ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የምትመራበትን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማሳደግና ምጣኔ ሀብቷን በዚያው ልክ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሏትን በርካታ የልማት መርሃግብሮች ነድፋ በመተግበር ላይ ትገኛለች:: በተለይም በየዓመቱ በእቅድ ተይዘው የሚሠሩት የግብርናው ዘርፍ የልማት መርሃግብሮች ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ብርቱ ጥረትና ክትትል ስታደርግ ቆይታለች:: በስንዴ ልማት መስክ የተመዘገበው ውጤትም የዚሁ ጥረት ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው::
ዘርፉን የሚመራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማትና አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለው የልማት ሥራም ይበል የሚያሰኘው ሆኗል:: በአንፃሩ ደግሞ ለዓመታት ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ሳቢያ ዛሬም አርሶአደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ይደመጣል:: ይህንን ችግር በመፍታት ረገድም ሚኒስቴሩ ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ ሲናገር አድምጠናል::
ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴሩንና የግብርና እና የተጠሪ ተቋማቱን የስድስት ወራት አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፤ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልም ሆነ ሀገሪቱ ከዘርፍ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ሥራዎች ተከናውኗል:: ከእነዚህም መካከል የማዳበሪያና የዘር አቅርቦት በበቂ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የተደረገው ርብርብ በጥንካሬ የሚወሰድ ነው::
‹‹ዘንድሮ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ የደረሰው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጅቡቲ ከደረሰው ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ኩንታሉን ሀገር ውስጥ ማስገባት ችለናል›› በማለት በዚህ ዓመት ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ 36 ነጥብ ስምንት በመቶ ሀገር ውስጥ መግባቱን ያመለክታሉ::
ባለፈው ምርት ዘመን በተለይም መኸር ላይ የተስተዋለውን የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በተደረገው ሪፎርም ማዳበሪያ በወቅቱና በተሻለ ገንዘብ መግዛት መቻሉን ያብራራሉ:: በአፈር ማዳበሪያ ግዢ የመንግሥትን የድጎማ ጫና በመቀነስ በማዳበሪያ ግዢ ውስጥ 20 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ሲያስረዱ፤
ለማዳበሪያ ግዢ በተመደበው 71 ቢሊዮን ብር 1 ነጥብ4 ሚሊዮን ቶን (19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል) ማዳበሪያ መገዛቱንም ያመለክታሉ:: ‹‹2016/17 ፍላጎት ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቶን ወይንም 23 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ለመፈጸም እቅድ ዘንድሮ ለማዳበሪያ ግዢ የተመደው አምና ከተገዛው ጋር የስድስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው›› ሲሉም ይጠቅሳሉ::
ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን ለእንደራሴዎቹ ሲያብራሩ፤ አምና የተመደበው አንድ ቢሊዮን እንዲሁም የትግራይን ጨምሮ 59 ቢሊዮን ዶላር 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሟል:: አምና 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት መንግሥት ድጎማ አድርጎ የነበረው 21 ቢሊዮን ብር ነበር:: ዘንድሮ 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቶ ድጎማ የተደረገው 16 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው:: የበልግና የመስኖን እርሻ ሊሸፍን የሚችል ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ገብቷል:: በቀን 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ እየተጫነ ይገኛል:: በተያዘው ፍጥነት ከቀጠለ ዘንድሮ የማጓጓዝ ሥራው ግንቦት ወር ላይ ይጠናቀቃል::
ዘንድሮ የአርሶአደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት ጭማሬ ማሳየቱን አመልክተውም፤ ‹‹ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ በዚህ ልክ የማዳበሪያ ጥያቄ አልነበረውም፤ አሁን እየጠየቀ በመሆኑ ጥያቄውን ለመመለስ ማቅረብ አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል:: ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ጨርሰናል ተብሎ ለአንድ አፍታም መዘናጋት እንደማይኖር አስገንዝበዋል:: አርሶ አደር ጋር ደርሶ ምርት ላይ እስኪውል ድረስ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን መደረግ እንዳለበትም ጠቅሰው፤ ለዚህ ትግበራ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ መሆኑም አስረድተዋል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ አማራ ክልልና ተመሳሳይ ትኩረት የሚሹ አካባቢዎችም መኖራቸውን ጠቁመው ‹‹በጸጥታ ችግር ምክንያት ማቅረብ በሚገባን ያክል ግብዓት ለማቅረብ አልቻልንም›› ይላሉ:: ይሁንና ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት ከሚመለከታቸው ጋር ንግግር ማድረጉን ነው ያመለከቱት::
ኢትዮጵያ በምግብ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርና ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ውስጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ የመኸር ወቅትን ብቻ ጠብቆ አንድ ጊዜ ማምረት አዋጭ አለመሆኑን ለምክር ቤቱ ያስረዳሉ:: በመሆኑም ግብርናው ሁሉንም ወቅቶች ባማከለ መልኩ ወደ ማምረት መሸጋገሩን ያመለክታሉ:: ‹‹መኸርን ስንጨርስ ወደ መስኖ አቅደን መግባት፣ መስኖን ስናጠናቅቅ በልግን ወደ ሥራ በማስገባት ምርታማነትን ማሳደግ ላይ አተኩረናል›› ሲሉም ይገልፃሉ::
እንደሀገር በበጋ መስኖ ልማት እየተከናወነ ስላለው የስንዴ ልማት ዙሪያም እንደተናገሩት፤ የስንዴ ምርት ከአምስት ዓመት በፊት ትግበራ ሲጀመር በመኸር የሚመረተው 1 ነጥብ 75 ሚሊዮን ሄክታር ነበር:: አሁን በመኸር የሚመረተው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደርሷል:: በየወቅቶቹ የምርት ግኝቱ ወሳኝና ተቀራራቢ ምርት ላይ እየደረሰ መጥቷል:: በዚህ ምክንያትም በሁለቱ ወቅቶች የሚመረተው ስንዴ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ያደርጋታል::
‹‹መጠኑ ቢያንስም በበልግ ወቅትም ስንዴ ይመረታል:: ባለፈው ዓመት ከ 300 ሺ ሄክታር በላይ በበልግ ስንዴ ተመርቷል›› ያሉት ዶክተር ግርማ በሌላ በኩል ደግሞ በየክልሉ የተለያዩ ጸጋዎች እና አቅሞች በመጠቀም አበረታች ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ያስረዳሉ:: ይሁንና ሁሉም አካባቢዎች በስንዴ ምርት አንደኛ መውጣት እንደማይችሉ ጠቅሰው፤ አንዳንድ አካባቢ መስራት የሚችለው በቆሎ በማምረት ሊሆን እንደሚችል፤ ሌላው ጋር ደግሞ ወሳኝ አቅም ያለው በእንስሳት ርባታ ሊሆን እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ይናገራሉ::
በመሆኑም አካባቢዎቹ እንደየጸጋቸውና አቅማቸው እንዲያመርቱ መደረግ እንዳለበት ይገልፃሉ:: በዚህ ረገድ ግብርና ሚኒስቴር በሁሉም አካባቢ ያለውን ጸጋና አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ትግበራ እንዲገባ ማድረጉን ያመለክታሉ:: በተለይም ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና ከግብርና ምርምር ጋር በመሆን በተለይ ለታዳጊ ክልሎች የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ነው የጠቀሱት::
‹‹ጋምቤላ ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት፣ አፋር ክልል ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት፣ ሶማሌ ክልል ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት፣ ደቡብ፣ ምዕራብ ምን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ለይተናል›› ይላሉ:: የአራት ክልሎች የግብርና ፍኖተ ካርታ መጠናቀቅን፤ በአሁኑ ወቅት እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን ያስረዳሉ:: ክልሎችን የመደገፍና በእቅዱ መሠረት ወደ ሥራ መግባታቸውን የማረጋገጥ ሥራ የሚሠራ መሆኑንም ለምክር ቤቱ አስገንዝበዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ማድረግ እንድትችል ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል:: ‹‹ከዚህ በፊት ስናወራ የነበረው ስለምርትና ምርታማነት ብቻ ነበር:: አሁን አስተሳሰቡን ቀይረናል:: ከምርት እስከ ማዕድ ድረስ ያለው ሙሉ የሂደት ስንሰለቱ መታየት አለበት›› ይላሉ:: አርባ ምንጭ የተመረተው ሙዝ ተገቢ የማጓጓዣ አቅርቦት ተመቻችቶለት ገበያ መቅረብ ካልቻለ በአካባቢው መመረቱ ብቻ በቂ አለመሆኑን ለአብነት ጠቅሰው ያስረዳሉ:: በመሆኑም አሁን በቀጠለው የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ምርት ላይ የሚሠራው ምርታማነትን መጨመር ላይ እንዲያተኩር፣ የማጓጓዣ ሥርዓቱ ላይም መሠራት እንዳለበት መግባባት መኖሩን አስገንዝበዋል::
በተጨማሪም እንደቲማቲም ያሉት ምርቶች በሎጅስቲክስ አቅርቦት ወደ ገበያ ባለመውጣታቸው ምርቱ እየበሰበሰ የሚጣልበት አጋጣሚ መኖሩን ለእንደራሴዎቹ ተናግረዋል:: የምርት ብክነቱን ለመከላከልም የምርት ማዕከላትን ከገበያ ማዕከላት ጋር በሎጅሲቲክስ የማገናኘትና የማስተሳሰር ሥራዎች ለማሳካት ሥራ መጀመሩን ነው የጠቆሙት::
ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን በምርቶች ላይ የሚታያውን የዋጋ ንረት አስመልክተውም ‹‹ለዋጋ ንረቱም ዋና መፍትሄ የሚሆነው ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ብቻ ነው:: በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ምርትና በሌሎቹም የግብርና ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው:: እነዚህን በማሳደግ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል›› ሲሉ አብራርተዋል::
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፤ የወተትና የስጋ ምርት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በወተት 31 ከመቶና ስጋ 74 በመቶ እድገት አሳይቷል:: የማርና የእንቁላል ምርት አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በማር 57 በመቶና በእንቁላል ምርት 52 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። በመሆኑም ተግባሩ የሌማት ትሩፋት ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማሳየቱን እንሚያመለክት መገንዘብ ይቻላል::
በሌላ በኩልም በቡና ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ካምና ያነሰ ውጤት ባይመዘገብም ነገር ግን በዋጋ መቀነሱን ሚኒስትሩ አልሸሸጉም:: ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ ‹‹አንድም የምርት ጥራት ነው:: በመሆኑም በቀጣይ የምርት ጥራት ማሳደግ እና ተወዳዳሪ መሆን አለብን›› ሲሉ ነው የገለፁት::
የምግብ ደህንነት እና ጤንነት ጭምር መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ሲገልጹ፤ አንዳንድ ምርቶች ተጠቃሚ ጋር እስኪደርሱ ድረስ በአግባቡ ካልተያዙ ችግር ይፈጥራሉ:: በመሆኑም ይህንን የሚመራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል:: ከዚህም ባሻገር መፍትሄ ሊያመጡ የሚችሉ 22 የሚደርሱ ቁልፍ የሆኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከተለምዶ አመራረት አውጥተው ማስፈንጠር የሚችል ትግበራ መጀመሩን አመላክተዋል:: ትግበራውን የሚያስተባብር 15 ሚኒስትሮች የተካተቱበት የሚኒስትሮች አብይ ኮሚቴ መቋቋሙንም አክዋል::
እንደአቶ ግርማ ማብራሪያ፤ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአግሪኮላ ሽልማት ያበረከተው ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት አመራርና ቁርጠኝነት ላሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ነው:: ጅምሩን በመመልከት ስኬታማ እንደሚሆንና ከግብ እንደሚደርስ በማመናቸው ነው:: ይህ ግብርናው ሽግግር ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: ይሁንና ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ ከጅምሩ እስከ ማዕድ ድረስ መመራት ይገባዋል::
በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት ግብርናው ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ማስገባቱን ያመለክታሉ:: የወጪ ንግዶች ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 10 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ በገቢ 195 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን፤ ከእቅዱ አንጻር ጉድለቶች እንዳሳየ ተናግረው:: የማካካሻ ሥራ እንደሚተገበር ጠቁመዋል::
ሚኒስትሩ ከዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘም እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የነበረውን ወደ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ታቅዷል:: ዘንድሮ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል:: በዚህ ረገድም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ለግብርና የሰጠው ትኩረትና ድጋፍ፣ ከክልሎች ጋር በጋራ በመወያየት ተቀራርቦና ተደጋግፎ የመሥራት መልካም ጅምሮች መኖራቸው ለዘርፉ መልካም አጋጣሚ መሆናቸውን አስገንዝበዋል::
በስድስት ወራቱ በአፈፃፀም ረገድ የተለዩ ድክመቶች እንደነበሩ ሚኒስትሩ ተናግረው፤ በዋነነትም በየደረጃው ያሉ አደረጃጀቶች ሪፖርትን ጥራቱን፣ ወቅቱንና ተከታታይነቱን ጠብቆ በተሟላ መረጃ አስደግፎ ያለመላክ፤ የተለያዩ የምርት ግብዓቶችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙ፤ የአሲዳማ አፈር ለማከም ኖራ ለማቅረብ የበጀት እጥረት መከሰቱ፤ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በመስክ በመገኘት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ አለማድረግ ተጠቃሽ መሆናቸውን አመላክተዋል:: በመሆኑም እንደተግዳሮት የተነሱት እነዚህ አብይ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ በቀጣዩ ስድስት ወራት ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት::
ተቋሙን የገመገመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግብርና ሚኒስቴር የግብርናው ትርንስፎርሜሽን ለማረጋገጥና ዘርፉን ለመደገፍ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የሀገርን ምርት እና ምርታማነት ለማሻሻል የተያዘውን ጥረት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስቧል:: የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ፤ የምግብ ዋስትናን ለመረጋገጥ የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን እንደሚገባ፣ አሲዳም አፈርን ለማከም አስፈላጊ የሆኑ የኖራ ግብዓቶችን በማቅረብ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም