ሌሊቱን ሙሉ ዕንቅልፍ ይሉት በዓይኑ አይዞርም። ቀኑን በሥራ ሲባትል የሚውል አካሉ እረፍት የለውም፡፡ እሱ ለአፍታ ዕንቅልፍ ካሸለበው የሚሆነውን ያውቃል። ቤቱን የሚገፋ፣ ማንነቱን የሚፈትን ጠላት ከጎኑ ነው፡፡ ድንገት ከተኛ ያደባው አውሬ ይነቃል፣ መድከሙን አይቶ ጥርሱን ያሾላል፣ ግድግዳውን ገፍቶ ሚስቱን፣ ልጆቹን ይጎትታል፡፡
ይህ እውነት ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት አልተለወጠም፡፡ አባወራው ስለቤተሰቡ መኖር የጅብ ኮቴ እያዳመጠ ፣ ከአውሬው እየታገለ የጭንቅ ዓመታትን ገፍቷል፡፡ ችግር መከራውን፣ ክረምት በጋውን ያለፈባት ደሳሳ ጎጆው ዛሬም አሮጌ ላስቲክ ሸራ እንደለበሰች ከእሱው ጋር ነች፡፡ በዚህች ጎጆ ትዳር ተቀልሶ፣ ስምንት ልጆች ተወልደው አድገዋል፡፡ መኖር ከተባለ ዛሬም በታዛው ስር ሕይወት ቀጥሏል፡፡ በጭንቅ በስጋት እየመሸ ይነጋል፡፡
መንዜው -ዓመታትን ወደኋላ …
የመንዝ ምድር ያፈራው እንቦቃቅላ ገና ከእናቱ ዕቅፍ እንደወረደ የእርሻ ሥራ ግዴታው ሆነ፡፡ አባቱ ብርቱ ገበሬ ናቸው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ቢሠሩ፣ ቢለፉ አይደክማቸውም፡፡ አንዳንዴ በእሳቸው ልክ ጠንካራ አራሽ ያለ አይመስላቸውም፡፡ ይህ እውነት ውሎ አድሮ በትንሹ ልጅ ቴዲ ትከሻ ሊተገበር ግድ አለ፡፡
ትንሹ ቴዲ ነፍስ ማወቅ ሲጀምር ትምህርት ቤት መግባት፣ ቀለም መለየት ፍላጎቱ ሆነ፡፡ እንደ እኩዮቹ ደብተር እርሳስ ይዞ ዕውቀት ሊገበይ ማልዶ ተነሳ፡፡ እንዲህ ይሆን ዘንድ ከጎኑ የቆሙት እናቱ ባቄላ አሹቁን፣ ጥሬ ቆሎውን እየቋጠሩ እንዲማር አበረቱት፡፡ አባት የእናት ልጅን ፍላጎት ባወቁ ግዜ ንዴት ገባቸው፡፡ ልጁ አርሶ፣ ጎልጉሎ ካልኖረ በልቶ ማደር እንደማይቻል አወጁ፡፡
እያደር በቤተሰቡ መሐል የፍላጎት ግጭት ነገሠ፡፡ እናት ከቴዲ ጎን ሆነው ስለትምህርቱ ‹‹በርታልኝ›› ማለትን ቀጠሉ፡፡ አባት በተቃራኒው ምን ሲደረግ ሲሉ ሞገቱ፡፡ ቴዲ ትምህርት ቤት ደርሶ መልስ የሰዓታት የእግር ጉዞ ይቆየዋል። ሜዳ መስኩን፣ ወንዝ ሸንተረሩን ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡
አንዳንዴ የእሱ ልፋት ድካም ለአደጋ ያደርሰዋል። ከሁሉም ግን ከቀናት በአንዱ የደረሰበትን ክፉ አጋጣሚ አይዘነጋም፡፡ ግዜው ክረምት የገባበት ዝናባማ ዕለት ነው። ቴዲ ሁሌም እንደሚያደርገው ሀገሬው የሠራውን አነስተኛ የእንጨት ድልድይ በሠላም ተሻግሯል ፡፡
ጥቂት ራመድ እንዳለ ግን ከየት መጣ ባልተባለ የውሀ ሙላት ተያዘ፡፡ በድንገቴው አደጋ የተዋጠው ተማሪ ራሱን ለማዳን እንደአቅሙ ታገለ፡፡ ደራሹ ትንሽዋን ድልድይ ጨምሮ እሱን አጥረግርጎ ሲወስድ ያዩ ተጯጩኸው ተከተሉት፡፡
ትንሹ ልጅ ከነደብተሩ ወንዙ አጣድፎ እያራቀው ነው፡፡ ዳርቻውን ይዘው ያሰሱ፣ የቧጠጡ በፍለጋ ደከሙ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ፍለጋው ተቃና፡፡ ‹‹ይሞታል›› የተባለው ቴዲ በሕይወት ተርፎ ተገኘ ፡፡
ይህ ክፉ አጋጣሚ የሕይወቱ ፈታኝ ምዕራፍ ሆነ። ቴዲ ነገን ካሰበው ለመድረስ ዛሬን መልፋት፣ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ይህ ዓላማው ግን በአባቱ ዘንድ ሞገስ አላገኘም። የእሱ መማር ምክንያት ሆኖ ባልና ሚስቱን አጋጭቷል። በልጅነት ጉልበቱ ጠዋት ማታ የሚሮጠው ታዳጊ ቤት ሲገባ ሠላም የለውም፡፡ አባቱ ሲያዩት ይበሳጫሉ፣ አርሶ፣ ዘርቶ አለማደሩ እያናደዳቸው ክፉ ቃል ይናገራሉ፡፡
እንደ ሰበብ …
አሁን የባልና ሚስቱ ትዳር ንፋስ ይገባው ይዟል፡፡ በጋራ ልጃቸው ‹‹ይማር፣ አይማርም›› ምክንያት የተፈጠረው ግጭት ከቅያሜ አልፎ ለከፋ ጠብ በር ከፍቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ልጁ ቴዲ ትምህርቱን አልተወም፡፡ በብርታቱ እያለፈ አንደኛ ደረጃን ተሻግሯል፡፡ ይህ ብቻውን ግን የአባቱን ልቦና አልቀየረም፡፡ የእሱ ክፍል መቁጠር ካለመታዘዝ ተቆጥሮ ውስጣቸውን አጉሿል፡፡
ውሎ እያደር የእናት አባቱ ግጭት አየለ፡፡ ችግራቸው በሽማግሌ አስታራቂ ሊፈታ ቸገረ፡፡ የልጃቸው መማር ሰበብ ሆኖ ለፍቺ ሲደርሱ ቴዲ እናቱን መክሮ ሊመልሳቸው ሞከረ፡፡ በእሱ ሰበብ ትዳር ከሚፈታ ሁሉን ትቶ ውትድርና ሊቀጠር ወሰነ፡፡ ስምንተኛ ክፍል እንደገባ ብዙ የለፋበትን ደብተር አስቀመጠ፡፡ ያለመውን፣ ያቀደውን ሁሉ ረሳ፡፡ ቀዬውን ትቶ ፣ ወላጅ እናቱን ተሰናብቶ ካገሩ ራቀ ፡፡
ወታደሩ …
1978 ዓ.ም፡፡ የመንዙ ልጅ፣ የመሐል ሜዳው ወጣት ውትድርና ሊገባ የቆረጠበት ጊዜ ሆነ፡፡ ወቅቱ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› የሚባልበት ነበር፡፡ ቴዲ የልቡን ከማድረግ ያገደው አልተገኘም፡፡ ትምህርት ናፋቂው፣ ሩቅ ዓላሚው ወጣት የአሁን ግቡ የሀገርን ድንበር ማስከበር ሆኗል፡፡
የውትድርናን ዓለም በዴዴሳ ጦር ማሠልጠኛ የተዋወቀው ቴዲ ብቁ ወታደር መሆኑን በምርቃት ካረጋገጠ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ከአለቆቹ ሌላ ትዕዛዝ ደረሰው፡፡ ወጣቱ ከሥልጠናው በኋላ ለአየር ወለድ ተልዕኮ ዳግም ወደ ብላቴ ማሠልጠኛ ሊገባ ግድ አለው፡፡ ወታደሩ ቴዲ የብላቴን ሥልጠና አጠናቆ እንደወጣ ወደ ጦር ግንባር ዘመተ፡፡ ግዜው የደርግ ሠራዊት ከሻዕቢያ ጋር የሞት ሽረት ትግል የሚያደርግበት ጦርነት ነበር ፡፡
ቴዲ በአሥመራ ከረን፣ አቆርዳት፣ ጊንዳና ተሰኔ ላይ በውጊያ ተሳተፈ፡፡ በሰማይ ጀቱ፣ በምድር ታንክ መትረየሱ ሲያጓራ በጀግንነት ተገኘ፡፡ የጦርነት ወላፈን ገረፈው፣ በድካም ውሀ ጥም ተፈተነ፣ ከእሳቱ ላንቃ ገብቶ ዋጋ ከፈለ፡፡ ጦርነቱ ሲፋፋም የትግል ጓዶቹ ከጎኑ ወደቁ፡፡ ዓይኑ እያነባ ውስጡ አዘነ፡፡
ቴዲን ክፉ አጋጣሚ አላለፈውም፡፡ በውጊያው መሐል፣ ራሱን፣ እጆቹንና ጀርባውን ተመቶ ቆሰለ፡፡ ለወራት ሆስፒታል ገብቶ አገገመ፡፡ ከዚህ በኋላ የጠበቀው ቦርድ መውጣት ውትድርናን መሰናበት ነበር፡፡
ቦርድ በወጣ ማግስት ለአገልግሎቱ የተሰጠው ክፍያ በወር ሰማንያ አምስት ብር ሆነ፡፡ በወቅቱ ኑሮ የተሻለ ቢሆንም ለቁስለኛው ወታደር በቂ የሚባል አልነበረም። ለሀገሩ መስዋዕት የሆነው ቴዲ አሁን እንደቀድሞው አይደለም፡፡ አካሉ ተጎድቶ ውስጡ ተዳክሟል፡፡ በሕይወት መኖሩ ግን ታላቅ ተስፋው ነበር፡፡ ተመልሶ ሀገር ቤት ገብቷል፡፡ ሁለት ልጆች ወልዶ አባት መሆን ችሏል፡፡ እንደትናንቱ ከእናት አባቱ አርፎ ሕ ይወትን ጀምሯል፡፡
1983 ዓም
እነሆ ዛሬ ትናንትን አልሆነም፡፡ በመላው አገሪቱ የለውጥ ንፋስ እያየለ ነው፡፡ አሁን ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ከደርግ ተረክቧል፡፡ ይህ ወቅት ቴዲን ለመሰሉ የሀገር ባለውለታዎች የፈተና ሕይወት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከሥራ ተፈናቅለዋል፡፡ በርካቶች ከሀገር ተሰደዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ታሪካቸው በክፉ አጋጣሚዎች ተቀይሯል፡፡
ቴዲ ይህን ግዜ በእናት አባቱ ቤት በእንግድነት አርፏል፡፡ የቆሰለ የደማው ስለ ሀገሩ ነውና ትናንት በሆነው አይቆጨም፡፡ ግዜውን እንዳመጣጡ ተቀብሎ ነገን በተስፋ ይጠብቃል፡፡ እንዲያም ሆኖ ችግር አላጣውም፡፡ የቀድሞ ወታደር መሆኑን ያወቁ አንዳንዶች ጣት ቀሰሩበት፡፡ በቤቱ ደብቆ ያስቀመጠው ክላሽ መኖሩን የሰሙ አካላት ካለበት ደርሰው በጥያቄ አጣደፉት፡፡
አንዳች የሚያውቀው እንደሌለ ሊያስረዳ ሞከረ፡፡ ቃሉን አምኖ የተቀበለው የለም፡፡ ሰዎቹ ግዜ አልፈጁም። ቤትና ግቢውን አገላብጠው ፈተሹ፡፡ አንዳች ፈልገው ባጡ ግዜ ዝም አላሉም፡፡ ቴዲ ተይዞ ወደ እስር እንዲላክ ፈረዱበት። በከንቱ ጥርጣሬ የተከሰሰው ወታደር ከቤተሰቡ ተነጥቆ እስርቤት ተወረወረ፡፡
ያን ዘመን ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስታውሰው ብዙ ጉዳዮች ውል ይሉታል፡፡ በወቅቱ እሱን ጨምሮ ሌሎች በክፉዎች እንዲንገላቱ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ቴዲ ወሎ ምድር ‹‹ደንቆሮ ዋሻ›› ከተባለ ቦታ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ቆየ። እስረኛው ነፃ ተብሎ ከተለቀቀ በኋላ ተመልሶ እናት አባቱ ቤት ገባ፡፡ ቆይታው እምብዛም አልዘለቀም፡፡
እንደቀድሞው ብርታት ጥንካሬው ከእሱ የለምና ስለራሱ አብዝቶ ተከዘ፡፡ እንደሀገሬው አርሶ፣ ዘርቶ እንዳያድር እጁ ታሟል፣ አካሉ ደክሟል፡፡ ይህን ሲያስብ ልቡ አርቆ አሰበ፡፡ ጓዙን ሸክፎ ቀዬውን ሊሰናበት ሲወስን መንገዱ አዲስ አበባ ነበር፡፡
ኑሮን እንደገና …
በአዲስ አበባ አካባቢውን ለመልመድ አልተቸገረም። ማረፊያውን ቂርቆስ አካባቢ አድርጎ ለራሱ መተዳደሪያ የቀን ሥራ ጀመረ፡፡ ከውሎው መልስ ጥበበኛ እጆቹ ሌላ ስራ አላጡም፡፡ ኑሮውን የሚደጉም አቅሙን የሚደግፍ ገቢ መፍጠር ያዘ ፡፡
ቴዲ ማዳበሪያ እየተለተለ በወጉ የሚያዘጋጀው ገመድ ለአህዮች መጫኛ ተመራጭ ሆነለት፡፡ መርገጡን፣ ማነቆና ጅራፉን አሳምሮ ለገበያ አቀረበ፡፡ ጥቅሙን ያወቁ ብዘዎች አይተው፣ ፈልገው መረጡት፡፡ ከሚሸጠው እየቆጠበ ሥራውን አጠናከረ፡፡ ይህ ብርታቱ ብቻውን አላቆመውም፡፡ ከትዳር አጋሩ አገናኝቶ ጎጆ አወጣው፡፡ ውሎ አድሮ የሦስት ጉልቻ ሕይወቱ ሰመረ፡፡ ቤቱ በልጆች በረከት ታደሰ፡፡
ከቀናት በአንዱ አባወራው ቴዲ ጤና እንዳልተሰማው ውስጡ ነገረው፡፡ ደርሶ የሚያስጨንቀውን ሕመም ሊረዳ ወደ ሆስፒታል አቀና፡፡ የምርመራው ውጤት የሳንባ በሽታ መሆኑ ተነገረው፡፡ ቀጣዮቹ ጊዜያት ለቴዲ ሕይወት እጅግ ፈታኝ ነበሩ፡፡ መላ ሰውነቱን ይዞ እስከ ጭንቅላቱ የዘለቀው ሕመም በቀላሉ የሚድን አልሆነም፡፡ ከዛሬ ነገ ሞተ እየተባለ ወራትን በስቃይ ገፋ፡፡ ውሎ አድሮ ማገገም መዳኑ አልቀረም፡፡
ያለፈበት በሽታ ያሳደረው ችግር የዋዛ አልሆነም፡፡ በጊዜ ሂደት ግን ጤናው ተመለሰ፡፡ ውስጡን እያስታመመ፣ አቅሙን እያባበለ ዳግመኛ ለሥራ ተነሳ፡፡ ብርቱ እጆቹ ከታዘዙበት ሊውሉ አልሰነፉም፡፡ የተጎዳ አካሉን በክራንች ተመርኩዞ ሌላውን ቀን ናፈቀ፡፡ ሕይወት ፊት አልነሳችውም፡፡ ለመኖር፣ ዳግመኛ ለመተንፈስ ተጨማሪ ዕድል አገኘ፡፡
ትዳር በላስቲክ ጎጆ
ጦርነቱ ያሳደረበት ጠባሳ እያደር መታየቱ አልቀረም። ጎኑ ሲጎዳ፣ ውስጡ ሲዳከም ጥይት ያገኘው አካሉ አቅም ያጣ ጀመር፡፡ ቴዲ በየቀኑ ቢንገዳገድም አልወደቀም፡፡ እጅ ላለመስጠት ከኑሮ ትግል ገጠመ፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር መሐል የትዳር አጋሩ ከጎኑ አልራቀችም፡፡ ጎዶሎውን እየሞላች ተስፋውን እያበራች አብራው ተጉዛለች፡፡
ባለቤቱን ያገኛት የሰድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ ትዳር አስበው ጎጆ እንደቀለሱ ጅምር ትምህርቷ ተቋርጧል፡፡ አስራ ስምንት ዓመታትን የቆጠረው ትዳራቸው የጸናው በደሳሳዋ የላስቲክ ጎጆ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ቤት ስምንት ልጆች ተወልደው አድገዋል፡፡
የካ ሚካኤል ደጃፍ ኪዳነምህረት ፀበሉ ጥግ ዓመታትን የቆጠሩት የቴዲ ቤተሰቦች ጆሯቸው የቅዳሴን ዜማ ብቻ አያዳምጥም፡፡ መሸት ብሎ ለዓይን መያዝ ሲጀምር አስገምጋሚው ድምፅ ይቀርባል፡፡ ይህን ድምፅ ለዓመታት ሲሰሙት ኖረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ሁሌም እንደ አዲስ ያስደነብራቸዋል፡፡
አንዳንዴ አያ ጅቦ በሩቁ ጮሆ መመለስን አይሻም፡፡ የሰው ጠረንና ወዝ ሲሸተው ይጎማጃል፡፡ ይህኔ ጠጋ ብሎ አቅመ ቢሱን ግድግዳ መግፋት ይፈልጋል፡፡ ቢመቸው ውስጥ ዘልቆ የልቡን ቢፈጽም ደስታው ነው፡፡ በዚህ ደሳሳ ቤት ስምንት ልጆች ውለው ያድራሉ፡፡ ከነዚህ መሐል ገሚሶቹ ነፍስ ያላወቁ እምቦቃቅላዎች ናቸው፡፡
ለፍቶ አዳሪዋ ሴት ልጆች አሳድጎ ወግ ለማድረስ አትሆነው የለም፡፡ ዘወትር ጧት ማታ ጉልበቷን ገብራ ላቧን ታፈሳለች፡፡ ልጆቿን ባዶ ቤት ትታ ለመተው በሰጋች ግዜ በየደረሰችበት ይዛቸው ትሄዳለች፡፡
የቴዲ ጎረቤቶች እንደሱ ኑሮ የከበዳቸው፣ ኑሮ የመረራቸው ምስኪኖች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ አካላቸው የተጎዳ፣ አቅማቸው የደከመ ነው፡፡ ስፍራውን የሙጥኝ ብለው ዓመታትን ሲገፉ ‹‹ነገሬ›› ያላቸው በጎ አሳቢ አልተገኘም፡፡ ይህ ስፍራ ለኑሮ አመቺ አይደለም፡፡ ከዓመት ዓመት ጨለማ ነው፡፡ አንድ ጄሪካን ውሀ በሀያ አምስት ብር ይገዛል፡፡
የበረቱ ያገኙትን ቀምሰው፣ ተካፍለው ያድራሉ። ያጡ የነጡት ጦማቸውን መደፋታቸው ብርቅ ። ዛሬ አባወራው የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሚሊኒየም መንገድ ከሚባለው አካባቢ በሥራ ተጠምዶ ይውላል፡፡ አካል ጉዳተኞች በጥረታቸው ካደራጁት ብሩክ ሀብታሙና ጓደኞቻቸው የስጋጃ አምራች ማኅበር አባል ነው፡፡ ሥራው ባለ ግዜ የእጅ ሙያውን አይሰስትም፡፡ ቴዲ የኑሮ ውድነቱን ጫና፣ የክረምት ውርጩን ፈተና ለዓመታት ሲታገለው ኖሯል። ስምንት ልጆቹ እሱ ባለፈበት መንገድ እንዲራመዱ አይሻም። በእሱ የቀረውን ትምህርት አጠናክረው ራሳቸውን እንዲያሸንፉ እየጣረ ነው፡፡ ለትምህርት የደረሱት ቀለም ቆጥረው ይመለሳሉ፡፡ አባት ሁሉን እንደየአቅሙ ታግሎ ያሳድራል፡፡
ሕይወት ከጅቦች ጋር
ለእሱ ከባዱ ፈተና በየግዜው ከሚዞረው ጅብ ጋር መተናነቁ ነው፡፡ አባወራው ይህን የሕይወት ትግል አሸንፎ ለመጣል ቀን ይቆጥራል፡፡ በዚህ መሐል ክንዱ ዝሎ እንዳይሸነፍ ብርታቱ የላቀ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በክፉ አጋጣሚዎች፣ መሐል መመላለሱ አልቀረም፡፡ ከቀናት በአንዱ ከቴዲ ልጆች በዕድሜው ትንሹ ድንገት ከቤት ወጥቶ በራፉን ራቀ፡፡
ግዜው መሸት ብሏል፡፡ ጨረቃ ደምቃለች፡፡ የልጁ መውጣት ምክንያቱ ሽንቱን ለመሽናት ነበር፡፡ ይህኔ ያደፈጠው፣ ያደባው አውሬ ዓይኖች አዩት፡፡ አያ ጅቦ እንደተጎማጀ ጥርሱን አሹሎ ሕጻኑን መዞር ያዘ፡፡ ልጁ አጠገቡ የቆመውን ፍጡር አይቶታል፡፡ ውሻ ነው ብሎ ችላ ብሎታል፡፡ ይህን በቅርቡ ያስተዋለ የቤተክርስቲያኒቱ ዘበኛ አጠገቡ ደርሶ ከመዘንጠል እስኪያስጥለው ማንም ያየው የለም፡፡
ይህ ቤተሰብ በእንዲህ አይነት የስጋት ኑሮ እንደተያዘ ዓመታትን ገፍቷል፡፡ ዛሬም ግን ስለመፍትሔው ያስተዋሉ ዓይኖች የሉም፡፡ አሁንም በዚህ ጎጆ ዕንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ቀጥለዋል ፡፡ ቴዴ ‹‹ቤት ስጡኝ›› ሲል ለዓመታት በቀበሌዎች ደጃፍ ተመላልሷል፡፡ ከባዶ ተስፋ በቀር ያገኘው የለም ፡፡
አባወራው ቴዲ ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት በወጉ ዕንቅልፍ አላየም፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር በክፉ ዓይን ለሚያየው ጠላቱ ዘብ እንደቆመ ዕድሜውን ፈጅቷል። ኑሮ ከችግር፣ ሕይወት ከጅቦች ጋር እንዲህ በመፋጠጥ ቀጥሏል። በአባወራው ቴዲ ታደሰ ቤተሰቦች ዘንድ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም