ራስ ላይ ማተኮር

እውቁ አሜሪካዊ ደራሲና አነቃቂ ንግግር ተናጋሪ ቶን ሮቢንስ ‹‹energy flows where the atten­tion goes›› ይላል፡፡ ጉልበትህ የሚፈሰው ትኩረትህ ወዳለበት ነው እንደማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ትኩረት ምን ማለት ነው? ትኩረት ማለት የምትፈልገውን ነገር ማወቅ፤ ቀጥሎ ዐይንህን ከምትፈልገው ነገር ላይ አለመንቀል ማለት ነው፡፡ ትኩረት ዐይንህን ከአንድ ነገር ላይ ሁልጊዜ መጣል ማለት ነው፡፡

መቼም ታውቃላችሁ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ በበረዶ ላይ የሚንሸራተቱ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በበረዶው ላይ ሲንሸራተቱ ከዛፎች ጋር አይጋጩም። ለምን ይመስላችኋል? ስለተለማመዱት?፣ ልምድ ስላላቸው?፣ ጎበዝ ስለሆኑ?፣ ተሰጥኦ ስላላቸው? አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዛፎቹ ጋር የማይጋጩት በፍፁም ዛፎቹን ስለማያዩ ነው፡፡ መንገዱ ላይ ነው ትኩረታቸው፡፡ መንገዱን ያያሉ፤ በመንገዱ እየተሸሎከሎኩ ያመልጣሉ፡፡

እርስዎም ዐይንዎ ችግሮዎ ላይ ከሆነ ከችግሮዎ ጋር ሄደው ይላተማሉ፡፡ ዐይንዎ ከሰዎችና ከሁኔታዎች ጋር ከሆነ ሁልጊዜ ሰዎችና ሁኔታዎች ያስቸግርዎታል፡፡ መቼም ደስተኛ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ ሙሉ ትኩረትዎ ራስዎ ላይ መሆን አለበት። ራስዎ ላይ ባተኮሩ ቁጥር ሰዎች ወደእርስዎ ማየት ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ ትኩረት ያስፈልግዎታል፡፡

ትኩረትዎ ድክመትዎ ላይ ከሆነ ሽባ ይሆናሉ። አቅምዎን መጠቀም አይችሉም፡፡ ትኩረትዎ የሚፈልጉት ነገር ላይ ከሆነ ግን ሙሉ አቅምዎን ሰብስበው የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ማንኛውንም ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ አይተው ከሆነ ሰዎች ከመሬት ተነስተው ገንዘብ ጠይቆዎት አይ! የለኝም ከየት አመጣለሁ? ብለው መልሰውላቸዋል እኮ፡፡ ግን በአጋጣሚ የሚወዱት ሰው ሲታመም ወይም ችግር ሲገጥመው ከየትም ብለው በአንድ ጊዜ ገንዘቡን ያመጡታል፡፡ ሃሳብዎ ብሩን ማግኘት ላይ ብቻ ነበር ማለት ነው፡፡ ለዚያም ነው ያገኙት። ‹‹ትኩረትዎ ያለበት ነገር ላይ በሙሉ ጉልበትዎ ይፈሳል ያለው ቶኒ ሮቢንስ እዚህ ጋር ነው፡፡

ትኩረትዎ ራስዎን መቀየር ላይም ከሆነ ይቀየራሉ፡፡ አይጠራጠሩ! ኃላፊነት ይውሰዱ። ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር ይለዩ፡፡ በሕይወትዎ ምንድን ነው ቅድሚያ የሚሰጡት? ለእርስዎ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ነገር ምንድን ነው? አንድ የተከበረ ኢትዮጵያዊ ሰው በሕይወቱ ለአምስት ነገሮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይናገራል፡፡ የመጀመሪያው ፈጣሪዬ ነው፣ ሁለተኛው ጤናዬ ነው፣ ሦስተኛው ቤተሰቤ ነው፣ አራተኛው ሥራዬ ነው፣ አምስተኛው ደግሞ መዝናኛ ነው ይላል፡፡

ስለዚህ ይላል ሰውዬው፡- ሁሌ ጠዋት ስነሳ በመጀመሪያ ቅድሚያ ለምሰጠው ለፈጣሪዬ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ከዚያ ለጤናዬ የሚጠቅመኝን ማለትም ውሃ እጠጣለሁ፣ ስፖርት እሠራለሁ፣ ገላዬን እታጠባለሁ ጥሩ ነገር እመገባለሁ፡፡ ከዚያ የምወዳቸው ቤተሰቦቼን እንዴት እንደሆኑና ደህንነታቸውን እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሥራዬ እገባለሁ፡፡ ጠንክሬ እሠራለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እዝናናለሁ፤ አዕምሮዬን ነፃ አደርገዋለሁ። ሁሌም ቅድሚያ የምሰጠውን ስለማወቅ፣ ለራሴ ቦታ ስለምሰጥ፣ ራሴ ላይ ስለማተኩር በጣም ደስተኛ ነኝ ይላል፡፡

አንዳንዴ ለሰዎች ቅድሚያ ሊሰጡ ይችላሉ። እርስዎ ግን ጠንካራ ካልሆኑ፣ ጤነኛ ካልሆኑ ለሌሎች ለሰዎችም ሸክም ነው የሚሆኑት፡፡ ለዚያ ነው እርስዎ መጠንከር ያለብዎት፡፡ ራስዎ ላይ ማተኮርና መለወጥ ያለብዎ ለዚያ ነው፡፡ አያችሁ! ራስ ወዳድነት አይደለም ራስን መቀየር፡፡ ራስን መቀየር ማለት ለሚወዷቸው ሰዎች ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡ ከፍ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ራስዎ ላይ ማተኮር አለብዎት፡፡

ራስዎ ላይ ሲያተኩሩ ችግር ማለት ለእርስዎ ከፍ የሚሉበት ደረጃ ነው፡፡ ፈጣሪም ቢሆን ውድ ስጦታውን በችግር ነው ያቀለለው፡፡ ችግርዎ እንዲፈታልዎ ውጪ ውጪ አይመልከቱ፡፡ እርስዎ ለምንም ነገር አያንሱም፡፡ ወደራስዎ ይመልከቱ። በሰው መደገፍ አያዋጣዎትም፡፡ በሌሎች ሰዎች አይተማመኑ፡፡

የሻሞላ ጎበዝ ተዋጊ መሆን ይፈልጋል፡፡ የሚገርማችሁ ወቅቱ መካከለኛው ዘመን/medival period/ የሚባልበት ነበር፡፡ በዚያ ዘመን በሻሞላ መዋጋት ታላቅነት ነበር፡፡ አንድ ልጅ የሻሞላ ጎበዝ ተዋጊ መሆን ፈለገ፡፡ አንድ ትልቅ የተከበረ የሻሞላ ማስተር ጋር ሄደ፡፡ ከዚያም ‹‹እኔ ጎበዝ የሻሞላ ተዋጊ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹ከእኔ ምንድን ነው የሚጠበቀው? ምን ላድርግ?›› ብሎ ማስተሩን ጠየቀው፡፡ ማስተሩ መለሰለት ‹‹ካንተ የሚጠበቀው ልምምድ ማድረግ ነው፡፡ በደንብ ከተለማመድክና በደንብ ከሠራህ ጎበዝ የሻሞላ ተዋጊ ለመሆን ሃያ አመት ይፈጅብሃል›› አለው፡፡

ልጁ ደንግጦ ‹‹እንዴ ማስተር! እኔ በደንብ ትኩረት አድርጌ በደንብ ጠንክሬ ሻሞላ ውጊያውን እለማመዳለሁ፡፡ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ መጨረስና ጎበዝ መሆን እፈልጋለሁ፤ እንደዚያ ካደረኩ ምን ያህል አመት ይፈጅብኛል?›› አለው፡፡ ማስተሩ ‹‹አይ ጥሩ! በደንብ ትኩረት አድርገህ ጥሩ የሻሞላ ተዋጊ ለመሆን ከጣርክ አርባ አመት ይፈጅብሃል አለው፡፡ ልጁ ድጋሚ ደንግጦ ‹‹እንዴ ማስተር! ጨመር አድርጌ ሌትም ቀንም እለማመዳለሁ፡፡ ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ምርጥ የሻሞላ ተዋጊ መሆን እፈልጋለሁ፤ ቶሎ መቻል ነው የምፈልገው ስንት አመት ይፈጅብኛል እንደዚያ ባደርግ አለው፡፡

ማስተሩም ‹‹በርገጠኝነት የሚፈጅብህ ስልሳ አመት ነው›› አለው፡፡ ልጁ ደነገጠ ‹‹እንዴ ማስተር እኔ ጉልበቴንና ልፋቴን በጨመርኩ ቁጥር ለምድን ነው አመቱ የሚጨምረው? ብሎ ጠየቀ፡፡ ማስተሩ መለሰ ‹‹የኔ ልጅ ያንተ ትኩረት እኮ ውጤቱ ላይ ነው፡፡ አንተ ምርጥ የሻሞላ ተዋጊ እሆናለሁ ስትልና እዚያ ላይ ስታተኩር በደንብ አትለማመድም። በደንብ አትችልም፡፡ ለዚያ ነው አመታት የሚፈጅብህ። አትቸኩል! ትኩረትህ ውጤቱ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ልፋቱ ላይ መሆን አለበት። የፈጀውን ጊዜ ይፈጃል እንጂ እኔ እለማመዳለሁ ማለት ነው ያለብህ፡፡ ጊዜው ማጠሩን አትይ አለው።

እርስዎም በሕይወትዎ ውስጥ ጊዜው እንዲያጥር ይፈልጉና ይረዝምብዎታል፡፡ መቼ ነው የምለወጠው፤ መቼ ነው ገንዘቡን የማስቀምጠው፤ መቼ ነው የምቀየረው እያሉ ይሆናሉ፡፡ ሕይወት እንደዚያ አይደለም፡፡ ትኩረትዎ ራስዎን መቀየርዎ ላይ ነው እንጂ የሚያገኙት ለውጥ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ከውጤቱ በላይ ከሂደቱ ጋር በፍቅር መውደቅ አለብዎ፡፡ ስፖርቱ ከሚሰጥዎ ቅርፅ በላይ ስፖርተኛ መሆን፣ በየቀኑ መሥራትዎን መውደድ አለብዎት፡፡

ከሚደርሱበት የተራራ ጫፍ በላይ እያላብዎ ተራራውን መውጣቱን ማጣጣም አለብዎ፡፡ ከመድረሻው በላይ ጉዞውን ማፍቀር ይኖርብዎታል። ለምን መሰለዎ? ትንሽ ተጉዘው በቃኝ ይላሉ። ትንሽ ሞክረው ያቆማሉ፡፡ ለዚያ እኮ ነው አንድ ሰሞን ጠዋት ተነስተው ስፖርት ይሠራሉ፣ ቋንቋን ይለማመዳሉ፡፡ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ይጀምራሉ፡፡ ከዚያ ግን ያቆማሉ፡፡ ትኩረትዎ ሽልማቱ ላይ ነው። የታል የከሳሁት፣ የታል ደመወዝ ያገኘሁት፣ የታል የተሳካልኝ ይላሉ፡፡

ስኬት የሚኖሩት ሕይወት እንጂ አሳደው የሚይዙት ጭራ አይደለም፡፡ ጠዋት መነሳት ሲጀምሩ ስኬታማ ሆነዋል እኮ! ራስዎን ማሳደግ፣ ማንበብ፣ መማር፣ ገንዘብ ማስቀመጥ ሲጀምሩ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ ይህች ዓለም ጥረትዎን እንጂ ውጤትዎን ላትሸልም ትችላለች፡፡ ሰዎች ለውጥዎን ቶሎ አይተው ላያደንቅዎት ይችላሉ፡፡ እርስዎ ግን ውስጥ ለውስጥ እየተለወጡ ነው፡፡ እውነተኛ ለውጥ ደግሞ ከውስጥ ነው መነሻው፡፡ ውጪው ጭራ ነው ውስጥዎን ተከትሎ የሚደምቅ ነው፡፡ እርስዎ ግን ራስዎ ላይ ያተኩሩ፡፡ ራስዎ ላይ መሥራት አለብዎ!

በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራ አይስሩ፡፡ አንዱን መርጠው እርሱ ላይ ያተኩሩ፡፡ learn local.org የተሰኘ አንድ ድረገፅ ‹‹አንተ ጥሩ የሆንክ መስሎህ ሁለት ሦስት ሥራ ስትሠራ ሳታውቀው አይ ኪውህን በአምስት እየቀነስከው ነው ስለዚህ ስማርት እንዳትሆን ያደርግሃል ይላል፡፡ ስለዚህ እርስዎም ሁለት ሦስት ሥራዎችን መሥራትዎን ያቁሙ። እርስዎ ምርጥ የሆኑበትን ይለዩ፡፡ እርሱ ላይ ያተኩሩ፡፡

ምን መሰለዎት! መሮጥ ብቻ አሸናፊ አያደርግም። የሚሮጡበትን መለየት አለብዎ፡፡ የአጭር ርቀት ሯጩ ከቀነኒሳ በቀለ ጋር 5 ሺ ሜትር ቢወዳደር በዝረራ ነው የሚሸነፈው፡፡ አዩ! እርስዎም ብዙ ሥራዎችን ስለሠሩ ይሳካልዎታል ማለት አይደለም። ጠንካራ ጎንዎን ለይተው ይወቁ፡፡ እርሱ ላይ ዋጋ ይክፈሉ፡፡ ሰው ከሰላሳ አምስት ወይም ከአርባ አመቱ በኋላ ይናቃል፡፡ ወይ ትዳር ሲይዝ አልያም ልጅ ሲወልድ ትኩረቱ ገንዘብና መለወጥ ላይ ይሆናል፡፡ ለምንድን ነው? ካላችሁ ያው ትዳር አለኝ ልጅ አለኝ በርትቼ ወጥሬ ልስራ ብሎ ሙሉ ትኩረቱን ራሱን መቀየር ላይ ስለሚያደርግ ነው፡፡

አንተም ራስህ ላይ ማተኮር ያለብህ እስክታገባ ወይም ሰላሳና አርባ አመት እስኪሞላህ ብቻ አይደለም፡፡ አሁኑኑ ንቃ ! አሁን ያን ትኩረት አምጣው፡፡ ራስህ ላይ አተኩር፡፡ ራስህን ስለመቀየር፣ ስለመማር፣ ስለመለወጥ፣ ገንዘብን ስለማስቀመጥና የሆነ ነገር ላይ ስለመግባት አስብ። ቆመህ ባለህበት ስለመቅረት አታስብ፡፡ ባለህበት አትራመድ፡፡ ራስህ ላይ ማተኮር ማለት ነገ የሚኖርህን ብስለት አሁን ማምጣት ነው፡፡

አስተውለህ ከሆነ በአንድ ቀስት ብዙ ኢላማ መምታት አትችልም፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀስት ለአንድ ኢላማ ነው የተፈጠረው፡፡ እርሱንም ቢሆን ጥሩ አድርገህ ካነጣጠርክ ነው ያ ቀስት ኢላማውን የሚመታው፡፡ በሕይወትም ብዙ ሥራ፣ ብዙ ቢዝነስ ስለሞከርክ ስኬታማ ትሆናለህ ማለት አይደለም፡፡ ደስ የሚለው ግን ብዙ በሞከርክ ቁጥር ስኬታማ የሚያደርግህን ዘርፍ እየለየህ ትመጣለህ። በተቻለህ አቅም አንድ ሥራ ከዳር ሳታደርስ ሌላ አትጀምር፡፡ ያለበለዚያ ጎዶሎ ነገር ይበዛብሃል። ከአንዱም ሳትሆን ትቀራለህ፡፡ ትኩረት የሌለው ሰው ከመንገድ ይቀራል፡፡ ጠቅላላ እውቀት ምንም አያደርግልህም፡፡ ግን በአንድ ነገር ጥልቅ እውቀት ነው የሚያስፈልግህ፡፡

ድምቅ ባለ ፀሐያማ ቀን ወረቀት ዘርግተው ከላዩ ላይ የሚነቃነቅ መስታወት ምንም አይፈጠርም። ግን መስታወቱን ቀጥ አድርገው አንድ ቦታ ላይ ቢያቆሙ ወረቀቱ በፀሐይ ጨረር እሳት ፈጥሮ መንደዱ አይቀርም፡፡ የፀሐዩ ጨረር የስኬት ጥማት ነው፡፡ ወረቀቱ ልፋት ነው፡፡ መስታወቱ ትኩረት ነው፡፡ በመጨረሻ እሳቱ ስኬት ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከጎደለ እሳቱ ወይም ስኬቱ አይኖርም፡፡

ብዙዎቻችን የሚጎድለን አንድ ነገር ነው፤ ትኩረት፡፡ ብዙ ሥራዎችን እንሞክራለን ግን የትኛው ሥራ ወደ አላማችን እንደሚያደርሰን አናውቅም፡፡ ራሳችንም ላይ አናተኩርም፡፡ ስኬታማ መሆን ፈልገህ ብዙ ነገር ላይ የምትሮጥ ከሆነ እንደሚነቃነቀው መስታወት ስለምትሆን እሳት የሆነ ስኬት አይኖርህም፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም አንድ ነገር ብቻ ላይ አተኩሩ፡፡ ስኬታማ ለመሆን የሚያስብ ሰው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሚፈልገውን መጨበጡ አይቀርም፡፡

እንደሳር ወደ ጎን ከማደግ ይልቅ እንደ ዛፍ ወደ ላይ ማደግ ይሻልሃል፡፡ አየህ! ብዙ ሥራ መሥራት ማለት፣ ብዙ ቦታ መሳተፍ ማለት እንደሳር ማደግ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሊሳካልህ ይችላል፡፡ በአንዱ ብቻ ብትሄድ ግን ትልቅ ጫፍ ልትወጣ ትችላለህ፡፡ ሳርም እኮ ያድጋል እንደዛፍ አይሁን እንጂ! ዛፍ ግን ላይ ጫፍ ድረስ ይወጣል፡፡ ማደግ እስከሚችለው ድረስ ያድጋል፡፡ አንተም አንድ ነገር ላይ አተኩረህ ማደግ እስከምትችለው ድረስ ማደግ አለብህ!!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You