የኢትዮጵያን ስጋት ግልፅ ያደረገው ዓለም አቀፋዊ ቀውስ

የዓለም ሀገራት በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው (Gulf of Aden) ላይ ያላቸው ፍላጎት ከምንግዜውም በላይ እየጨመረ መጥቷል። ኃያላን ሀገራት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚረዳቸውን ሰርጥ ለመቆጣጠር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይምሱት ጉድጓድ የላቸውም። ንግድን ለመቆጣጠር፣ የሽብር ጥቃትን ለመከላከል እና በዓለም የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የፊት መስመሩን ተቆጣጥሮ ለመቆየት ደረቅ መሬት ብቻ ሳይሆን ውቅያኖሶችን በመዳፋቸው ስር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠንቅቀው ያውቁታል።

በዚህ ፍትጊያ ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ለማንሳት ይራኮታል። በመሬት ላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት የተያዘበት በባህር ላይ ያምፃል። በዚህ የተነሳ ፍላጎቱ ከፍተኛ ውጥረት እያስከተለ ነው። ውቅያኖሶቹ በወጀቡ እየተናጡ ይገኛሉ። ከሰሞኑ በእነዚህ ቁልፍ የዓለማችን የውሃ ክፍሎች ላይ የሚደረጉ መሳሳቦች መሠረታዊ ምክንያትም ይሄው ነው።

ውቅያኖሶች አንደኛውን የዓለማችን ክፍል ከሌላኛው ጫፍ ያገናኛሉ። የንግድ መርከቦች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ቁሶችን ጭነው ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ወጀብ ጋር እየተፋተጉ ሳምንታት፣ ወራትን ጉዞ ያደርጋሉ። የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት የሚሟላው በባህር ላይ የንግድ መስመሮች ሰላም ላይ ተመስርቶ ነው። መንግሥታት የዜጎቻቸውን ደህንነት፣ ሉዓላዊነት፣ ለማረጋገጥ የግዴታ እነዚህን የባህር ክፍሎች መቆጣጠር ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ በሳምንታት ጉዞ የሚጠናቀቀው የባህር ላይ ትራንስፖርት ሌላ አቅጣጫ ሲቀይር የወራት ጊዜን ሊፈልግ ይችላል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ነው የጂኦ ፖለቲካ ፍጥጫ የሚከሰተው። ይህ ጉዳይ ግልፅ እንዲሆንልን እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በምን ምክንያት የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ከጉዳዩ ጋር እንደሚገናኝ ለመረዳት እንድንችል የሰሞኑን ሰው ሰራሽ የቀይ ባህር ወጀብ ጥሩ ማሳያ ነው። እስቲ እንደሚከተለው ይህንን ትኩሳት በዝርዝር ለመመልከት እንሞክር።

የሁቲ ጥቃት ሰሞነኛው ቀውስ

በቀይ ባህር ላይ የተነሳው ወጀብ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ነው። የዓለም ኃያል ሀገራት እና ግዙፍ መርከቦቻቸውን አቅጣጫ ያስቀየረ ትኩሳት ነው። ወጀቡ የተፈጥሮ ሳይሆን ሰው ሰራሽ ነው። አማፂያን የንግድና ወታደራዊ የባህር መስመሮችን በማወክ፣ የጣሉትን ክልከላ የተላለፈውን ደግሞ በሚሳኤል፣ በድሮንና በቀጥታ የባህር አጥቂዎች አማካኝነት ጥቃት በመሰንዘር ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈፀም እየሞከሩ ነው። ከዚህ መነሻ የዓለም ትልቁ የባህር የንግድ መስመር የሆነው ቀይ ባህር የግጭት ቀጣና ከሆነ ሰነባብቷል። መርከቦች በየመን ሁቱ አማፂያን የድሮንና የሚሳኤል ሰለባ እየሆኑ ነው።

የግጭቱ መነሻ የእስራኤልና የጋዛ ጦርነት ሲሆን ወገንተኝነታቸውን ለፍልስጤሙ ሀማስ ያደረጉት ሁቱዎች ‹‹ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው›› ያሏቸውን የንግድ መርከቦች ኢላማ እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ የንግድ መስመሮችን የበለጠ ለአደጋ ያጋለጠ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ ጉዳይ ነው። ወትሮውንም በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት እና በባህር ላይ ወንበዴዎች (Pirates) እየተፈተነ የነበረው የቀይ ባህር መስመር አሁን ደግሞ ዓለም አቀፍ ቅርፅ በያዘ አጀንዳ መናወጥ ጀምሯል።

አጀንዳው የእስራኤል፣ የምእራባውያንና በፍልስጤም ወገን የተሰለፉ ሀገራት ቢሆንም ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ትናንሽ ሀገራትም ጭምር ሰለባ እየሆኑ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹አያገባኝም አሊያም ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ብሎ እጅን ታጥቦና አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም። እንኳን በቀይ ባህር አፍንጫ ስር እየኖሩ ይቅርና ከሌላኛው የዓለም ክፍል ሆኖም በዚህ አጀንዳ ላይ ማፈግፈግ አላዋቂነትም የዋህነትም ነው።

ተፅእኖው ምን ያህል ነው

በዓለም ላይ በብዛት ከተጨናነቁ የመርከብ መስመሮች አንዱ የሆነው ቀይ ባህር የሚገኘው ከስዊዝ ቦይ በስተደቡብ ሲሆን አውሮፓን ከእስያና ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው ዋነኛ የውሃ መንገድ ነው። በደቡባዊ ጫፍ ላይ በጅቡቲና በየመን መካከል 20 ኪሎ ሜትር ያህል ስፋት ያለው ጠባብ የውሃ ጠለል ይገኛል። የየመን የሁቲ አማጽያን ያነጣጠሩበት አካባቢ ባብ ኤል- ማንዴብ የባህር ወሽመጥን ነው። አማፅያኑ የፖለቲካ ፍላጎቶቻችንን ያሳካልናል ያሉትን ክፍል ይቆጣጠሩ እንጂ በተለያየ ጊዜያት ሌሎች የባህር ላይ ወንበዴዎች ልዩ ልዩ የቀይ ባህር ክፍሎችን ኢላማቸው ሲያደርጉ ቆይተዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዓለም አቀፉ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ 12 በመቶ የሚሆኑት በቀይ ባህር ያልፋል። ይህ የዓለም አቀፉ ኮንቴይነር ትራፊክ የሚይዘውን 30 በመቶውን ጨምሮ ነው። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገመት የንግድ ሸቀጥና ቁሳቁስ በቀይ ባህር ውስጥ ያልፋል።

ለዚህ ነው መሰል የንግድ መስመሩን የሚያውኩ ቀውሶች ሲፈጠሩ የነዳጅ ዋጋ፣ በኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችና በሌሎች የዓለም ንግድ ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት የሚያይለው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በሁቲዎች ጥቃት ምክንያት የተስተጓጎለውን የንግድ እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፈን ስንመለከት ነው።

ለምሳሌ ያህል መርስክ፣ ሃፓግ-ሎይድን እና ኤም ኤስ ሲን የተባሉ ታዋቂ የመርከብ ኩባንያዎች የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ቀይ ባህርን ላለመጠቀም ወስነዋል። የአትላንቲክ ካውንስል የተባለ አንድ የምርምር ተቋም ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በገበያ ድርሻቸው ከፍተኛ ከሆኑት አስር ትልልቅ የመርከብ ኩባንያዎች መካከል ሰባቱ በቀይ ባህር ውስጥ የሚተላለፉ እንቅስቃሴዎችን ዘግተዋል።

አንዳንድ መርከቦች በደቡባዊው የአፍሪካ ጫፍ ላይ በምትገኘው ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ አካባቢ እየተዘዋወሩ የጉዞ ጊዜያቸውን እስከ ሁለት ሳምንት ከፍ በማድረግ ላይ ናቸው። በኃይል አቅርቦት ላይ ታዋቂ የሆነው እና በነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚሰራው ቢፒ የተሰኘው ትልቁ ካምፓኒ ሰኞ እለት በቀይ ባህር በኩል የሚያስተላልፈውን የነዳጅና የጋዝ ጭነት በሙሉ ማቆሙን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ከሰሞኑ በቀይ ባህር ጠለል ላይ የተከሰተው ኮሽታ ምን ያክል የዓለማችንን ኢኮኖሚ እንደሚያናጋው ማሳያ ነው። በቅርቡ በያላኑ ትኩረት ያገኘው የሁቲዎች ጥቃት መጠነ ሰፊ ተፅእኖ ስላለው እንጂ በየጊዜው በባህር ላይ የሚከሰቱ ውንብድናዎች አሉ። መርከቦች ይዘረፋሉ፣ የጉዞ ባለሙያዎች እና ካፒቴኖች ይታገታሉ። በጥቅሉ ሰው ሰራሽ ወጀቡ በሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ክትትል ካልተደረገበት የጥቃቱ ዓላማና መጠን እየጨመረ መሄዱ የማይቀር ነው።

የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሰሞኑ ትኩሳት አንፃር

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ እንደመገኘቷ ይህ ጉዳይ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ይመለከታታል። ጎረቤት የሚነደው እሳት ሰደድ ሆኖ ሌላውን እንደሚያቃጥል ሁሉ በቀይ ባህር ላይ የሚከሰት ማንኛውም ቀውስ ቀድሞ ወላፈኑ ኢትዮጵያ ላይ መድረሱ የማይቀር ነው። በዚህ ምክንያት የንግድ፣ የሰላምና የትብብር ጉዳዮች ላይ ዋነኛ ተዋናይ የመሆን ፍላጎት ቢኖራት አያስደንቅም።

ኢትዮጵያ አብዛኛውን መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ ፍላጎት በቀይ ባህር በኩል ከውጪ ታስገባለች። በርካታ የሀገር ውስጥ ምርቶችንም በዚሁ በኩል በማስወጣት ትነግዳለች። በዚህ ምክንያት በመስመሩ ላይ የሚከሰት ውንብድና አሊያም የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈፀም የሚደረግ ጥቃት ቀጥተኛ ተጋላጭ ነች። ይህንን ጥቃት ለመከላከል ከራሷ ከባለቤቷ (ከኢትዮጵያ) በላይ ማንም አይኖርም።

ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባኛል ጥያቄን ስታነሳ በምክንያትነት ከተጠቀሱ አጀንዳዎች መካከል ይሄው የደህንነት ጉዳይ አንዱ ነው። በቀይ ባህር አፍንጫ ስር ሆና እያለ በአካባቢው የሚከሰት ቀውስን ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ብሎ ሊታለፍ የሚችል አይደለም። ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እንዲሁም የንግድ መስመሩ ላይ ያላትን ድርሻ እየገነባች ባለችው የባህር ኃይል የመከላከል ህጋዊ መብት አላት። ለቀጣናው ሰላም መሆን እንዲሁ በትብብር የድርሻዋን ማበርከት ይኖርባታል። የሰሞኑ የሁቲ ጥቃቶችና በቀይ ባህር ላይ እየተከሰተ ያለው ሽኩቻም ይህንን እውነት የበለጠ ግልፅ አድርጎታል።

በቀይ ባህር ላይ እየተከሰተ ያለው ቀውስ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የበለጠ ምክንያታዊ የሚያደርግ ነው። ይህ አመክንዮ መሬት ላይ ያለ እውነታ በመሆኑና ወቅታዊ አጀንዳ ስለሆነም ጭምር መንግሥት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ሥራዎችን ሊያከናውንበት ይገባዋል።

የኢትዮጵያ ወደፊት መምጣት ከባቢውን ከዚህ መሰል ጥቃት አሊያም የባህር ላይ ውንብድና ለመታደግ ሁነኛ ምርጫ እንደሚሆን ማሳየት ተገቢ ነው። የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ልክ እንደሌሎቹ ሀገራት ሁሉ በዚያው በቀይ ባህር ላይ ሆኖ ለመቆጣጠር ህጋዊ መብት እንዳለን ጭምር ማሳየት ተገቢ ነው።

ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ሽብርተኝነትን ስትዋጋ ነበር። ለዚህ ማሳያው በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የፊት መስመር ተዋናይ መሆኗ ነው። የሶማሊያው አልሸባብ ከመስፋፋት እና በየጊዜው ሊያደርሰው ከሚያስበው መጠነ ሰፊ ጥቃት የተገታው በኢትዮጵያ ጠንካራ መልሶ ማጥቃትና ተሳትፎ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም።

ሽብርተኛ ቡድኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ደግሞ ድንበሮችን ብቻ አይደለም ጥሰው የሚገቡት። ይልቁኑም የጥቃት አድማሳቸውን ከየብስ በተጨማሪ በባህር ላይ ውንብድናም እያስፋፉ የንግድ መስመሮችን እያወኩ ይገኛሉ። ይህ አዲስ ስልት ሳይሆን መሬት የነካ ሃቅ ነው። ለእነዚህ አማፅያንና ሽብርተኞች ደግሞ ቀይ ባህር ቁልፍ ወሽመጥ ነው።

ቀይ ባህር በዓለም ላይ ከፍተኛ ጉዞ ከሚደረግባቸው የውሃ አካላት አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ወሳኝ የሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲኖረው አስችሎታል። ጠባቡ የቀይ ባህር ርዝመቱ 2ሺህ 250 ኪሎ ሜትር እርዝመት እና 355 ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።

በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል የሚገኘው ቀይ ባህር ከህንድ ውቅያኖስ ወደ ደቡብ፣ ከስዊዝ ቦይና ከሜድትራኒያን ባህር ወደ ሰሜን አቅጣጫ ስለሚያገናኝ ከአውሮፓ ወደ እስያ በሚወስደው አጭር የባህር መንገድ ላይ ቁልፍ ወሽመጥ ነው። በጥቅሉ በዚህ ወሳኝ ስፍራ ውስጥ (ሊያውም በአፍንጫው ስር ተቀምጦ) ድርሻን ሳይዙ መቀመጥ እንደ ግዙፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ሊታይ ይገባል። ከሰሞኑ የተፈጠረው ወጀብም የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ይበልጡኑ ግልፅ አድርጎታል የምንለው ከዚሁ መነሻ ነው። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You