የዙፋኑ አልጋ አዳሽ

እልፍ የዘመን ፍርግርጎችን በመርገጥ ወደ ኋላኛው ዘመን የታሪክ ቋት ስናመራ ዘመን እንደ ቀልድ ያለፋቸው አንድ ሰው እናገኛለን፤ አለቃ ገብረ ሀናን። በአብዛኛዎቻችን የልጅነት ትዝታዎች ውስጥ የአለቃ ገብረ ሀና ቀልድ አይጠፋም።

አሉ፤ እያልን የምናወራቸው እልፍ ነገሮች ነበሩ። በእውንም አለቃ ገብረ ሀና የሚባሉ ሰው ነበሩ? ገሚሱ ነበሩ፤ ገሚሱ ደግሞ አፈታሪክ እንጂ በጭራሽ አልነበሩም እያለ ሽንጡን ገትሮ ይሞግታል። የምናስታውሳቸው በቀልዳቸው ብቻ ሆነ እንጂ መኖርስ ነበሩ። እውነተኛው የሕይወት ማድጋቸውን ብንከፍት የያዘው ብዙ ነው። ቤተ መንግሥቱ ያለሳቸው አይደምቅም ነበር። በዙፋኑ ላይ አልጋ ወራሽ ባይሆኑም፤ የአልጋው አዳሽ ሆነው በዚሁ ዙሪያ ያለውን ሰው በሙሉ ለማደስ ሲታትሩ ነበር።

የወላለቀውን ለመጠገን፤ የጎበጠውንም ለማቅናት የሚጠቀሙት ቅኔ ነበር። ከአንደበታቸው እውቀት እንደ ዥረት የሚፈስ ቢሆንም፤ በብዙው የሚታዩት ግን ደፍርሰው ነበር። ሊቅነታቸው በአንዲት ጉዳይ ብቻ ያረፈች አልነበረችም። ከመንፈሳዊውና አለማዊው፤ ከሰማዩም፤ ከምድሩም፤ ከእግዜሩም ከሰይጣኑም ብቻ የሚቀራቸው የለም።

አለቃ ነገሮችን የሚያዩበትም ሆነ የሚስሉበት መንገድ ፍጹም የተለየ ነበር። ብልሀት፤ እውቀትና አስተሳሰባቸው ከቀልደኝነታቸው ጋር ተጣምረው በብዙ ነገሮች ከማኅበረሰቡ ያፈነገጡ አደረጋቸው። ተቀባይ አጡ እንጂ የሚሰጡትስ ብዙ ነበር። የማያደርጋቸው ነገርም አልነበረም። ሲያሻቸው ባለቅኔ፤ ሲያሻቸው ፈላስፋ፤ የሕግ ሊቅ፤ የድጓ ዝማሜው አስተማሪ፤ አስታራቂ የሀገር ሽማግሌ፤ ኮሚክ፤ ቁጡ፤ አስቂኝ፣ አናዳጅ፤ ብቻ ማርም እሬትም ነበሩ።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፤ አለቃ ገብረ ሀናን ሲገልጹ፤ “አለቃ ገብረሀና እጅግ የተማሩ የጎንደር ሊቅ ነበሩ። በዚህም ላይ ጨዋታና ኃይለ ቃልን ያውቁ ነበር” ሲሉ፤ የደራሲ መንግስቱ ለማ አባት፤ አለቃ ለማ ኃይሉ ደግሞ “የሙያ መጨረሻ እሳቸው አይደሉም ወይ? የሐዲስ መምህር ናቸው። የፍትሐ ነገሥት መምህር ናቸው። … ሁሉን ስለሚያውቁ ደፍሮ እሳቸው ፊት የሚቆም አነበረም” በማለት ይገልፇቸዋል፡፡

የአለቃ ገብረ ሀና የሕይወት ታሪክ፤ የመነሻ ህብለ ሰረሰሩን ስንመዝ፤ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ ይወስደናል። በ1814 ዓ.ም የወረታው ደስታ ተገኝ እና ወይዘሮ መልካሜ ይልማ እኚህን ለሰው ሁሉ ቅኔ የሆኑትን አለቃ ገብረ ሀናን ወለዱ። ገና ከልጅነታቸው የመናገርና ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት ችሎታቸው እጅግ ከፍተኛ ነበር።

በዚያው በትንሽ ዕድሜ ከተወለዱበት አካባቢ ከፊደላት ጋር ተዋወቁ። የግእዝን ፊደላት እንደ ሽንብራ እየጠረጠሩ በማወቅ እስከ ማብጠርጠር ደረሱ። ከዚህን በኋላ እንግዲህ ከአእምሮ እየወጣ በአፍ የሚንቦገቦገውን የልጃቸውን የእውቀት ነበልባል የተመለከቱት ደስታ ተገኝ እንቦቀቅላውን ልጅ ይዘው ወደ ጎንደር ተሻገሩ። ከጎንደር የቄስ ትምህርት ቤት ገብተውም ዳዊቱንም፤ ድጓውንም፤ ዜማና አቋቋሙንም ከቅኔ ጋር አዋህደው ማጉት።

አለቃ የእውቀት እንጎቻ ቆርሰው እንደበሉ 26 ዓመት ዕድሜ ላይ ደረሱ። በሊቀ ካህንነት ተሹመውም ሰባት ዓመታትን በዚሁ ሲያገለግሉ ቆዩ። ሊቅነትና ነገር አዋቂነታቸው ባየ፤ በሰማቸው ዘንድ ሁሉ ጎልቶ መውጣት ጀመረ። ፍትሐ ነገሥትን ከስር መሰረቱ መርምሮ በማወቅ፤ በወቅቱ አለቃን የሚስተካከል አንድም አልነበረም።

በዚህም ምክንያት በዳኝነት ሸንጎ ላይ ተሰይመው ፍርድ ሰጪ፤ ፍትህ አምጪ፣ እንዲሆኑ ተደረገ። ከችሎት ወንበሩ ላይ ወጡ። የዚህን ጊዜ ነበር አለቃ ቀልደኛና ባለቅኔ ተረበኛ መሆናቸው የታወቀው። በነገር ወጋ ወጋ እያደረጉ፤ ብዙ እንዳይደማ በቅኔ እያሻሹ በማከም ከስህተትና ህጸጹ እንዲመልስ “ቢገባህ” ሲሉ ይነግሩታል። የገባውም፣ ያልገባውም በሳቅ ሲያውካካ፤ የተነካው ደግሞ መፈራገጥ ይጀምራል፡፡

ሸንጎ ላይ ሕዝብ ሰብስበው፤ ከሳሽና ተከሳሽ ችሎት አቁመው ሌባውን ሌባ፤ ቀማኛውን ቀማኛ እቅጭ እቅጩን እየነገሩ ልክ ያስገቡታል። ሰዎች በአለቃ ቀልድ፤ ለየስህተታቸው የሽሙጥ መርፌ መወጋቱ ቢሰለቻቸው ጊዜ፤ “ተው እንጂ፣ እርሶ ትልቅ ሰው አይደሉም” በማለት መክረው ቢያስመክሯቸውም የሚሰሙ አልሆኑም፡፡

ጠሊቅነታቸው፤ በተለይ በሁለት ነገሥታት ዘመን፤ አንዱ ሔዶ ሌላው ሲመጣ አለቃ ከቤተ መንግሥቱ ቁጭ እንዳሉ አሉ። አልጋ ወራሽ ባይሆኑም፤ በግብራቸው አልጋ አዳሽ፤ ጥበብ አጉራሽ ናቸውና “ኖር!” በማለት፤ የሚመጣውን እየተቀበሉ ፊት ኋላ፤ ግራ ቀኙን ያጤኑታል። የቤተ መንግሥቱ መውጫና መግቢያም ቢሆን፤ ነገሥታቱ እንኳን እንደሳቸው አያውቁትም። የቀራቸው ነገር ቢኖር ዙፋኑና አጼ የሚለው የንግሥና ማዕረግ ብቻ ነው። በዚህ ጥልቅ እውቀትና በነገር አዋቂነታቸው በነገሥታቱ ዘንድ ተፈላጊ ቢያደርጋቸውም፤ ነገር ግን ያዩትን ስህተት ሁሉ ካላረምኳችሁ ማለታቸው ምቾትን የሚሰጥ አልነበረም። ወዳጅነታቸው እንዳይቀጥልም እንቅፋት ሆኗል። የተበላሸ ነገር በተመለከቱ ቁጥር የቅኔ ዱላ እያወረዱ፤ በአፍጢም ስለሚደፉ፤ ጠቢብነታቸው ትክክለኛውን ስፍራ ለማግኘት አልቻለም።

ቅሉ ምን ሞገደኛ መምህር ቢሆኑም፤ በቤተ መንግሥት በኩል ከመፈለግ አላገዳቸውም። የትንሹ ዓሊ አጫዋችና የእውቀት አባት ሆኑ። እየኮረኮሩ ማሳቁንም ሆነ ማደስ መስራቱን እንደሆን ተክነውበታል። ከቤተ መንግሥቱ መንደርም ዝናቸው እየናኘ መምጣት ጀመረ። በዚህ መሀል አጼ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘውዳቸውን ጭነው ወደ ዙፋኑ መጡ። እየዋሉ እያደሩ አለቃን ቢያዩዋቸው ጊዜ፤ ፈገግም ቆጣም ያሰኟቸው ጀመር።

የቤተ መንግሥቱን ሰዎች በነገር ሸንቆጥ እያደረጉ አሳራቸውን እያበሉ አስቸገሩ። በዚህም የተነሳ ወደ ንጉሡ የማይመጣ ስሞታና አቤቱታ አልነበረም። ከአጠገባቸው ዞር አድርገው ያን ድንቅ እውቀትና ችሎታቸውን ለማጣት አልፈለጉምና እንደ ጸሀይም እንደ ደመናም የሆነውን የአለቃን ባህሪ ቻል አድርገው ቆዩ። አለቃም ፍትሐ ነገሥትን ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉመው ጻፉ። በዚህም የመጀመሪያው ሰው ነበሩ።

ከዕለታት በአንዱ ቀን አጼ ቴዎድሮስ አለቃን አስጠሯቸው። አለቃም እጅ ነስተው ከፊት ቆሙ። “ገብረ ሀና” አሉ አጼ ቴዎድሮስ። “አቤት ጌታዬ!” “ገብረ ሐና ፍትሐ ነገሥቱን ጻፍ፤ ፍርድ ስጥ .. ገንዘብ ያውልህ፤ ቀልድህን ግን ተወኝ!” አሉ፤ በትዕዛዝም በተማጽኖም። የአለቃ ባህሪ ግን የማይፋቅ፣ የማይፈቀፈቅ ሆነና እንኳንስ ሊያቆሙ ይበልጥ ባሰባቸው።

በቤተ መንግሥቱ ስር ካሉት ሁሉ አለቃ በነገረ ቅኔ አንካሴ እየወጉ የሚያስጨንቁት ብላታ አድጎ የተባለ የንጉሡ ባለሟል ነበር። ስሙን እያነሱ፤ “አድግ ማለት በግዕዝ አህያ ማለት ነው” ይሉታል። አድጎ፤ በየጊዜው የሚሰነዙርበትን ትችት እየወሰደ ለንጉሡ ቢዘረግፍላቸው ጊዜ፤ መሸከም ሰለቻቸውና “በሉ አሁንስ በምላስ ሳይሆን ታገሉና በጉልበት ተፈታተሹ” በማለት መለሱላቸው። ሁለቱም ወደ ትግሉ ሜዳ ገቡ።

አለቃ የምላስ እንጂ የጉልበቱ ጡንቻ ነገር አልሆንልህ አላቸውና ተሸነፉ። “ታዲያ አሁንስ ምን ይውጥህ” አሏቸው አጼ ቴዎድሮስ፣ አለቃን። “ድሮስ ቢሆን ትግል የአህያ አይደል” አሉ አለቃም። አጼ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን አንጸው ነበርና አለቃን ጠርተው “እንዴት አየኸው?” በማለት፤ “ይህ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ነው ወይንስ ጠባብ?” ይሏቸዋል፤ አለቃም “ኧረ! ሰፊ ነው እንጂ፤ ምን ጎድሎት? ለሁለት ቀሳውስትና ለሦስት ዲያቆናት ይበቃል” ሲሉ መለሱ፡፡

በጊዜው ለአንዲት ደብር ሁለት ቄስና ሦስት ዲያቆን ይበቃል፤ በማለት የወሰኑትን ውሳኔ፤ አለቃ በነገር ሸንቆጥ እያደረጓቸው ስለመሆኑ፤ አጼ ቴዎድሮስ ገባቸው።

ከዛ ወዲያ፤ አጼ ቴዎድሮስ ብዙ ጉዳዮችን አውጥተውና አውርደው ይበጃል በማለት አለቃ ገብረ ሀናን ለጨለቆት ሥላሴ አለቃ አድርገው በመሾም ወደ ትግራይ ላኳቸው። እንግዲህ ከነገሩ ጾም ይደሩ ማለታቸው ነው። አለቃም በዚያው በትግራይ ሲያገለግሉ ቆይተው በአንድ ወቅት ካህናት በንጉሡ ላይ ባስነሱት አመጽ ቀንደኛው ተሳታፊ ሆነው ተገኙ።

የዚህን ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ የአለቃ ነገር ቆረጠላቸው። አልጋ አዳሽ ሳይሆን አልጋ አፍራሽ መስለው ታዩአቸው። በጣም ተቆጥተውም ዛቱ። አለቃም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርሀት ገባቸው። አጼ ቴዎድሮስ ማምረራቸውን ስላወቁ፤ ሸሽተው ጣና ሐይቅ፣ ሬማ መድኃኒዓለም ገዳም ገቡ። በዚህ ገዳም ሳሉ ከፈጣሪያቸው ብቻም ሳይሆን፤ ከራሳቸው ጋርም የሚነጋገሩበትን የጥሞና ጊዜ በማግኘታቸው፤ ያላቸውን ሁለ-ገብ እውቀት በመጠቀም በርካታ ነገሮችን ለመፍጠር ችለዋል።

በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ “የተክሌ አቋቋም” እየተባለ ዛሬም ድረስ በብዛት በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የሚጠቀሙትን ዝማሜ በዚህ ጊዜ ነበር ያዘጋጁት። ተክሌ የአለቃ ገብረሀና የበኩር ልጃቸው ነበር። የዝማሜውን ሀሳብ ያገኙትም ድንገት ሸንበቆ በንፋስ ሲወዛወዝ ተመልክተው ነበር።

በ1864 ዓ.ም አጼ ቴዎድሮስ ሲሞቱ፤ አጼ ዮሐንስ በትግራይ መንገሣቸውን ሰሙና ከገዳሙ ወጥተው ተመልሰው ወደ ትግራይ አመሩ። ቤተ መንግሥት የለመዱ ናቸውና፤ ከአጼ ዮሐንስ ጋር ግንኙነት ስለመፍጠራቸው ግን በውል አይታወቅም። የኋላ፣ እንደገና ሌላ ነገር ሰሙ፤ አጼ ምኒልክ በሸዋ ነግሠዋል የሚል። ይሄኔ፤ በሉ ደህና ሁኑ ሲሉ፤ እንደገና ወደ ሸዋ ገሰገሱ።

የሸዋው ምኒልክና አለቃ ገብረ ሀና መልካም ግንኙነት ፈጠሩ። አጼ ምኒልክ ትንሽ ልጅ ሳሉ አለቃን በአጼ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያውቋቸው ነበር። ልጅ ሆኖ አለቃን የሚወድ እንጂ የሚጠላ አልነበረምና በዚያው የልጅነት ትውስታ እጃቸውን ዘርግተው በደስታ ተቀበሏቸው። መቀበል ብቻም አይደለም፤ በደቡብ ጎንደር በሚገኘው በአቡነ ሐራን ገዳም ላይ ሾሟቸው። ታዲያ በአንድ ወቅት አካባቢው በከባድ ረሀብና ድርቅ ተመታ፡፡

አለቃ ያ ውልፍ የሚያደርጋቸው የቸርነት ውቃቢያቸው ተነሳና ከገዳሙ ገንዘብ ላይ አንድ ሺህ ብር አውጥተው እየዞሩ ለገበሬው አከፋፈሉት። በዚህ ምክንያትም ወንጀል ሠርተዋል በማለት፤ ለፍርድ ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው። በወቅቱ የፍርድ ሚኒስትር የነበሩት አፈ ንጉሥ ነሲቡ “አለቃ ስህተት ሠርተዋል” በማለት ፈረዱባቸው።

በመሃል ወሬው አጼ ምኒልክ ጋር ደረሰ። ጉዳዩ በሰበር ወደ ዙፋን ችሎቱ ተሸጋገረና በንጉሡ ፊት ቆሙ። “ምንድን ያጠፋኸው?” ቢሏቸው፤ ያደረጉትን አስረዱ። አጼ ምኒልክም፤ “ይሄማ የሚያሸልም እንጂ የሚያስከስስ አይደለም” በማለት ነጻ አወጧቸው። በእንጦጦ ማርያም ገዳምም አለቃ አድርገው እንደገና ሾሟቸው።

ከዕለታት በአንዱ ቀን በዚያው ደብር የሚያገለግል አንድ መልከ ጥፉ ደብተራ አለቃ በባዶ እግራቸው ሲራመዱ ተመለከተና “መምህር ምነው በባዶ እግርዎ ጫማ አይገዙም?” ቢላቸው፤ “እስቲ አንተ ፊት ግዛ እኛ ደግሞ ኋላ እንገዛለን” በማለት፤ የጥያቄውን መልስ በዱላ አስታቀፉት። ከዛ ወዲያ አለቃ ወደ ጎንደር ተመልሰው፣ የነበራቸውን ተባእታዊ ክብረ ንጽህና አፍርሰው ቆንጆዋን ልጃገረድ – ማዘንጊያን አገቡ። ስንቱን ችለው አልፈውት እንጂ፣ ዝነኛና የቤተ መንግሥቱ አውራሽ፣ አጉራሽ ከመሆናቸው የተነሳ አለቃን የሚፈልጉ ሴቶች ጥቂት አልነበሩም።

አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ፤ እንዲያውም ይሻሙባቸው ነበር። ከማዘንጊያ ጋር ውሀ ተጣጥተው ጎጆ ከቀለሱ ኋላ ተክሌ የተባለውን ወንድና በፍታ የተባለችውን ሴት ልጅ ወልደው፣ ከብረው፣ ሠላሳ ጥጆችንም አስረው ኖረዋል። የተክሌ አቋቋም የተሰኘውንም ዝማሜያቸውን፤ ለወንድ ልጃቸው በግል እያስተማሩት ኋላም እንደ አባቱ ሊቅ ሆኖ በስሙ የተሰየመውን የአባቱን ዝማሜ አበረከተ። በአንድ አጋጣሚ፤ ተክሌ ዝማሜውን በተመስጦ ሲያቀርብ ተመልክተው የወደዱት የወሎው ንጉሥ ሚካኤል በስሙ እንዲሰየም አደረጉ።

አለቃ ይሉኝታና ውለታ የሚያስራቸው ሰው አልነበሩም። ነገሮችን የሚመለከቱበት መነጽር ከብዙኀኑ የተለየ ነበር። አንዳች የማይመስል ነገር ከተመለከቱ ከማረም ወደ ኋላ አይሉም። ያደረገልኝ ሰው ነው ብለው በይሉኝታ እራሳቸውን አይጠፍሩም። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከመሳፍንቱና መኳንንቱ ጋር ቁጭ ብለው ሲጨዋወቱ እንኳን ያልጣማቸውን በቅኔና በቀልድ አስደግፈው ይሸርቡታል። ይህ ነገር ከብዙዎቹ ጋር ያጎረብጣቸው ያዘ።

በአድዋ ጦርነት ወቅት ታላቅ ጀብዱ ፈጽመው ለነበሩት ለደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ምኒልክ የሚወዱትን ጎራዴ አንስተው ሸለሟቸው። ይህን ጊዜ ታዲያ “ወይ ጎራዴ፣ ወይ ጎራዴ ከቤቷ ገባች …” ሲሉ በሽሙጥ በመናገራቸው፤ ባልቻም ካልገደልኩት ብለው ተነሡ። በዚህ ሳያበቃ ከእቴጌ ጣይቱ ጋርም በሌላ ነገር ኩርፊያ ውስጥ ገቡ። ሰበብ ሲፈልግ የከረመው መላው የቤተ መንግሥት ሰው አጋጣሚዋን በመጠቀም አደሙባቸው።

አጼ ምኒልክም፤ አለቃን አብዝተው ቢወዷቸውም የማይነኩትን ሁለት አይኖቻቸውን ነክተዋልና ቅር ተሰኙባቸው። አዲስ አበባን እንዲለቁም ተወሰነባቸው። በጎንደር የተወሰነ ከቆዩ በኋላ ልጃቸው ተክሌን ጠርተው አለቃ ገብረ ሀና ሞተዋል ብለህ ተናገር በማለት ወደ አዲስ አበባ ሰደዱት። መርዶው ሲሰማም ሁሉም ቅሬታውን እረስቶ በቤተ መንግሥቱ ታላቅ ሀዘን ሆነ፡፡

ከዚያው ሆነው እርማቸውን ካወጡ ከጥቂት ቀናት በኋላም አለቃ ገብረ ሀና አዲስ አበባ መጥተው “እንደምን ከረማችሁ?” በማለት ከቤተ መንግሥቱ ዘው ብለው ገቡ። አገር ምድሩ ጉድ! አለ። አጼ ምኒልክም “ሞቱ ከተባሉ በኋላ ከየት ነው የመጡት?” ቢሏቸው ጊዜ “በሰማይ ጣይቱ የለች፤ ምኒልክ የለ፤ ጠጅ የለ፤ ጮማ የለ፤ ባዶ ቤት ቢሆንብኝ ለጠባቂው ጉቦ ሰጥቼ መጣሁ” ሲሉ አሳቋቸውና የተኳረፏቸውን ሁሉ ይቅር አስባሏቸው፡፡

የመጨረሻው ስንብት፤ አልጋ አዳሹ፤ የቤተ መንግሥቱ ሊቅ ጠሊቅ፤ አለቃ ገብረ ሀና ፍትሐዊ አይደለም ባሉት በአንድ ጉዳይ ላይ ከአጼ ምኒልክ ጋር የከረረ ሙግት ውስጥ ገቡ። በዚህ ምክንያትም ፍቅራቸው ዳግም ሻከረና ጠቅልለው ወደ ቀያቸው ተመለሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም አለቃ ሌላ ሰው፤ ሌላ ማንነት ያዙ። እንደ ቀድሞው መሳቅና ማሳቅ፤ ከእውቀት ባህር እየጨለፉ ማጠጣት ቀርቶ ለመናገር እንኳን አልፈለጉም። ዝምታን መረጡ።

“ምን ሆኑ?″ ቢባሉ ምላሽ እንኳ አይሰጡም። አፋቸው የሚከፈተው ለምግብና ውሀ ብቻ ሆነ። ከጥሩ ምግብም ሆነ ከጥሩ መጠጥ ተቆጠቡ። ብዙ መጻሕፍትን በዙሪያቸው ሰብስበው ከፈጣሪያቸውና ከመጻሕፍቱ ጋር ብቻ በንስሀ ያወራሉ። እድሜያቸውም በጣም ገፋ፤ እርጅናም ተጫጫናቸው፤ በመጨረሻም ዝም ብለው ዝም እንዳሉ 1984 ዓ.ም አረፉ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You