ኢትዮጵያ ውስጥ ፓስፖርት ማግኘት ሰባቱን አህጉራት አዳርሶ እንደመምጣት እየታየ ነው:: ለመሄድ የታሰበበት ሀገር ከመሄድ ይልቅ ፓስፖርቱን ማግኘት የበለጠ ፈተና እየሆነ ነው:: ሲቀጥል ፓስፖርት የሚያስፈልገው፤ የግድ ለዓለም አቀፍ ጉዞ ብቻ አይደለም:: ማንም ሰው ፓስፖርት ቢኖረው ጥሩ ነበር፤ ዳሩ ግን እንኳን ማንም ሰው ሊኖረው የሆነ ዕድል ተገኝቶ ለመሄድ እንኳን ፓስፖርት ማግኘት አዳጋች እየሆነ ነው:: አዲስ ማግኘትም ሆነ የነበረውን ማሳደስ ማሰቡ በራሱ ያደክማል::
ዶቼ ቬለ ባለፈው ኅዳር ወር በዚሁ ጉዳይ ላይ ዘርዘር ያለ ሐተታ ሠርቶ ነበር:: ባለጉዳዮች ለጣቢያው እንደተናገሩት፤ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደሚገኘው የኢሚግሬሽን አገልግሎት ይሄዳሉ:: ይህም ሆኖ ከአንድ ሳምንት በላይ ይመላለሳሉ:: በአገልግሎት ማግኛ ቦታው ከፍተኛ የሆነ ወከባ እና ግርግር አለ:: የትኛው ጉዳይ የት ጋ እንደሆነ አይታወቅም:: በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሄዱ ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ሰዓት የሚያባክኑት በተቋሙ ውስጥ የሚፈልጉት ጉዳይ የሚገኝበትን ቦታ በመፈለግ ነው:: እስከዚህ ድረስ የተተራመሰ ነው::
በቅርቡ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል የሚል ዜና ሲሰራጭ ቆየ:: በተቋሙ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ሲሠሩ ነበር የተባሉ ሠራተኞችና አመራሮችም ታሰሩ ተባለ:: የተመዘገቡ ሰዎች እስከዚህ ቀን ድረስ ሁሉም መውሰድ ይችላሉ የሚል አስደሳች ዜና ሲዘዋወር ከረመ:: ዳሩ ግን ከዜናነት ያለፈ አስደሳችነት ሊኖረው አልቻለም:: አሁንም እነዚያ ውስብስብ አሠራሮች፣ ወከባ እና ግርግሩ ሊጠፉ አልቻሉም፤ እንኳን ሊጠፉ የቀነሱ ራሱ አይመስልም::
አንድ ሰው አዲስ ለማውጣት ቢፈልግ፤ መጀመሪያ በድረ ገጽ ይመዘገባል:: የስድስት ወር ቀጠሮ ይሰጠዋል:: በስድስተኛው ወር በተሰጠው ቀንና ሰዓት የኢሚግሬሽን አገልግሎት ይሄዳል:: አሻራና ፎቶ ይሰጣል:: ከዚያ በኋላ በድጋሚ ይቀጠራል:: እንዲህ እንዲህ እያለ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል:: የጊዜው መርዘም አይደለም ችግሩ:: በዚህ ሁሉ ውስጥ የተወሳሰበ አሠራር፣ ግርግር እና ወከባ የበዛበት መሆኑ ነው:: ከዛሬ አንድ ዓመት በኋላ በዚህ ቀን ፓስፖርቱ እጅህ ይገባል ቢባል ቢያንስ የተሻለ ነበር፤ ዳሩ ግን መቼ እንደሚያገኝም አያውቀውም::
በድረ ገጽ የተመዘገበ ሰው ወሩ፣ ቀኑ እና ሰዓቱ ሁሉ ሳይቀር ይነገረዋል:: ችግሩ ግን በተጠቀሰው ወር፣ ቀንና ሰዓት ሲሄድ በፍለጋ እና በግርግር ብዛት የተቀመጠው የሰዓት ገደብ ሊያልቅ ይችላል:: ከዚያ በኋላ ሰዓትህን አሳልፈሃል፣ ቀንህን አሳልፈሃል እየተባለ ሌላ መጉላላት ይፈጠራል ማለት ነው::
እዚህ ላይ ግን አንድ እውነት አለ:: ተገልጋዩም ለሠለጠነ አሠራር ምቹ አይደለም:: ቀን እና ሰዓት ተቀምጦ ተነግሮት ግርግር መፍጠር የሚፈልግ ብዙ ተገልጋይ አለ:: በማይመለከተው ሰዓት ውስጥ ሄዶ በሰዓታቸው እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎችን አሠራር ያጉላላል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ለዘመናዊ አሠራር ሩቅ የሆኑ ናቸው:: ችግሩ ግን የተማረ የሚባለው ዜጋ የባሰ መሆኑ ነው:: የሚፈልገውን አገልግሎት ጠይቆ የሚመለከተው ጋ መሰለፍ ሲገባው የእሱ ባልሆነ ሰዓት አገልግሎቱን ካልሰጣችሁኝ ብሎ የሚያተራምስ ብዙ ነው:: የአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች ጉዳይ የሚመለከተውን እና በራሱ ሰዓት የሚስተናገደውን ሰው ከማስተናገድ ይልቅ የራሱ ባልሆነ ሰዓት መረጃ የሚጠይቀውን ሰው ለማስተናገድ ይገደዳሉ:: በዚህን ጊዜ ይሰላቻሉ፤ በሥራው ላይም ከፍተኛ መጉላላት፣ ወካባና ግርግር ይፈጠራል ማለት ነው:: እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ፓስፖርት የማግኘትን አገልግሎት አሰልቺ ያደርጉታል ማለት ነው፤ የተቋሙ ስም በወቀሳ ይነሳል ማለት ነው::
አንድ ተቋም ከፍተኛ ወቀሳ ሲበዛበት እርምጃ ተወሰደ ይባላል:: ይህን ያህል አመራሮች፣ ይህን ያህል ሠራተኞች ታሰሩ፣ ተቀጡ ይባላል:: ችግሩ ካልተቀረፈ ግን የጥቂት አመራሮችና ሠራተኞች መታሰር ብቻውን ለውጥ አያመጣም:: ጥፋተኛ የሆኑ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፣ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው:: ዳሩ ግን አገልግሎቱን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ የሚያደርገው፤ እርምጃ መውሰድ ብቻውን ሳይሆን ዳግም ብልሹ አሠራር እንዳይሠራ መቆጣጠር ነው:: በሥራ ላይ ያሉትንም መከታተል ነው:: የልባቸውን ሠርተው ቢታሰሩ ተቋሙ ከጉዳት፣ ሕዝብም ከመጉላላት አይድንም::
ብልሹ አሠራሮች ለሙስና በር ይከፍታሉ:: እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አሠራሮች አሰልቺ እንዲሆኑ የሚደረገው በአቋራጭ ሙስና ለመብላት ነው የሚባል ሐሜትም አለ:: ለምሳሌ፤ አንድ ሰው ፓስፖርት በአፋጣኝ አስፈለገው እንበል:: በመደበኛው አሠራር ለማግኘት ከአንድ ዓመት በላይ ያስፈልጋል:: ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚከፍል ግን በፈለገው ጊዜ ይሰጠዋል ማለት ነው:: አሠራሩ ቀልጣፋ ቢሆን ግን በመደበኛው አሠራር ቶሎ ያገኛል:: ቶሎ አገኘ ማለት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለመክፈል አይገደድም ማለት ነው:: ስለዚህ በተቋሙ ውስጥ ያለ ሌባ አመራር ወይም ሠራተኛ መስረቅ አልቻለም ማለት ነው::
የፓስፖርትን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ በብዙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያለው ብልሹ አሠራር ተመሳሳይ ነው:: በመደበኛው አገልግሎት በአጭር ጊዜ እና በቀላል ዋጋ ሊገኝ የሚገባውን አገልግሎት በአሠራር ዝርክርክነት ይጓተታል:: ይህኔ ደንበኛው አገልግሎቱን ለማግኘት ሲል ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ይከፍላል ማለት ነው:: መደበኛውን አሠራር ስለሚያውቀው በአማላጅ በኩል መደራደር ይጀምራል ማለት ነው::
ይህ ችግር ግን የኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች ብቻ አይደለም፤ የዜጋውም አለመሠልጠን ነው:: ሙስናን የሚያበረታታ ልማድ ነው ያዳበርነው:: የዛሬን አገልግሎት ላግኝ እንጂ እኔ ምን አገባኝ ባይነት በዝቷል:: ሁሉም ‹‹ለምን?›› ብሎ የሚጠይቅ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ መጉላላት አይፈጠርም ነበር:: ከወራት በፊት ባስነበብናችሁ አንድ ትዝብት ‹‹ኢንጂነር ጌታሁን ሔራሞ›› የተባሉ ባለሙያ፤ ብልሹ አሠራር ሲሠራ ያስተዋሉትን አንድ የትራፊክ ፖሊስ የት ድረስ ሄደው እንደከሰሱት አይተናል:: ምንም የተለየ በደል ደርሶባቸው ሳይሆን አሠራሩ ለሀገር ኋላቀርነት ምክንያት መሆኑ ስላስቆጫቸው ነው:: ብዙ ሰው በዚህ ልክ ብልሹ አሠራርን የሚያጋልጥና የሚታገል ቢሆን ጥቅሙ ለራስ ነበር፤ አገልግሎት ስንፈልግ በተገቢው ጊዜ እና ዋጋ እናገኛለን ማለት ነው::
ወደ ፓስፖርት ጉዳይ ስንመለስ፤ አሁንም የሚያማርሩ ሰዎች እንዳሉ ናቸው:: ብዙ ተጉላልተው ፓስፖርት ያገኙ ሰዎች፤ ድግስ ደግሰው የእንኳን ደስ ያላችሁ ፕሮግራም ሊያዘጋጁ ምንም አልቀራቸውም:: ዜጋ በመሆን ብቻ ሊገኝ የሚገባውን ነገር በልዩ ጥረት፣ በታጋሽነት እና ዕድለኛ በመሆን ብቻ የሚገኝ ያስመሰለው አሠራሩ ነው:: ስለዚህ ተገልጋዩም አገልጋዩም በሠለጠነ መንገድ ይሥሩ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016