ሀገር አቀፍ የስፖርት የጸረ-አበረታች ቅመሞች ንቅናቄ ይካሄዳል

የየትኛውም ስፖርት ጸር የሆነው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት(ዶፒንግ) በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና ታዋቂ አትሌቶችንም ጭምር እየጎዳ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑንና ስፖርቱን በበላይነት እየመራ ባለው ተቋም ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቁን ተከትሎ የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቷል።

በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ በተዘጋጀው በዚህ ሀገር አቀፍ የምክክርና የንቅናቄ መድረክ ላይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል።

በተለያዩ ዓለማት ላይ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በበላይነት በማጠናቀቅ ትልቅ ስምና ዝና እንዳላቸው ይታወቃል። ያም ሆኖ ከአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ በሚደረጉ ምርመራዎች በዚህ ቅሌት ውስጥ የሚገኙ አትሌቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ ይገኛል። ይህ ሁኔታም በጸረ አበረታች መድኃኒቶች ባለስልጣኑና ፌዴሬሽኑ አቅም ብቻ የማይገታ በመሆኑ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም ጉዳዩን በሚመለከት በከፍተኛ ትምህርት ባለሙያዎች ጥናታዊ ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከቀናት በኋላ በሚደረገው የንቅናቄና የምክክር መድረክ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የመጨረሻ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለተግባራዊነት ወደ ሥራ እንደሚገባም ነው የተጠቆመው።

ኢትዮጵያ መልካም ገጽታዋን ከገነባችባቸው ዘርፎች መካከል ቀዳሚ በሆነው አትሌቲክስ በላብና በጥረታቸው ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን ታሪክ የሚያጎድፍ እንዲህ አይነት ችግር እየተስፋፋ መምጣቱ እንደ ሀገርም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል።

በመሆኑም በምክክር መድረኩ ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ባለፈ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጤና ሚኒስትር፣ ትምህርት ሚኒስትር፣ የፍትህ አካላት፣ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ወዘተ ተካፋይ እንደሚሆኑ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ ገልጸዋል።

አበረታች ቅመሞችን በሚመለከት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተገበረቻቸው ጠንካራ ሥራዎች ለሌሎች ሀገራት አርዓያ በመሆን ተሞክሮዋን ስታካፍል ቆይታለች። ይሁን እንጂ አሳሳቢው የዶፒንግ ተጠቃሚነት ጉዳይ በኢትዮጵያ መጨመሩ በተደጋጋሚ ተነስቷል። ይህንን ተከትሎም የሀገሪቱን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተግባር ለተቆጣጣሪው አካል ድጋፍ መስጠትና ክትትል ማድረግ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ዶፒንግን ለመቆጣጠር እንደ አፍሪካ ጠንካራ ሥራ ተከናውኗል፣ ነገር ግን ጉዳዩ ብዙ መልክ ያለው በመሆኑ ሊሰፋ ችሏል። በተለይም ከባለስልጣኑ ተግባር ጎን ለጎን የሕግ አካሉ እገዛ አናሳ መሆኑ ተመላክቷል። የፍትህ አካላት በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ግንዛቤ አላቸው እንዲሁም የወንጀል ሕጉ በምን መልኩ ይፈጸማል የሚለውም በውይይት መድረኩ ትኩረት የሚያገኝ ጉዳይ ነው።

ከዚህ ቀደም መሰል ጉዳዮች ላይ የመዘናጋትና ረጅም ጊዜ በመውሰድ መፍትሄ ሳይገኝ የተረሳበት ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎም የሕግ አካላት በተዘጋጀው ጥናት ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

በስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ቢቻልም በተለይ አሰልጣኞች ከውጪ ሀገራት ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይስተዋላል። በመሆኑም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ይህንን በሚመለከት እንዲሳተፍ ተደርጓል። የመድኃኒት መደብሮችም ከችግሩ ምንጮች መካከል የሚካተቱ መሆኑን ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ጉዳዮች ማሳያ ናቸው። በግል የሚሰለጥኑ አትሌቶች መብዛትን ተከትሎ የማናጀሮች ቁጥር ቢያሻቅብም መሰል መርሀ ግብሮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ግን አናሳ ነው። በመሆኑም በዚህ መድረክ ማናጀሮች በዋናነት ተሳታፊ ይሆናሉ።

በስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በአስከፊ ሁኔታ ተዘፍቆ የቆየው የኬንያ አትሌቲክስ እየቀነሰ የመጣበት ተሞክሮም በጥናቱ እንዲካተት ተደርጓል። ተሞክሮውን መነሻ በማድረግም የተሻለ ሥራ ለማከናወን በማቀድ ንቅናቄው ይካሄዳል። በቀጣይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው በስፋት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ችግሩ ሲፈጸም ደግሞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። ነገር ግን ከታዳጊዎች አንስቶ ስለ ስፖርት አበረታች ቅመሞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር በሥርዓተ ትምህርት አካቶ ጠንካራ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል።

የመገናኛ ብዙኃንም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለሕዝቡ ግንባቤ ለማስጨበጥ እንዲተጉ ሥራ አስፈጻሚው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You