አዲስ ዘመን ድሮ

የዛሬው አዲስ ዘመን ወደ 1969 ዓ.ም ይወስደናል። ወንጀል ማኅበራዊና ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ያስቃኘናል። ያለምንም ምክንያት በእብሪት ተነሳስቶ በአንድ ጀንበር ሦስት ሰዎችን የገደለው ወንጀለኛ፤ በአንድ ሰዓት ብቻ አንድ ሺህ 649 ሰዎችን ጢም የላጨው ግለሰብ፤ እንዲሁም አደንና አዳኝ እንስሳቱ እንዴትስ አለቁ የሚሉ ጉዳዮችን ከትዝታ ማኅደራችን መዘን አቅርበናል።

በእብሪት ሦስት ሰዎች የገደለው ተፈረደበት

በእብሪተኝነትና በጥጋበኝነት ተነሳስቶ የሁለት ሰዎች ሕይወት ካጠፋ በኋላ ተሰውሮ በውንብድና ሲኖር የነበረውና በዚህም ወቅት የአንድ ሠላማዊ ሰው አጥርና የከብት መኖ አቃጥሎ፤ ግለሰቡንም ከእንቅልፉ ቀስቅሶ በጥይት የገደለው ጀፍላ ደገፋ ሕዝብ በተሰበሰበበት በገበያ ቀን በስቅላት በሞት እንዲቀጣ በቅርቡ ያስቻለው የሸዋ ክፍለ ሀገር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ማስረጃ ሲሰማና ሲመረምር፤ ሟቾቹ ዘውዴ ሩፌና ከተማ ዘውዴ ከለቅሶ ሲመለሱ አንድ ቤት ገብተው ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው አረቄ ሲጠጡ ጀፍላ ደገፉም እዚያ ቤት ሄዶ ዘውዴ ሩፌን የገዛችሁትን አረቄ ልጠጣ ሲላቸው መከልከላቸውንና እሱም “ይህ ጠብመንጃ ነገ ሴራ ሚካኤል ያመጣችኋል” ብሎ መውጣቱንና እነርሱ ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጥይት ድምፅ መሰማቱን ምስክሮች ለዐቃቤ ሕግ በሰጡት ቃል ተረድቷል።

በውንብድና በሚኖርበት ጊዜ ቱጃር ደምሴን በመግደሉና በአጠቃላይ የሦስት ንጹሐን ዜጎችን ደም ማፍሰሱ ልማድ ያደረገ በክፉ ፍላጎትና በጨካኝነት የተነሳሳ ልማደኛ ወንጀለኛ ሆኖ ማግኘቱንም ፍርድ ቤቱ ገልጧል።

(አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 1969 ዓ.ም)

በአንድ ሰዓት -በአንድ ሰው እጅ የሺህ 649 ሰዎች ጢም ተላጨ

የዘር ሐረጉም ሀገረ ትውልዱ ከወደ እንግሊዝ እንደሆነ የሚነገርለት ሚስተር ዲኒ ሮው ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ የአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠኝ ሰዎች ጉንጭና አገጭ ላይ የተከመረ ጢም በአንዲት ሰዓት ውስጥ ሙልጭ አድርጎ እየላጨ፤ ብርቱካን በማስመሰል የምድራችን ቁንጮ ጢም ላጭ ለመባል በቅቷል።

….

ጠጉርን በባልጩት ቀስ በቀስም በምላጭ እየተሸለተ የኖረው የሀገሬ ሰው ከዘመን አመጣሾች መቀሰኛና “ክሊፐርና ሸቨር” መተዋወቅ የጀመረው መች እንደሆነ በትክክል አላውቅም።

….

ካቻምና ደሴ ከተማ ስለሚገኙት ፀጉር አስተካካይ ሴት ወይዘሮ በጻፍኩ ጊዜ ሌላም ቦታ የወንዶችን ፀጉር የሚያስተካክሉ ሴቶች ካሉ ጻፉልኝ ብዬ ነበር። ስለሌሉ ነው መሰለኝ ምላሽ አላገኘሁም። ባሕር ማዶ ሴቶች የወንዶችን ፀጉርና ጢም በማስተካከል ሞቅ ያለ ገበያ ያገኛሉ። ታዲያ ሴቱ ሁሉ ከመሬት እየተነሣ መቀስና ምላጭ አንጠልጥሎ “ዘመናዊ” ጠጉር አስተካካይ ነኝ የሚል እንዳይመስላችሁና አደራ።

(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 1967 ዓ.ም)

በደስታ በሽታ ቁጥጥር ላይ ሴሚናር ተጀመረ

የማዕከላዊ ቀጠና ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት የዳልጋ ከብቶችን ጤንነት ለመንከባከብና የደስታ በሽታን ከክልሉ ለማጥፋት እንዲቻል ያዘጋጀው ሴሚናር መስከረም 12 ቀን 1969 ዓ.ም ተጀምሯል።

….

ጓድ መስፍን በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ለዳልጋ ከብቶች ሕይወት አስጊ የሆነውን የደስታ በሽታ ከአፍሪካ ምድር ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት መሠረት በኢትዮጵያም ይኸው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 1969ዓ.ም)

አደንና አዳኝ

ምንም እንኳን በሀገራችን በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በሌላው ዓለም ውስጥ የሌሉ በጣም ብርቅዬ የሆኑ የዱር እንስሳት ቢገኙም፤ ከጥንቱ ጋር ሲወዳደር ግን በቁጥርም ሆነ በዓይነት በጣም አናሳ መሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ተገልጿል። ለዚህም የዱር እንስሳት ቁጥር እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ ሰበብ ኋላ ቀር ልማድና ወግ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ለአብነት ያህል የሚከተለውን እንመልከት።

፨ ዝሆን ገዳይ_ አዳኙ 30 ሰው እንደገደለ ይቆጠርለታል።

፨ አውራሪስ ገዳይ_ አዳኙ 15 ሰው እንደገደለ ይቆጠርለታል።

፨ አንበሳ ገዳይ _ አዳኙ 5 ሰው እንደገደለ ይቆጠርለታል።

፨ ቀጭኔ ገዳይ_ የቀጭኔ ገዳይ ሚስት በውሀ መቅዳት ቅድሚያ ይሰጣታል።

፨ ግሥላ ገዳይ_ ግሥላ ገዳይ ሳይፎክር ቀድሞ የሚነሣ የለም።

፨ ተኩላ ገዳይ_ ሌሎች ገዳዮች እየፎከሩ ሳሉ ተኩላ ገዳይ ቢነሣ ሁሉም ዝም ይላል።

፨ ነብር ገዳይ_ ነብር እሱው አጥር ግቢ ገብቶ ሴት ገደለችው የሚል ንግርት ስላለ ገዳዩ ለ15 ቀን ብቻ ቂቤ ይቀባል።

(ከዝክረ ነገር የተወሰደ)

(አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 1968 ዓ.ም)

“ጠራርግና ፕላስተር ለጥፍለት”

በሐረርጌ ክ/ ሀገር በወበራ አውራጃ በሜታ ወረዳ በጨለንቆ ከተማ የሚገኘው አንድ ጤና ጣቢያ (ክሊኒክ) ቀድሞ በአንድ ባለሙያ ቅን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ዛሬ ሁለት ባለሙያዎች ተመድበውለት ይገኛል።

ሕመምተኛውን እያዩ እንዳላዩ በመሆን ከአንዳንድ ቦዘኔዎች ጋር አብዛኛውን የሥራ ጊዜ በዋልጌነት ሲያሳልፉ ይታያሉ።

ለዚህ አስተያየት መነሻ የሆነን ግን ባሁኑ ጊዜ ይባስ ብለው፤ የመርፌ መውጋቱን ተግባር አልጀመሩም እንደሆን እንጂ ቁስል ነክ የሆነ ታማሚ ሲመጣ “ጠራርግና ፕላስተር ለጥፍለት” በማለት ለጤና ጣቢያው ዘበኛ ትዕዛዝ በመስጠትና እነሱ በዋልጌነታቸው በመቀጠል ምንም ሙያ የሌለው ዘበኛ ሐኪም መሆኑ ነው። ይህ በማናለብኝነት ፈሩን የለቀቀ አሠራር ቀጥሎ በሕይወት ላይ ሌላ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሚመለከተው ክፍል አንድ ይበልልን።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 1969 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You