ውጤታማ የፕሮጀክት አፈፃፀሞች የፕሮጀክቶች መጓተት ስብራቱን ለመጠገን

ሀገሪቱ በአንድ ወቅት ግንባታ እንደ አሸን እየፈላባት ያለች ሀገር እንዳልተባለች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፕሮጀክቶች ተጀምረው የማይጠናቀቁባት እስከመባል መድረሷ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ይህ ገጽታ መቀየር መጀመሩን የሚያመለክቱ እና ተምሣሌት የሚሆኑ ውጤታማ የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀሞች መታየት ጀምረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ መንግሥት በሚያካሂዳቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ልማት እየታየ ነው፤ አንዳንድ የግል የግንባታ ድርጅቶች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እያደረጉ ያለበት ሁኔታም እየታየ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ትብብር እና በራስ አቅም ግንባታው የተጀመረው በፈተናዎች ታጅቦ እና አሁን ላይ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ታላቁ የዓባይ ግድብ ፕሮጀከት ፕሮጀክቶችን የመፈፀም አቅም እያደረገ በመምጣቱ ላይ ፈር ቀዳጅ መሆኑም አያጠራጥርም። በዚህ መካከል ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሀገር የተጀመሩ የጎርጎራ፣ የኮይሻ እና የወንጪ ፕሮጀክቶችም አፈፃፀም አስደናቂ ነው። በበላይ አመራሩ በኩልም ተከታታይ ክትትሎች የተደረገባቸው መሆኑም ለውጤቶቹ መገኘት ምክንያት ይሆናል።

በተለይም በመዲናዋ በትላልቅና ሜጋ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እና በከተማዋ ከንቲባ ከፍተኛ ከትትል ተደርጎባቸው ለፍፃሜ የደረሱ በተለይም መንግሥት በባለቤትነት በያዛቸው በርካታ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በፈጣን አፈጻጸማቸው ይጠቀሳሉ። በጊዜ፣ በጥራት፣ በዲዛይን ቴክኖሎጂን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ተጠናቀው ለሚፈለገው አገልግሎት የበቁም በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ።

ከእነዚህ መካከል የዓድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ይጠቀሳል። በሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነው እና ለሰው ልጅ ክብር ትልቅ ትርጉም ያለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፤ ፕሮጀክቱ ግንባታ በተለይም የከተማ አስተዳደሩ ከፕሮጀክቱ ከከተማ አስተዳደሩ በቅርበት ከመገኘቱም አንጻር ተከታታይ ክትትል ማድረጉ መቻሉ ከፍፃሜው እንዲደርስ እና ለአገልግሎቱ ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል።

ከንቲባዋ በየዕለቱ እስከ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ድረስ ግምገማ በማድረግ ጥብቅ ክትትል ሲያደርጉበት እንደነበረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ተናግረዋል። ይህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች በሥራቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ላይ በየጊዜው ክትትል እንዲያደረጉባቸው፣ የሚገጥሙ ችግሮችን በቅርበት አውቀው በወቅቱ እንዲፈቱ እና ፕሮጀክቶችን በተመሳሳይ ለፍጻሜ እንዲያበቁ የሚያሳስብ ነው። በሀገራችን በሁሉም ክልሎች ጭምር የሚገኙ ከመንገድ እስከ ሆስፒታል እና ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ጥብቅ ክትትል ተደርጎላቸው ለፍጻሜ ሊበቁ እና ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ሊደርሱ ይገባል።

በርካታ ለፍጻሜ የበቁና ለሕዝብ አገልግሎት የደረሱ ፕሮጀከቶች ያሉ ቢሆንም በዚያው ልክ በተገለቢጦሽ ደግሞ ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው ባሉበት ቆመው የቀሩና ወደ መረሣት የደረሱም በየአካባቢው ይታያሉ። ከሰሞኑም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ክትትል ካደረገባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው 45 ፕሮጀክቶች ብቻ መሆናቸውን መግለፁ የሚታወስ ነው።

ቋሚ ኮሚቴው በዚህ ወቅት በመላ ሀገሪቷ 109 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተታቸውን ተገልጿል፤ 84 የመንገድ ፕሮጀክቶችም በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተቋረጠ መሆኑንም ተጠቁሟል። የምክር ቤት አባላት የመረጣቸውን ሕዝብ በሚወያዩበት ጊዜ ሕዝቡ ቅሬታ ካነሳባቸው መካከል አንዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከመዲናዋ ወደ ጅማ መንገድ ሲኬድ በ18 ኪሎ ሜትር ርቀት በዓለም ገና አከባቢ ግንባታው ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ወቅት የተጀመረው የሆስፒታል ፕሮጀክት ግንባታው የተጓተተ ብቻም ሳይሆን የዲዛይን ችግር ጨምሮ በነበረበት ሰፊ ችግር ከዓመታት በኋላ ብዙ ኪሳራ እና ብከነት አስከትሎ እንደገና ግንባታው እየተከናወነ የሚገኝ ነው።

ለሀገር እና ለሕዝብ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠትም በተለይ የዚህ አይነቱ ፕሮጀክት ከጅምሩ ከዲዛይን እና የግንባታ ጥራት እንዲሁም የብልሹ አሠራር ክፍተት እንዳይኖር እና ዳግም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ትምህርት መውሰድ ይገባል። ለዚህ አይነቱ ፕሮጀክት የሲሚንቶ ዋጋ ንረት እና የመሣሠሉ ምክንያቶች ቦታም አይኖራቸውም። ይልቁንም የሕዝብን አገልግሎት እና ሀገርን ካለማስቀደም እንዲሁም ጥልቅ ክትትል ካለማድረግ የመጣ ችግር እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በፕሮጀክቶች ግንባታ ዘርፍ የተሠማሩ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት እና የግል ሴክተሮችም ፕሮጀክቶች ከመፈፀም አንጻር ያሉ ተግዳሮቶችንና ምክንያቶችን ጭምር በማሸነፍ እና በየቀኑ ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቶችን በጊዜ በጥራት ማጠናቀቅ እና ለሚፈለገው አገልግሎት ማድረስ ይኖርባቸዋል። በመንግሥት የተጀመሩ እና በሚያስገርም ጥራት ፍጥነት እና ዲዛይን ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ኦቪድ ግሩፕ ከመሳሰሉት በተለይ በኪራይ ቤቶች በተገነቡ የመንግሥት ቤቶች ግንባታ የታዩ የሚበረታቱ አፈጻጸሞች አሉ። በተመሳሳይ ሌሎችም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚከናወኑ የተለያዩ ዓይነት ፕሮጀክቶችም አፈጻጸም ላይ ለውጥ ማምጣት ይኖርባቸዋል።

ለግንባታ ዘርፉ ተግዳሮት በመሆኑ በተደጋጋሚ የሚነሱ የወሰን ማሰከበር፣ የአቅርቦት እና የፋይናንስ በጀት ችግሮችን ለመፍታት በተለይ የበላይ አመራሮች የቅርብ ክትትል የራሱ ሚና ይኖረዋል። ሲሚንቶ የመሳሰሉ የአቅርቦት ችግሮችን ከመፍታት በኩል ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም የማሳደግ ሥራዎች በዘርፉ የደረሰውን ስብራት እንደገና ለመጠገን የራሱ ሚና ይኖረዋል።

በጥሬ እቃ አቅርቦትም ረገድ መንግሥት ለሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ አቅርቦት የሰጠው ትኩረትም ሌላው ለፕሮጀክቶች ግንባታ የመጓተት ችግሮች መፍትሔ እና የዘርፉን ስብራት የሚጠግን እንደሚሆን ይታመናል። ሀገራችን በተለይ በበርካታ ሀገራት በቀላሉ የማይገኙ የጥቁር ድንጋይን ጨምሮ ለግንባታ ሥራዎች ተፈላጊ የሆኑ ጥሬ እቃዎች ያሏት በመሆኑም ለሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ አቅርቦቱ ትኩረት መሰጠቱ እና ለዚህም አጋዥ የሆኑ ማሽነሪዎችን ማስፋፋቱም ተገቢ ነው ።

በአጠቃላይ በፕሮጀክቶቻችን ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ፣ የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ አቅርቦቱን ተግባራዊ በማድረግ፣ በዲዛይን፣ በጥራት፣ የግንባታ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ እና የወሰን ማስከበር፣ የፋይናንስ ችግሮች እና ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት የሆኑ እና ሌሎች ችግሮችን በተቻለ አቅም በመፍታትና የማስፈጸም አቅም በማሳደግ ፕሮጀክቶቻቸንን በወቅቱ ከፍጻሜ ማድረስ እና ለታለመላቸው አገልግሎት ማብቃት ይገባል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016

Recommended For You