ታዳጊው ፈረሰኛ

ፈጠነ ንጉሱ ይባላል:: የ13 ዓመት ታዳጊ ነው:: የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ነዋሪነቱ በሸገር ከተማ አስተዳደር አካኮ መና አብቹ ክፍለ ከተማ ነው:: እድሜው ለጋ ቢሆንም ፈረስን እንደ አክሱም ሃውልት ቀጥ አድርጎ የማቆም ችሎታ ተችሯል:: ቀልብን የሚማርክ የፈረስ ትርኢት ማሳየትና የሽምጥ ግልቢያን ተክኖበታል። ብቃቱ አጀብ የሚያሰኝና አፍን በእጅ የሚያስጭን ነው::

ታዳጊውን ያገኘነው በሰሜን ሸዋ ዞን በሰንዳፋ በኬ ከተማ በተካሄደው የኦሮሚያ ፈረስ ጉግስ ፌስቲቫል ላይ የቤካ ፈርዳ ራንች ቡድንን ወክሎ ተሳትፎ ባደረገበት ወቅት ነው:: ይህ አጓጊ የፈረስ ጉግሥ ትርዒትና ውድድር የሚካሄደው በዓመት አንድ ጊዜ ነው።

ታዳጊው ፈረሰኛ ባሳለፍነው ዓመት በፌስቲቫሉ ላይ ባሳየው ትርኢትና ብቃት የቀዳሚነት ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል:: ዘንድሮ በተካሄደው በዚሁ የፈረስ ስፖርት ውድድርና ትርኢት ላይም ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቧል:: ‹‹ችሎታዬን እንዳዳብርና በፈረስ ግልቢያ በራስ መተማመን ኖሮኝ ለዚህ እንድበቃ ያደረጉኝ የቡድን አሰልጣኞቼ ናቸው›› ይላል ታዳጊው ፈረሰኛ::

የፈረስ ግሊቢያን ገና በለጋ እድሜው የጀመረው ፈጠነ፣ ከዓመት በፊት ኢትዮጵያን ወክሎ በአልጀርስ በተካሄደው የአፍሪካ ታዳጊዎች የፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና ተሳትፎ የወርቅ ሜዳልያ አጥልቋል:: በአልጅርሱ ውድድር ኢትዮጵያን ለመወከል የበቃውም በጃን ሜዳ በተካሄደ ዓመታዊ የፈረስ ስፖርት ውድድር ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት ነበር:: ይህም ታዳጊው ፈረሰኛ በስፖርቱ ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል::

ህልመኛው ታዳጊ ‹‹በፈረስ ጉግስ ትርኢትና ውድድር በዓለም መድረኮች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ በማድግ ለሀገሬ ዋንጫ አመጣለሁ ብዬ ቃል እገባለሁ›› ሲል በጣፋጭ የልጅ አንደበቱ ምኞቱን ይገልጻል::

በቅርቡ የሚሳተፍባቸው የተለያዩ ውድድሮች እንዳሉ የሚያነሳው ታዳጊው ፈረሰኛ፤ አቅምና የአእምሮ ማስተዋልን ለሚሻው የፈረስ ግልቢያ የሚያደርገው ዝግጅት የትምህርት ጊዜውን እንዳይሻማበት በሳምንት አንድ ቀን በእለተ ቅዳሜ ልምምዱን እንደሚያከናውን ይናገራል::

የቤካ ፈርዳ ራንች ቡድን ምክትል አሰልጣኝና የታዳጊ ፈጠነ የቡድን አጋር ተገኑ አራርሶ፤ ፈጠነ ለፈረስ ግልቢያ ያለው ፍቅርና ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን ይናገራል:: በዚህም ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭ ሀገር ኢትዮጵያን ወክሎ ባደረገው ውድድር አሸናፊ መሆን እንደቻለ ስለታዳጊው መስክሯል::

የፈረስ ግልቢያ እንደ ዋና፣ ሩጫ፣ እግር ኳስና ሌሎች ስፖርቶች ሁሉ በቂ ልምምድ ከተደረገበት ትልቅ ደረጃ ይደረስበታል የሚለው የፈጠነ አሰልጣኝ፤ በልምምድም ሆነ በውድድር ወቅት እንደታዳጊ ሳይሆን እንደ አዋቂ ያስተውላል፤ ይህም ርቆ እንደሚጓዝና ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ የሚያሳይ ነው ሲል ታዳጊውን አሞካሽቶታል::

ፈጠነ በቤካ ፈርዳ ራንች ቡድን መሰልጠን ከጀመረ ሶስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ የሚያስታውሰው አሰልጣኝ ተገኑ፤ የቡድኑ አባላት ስልጠናዎችን በሚወስዱበት ወቅት የስልጠናውን ሰዓት አክብሮ በቦታው ከመገኘት ጀምሮ ለልምምዱ ያለው ተነሳሽነት አስደናቂ መሆኑን ይናገራል::

እንደ አሰልጣኝ ተገኑ ገለጻ፤ በቅርቡ በአልጄሪያ ለሚካሄደው የመላው አፍሪካ ውድድር በፈረስ ዝላይ ኢትዮጵያን በመወከል ለመካፈል ዝግጅት እየተደረገ ነው:: በዚህም ከ18 እና ከ15 ዓመት በታች እንዲሁም አዋቂዎችን ጨምሮ 15 አባላትን የያዘ ልዑክ ወደአልጀርስ ያቀናል:: ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ውደድሮች ላይ አሸናፊ ሆነው መመለስ የቻሉ ተወዳዳሪዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ታዳጊ ፈጠነ ንጉሱ አንዱ ነው::

ታዳጊ ፈጠነ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስና በፈረስ ጉግስ ትርኢትና ውድድር በዓለም መድረኮች ላይ ተሳትፎ ሀገሩን የማስጠራት እቅዱ እንዲሳካ በቡድኑና አሰልጣኞቹ ዘወትር የማያቋርጥ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚቀጥልም አሰልጣኝ ተገኑ አረጋግጧል::

የፈረስ ስፖርት በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ አለው:: በአውሮፓና በሌሎችም ሀገሮች የፈረስ ስፖርት ከሚወደዱና ከሚዘወተሩ ስፖርቶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል:: በአሜሪካ የሚካሄደው ዓመታዊው ‹‹የኬንታኪ ደርቢ›› ውድድር አንዱና ዋናው ነው:: በተመሳሳይም በእንግሊዝና ዱባይ በስፋት የሚዘወተር ስፖርት ከሆነም ሰነባብቷል:: ስፖርቱ ምንም እንኳ በተደራጀና በተጠና መልኩም ባይሆን በኢትዮጵያ ቀድሞ ወደነበረበትና ከዚህም አልፎ በተሻለ አደረጃጀት ተወዳጅነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል:: በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ዘጠኝ ክለቦች ተቋቁመው የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ:: ከእነዚህ መካከል ታዳጊውን ፈረሰኛ ፈጠነን ያፈራውና አጭር የምሥረታ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት የቤካ ፈርዳ ራንች የፈረስ ስፖርት ክለብ አንዱ ነው::

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You