ጉዳፍ ፀጋይ የ5ሺ ሜትር ክብረወሰንን ዳግም ለማሻሻል አቅዳለች

ኢትዮጵያዊቷ የ10ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮን እንዲሁም የ5ሺ ሜትር ክብረወሰን ባለቤቷ ድንቅ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ለተጨማሪ ክብረወሰን እየሠራች መሆኗን አስታውቃለች:: 5ሺ ሜትርን ከ14 ደቂቃ በታች በማጠናቀቅ የራሷንና የዓለምን ክብረወሰን ዳግም ለማሻሻል ያቀደች ሲሆን፤ ጠንካራዋ አትሌት ኢትዮጵያ በርቀቱ ያላትን የበላይነት እንደምታስቀጥልም የስፖርት ቤተሰቡ እምነት አሳድሮባታል::

ጉዳፍ ባለፈው የአትሌቲክስ ውድድር ዓመት በኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን እጅ ገብቶ ለሦስት ወራት የቆየውን የርቀቱን ፈጣን ሰዓት በአምስት ሰከንዶች በማሻሻል ክብሩ ዳግም የኢትዮጵያውያን ማድረጓ ይታወሳል:: በ5ሺ ሜትር የሴቶች ሩጫ ታሪክ ለ17 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያለተቀናቃኝ ክብረወሰኑን እየተቀባበሉ ሲያሻሽሉት ኖረዋል:: በእነዚህ ዓመታት ሰዓቱ በሌላ ሀገር አትሌት እጅ የገባው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ቆይታውም የጥቂት ወራት ዕድሜ ነው::

እአአ በ2006 አትሌት መሠረት ደፋር በቱርካዊቷ አትሌት ኤልቫን አቢይ ለገሰ ለሁለት ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በማይክሮ ሰከንዶች ብቻ በማሻሻል ነበር ክብሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣችው:: ጀግናዋ አትሌት በዓመቱ ደግሞ ኦስሎ ላይ በ8 ሰከንዶች የራሷን ሰዓት በማሻሻል አስደናቂ ገድል ስታስመዘግብ፤ በርቀቱ ታሪክ በተከታታይ ክብረወሰን የሰበረች ብቸኛዋ አትሌት በመሆን ነው::

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እዚያው ኦስሎ ላይ ሌላኛዋ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በሀገሯ ልጅ የተያዘውን ፈጣን ሰዓት በድጋሚ በማሻሻል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በርቀቱ ያላቸውን የበላይነት ማጠናከር ችላለች:: 14 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ከ15 ማይክሮ ሰከንዶችን ያስቆጠረው ይህ ሰዓት ለ12 ዓመታት በአንድም አትሌት ሳደፈር ቆይቷል:: ከዓመታት በኋላ የርቀቱን ቁጥር አንድ አትሌትነት የያዘችው ደግሞ ሌላኛዋ ብርቱ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ስትሆን፤ እአአ በ2020 ቫሌንሺያ ላይ 14:06.62 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ሦስተኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በመሆን ታሪክ ልታስመዘግብ ችላለች:: ይህንን ሰዓት ከኬንያዊቷ ተፎካካሪዋ እጅ ፈልቅቃ በማውጣት ዳግም ያሻሻለችው ደግሞ ጉዳፍ ጸጋይ ናት::

አትሌቷ የክብረወሰኑ ባለቤት የሆነችው በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ርቀት አስደናቂ ተጋድሎ በማድረግ የወርቅ ሜዳሊያ ካጠለቀች ከቀናት በኋላ ነው:: በቻምፒዮናው ሌላኛውን ድል ለማሳካት ባቀደችበት 5ሺ ሜትር እግሯ ላይ በደረሰው ጉዳት እንዳሰበችው መሮጥ ባትችልም ከሳምንት በኋላ ኦሪጎን ላይ በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኑን 14:00.21 በሆነ ሰዓት ልትሰብር ችላለች:: ይህንን ሰዓት በማሻሻል ከ14 ደቂቃ በታች መግባት ደግሞ የዚህ ውድድር ዓመት እቅዷ መሆኑንም በግል የማኅበራዊ ገጿ በኩል አስታውቃለች::

በየትኛው ውድድር ሰዓቷን ለማሻሻል እንዳሰበች በግልጽ ባታሳውቅም፤ ጉዳፍ ካለችበት ወቅታዊ አቋም አንጻር ግን የቀሯትን 21 ማይክሮ ሰከንዶች በማሻሻል የርቀቱን ፈጣን ሰዓት ሌሎች እንዳይደርሱባት አድርጋ ትሰቅለዋለች ተብሎ ይጠበቃል::

በአስደናቂ ወቅታዊ አቋም ላይ የምትገኘው አትሌቷ አዲሱን የውድድር ዓመት በቤት ውስጥ የዙር ውድድር የጀመረች ሲሆን፤ የተለመደውን ስኬታማነቷን እያስመሰከረች መሆኑም ይታወቃል:: የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የቦስተን የዙር ውድድር በ1ሺ500 ሜትር የተሳተፈችው የርቀቱን የቤት ውስጥ ክብረወሰን የሆነ ሰዓት ለማሻሻል ቢሆንም በውድድሩ የመጨረሻ ርቀት ያጋጠማት የቁርጭምጭሚት ወለምታ በጥቂት ሰከንዶች ስላዘገያት ያሰበችውን እንዳታሳካ አድርጓታል:: ሆኖም የገባችበት 3:58.11 የሆነ ሰዓት የቦስተን የቤት ውስጥ ውድድር ፈጣን በሚል ተይዞላታል::

አትሌቷ ቀጣዩ የቤት ውስጥ የዙር ውድድር መዳረሻዋ በነበረው ሌቪን ደግሞ በ3ሺ ሜትር ለፈጣን ሰዓት ብትሮጥም ክብረወሰን በማስመዝገብ ረገድ ስኬታማ ልትሆን አልቻለችም::

በምታስመዘግባቸው ነጥቦች በግላስኮው የዓለም የቤት ውስጥ ዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያን በቀጥታ የመወከል ዕድል እንደሚኖራት ይታመናል:: በቻምፒዮናውም ምናልባትም በ1ሺ500 ሜትር እንዲሁም በ3ሺ ሜትር ልትሮጥ እንደምትችል ነው የሚገመተው:: የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌቷ ጉዳፍ በትልልቅ የውድድር መድረኮች ባላት ተሳትፎ የተለያዩ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች:: የዚህ ዓመት ዋነኛ ግቧም የታወቀችበትን የ5ሺ ሜትር የክብረወሰን ንግሥናዋን ከማስጠበቅ ባለፈ በዓመቱ መጨረሻ በፓሪስ በሚደረገው ኦሊምፒክ የ5ሺ ሜትር እንዲሁም የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮን በመሆን የኢትዮጵያን ክብር ማስጠበቅ ይሆናል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You