂያ የሌለበት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡

ይህም ከሕዝቡና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት በማድረግ የመጣ ውጤት ነው መሆኑን በመግለጽ፤ ከሦስት ዓመት በፊት ወላይታ በተለይ ከክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ፈተናዎች የበዙበት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በተደረገው ውይይትና ምክክር ሕዝቡ ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት ጀምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ዞኑን ከዚህ በበለጠ የሠላም ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞም በዞኑ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ እየተሠራ ነው፡፡ አገልግሎት ፈላጊው አካል ያለምንም እንግልት ይስተናገድ ዘንድም እየተሠራ ነው። የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ቀልጣፋ እንዲሆንና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንዲያስችል ትልቅ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ተቋማትን ከሚመሩ አካላት ጋር ሰፊ ወይይት በማካሔድ መግባባትም መፍጠር ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ሕዝቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚማረርባቸው አንዱ ተቋም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ነበር፡፡ በዚህ ተቋም በተለይ ከመሬት ጋር እና ሕገ ወጥነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ያንን ችግር ነቅሰን አውጥተን በችግሮቹ ዙሪያ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የሶዶ ከተማ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ፍሬሕይወት ወልደመስቀል በበኩላቸው፤ የሶዶ ከተማ አሁን ባለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎትና እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የልማቱ ሥራ ቀንና ሌሊት መካሔዱን ጠቅሰው፤ ይህን ለመሥራት ከሁሉ በላይ የከተማዋን ሠላም ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራ ጠንካራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች የልማት ሥራዎች ሠላም ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከዚህ የተነሳ ከሁሉ በላይ መቅደም ያለበት ሠላምን ማስፈን ስለሆነ ሠላምን የማስፈኑ ተግባር የፀጥታውን ሁኔታ ለሚመራ አካል ብቻ የሚተው አለመሆኑንና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ነው ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ፍሬሕይወት ገለጻ፤ ሁሉም ለሠላም መስፈን የድርሻውን ሲወጣ ኢንቨስትመንቱ የተፈለገውን ያህል ርቀት መሄድ ይችላል፡፡ የሶዶ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሜትሮፖሊታን ደረጃ ለማድረስ ታልሞ እየተሠራ በመሆኑ ከተማዋ በዚህ አጋጣሚ ያላትን ፀጋ ልትጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ምቹ አጋጣሚዎቿም ከተማዋ ሰባት መውጫ እና መግቢያ በሮች ያሏት መሆኑ አንዱ ሲሆን፤ በሰባቱም የመውጫ እና መግቢያ በሮች የንግድ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ከተማዋ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉባት ነውና ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው ከተማዋ ለኑሮ ምቹ የሆነችና የአየር ፀባይዋም መልካም የሚባል መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ነዋሪዎቿ እጅግ ሥራ ወዳድና እንግዳ ተቀባይ መሆናቸው እንዲሁም በርካታ የተማረና አምራች ዜጋም የሚገኝባት መሆኗም ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርንም ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው ወደ ወላይታ የሚመጡ ኢንቨስተሮች በፍጹም አይከስሩም፤ ይልቁኑ በብዙ ያተርፉበታል ነው ያሉት፡፡

አቶ ፍሬሕይወት እንደሚሉት፤ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ በመሆኑም በ2015 በጀት ዓመት ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የሆነውን የከተማውን ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሁም ሰፊ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥርን ይቀንሳል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በአሁኑ ወቅት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፤ የስድስት ወር አፈጻጸም አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነሱም በዋናነት በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎትና በከተማ ግብርና ላይ ትኩረት ያደሩጉ ናቸው፡፡ ፍሰቱም በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ማኑፋክቸሪንግ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል በመሆኑ ነው፡፡

በአገልግሎት ዘርፉ ሲታይ በርካታ ንዑሳን ዘርፎችን በውስጡ ያካተተ ነው፡፡ ለምሳሌ የሆቴል ቱሪዝም በዚሁ ዘርፍ የሚገኝ ነው፡፡ ለአብነት በሶዶ ከተማ በርካታ የሕክምና ተቋማት አሉ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ደረጃቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የጠበቁ ሆስፒታሎች እየተገነቡና የገቡበትም ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሁንና አሁንም ለዚህ ዘርፍ አይበቃንም ብለን ስለምናስብ በብዛትና በጥራት እንዲሠራ ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡

ከሆቴል ዘርፍ ጋር ተያይዞ ሪዞርቶችና ሎጆች ለአካባቢያችን ያስፈልጉናል የሚሉት አቶ ፍሬሕይወት፤ ብዙ የእንግዳ ማረፊያዎችም አስፈላጊ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ መሆኗን በመጥቀስ ይህ ደግሞ ለከተማዋ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በከተማዋ በቀጣይም ቢሆን በርካታ ጉባኤዎች የሚካሔዱ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ይህን ፍላጎት የሚመጥን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መካሄድ ስላለበት በእነዚህ ዘርፎች በስፋት እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ አካላት ከተማዋ የተሟላ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡ ከዚህም መካከል ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሠላም የተረጋገጠበት ከተማ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ሰፋ ባለ መልክ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለባለሀብቱ ማቅረብ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዋናነት እነዚህን አማራጮች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ሥራ ወዳዱን የወላይታ እና አካባቢውን ሕዝብ በማቀናጀት ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ከተማዋ 24 ሰዓት የመብራት እና የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ናት፡፡ በተጨማሪም የአራተኛው ትውልድ የኤል.ቲ.ኢ ኔትዎርክ ሽፋንም ያላት ከተማ ናት፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባሉበት ቦታ ሆነው ንግዶቻቸውን ከሀገር ውጭ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ማድረግ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል፡፡ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ባለሀብቶችን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር የመሳብ ሥራ ከተማዋ ቀጥላለች፡፡ ከዚህ የተነሳም በቁጥር በርከት ያሉ ባለሀብቶች በሶዶ ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ይህ ፍሰት ሊኖር የቻለው ባለሙያ ምቹ አጋጣሚ ሲሆን፣ በተለይ በሠላሟ፣ ባላት ሥራ ወዳድ ዜጋ እና የተማረና አምራች ዜጋ በአካባቢው በመኖሩ ነው፡፡ ይህ ሥራ ግን አሁንም የሚበቃ አይደለም፡፡ አሁንም በስፋት ታቅዶ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡

ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከተማ አስተዳደሩ ከሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት እና ከኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዩኒት ጋር በቅንጅት ይሠራል፡፡ በሦስቱም ዘርፎች (ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎት እና ግብርና ዘርፎች) የሚሆን መሬት ተዘጋጅቷል፡፡ ከተማዋ ብዙ ኢንቨስትመንት አማራጮች አሏት፡፡ ስለዚህ በሦስቱም ዘርፎች የመሬት ሁኔታ የሚያሳስብ አለመሆኑን ያመላከቱት አቶ ፍሬሕይወት እንደሚሉት፤

የኢንቨስትመንት ሥራ ሁሉንም ባለሀብት የሚያካትት ነው፡፡ ባለሀብቱ ደግሞ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በሶዶ ከተማ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል፡፡ በተለይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ወደ ሶዶ ከተማ መጥተው እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በተለይም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሳብ አመንጪነት በተደረገው ‹‹ዲያስፖራዎች ሀገር ቤትን ጎብኙ›› በተባለው ግብዣ ሰፊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ በዚህ መነሻም እኤአ ከ2023 ጀምሮ ሰፊ የሆነ የዲያስፖራ እንቅስቃሴ ተስተናግዷል፡፡ በተለይም ከአምና ጀምሮ የነበረው እንቅስቃሴ ሲስተዋል በቁጥር 30 የሚሆኑ ዲያስፖራዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የከተማውን ውሳኔ ማግኘት በመቻላቸው ወደቀጣዩ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ተደርገዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረትም የከተማ አስተዳደሩን ውሳኔ አግኝተዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

Recommended For You