ቱሪዝም-  የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሌላኛው መልክ

በጣሊያን ወረራ ምክንያት የተደረገው የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል አድራጊነት ከተካሄደ 128 ዓመታትን አስቆጠረ። ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረው ይህ ድልም በትውልድ ቅብብሎሽ ታሪኩ ሲዘከርና የጀግንነት ተምሳሌት ተደርጎ ሲቆጠር ይኖራል። ከኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተሻግሮ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የፓን አፍሪካ መሰረት ለመሆንም በቅቷል።

የአድዋ ድል ለበርካታ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ነግሶ ተገቢውን ክብር አግኝቶ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበርና ሲዘከር ነበር። ይህ ድል የግዙፍነቱን ያህል በመንግስታት የሚገባውን ስፍራ አግኝቶ የሚመጥነው መታሰቢያ ባይገነባለትም ኢትዮጵያውያን ግን አንድም ቀን የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ ዘንግተውት አያውቁም ነበር። ታሪኩን ለመዘከር ወደ አደባባይ በመውጣት ክፍለ ዘመን ለተሻገሩ ዓመታት ሲያስታውሱት ነበር።

የአድዋ ድል አሁን ከዜጎች ልብ ተሻግሮ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ለድሉ የሚመጥን መታሰቢያም ኢትዮጵያውያን ወደ ጦርነቱ ለመሄድ በአንድነት በተሰባሰቡበት መሀል አዲስ አበባ ፒያሳ ተገንብቶለታል። ይህ መታሰቢያ የጀግኖች አርበኞች ድልን ዛሬ በሚመስል መልኩ ከማስታወስ ባሻገር ትውልዱ እንዲበረታ፣ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆኑን እንዲገነዘብ፣ ሕብረትና አንድነት ለድል እንደሚያበቃ፣ ኢትዮጵያ የመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምሳሌ እንደሆነች፣ የአባቶቹን ብልህነት፣ አሸናፊነትና በፈተናዎች መፅናት እንዲያውቅ ህያው ሆኖ የሚቆም ነው።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ብዙ መልክ አለው። አንድም የጀግኖች አርበኞችን መዘከሪያ፣ ሁለትም ለአዲሱ ትውልድ ማስተማሪያነት ግዙፍ ፋይዳ ያለው ነው። ከሳምንት በፊት በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ‹‹ከታሪክ ታሪክን መዘከር ብቻ ሳይሆን ከታሪክ መማር አለብን›› በማለት መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

መልዕክቱ የሚያሳየን በአድዋ ጦርነት ላይ ከተመዘገበ ድልም ያለፈ ትርጉም እንዳለው ነው። ይህን ለመረዳት የቀደመውን የአባቶችን ጥበብ፣ ጀግንነት፣ ትዕግስት፣ ዲፕሎማሲ እና ለጠላት ትምህርት የመሆን ተግባርን በቅርቡ ከተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ማግኘት ይቻላል። ይህ መታሰቢያ በመላው ዓለም ሕዝቦች የሚጎበኝ ግዙፍ የታሪክ ትምህርት ቤት (ሙዚየም) ነው። በመሆኑም በቱሪዝም ዘርፍ አንድ የታሪክ ክፍል ሆኖ እንደሚያገለግል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ለዚህም ሙዚየሙን ለአገር ውስጥና ለመላው ዓለም ሕዝብ ማስተዋወቅ የሚኖረውን ፋይዳ የዝግጅት ክፍላችን ከዚህ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ይወድዳል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የአድዋን ድልን የሚዘክረው (አድዋ ዜሮ ዜሮ) ሙዚየም በፒያሳ እምብርት ላይ ሲታነፅ መስሪያቤታቸው በአማካሪነት እንደ አንድ ባለድርሻ ተሳታፊ ነበር። እርሳቸው የሙዚየም ግንባታውን በማስመልከት ሲናገሩ፤ በተገነባው መታሰቢያ በአድዋ ዘመቻ ወቅት ጀግኖች አርበኞች ሴቶችም ወንዶቹም፣ ገበሬዎችም ይዘውት የዘመቱት ጦር መሳሪያና ሌሎችም ቅርሶችን በሙዚየሙ ውስጥ አሰባስቦ ይዟል።

‹‹ሙዚየሙ ከጦር መሳሪያ እስከ እለት ምግብ መመገቢያ ያሉት የአድዋ ዘማች አርበኞች መገልገያ በመያዙ ያንን ለትውልድ ማሳየት ይገባል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ይህ መሆኑ ታሪክን ለማሳየት እንደሚረዳ ይናገራሉ። የተማረኩ መድፎች፣ የጦር መሳሪዎች የተጠቀሙባቸው ጎራዴዎች መኖራቸውን በመግለፅ ይህ በግዜው የነበረውን ሁነት ለማሳየት እንደሚረዳ ይገልፃሉ።

አድዋ ከቅርሶቹ ባሻገር ለትውልድና ለቀሪው ዓለም ማሳየት ይቻላል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለዚህ ስነ ጥበብ አንዱ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ። በአድዋ መታሰቢያ ውስጥ የተገነቡ ቅርፆች (የጀግኖች መሪዎችና የጦር ጀነራሎች ሀውልቶች) መኖራቸውን ይናገራሉ። ቅርፆቹ የተሰሩት በምናባዊነት ሳይሆን በወቅቱ ከነበሩ ስዕሎች ያካተተ መሆኑን ይገልፃሉ።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአድዋ ድል መታሰቢያ በውስጡ በርካታ ቅርሶችን፣ መስህቦችን እና ታሪካዊ እውነታዎችን ይዟል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የወቅቱን የአድዋ ጦርነት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያሳይ (ቨርቹዋል ሪያሊቲ)፣ የአፄ ሚኒሊክና የእቴጌ ጣይቱ ሀውልት፣ የ12 ጦር አዝማች ጀነራሎች ሀውልት፣ የፓን አፍሪካኒዝም ገላጭ ምስሎች፣ በመታሰቢያ ሙዚየሙ በርካታ አዳራሾች ሲኖሩ ባለሙያዎች እነዚህ አዳራሾች የማይስ (ስብሰባ ቱሪዝም) እንደሚያሳድግ ሲገልፁ ተደምጠዋል።

አቶ እንደኛነው አሰፋ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ነው። እርሱ እንደሚለው፤ መታሰቢያው በዋነኝነት የአድዋን ድል እና ታሪኩን ጠብቆ ለማቆየት፣ ለትውልድ ለማስተማር፣ ለዓለም ዓቀፍ ጎብኚዎች እድል ለመፍጠር ታስቦ መሰራቱን ይናገራል። ማኅበሩና በውስጡ በዓባልነት የሚሳተፉት አስጎብኚዎች ይህንን መስህብ ከኢትዮጵያ የድል ታሪክነቱ ባሻገር ለቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እንደሚያምኑም ይገልፃል።

‹‹ቱሪዝም ባሕል፣ ተፈጥሮ፣ ታሪክን አጉልቶ የሚያሳይ ነው›› የሚለው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፤ አድዋም ከታሪክ ዘርፍ የሚመደብ ለዓለም ሕዝብ በኩራት ልናሳየው የምንችለው የድል ታሪክ መሆኑን ይገልፃል። አንዳንድ አገራት መጥፎ ታሪክ የደረሰባቸው ቢሆንም እርሱን ለዓለም ሕዝብ በሙዚየምነት በማሳየት ታሪኩን ከማስተዋወቅ ባሻገር የቱሪዝም አንዱ ዘርፍ አድርገው አንደሚወስዱት ይናገራል። በሩዋንዳ የደረሰው የዘር ጭፍጨፋን እንደ ምሳሌ ያነሳል። በማሊ፣ ሴኔጋልና ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን ታሪክ፣ የደረሰባቸውን በደል፣ ሲያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ (የባሪያ ንግድና የቅኝ ግዛት ታሪካዊ ማስታወሻ) እንዲሁም አጠቃላይ ታሪክ በሙዚየሞች እና በልዩ ልዩ ታሪካዊ መገለጫዎች ለጎብኚዎች ይፋ እንዳደረጉም ያስረዳል። ትውልዱን ከቀደመው ታሪክ ከማስተማራቸውም ባሻገር እንደ አንድ የቱሪዝም የገቢ ምንጭ እና የገፅታ ግንባታ እንደሚጠቀሙበት ያስረዳል።

‹‹እኛ ደግሞ የአኩሪ ድል ባለቤት ነን›› የሚለው አቶ እንደእኛነው አሰፋ፤ ይህንን የአድዋ ድል ጀግንነት፣ የአርበኞችን ተጋድሎና የነፃነት ቀንዲል እንደ አንድ የቱሪዝም አካል አድርጎ ታሪኩን ለዓለም ሕዝብ ማሳየት እና ለአገር ገፅታ ግንባታ፣ ለትውልድ መማሪያና ለፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና መሰረት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይናገራል።

የአድዋ ድል ብዙ መልክ አለው። ከዚህ ወስጥ አንዱ አድዋን ልክ እንደ አንድ የቱሪዝም መስህብ መጠቀም ነው። አቶ እንደእኛነውም ይህን ሀሳብ ይጋራል። አስጎብኚዎች፣ የታሪክ ፀሀፊዎች፣ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች የአድዋን ድል ለአገር ገፅታ መገንቢያ፣ ለቱሪስት ፍሰት ማደግና ለኢኮኖሚ ምንጭ ለማዋል በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳል። አድዋንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ታሪኮች በመሰል ማራኪ መታሰቢያዎች በአግባቡ ሰንዶና አዘጋጅቶ ለቱሪዝም መስህብነት ማዋል እንደሚገባም ይገልፃል።

የአድዋ መታሰቢያ ለማኅበረሰቡ የተለያዩ ጥቅሞችን የሚሰጡ እድሎችን ይዞ መምጣቱን የሚናገረው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፤ ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንፍረንስ ማዕከል እንደመሆኗ የአድዋ መታሰቢያ ግንባታም ያንን ታሳቢ በማድረግ ለግንኙነት ምቹ የሆኑና የማይስ ቱሪዝም አቅምን የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ አዳራሾችን ጭምር በመያዙ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ያስረዳል። የአድዋን ድል ታሪክ እያዩ፣ ታሪክን እየዘከሩ እግረ ስመንገድ ስብሰባዎችን መካፈልና ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ መታደም ስለሚቻል ፕሮጀክቱን ልዩ እንደሚያደርገው ይገልፃል።

‹‹የአድዋ ሙዚየም መገንባቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የጥቁር ሕዝብ ድል መሆኑን ማሳየት ይገባናል›› የሚለው አቶ እንደኛነው አሰፋ፤ ፕሮጀክቱንም ሆነ የአድዋን ታሪክ በዚህ አግባብ ለዓለም ሕዝብ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ይመክራል። የቱሪስት አስጎብኚዎችም የአድዋ ሙዚየም በአዲስ አበባ ውስጥ አዲስ የመስህብ አማራጭ መሆኑን ገልፀው እርሱን እንደ አንድ የቱሪዝም ምርትና መስህብ አማራጭ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ልንጠቀምበት እንደሚገባ ያሳስባል።

አድዋ በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የነፃነት ጮራ የፈነጠቀ ድል ተደርጎ ይቆጠራል የሚለው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያውያን ደግሞ በባለቤትነት ለትውልድ ማሻገር ይገባል ይላል። በተለይ በቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ አስጎብኚ ባለሙያዎች አሁን የተገነባውን የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት (ሙዚየም) መነሻ በማድረግ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ብሎም የድሉን ታሪክ እንዲጎበኙ በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ይገልፃል። በጥቁር ሕዝብ ትግል ውስጥ የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዘው የአድዋ ድል መሆኑን በማንሳትም ድሉን ሁሉም ሰው የራሱ እንዲያደርገውና ኢትዮጵያንም በዚያ መልኩ እንዲመለከት መስራት እንደሚጠበቅብን ምክረ ሀሳቡን ይሰጣል።

የቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር በአዲስ አበባ እምብርት ላይ የተገነባው መታሰቢያ የአድዋ ድልን በሚገባ የሚገልፅና ተገቢ ፕሮጀክት መሆኑን ያምናል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ይህንን ታሪክ በዚህ ሙዚየም ብቻ መወሰን እንደማይገባ ገልፀው ሌሎች ድሉንና ታሪኩን አጉልተው የሚያሳዩ ተጨማሪ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ቦታዎች መሰራት እንዳለባቸው ነው ያስረዳው።

‹‹የአድዋ ድልና ታሪካዊ እውነቶችን የቱሪስት አስጎብኚዎች በሚገባ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ ይህ ሲሆን ለጎብኚዎች ታሪካዊ ሁነቶቹን ማሳወቅና ትውልድን ማስተማር እንደሚችሉ ይገልፃሉ። በመሆኑም አዲስ የተገነባውን ሙዚየም ሁሉም ባለሙያዎች ሊያዩትና እራሳቸውን ሊያዘጋጁበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ መውጫ

የአድዋ ድል 128ተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ቢሆንም ሙዚየሙ ተገንብቶ እስከተጠናቀቀበት ግዜ ድረስ ምንን አይነት ግዙፍ መታሰቢያ ሳይገነባለት ቆይቷል። አሁን ግን የአድዋ ሙዚየም (አድዋ ዜሮ ዜሮ) በመንግስት ፕሮጀክት ተገንብቶ ለእይታ ክፍት ተደርጓል። የካቲት 23 ቀን በብሄራዊ በዓልነት በድምቀት የድል በዓሉ ሲከበርም በሙዚየሙ ደማቅ ስነስርዓት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

የምረቃ ስነስርዓቱ እለት ሙዚየም ግንባታውን አስመልክቶ ንግግርን ያደረጉት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፤ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ወደ ዓውደ ውጊያው ተምመዋል፤ በዚህም የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድልን አስመዝግበዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጀግንነት ገድል የደመቀበት በማለትም፤ ተበታትነው የነበሩ የታሪክ ማስረጃዎች የተሰበሰቡበት፤ የተረሱ የታወሱበት መሆኑን ገልፀው ነበር። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጀግኖችን በሚገባቸው ከፍታ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቅሰውም ትውልዱ በአንድነት ሆኖ ማሸነፍንና የሀገር ፍቅርን የሚማርበት መሆኑንም አንስተው ነበር። የዓድዋ ድል መታሰቢያ መላ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቋንቋ እንዲግባቡ የማድረግ ኃይል ያለው መሆኑን በመግለጽ ትናንትን ከዛሬ ዛሬን ከነገ የሚያስተሳስር ድልድይ በመሆኑ ለመጪው ትውልድ ስጦታ መሆኑን ገልፀዋል።

የመታሰቢያ ሙዚየሙም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከመላው ዓለም ታሪኩን ለማወቅ ለሚመጡ ጎብኚዎች ከየካቲት 5 ጀምሮ ክፍት እንደሆነ ተነግሯል። ከወዲሁ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ሚኒስትሮች እና ልዩ ልዩ ዲፕሎማትን ጨምሮ ለቁጥር በበዙ ቱሪስቶች እየተጎበኘ ይገኛል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You