እንዴት ናችሁ ልጆችዬ? ሠላም ናችሁ? የአንደኛ ወሰነ ትምህርት (ሴሚስተር) ፈተና ወስዳችሁ ከጥቂት የእረፍት ቀናት በኋላ እንኳን ወደ ሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ተመለሳችሁ እንበላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ። ታዲያ ልጆችዬ ጓደኞቻችሁን፣ መምህራኖቻችሁን፤ እንዲሁም፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉትን ሰዎች ስታገኟቸው ምን ተሰማችሁ? በጣም ደስ እንዳላችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም።
ሰዎች እረፍታቸውን የተለያዩ ነገሮችን በመከወን እንደሚያሳልፉ ታውቃላችሁ። እና ልጆችዬ የእናንተስ እንዴት ነበር? ግማሾቻችሁ መጻሕፍትን በማንበብ (የትምህርት እና የተለያዩ መጻሕፍትን)፣ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት፣ ስዕል በመሳል፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወት (በመለማመድ) ቤተሰብ በመጠየቅ፤ ከወላጆቻችሁ (አሳዳጊዎቻችሁ) ጋር በመዝናናት፣ በመጫወት በመረዳዳት፤ ብቻ በተለያዩ ነገሮች እንዳሳለፋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ልጆችዬ፣ የፈተና ውጤታችሁስ እንዴት ነው? በጣም ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ውጤት ያመጣችሁ ተማሪዎች እንደምትኖሩ እንገነዘባለን። ከፍተኛ ውጤት ያመጣችሁ ልጆች በጥንካሬያችሁ፤ እንዲሁም፣ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ያገዛችሁን መንገድ አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል። ብትችሉ ደከም ያለ ውጤት ላመጡ ጓደኞቻችሁ ልምዳችሁን ብታካፍሉ መልካም ነው።
እዚህ ላይ፣ “ጥሩ ውጤት ያላመጣነውስ ምን እናድርግ?″ የሚል ጥሩ ጥያቄ ልታነሱ እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ለእናንተም የምንላችሁ አለን፡፡
ልጆችዬ፣ ምን ማድረግ አለባችሁ መሰላችሁ? በቅድሚያ የዓመቱን ትምህርት ለማጠናቀቅ ጥቂት ወራቶች እንዳሉ መገንዘብ ይኖርባችኋል። ‹‹በቃ አንደኛ ሴሚስተርን አላለፍኩም፡፡›› ብሎ ከማዘን እና ከመቆጨት ይልቅ አሁንም በርትቼ ጥሩ ውጤት ማምጣት እችላለሁ ብላችሁ ማሰብ፤ ከዛም ማጥናት እና በትኩረት ትምህርታችሁን መከታተል። ይሄንን ካደረጋችሁ፣ በቃ – ለሚቀጥለው 100 በ100 ውጤት የእናንተ ይሆናል ማለት ነው።
ሌላው ደግሞ ልጆችዬ፣ ‹‹እኔ እኮ ትምህርት አይገባኝም፡፡›› በፍጹም እንዳትሉ እሺ። ምናልባት አንድ የሠራችሁት ወይም ልብ ያላላችሁት ስህተት ይኖራል እንጂ ትምህርት የማይገባችሁ ሆናችሁ አይደለም። እናም ድክመታችሁ የቱ ጋር እንደሆነ ራሳችሁን በሚገባ ፈትሹ። ያን ጊዜ የእናንተ ችግር ምን እንደሆነ እና ለምን ጥሩ ውጤት እንዳላመጣችሁ ትገነዘባላችሁ ማለት ነው። በተጨማሪም ለወላጆቻችሁ፣ ለታላላቆቻችሁ እና ለመምህራኖቻችሁ ድጋፍ እንዲያደርጉላችሁ ብትነግሯቸው መልካም ነው፡፡
ከዚህ በኋላም ቢሆን በትምህርት ቤት ውስጥ ያላችሁን ትርፍ ሰዓት በጨዋታ ብቻ ከማሳለፍ ይልቅ፤ ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄዳችሁ በርትታችሁ ካጠናችሁ ውጤታችሁ የማይስተካከልበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ጎን ለጎን ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ጋር በጋራ በማጥናት፣ በመረዳዳት እና ስለ እምትማሩት ትምህርትና ስላልገባችሁ ጉዳይ በመጠያየቅ ብታሳልፉ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ያግዛችኋል እሺ ልጆች።
ልጆችዬ ፈተና ስትቀበሉ የመጀመሪያ ሥራችሁን ራሳችሁን መመዘን እንደሆነ ከዚህ በፊት ተጨዋውተን ነበር አይደል? ከዚህ በኋላም ቢሆን የአጠናን ስልታችሁን ማወቅ፣ በክፍል ውስጥ የሚኖራችሁ ተሳትፎ፣ ለፈተና የምታደርጉት ዝግጅት እና ሌሎች ነገሮች ጥሩ ውጤት ለማምጣት፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ጥሩ ውጤት ላላመጣችሁ ተማሪዎችም እንድታሻሽሉ ያግዛችኋል፡፡
ልጆችዬ፣ ወላጆቻችሁ እቤት ውስጥም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው ሥራዎችን ይሠራሉ። እናንተ በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት እንድታመጡም በጣም ይደክማሉ። እንደውም አንዳንዶቹ ከተጣበበ እና ከተጨናነቀ ጊዜያቸው ላይ ቀንሰው፤ እንዲሁም ከሥራ ቦታቸው እረፍት በመውጣት እናንተን ለማስጠናት፣ ለማሳወቅ፤ እንዲሁም ከማዝናናት በተጨማሪም የእናንተ የነገ ሕይወታችሁ የሠመረ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል? “በሚገባ!!!″ የሚል ምላሽ እንደምትሰጡኝ ምንም ጥርጥር የለኝም። እናንተስ እነሱን ለማስደሰት ምን እያደረጋችሁ ነው? ልጆችዬ ወላጆች ከእናንተ የሚፈልጉት ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጎበዝ ተማሪ፣ ውጤታማ ልጅ፣ ሀገሩን የሚያስጠራ እና ጥሩ ሰው መሆንን ብቻ ነው የሚፈልጉት። ይህንን አውቃችሁ በርትታችሁ ተማሩ፤ እሺ ልጆችዬ፡፡
ወላጆችም ብትሆኑ ልጆቻችሁ ጥሩ ውጤት ካላመጡ “ለምን?″ ብላችሁ በጋራ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩበት። ልጆቻችሁን በፍፁም ከሌሎች ልጆች ጋር አታወዳድሯቸው። አቅም፣ እውቀቱ፤ እንዲሁም ጊዜው ካላችሁ አስጠኗቸው። ጎበዝ ተማሪ ጓደኛ እንዲኖራቸው፣ በክፍል ውስጥ በንቃት እንዲከታተሉ፣ ያልገባቸውን ነገር ያለፍርሃት እንዲጠይቁ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ ተማሪዎች እንዲሆኑ፤ ከትምህርት ቤት መልስ ቤት ውስጥ በጥሩ እና በተረጋጋ መንፈስ እንዲያጠኑ ብሎም የቤት ሥራዎቻቸውን እንዲሠሩ በሚገባ ማገዝ ይኖርባችኋል፡፡
ልጆችዬ፣ ከዚህ ቀደም ስለ ፈተና ዝግጅታችሁ፣ እረፍታችሁን እንዴት መጠቀም ወይም ማሳለፍ እንዳለባችሁ፤ ዛሬ ደግሞ ከእረፍት መልስ ትምህርታችሁን እንዴት መማር እንዳለባችሁ እና ማሻሻል ያለባችሁን ነገሮች ጠቆምናችሁ አይደል? እናተም “ይጠቅመናል″ የምትሏቸውን ሃሳቦች ወስዳችሁ በሚገባ እንደምትተገብሯቸው ተስፋ አደርጋለሁ።
በሉ እንግዲህ ልጆችዬ፣ ትምህርታችሁን በርትታችሁ አጥኑ፤ አንብቡ፤ ጨዋታ ቀንሱ። ልጆችዬ፣ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ በማድረግ እና መልካም ነገሮችን ሁሉ ለእናንተ በመመኘት በዚሁ እንሰነባበታለን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም