ጥራት ያለው ባለሙያ ለማፍራት…..

ትምህርት የሁሉም ሙያዎች መሠረት ነው :: በትምህርት ጥራት ላይ የሚሰራ ሥራ የሌሎችን የሙያ መስኮች ጥራት ማስጠበቅ የሚያስችል ነው:: ለትምህርትና ሙያ ጥራት መምጣት ደግሞ ፈተና አንዱ አማራጭ ነው፤ ብቸኛው ነው ብሎ ማሰብ ግን የዋህነት ይመስለኛል::

በትምህርት ጥራት ላይ በትብብር መሥራት ካልተቻለ የሌሎችን የሙያ ዘርፎች ጥራት ማምጣትም፤ በእውቀትና በክህሎት የሚሠራ ብቁ ባለሙያ ማግኘትም “ልፋ ያለው በህልሙ አቅማዳ ይሸከማል” ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም:: ለሌላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻ ሊሆን እንደሚችልም ማሰብ ተገቢ ነው ::

የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ ሊወድቅ የሚችለው ድንገተኛ በሆነ ክስተት ሳይሆን፤ በረጅም ዓመታት ሲንከባለሉና ትኩረት በተነፈጉ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ያለውን የመማር ማስተማር ሥርዓት መፈተሽና አስፈላጊውን እርምት በየደረጃ መውሰድን የሚጠይቅ ነው::

የትምህርት ጥራት በትምህርት ሚኒስቴር፣ በየክልሉ ትምህርት ቢሮዎች፣ በየዞን ትምህርት መምሪያዎች፣ በየወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ባሉ የትምህርት ባለሙያዎችና በመምህራን በሚሠሩት ሥራ ብቻ ማምጣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም በመንግሥት ጥረት ብቻ ይፈታል ብሎ መገመት የትምህርትን ጥራት ማምጣት ቀርቶ አሁን ባለበት ደረጃ ለመቆየቱም ያጠራጥራል::

ለትምህርት ጥራት መምጣት ከላይ ከዘረዘሩት አካላት በተጨማሪ የወላጆችን፣ የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ የፖለቲከኞችን፣ የምሁራንን፣ የሁሉም ቤተ እምነት የሃይማኖት መሪዎችን…ወዘተ ርብርብ የሚፈልግ ነው። በመወያየት ችግሩ ካልፈታ በስተቀር የትምህርትና የሙያ ጥራትን ማምጣት የማይታሰብ ነው::

ይህን የምለው ሟርተኛ ወይም ጨለምተኛ ሆኜ ሳይሆን ሁሉም የሙያ ዘርፎች የሚመዘዙት በትምህርት ስለሆነ ነው:: የትምህርት ጥራት ሳይጠበቅ ብቃት ያላቸው መምህራንን፣ አስተዳዳሪዎችን፣ ሐኪሞችን፣ ዳኞችን፣ መሐንዲሶች እና የመሳሰሉትን ባለሙያዎች ማግኘት የሚከብድ ነው:: የአንድ ሀገር የትምህርት ጥራት ከተበላሸ የሁሉም የሙያ ዘርፎች እንደሚበላሽ ግለፅ ስለሆነ ጭምር ነው::

ለምን ሲባል ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቂ የትምህርት ግብዓቶች ሳይሟሉላቸውና ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠርላቸው እየተማሩ የመጡ ተማሪዎችን 12ኛ ክፍል ደርሰው ሲፈተኑ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አላመጡም ብሎ መቆጨትም ትርጉም አልባ ቁጭት ይሆናል:: ከዚህ ይልቅ ፤ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ተማሪዎችን በጥራት በማስተማር ለፈተና ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ የፈተና ውጤት ማሻሻልም ሆነ የትምህርትን ጥራት ለማምጣት መሞከር ያልዘሩትን ለማጨድ የመቋመጥ ያህል ነው::

በሀገሪቱ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ያለው እውነታ ፤ ካለው የውጤት መዛነፍ ባለፈ ከትላልቅ ከተሞች ርቀው የሚኖሩ ትምህርት ቤቶች ይቅርና በትልልቅ ከተሞች ያሉ ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉ የትምህርት ግብዓቶች ተሟልተውላቸዋል ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል::

አሁን አሁንማ የማጣቀሻ መጽሐፎች፣ የሙከራ ቤቶች እና የመሳሰሉት ለትምህርት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የትምህርት ግብዓቶች ይቅርና የተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍት ማግኘትም ቅንጦት እየሆነ መምጣቱን ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከራከር አካል ካለ አንድ ሁለት ብሎ ካስረዳኝ ዘመኑ በመወያየት ችግሮች የሚፈቱበት ወቅት ነውና ብንወያይበት ደስ ይለኛል::

ባለፈው ዓመት አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊ ቢሆንም፤ተማሪዎች ግን ያለ መማሪያ መጽሐፍት ስለሚማሩ የቤት ሥራ ለመስጠት ይቸገሩ ነበር:: ይህንን በተደጋጋሚ የትምህርት ኃላፊዎች በመገናኛ ብዙኃን ሲገልፁት የነበረ ጉዳይ ነው:: በዚህ ዓመት በቂ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለተማሪዎች ባይዳረሱ እንኳን ዕድሉ ያላቸው ጥቂት ተማሪዎች በሶፍት ኮፒ እንዲያነቡ በመደረጉ በጥቂቱም ቢሆን ችግሩን ፈትቷል ብዬ አስባለሁ::

ይህም ሆኖ ግን አሁንም ተማሪዎች በሶፍት ኮፒ የማግኘት ዕድሉ የላቸውም:: በተለይ 85 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደርና አርብቶ አደር በሚኖሩባቸው ራቅ ባሉ ገጠር አካባቢዎች ለሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ የመማሪያ መጽሐፍቱን በሶፍት ኮፒ ማግኘት ቅንጦት ይሆናል::

ድሮ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልነበረበት ወቅት የእምነት ትምህርት ቤቶች ፊደል አስቆጥረውና የየእምነቶቻቸውን መጽሐፎች ማንበብ ከቻሉ በኋላ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ስለሚገቡ ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤትም የተሻለ እንደነበር የሚረሳ አይደለም:: አሁን አሁን በእምነት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት በመቅረቱም ለትምህርት ጥራት መጓደል የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ብዬ አስባለሁ:: በሀገር በቀል እውቀት አለመጠቀም ችግር ነው የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል::

ይህ ማለት ከእምነት ትምህርት ቤቶች ተምረው የሚመጡ ተማሪዎች በደንብ ማንበብና መጻፍ ችለው፤ ቁጥር ቆጥረውና አራቱን የሂሳብ መደቦች ማስላት ችለው ስለሚመጡ በመደበኛው ትምህርት ቤቶች ብዙ ጊዜ የሚጀምሩት ከ3ኛ ክፍል፣ አልፎ አልፎም ከ2ኛ ክፍል ነበር:: በደርግ ጊዜ ሲሰጥ የነበረው መሠረተ ትምህርትም ተማሪዎች ማንበብና አራቱን የሂሳብ መደቦች እንዲያውቁ አስተዋጽኦ ነበረው::

ይህንን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ይመስለኛ የመጀመሪያ ደረጃ የአንደኛ ሳይክል ተማሪዎች (በተለይ ከ1ኛ ክፍል እስከ 3ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች) ማንበብና መጻፍ፣ አካባቢያቸውን መገንዘብና አራቱን የሂሳብ መደቦች በትክክል ማስላት ከቻሉ ሌላ ውስብስብ ነገር ማወቅ ስለማይጠበቅባቸው በየጊዜው በክፍል ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴና የክፍል ውስጥ ተከታታይ ምዘና እየተሰጣቸው ወደሚቀጥለው ክፍል ማለፍ ይችላሉ ተብሎ የነበረው::

ነገር ግን በታችኛው እርከን ባሉ የትምህርት ባለሙያዎችና በመምህራን የተሳሳተ ግንዛቤ ከ1ኛ ክፍል እስከ 3ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች መድገም የለባቸውም እየተባለ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ፣ ቁጥር በአግባቡ የማይቆጥሩና አራቱን የሂሳብ መደቦች የማያሰሉ ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል እንዲዛወሩ መደረጉም ሌላው ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዱ መንስኤ ይመስለኛል:: ችግሮችን ከታች ወረድ ብለን ማየት ይኖርብናል የምለው እነዚህንና መሰል ጎዳዮችን ለማየት የተሻለ እድል ስለሚፈጥር ነው።

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሰፈር)

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You