የካቲት 12 ሲታወስ

መቼም ስለ የካቲት 12፣ 1929 የፋሺስት የአዲስ አበባ ጭፍጨፋ በተወሳ ቁጥር በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ መጽሐፍት የኢያን ካምቤል ፤”THE MASSACER OF ADDIS ABABA”ይገኝበታል። የወቅቱ የጣሊያን ፋሽስት መሪ ቢኒቶ ሙሶሊኒ ፋሽዝምን በመላው ዓለም ለማስፋፋት ካለው የቀን ቅዠትና በሀገሬው ዘንድ ያለውን ተቀባይነትና ድጋፍ ለማሳደግ ሲል ኢትዮጵያን ወረረ።

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በኋላ ቀር የጦር መሣሪያ፣ በጦር ፣ በጎራዴና በጋሻ ለተከታታይ ስምንት ወራት ገትረው ቢዋጉም፤ የፋሽስቱን የመርዝ ጭስ፣ የአውሮፕላን ድብደባና ሜካናይዝድ ጦር መቋቋም ባለመቻላቸው አዲስ አበባን በፋሽስት እጅ ከመውደቅ አላዳኗትም ። ወረራው በሌላ በኩል የመንግሥታቱን ማኅበር/League of Nations/ከማኮስመኑ ባሻገር የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው ይለናል ኢያን በዚህ ገራሚ መጽሐፉ።

ሰላማዊ ዜጎች በፋሽስቱ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃና ጭፍጨፋ አለቁ። የሚያሳዝነው አዲስ አበባ እንዲህ በደም ጎርፍ ስትታጠብ አብዛኛው ዓለም መረጃው አልነበረውም። የሚያውቁም ስለጉዳዩ እንዲነሳ ካለመፈለጋቸው ባሻገር የወራሪውን ፋሽስት ግፍ ደፍሮ ያወገዘ አልነበረም። የፋሽስት ወታደሮች ጭፍጨፋውን የፈጸሙት በተቻላቸው መጠን ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይወጣ ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግ ነው።

በአዲስ አበባና በአካባቢው የሰዓት እላፊ በመጣል፤ የስልክ አገልግሎትን በማቋረጥ፤ ማንም ከአዲስ አበባ እንዳይወጣ በመከልከልና ከእነሱ ውጪ ካሜራ ይዞ የተገኘን የውጭ ሀገር ዜጋን ሳይቀር በመቀማት፤ ጭፍጨፋው ሲፈጸም ያዩ ኢትዮጵያውያን ሳይቀር ሆን ተብሎ ተገድለዋል። ጭፍጨፋውን በፊትአውራሪነት የመሩና ያስተባበሩ አብዛኛዎቹ የፋሽስቱ አዛዦችም ሆን ብለው መረጃ በጽሑፍም በፎቶም አላስቀሩም። ሌላው ይቅርና ወደ ሮም የላኩት መረጃ የለም። ቢኖርም እምጥ ይግባ ስምጥ አይታወቅም ይለናል ኢያን መጽሐፉን ለማዘጋጀት የገጠመውን ፈተና ሲገልጽ።

«ራስን ካንገት ላይ፣ ቆራርጦ እየጣለ፤

በችንካር ቸንክሮ፣ ሰው እየገደለ፤

ሰውን ከእነቤቱ ፣ አብሮ እያቃጠለ፤

ማነው እንደ ፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ?

ሥጋችንን ገድለው፣ ሊቀብሩት ከጀሉ፤

በዚህ ያልነበሩ፣ ሐሰት እንዳይሉ፤

እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ።

ይህን ታላቅ ሥቃይ፣ መከራና ግፍ፤

ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ።…»

እነዚህ ስንኞች፦ ከ87 ዓመታት በፊት፣ በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐፀድ በቆመው ሐውልት ግርጌ ከሠፈረው ግጥም የተወሰደ ነው ይለናል «ያቺ የካቲት 12 ቀን ! » በሚል ርዕስ ሔኖክ ያሬድ በአማርኛው ሪፖርተር ከሁለት አመት በፊት ባስነበበን ማለፊያ የሰማዕታት ዝክረ እንጉርጉሮ አዘል መጣጥፉ።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ «የኢትዮ ጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966» በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የጣሊያን ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ነው። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት። «ጥቁር ሸሚዝ» እየተባሉ የሚታወቁት የፋሺስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት። የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ። ቤቶች ከእነ ነዋሪዎቻቸው ጋዩ።

እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ። የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማዪቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ  ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በሀገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ።

በዘመኑ የነበሩት ደራሲ ተመስገን ገብሬ «የዓይን እማኙ ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12» በተሰኘ ጽሑፋቸው እንዲህ ጽፈዋል፡-«ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሺስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርዓያን እግራቸውን ጠርቅመው አሠሯቸው። ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው ‘እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል። ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል!’ የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ። ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ። ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርዓያ ወደቁ። ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው።

ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል። ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው። እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው አኑረዋል። ከዚያም መሀል ጨመሩን። ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል። በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገድለዋቸዋል። ሬሳቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ። እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ።

ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን። አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ። የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ። ፋሺስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል። እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ምራቄ ደረቀ። በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን። ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር።«ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ ለኔፕልስ ልዑል ልደት ክብር ተብሎ በተዘጋጀው መሰናዶ አጋጣሚ፣ በወቅቱ የተፈጠረውን የፋሺስት ጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ «የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት» መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡-

«ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ። … በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም። ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ሥውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር።»

እርመኛ አርበኞቹ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በተሽከርካሪው ወደ ፍቼ የወሰዳቸው ስምዖን አደፍርስ ነበር። የፋሺስቶች የግፍ ሰለባ ስለሆነው ስምዖን አደፍርስ በጴጥሮስ ጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በሚገኘው ሐውልቱ ላይ ገድሉን እንዲህ ጽፎታል። ‹‹ወጣቱ አርበኛ ስምዖን (1905-1929) የአብርሃና የሞገስ የልብ ጓደኛ ነበር። ከአደጋውም በኋላ ከአዲስ አበባ ያሸሻቸው በታክሲ መኪናው ነበር። ከዚያም በኋላ ተይዞ ደጃች ውቤ ሠፈር በግራዚያኒ ወህኒ ቤት ማቅቆ አካሉ ከሰውነቱ ውጪ ሆኖ በመርዝ ተገደለ። ዘመዶቹ በድብቅ ቀበሩት።»

አበው«ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ፤» ይላሉ። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከጥቁር ዓለም ልቃ በነፃነት የኖረችበት በቅኝ ገዢዎች በአካል ያለ መንበርከክዋ ምሥጢር የሚቀዳው ከነበር ታሪኳ ለመሆኑ እነዚያው አበው ብሂሉን ማጣቀሻ አድርገው ያቀርባሉ። ኢትዮጵያ ከ136 ዓመታት በፊት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን በዶግአሊ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊትን በራስ አሉላ ጠቅላይ አዝማችነት የደመሰሰችበት የመጀመሪያው በአውሮፓ ላይ የተገኘ ድል ነበር።

ከዶግአሊ ዘጠኝ ዓመት ቆይታ በኋላ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ግዙፉን የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት ዓድዋ ላይ በድል መደምደሙ በተለይ የጥቁር ዓለም መኩሪያ ለመሆን በቅቷል። የ40 ዓመት ቂም የቋጠረው የኢጣሊያ ፋሺስታዊው መንግሥት በ1928 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የፈጸመው ወረራ ከአምስት ዓመት የአርበኞች እርመኛ ትግል በኋላ በድል ተደምድሟል። ይሁን እንጂ በአምስቱ አመት የፋሺስት ወረራ ዘመን ከተፈጸሙት ግፎች አንዱ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ነው።

ከፍ ብሎ እንደተመለከተው በፋሽስት ኢጣሊያ ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎና በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሐውልቶች ቆመዋል። እነዚህን ሰማዕታት ለመዘከር ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በብሔራዊ በዓልነት እስከ 1966 ዓ.ም ሲከበር ኖሯል። የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ሥልጣን ከያዘበት 1967 ዓ.ም ወዲህ ግን በመሠረዙ እስካሁን ታስቦ እየዋለ ነው።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ዘመነ ፍዳውን የሚያስታውስ ነው።«ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓም …»

ይህ የአፅሞች ማረፊያ በኢጣሊያ ፋሽስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው፤ በሚል የሚንደረደረው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣ በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል።

የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከብሪታኒያ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ስፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው። ዝክረ ነገሩ እንደታሰበው ዓመት ታመት በክብር እየዘለቀ እንዳልሆነ የሚናገሩት መምህር መንክር ገብሩ፣ በባሕር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያውን በማክበር ብቻ ሳይወሰኑ የኢጣሊያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል እየጠየቁ መሆኑ ያስደስታል፤ እኛም የነሱን አርአያ መከተል አለብን፤» ይላሉ። የሮዶልፎ ግራዚያኒ የያኔዋ የፋሺስት ጣሊያን በአምስት ዓመቱ ወረራ ወቅት በዓለም የተከለከለ መርዝ ጋዝ ከአውሮፕላን መወርወርን ጨምሮ በርካታ የጭካኔ ተግባራትን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጽማለች። በአዲስ አበባ እና በደብረሊባኖስ ገዳም የተጨፈጨፉትን ጨምሮ በአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅት በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መስዋእት መሆናቸው ይጠቀሳል።

ይሁንና ለዚህ ግፍ፣ ሰቆቃና ጭፍጨፋ የጣሊያን መንግሥት በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ ይቅርና በሥርዓት እውቅና አልሰጠም። በፋሺስት ጣሊያን የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባና በደብረ ሊባኖስ በንጹሐን ላይ ለተፈጸመው ጭፍጨፋ ግፈኞች ለሕግ ስላልቀረቡ፣ ተጸጽተው ይቅርታ ስላልጠየቁና ሀገራቸውም እውቅና ስላልሰጠ፤ ሀገር በቅጡ ያልተጽናናችበትና ጠባሳዋም ያልሻረበት ጥቁር ቀን ነውና፤ መንግሥት ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመቀናጀት የጣሊያን መንግሥት ለተፈጸመው ግፍ እውቅና እንዲሰጥ፣ ይቅርታ እንዲጠይቅና ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል ከማድረግ ጎን ለጎን በሀገር ውስጥ ደግሞ የሰማዕታት ቀን ታስቦ ከመዋል ይልቅ እንዲከበር በማድረግ ትውልዱ እንዲማርበት ሊያደርግ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

Recommended For You