የወጣትነት ዘመን ብዙዎች እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል የሚያስቡበት የእድሜ ክልል ነው። አንዳንዶች የስኬትን መንገድ ጀምረው ለጉዞው ደፋ ቀና የሚሉበት የሕይወት ምዕራፍም ነው፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ገና በወጣትነታቸው ከስኬት ጋር ጥልቅ ትውውቅ ይኖራቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከእያንዳንዱ የሕይወት ገጠመኝ ልምድና ተሞክሮ የሚቀስሙ እና ልምዱን በማስተዋል የሚተገብሩ፣ አዳዲስ ተግባራትን በፅናትና በጥንቃቄ የሚሞክሩ እንዲሁም መነሻቸውን የማይዘነጉ የስኬት አርዓያዎች ናቸው፡፡ የ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ባለቤትና ስራ አስኪያጅ በሱፍቃድ ተስፋዬ፣ በአዲስ ስራና በጠንካራ ትጋት ታጅበው በስኬት ጎዳና ላይ ከሚገኙ ስኬታማ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በሱፍቃድ የተወለደው በ1983 ዓ.ም፣ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ አካባቢው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአረርቲ ከተማ ተምሯል። የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤቱ እንዳሰበው ሳይሆንለት መቅረቱ ሕይወትን በሌላ አቅጣጫ እንዲመለከታት አደረገውና ከቤተሰቦቹ ባገኘው መነሻ ካፒታል ወደ ንግድ ስራ ገባ። በግብርና ስራ ላይ ከተሰማሩ ቤተሰቦች የተገኘው በሱፍቃድ፣ ወደ ንግዱ ዓለም ለመግባት የመጀመሪያው የቤተሰቡ አባል ነው፡፡
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በደብረ ብርሃን ከተማ በሞተር ሳይክል፣ ባጃጅና በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ንግድ ላይ ተሰማርቶ ሲሰራ ቆየ፡፡ በሱፍቃድ አዳዲስ የስራ ዘርፎችን የመሞከር ፍላጎት ስለነበረው ቤቶችን ገንብቶ ወደመሸጥ ተግባር አዘነበለ፡፡ በዚህም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሃን፣ ምንጃርና በረኸት አካባቢዎች ጥቂት ቤቶችን እየገነባ ይሸጥ ነበር፡፡ በወቅቱ በአረርቲ ከተማ ብቻ ከ48 በላይ ቤቶችን በጥራት ገንብቶ መሸጥ ችሏል፡፡
ውጤታማነቱን የተመለከቱ ወዳጆቹ ስራውን ይበልጥ በማስፋት ወደ ሪል እስቴት ዘርፍ እንዲገባ መከሩት፤ አበረታቱት፡፡ እርሱም በቤት ግንባታና ሽያጭ ያከናወናቸውን ስራዎች፣ ያስመዘገባቸውን ስኬቶችና ያገጠሙትን ፈተናዎች ማሰላሰል ጀመረ። የቤት ግንባታና ሽያጭ ስራውን አስፍቶ መስራት እንዳለበት ወሰነ፡፡ ታዲያ ይህን ሲደርግ በገበያ ላይ ካሉት ቤት አልሚዎች በተሻለ ሁኔታ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ይዞ ወደ ስራው መግባት እንዳለበት በአፅንዖት አስቦበታል፡፡
በሪል እስቴት ልማት ዘርፍ እውቀት ካላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ምክርና ልምድ መውሰድ እንዳለበት ስላመነ፣ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸውን አካላት ተሞክሮ ከራሱ ልምድና ዓላማ ጋር በማዋሃድ የሪል እስቴት ልማት ዘርፉን ተቀላቀለ፡፡ ታዲያ በእያንዳንዱ የስራው ደረጃ ‹‹ከሌሎቹ የሪል እስቴት ኩባንያዎች በተለየ መልኩ፣ ኅብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግና በኅብረተሰቡም ዘንድ እምነት የሚጣልበት ስራ እውን የማድረግ›› ዓላማውን በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት ይጠብቀው ነበር፡፡
‹‹በወቅቱ ስራው አዋጭና ገበያ ያለው ነበር። ቀደም ሲል ገንብቼ የሸጥኳቸው ቤቶችም ጥራት ያላቸው ስለነበሩ ከፍተኛ የቤት ፍላጎት ነበር። በስራው ላይ ተሰማርተው ከነበሩት ግለሰቦችና ተቋማት ያገኘሁት ተሞክሮም ጠቃሚ ነበር። ቤቶችን እየገነባሁ ስሸጥ መቆየቴ፣ የወዳጆቼ ማበረታቻ እንዲሁም የባለሙያዎች ምክር ወደ ሪል እስቴት ልማት ዘርፍ እንድገባ አስችሎኛል›› በማለት ስለሪል እስቴት ልማት ጉዞ አጀማመሩ ያስታውሳል።
በሱፍቃድ ስራውን ለመጀመር ተጨማሪ የገበያ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ እንደነበር ስላመነበት፣ ስራውን ለመጀመር ባቀደባት አረርቲ ከተማ ስላለው የኅብረተሰቡ አጠቃላይ ሁኔታና የቤት ፍላጎት ጥናት አደረገ፤ ኅብረተሰቡንም አወያየ፡፡ በዳሰሳውም ከፍተኛ የቤት ፍላጎት እንዳለ አረጋገጠ፡፡
በትልልቅ ከተሞች የተለመደውን የሪል እስቴት ልማት በትንሽ ከተማ ማከናወን ብዙ ፈተናዎች እንደሚኖሩት ግልጽ ነው፡፡ በሱፍቃድም ይህን ፈተና ቀድሞ ተገንዝቦታል፡፡ ይሁንና ይህን ታላቅ ዓላማ ሰንቆ የሚገጥመውን ፈተና በፅናት ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚገባው በማመን ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በሪል እስቴት ልማት የተለየና አዲስ አሰራር በማስተዋወቅ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማውን ሰንቆ፣ በዘርፉ ለመሰማራት በ2012 ዓ.ም ጉዳዩ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥያቄውን አቀረበ፡፡ በ2013 ዓ.ም ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ተመሰረተ፡፡ ‹‹በ2012 ዓ.ም ጥያቄ አቅርበን በግንቦት 2013 ዓ.ም በክልሉ መንግሥት ጥያቄያችን ውሳኔ አገኘ፡፡ ለስራውም 23 ሄክታር (230ሺ ካሬ ሜትር) መሬት ተፈቀደልን፡፡ በጊዜው የመኸር እርሻ የዘር ወቅት በመድረሱ ለአርሶ አደሮች ካሳ በመክፈል ቦታውን መረከብ ያስፈልግ ስለነበር፣ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳና የሊዝ ክፍያ በመክፈል ወደ ስራ የገባነው በጥር 2014 ዓ.ም ነበር›› በማለት ስለድርጅቱ አመሰራረትና ስራ አጀማመር ያስረዳል፡፡
ምንም እንኳ በሱፍቃድ ባደረገው የገበያ ጥናት ከፍተኛ የቤት ፍላጎት እንዳለ ቢያረጋግጥም፣ ኅብረተሰቡ ስለሪል እስቴት ልማት ዘርፍ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ‹‹አረርቲ ሌሎች ድርጅቶች የሪል እስቴት ልማት ከሚያካሂዱባቸው ትልልቅ ከተሞች ጋር ስትወዳደር ትንሽ ከተማ ናት። በትንሽ ከተማ ውስጥ በሪል እስቴት ዘርፍ መሰማራት ሊያመጣ የሚችለውን ኪሳራ ቀድመን አስበንበታል። ስራውን የጀመርነው አዲስ ነገር ለማሳየትና ኅብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ክፍለ ሀገር ላይ በሪል እስቴት ዘርፍ መሰማራት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ስለሪል እስቴት ልማት ዘርፍ ያለው ግንዛቤ በቂና ሰፊ አልነበረም፡፡ የግንዛቤ ለውጥ እንዲኖር የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በብዙ ድካም የታጀበ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል›› በማለት የግንዛቤ ችግር ገና በጠዋቱ ለስራው መሰናክል ሆኖበት እንደነበር ይገልፃል፡፡
የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ኅብረተሰቡን ስለ ሪል እስቴት ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ ነበርና በሱፍቃድና የስራ ባልደረቦቹ ስለሪል እስቴት ምንነትና አሰራር ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ፈጠሩለት። ቀስ በቀስም ጥረታቸው ከስራቸው ጋር ተደምሮ ፍሬ አፍርቶ የ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ደንበኛ ለመሆን ፍላጎት የሚያሳዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡
በአሁኑ ወቅት የጣራ ስራ ላይ የደረሱና በዚህ ወር የሚጠናቀቁ 75 ቤቶች አሉ፡፡ 200 ቤቶች ደግሞ በመሰረት ግንባታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የሌሎች ቤቶች ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጀመራል። በአጠቃላይ በ2016 ዓ.ም መጨረሻ 570 ቤቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እቅድ ይዟል። ከድርጅቱ 570 ደንበኞች መካከል 117 የሚሆኑት ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡
‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ከሌሎች ቤት አልሚ ኩባንያዎች የሚለይባቸው አሰራሮች እንዳሉት የድርጅቱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ በሱፍቃድ ተስፋዬ ይገልፃል። ‹‹የእኛ ሪል እስቴት ከሌሎቹ ሪል እስቴቶች የተለየ አሰራር አለው፡፡ ይዘን የቀረብነው የማኅበረሰቡን አቅምና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ አሰራር ነው፡፡ ስራው ከማኅበረሰቡ የተዋቀረ ኮሚቴን ያሳትፋል፡፡ እያንዳንዱ ቤት የሚገነባው ከማኅበረሰቡ በተመረጠ ኮሚቴ ተሳትፎና አመራር አማካኝነት ነው፡፡ ባልሰራነው ነገር ተገቢ ያልሆነ ክፍያ አንቀበልም፤ የኅብረተሰቡን አቅምና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ባስገባ አሰራር እና በሰራነው ልክ ብቻ እንቀበላለን። የምንገነባቸው ቤቶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ ስራችንን የምናከናውነው ከማኅበረሰቡ፣ ከደንበኞች፣ ከሰራተኞችና ከመንግሥት ጋር በትብብር ነው›› በማለት ስለድርጅቱ ልዩ የአሰራር ስርዓቶች ያብራራል፡፡
‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ብዙ ማኅበረሰብ የተሰባሰበበት የቤት ልማት መድረክ ነው። በ230ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ ግዙፍ የቤት ልማት ፕሮጀከት፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን (ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ የእምነትና የንግድ ተቋማት… ) አካትቶ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የቤት ልማት መንደሩ እንደመብራት ያሉ መሰረተ ልማቶችም አስቀድመው ተዘርግተውለታል።
‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› በትጋት ሰርቶ ማሳየት በመቻሉ፣ ኅብረተሰቡ ትናንት ስለሪል እስቴት የነበረው ‹‹ገንዘብ ሰብስቦ የመጥፋት›› አስተሳሰብ ዛሬ ተቀይሯል። የሪል እስቴት ልማት እንደ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ዓይነት ባሉ አልሚዎች የሚመራ ከሆነ፣ ኅብረተሰቡን ባልተጋነነ ዋጋና ትርፍ የቤት ባለቤት የሚያደርግ የቤት ልማት ዘርፍ እንደሆነ በተግባር ታይቷል፡፡
‹‹ስለሪል እስቴት ልማት በቂ ግንዛቤ ባልነበረው ኅብረተሰብ ውስጥ ስራውን መጀመራችን ትልቅ ፈተና ሆኖብን ነበር፡፡ ኅብረተሰቡ ገንዘብ ሰርቀንና አጭበርብረን እንደምንሄድ ያስብ ነበር፡፡ እኛ ግን ዓላማችን ያ እንዳልሆነ ሰርተን በተግባር ስላሳየን አሁን ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ፈፅሞ የለም። የኅብረተሰቡን እምነት ለማግኘት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብን ስለነበር ግንዛቤውን ለመፍጠር ብዙ ትግል አድርገናል።
ይህ ጥረታችንም ፍሬ አፍርቶ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ኅብረተሰብ ስለሪል እስቴት ልማት የተሻለ ግንዛቤ አለው›› በማለት ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት›› ስለፈጠረው አዎንታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስረዳል፡፡
በትልልቅ ከተሞች የሚታየውን የሪል እስቴት ልማት በትንሽ ከተማ በማስተዋወቅ ስኬታማ ስራ ያከናወነው ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት››፣ ስኬትን ያስመዘገበው በቀላሉ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ስለሪል እስቴት ልማት ዘርፍ ያለውን ዝቅተኛና የተዛባ ግንዛቤ በመቀየር የዛሬው ስኬቱ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ፈተናዎቹ ጥቂት አይደሉም፡፡ የውሃ እንዲሁም በፀጥታ ችግሮች ምክንያት የሚፈጠር የማቴሪያል (ሲሚንቶና ብረት) አቅርቦት እጥረት በድርጅቱ ስራ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል፡፡ ስለነዚህ ፈተናዎች በሱፍቃድ ሲረዳ፣ ‹‹ወቅታዊው የፀጥታ ችግር በእጅጉ ፈትኖናል፡፡ ሲሚንቶና ብረት ለማግኘት ለፋብሪካዎቹ ክፍያ ብንከፍልም እቃዎቹን በሚፈለገው ጊዜ አናገኝም። የውሃ ተቋም ግንባታ በመንግሥት በጀት እንዲከናወን ተገልፆ የነበረ ቢሆንም፣ ስራው በመዘግየቱ ምክንያት ቦቴ ተከራይተንና የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ገዝተን ከሩቅ ቦታ እያመጣን ለመስራት ተገድደናል›› ይላል።
ስራውን ሲጀምር ብዙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ቀድሞ የተገነዘበው በሱፍቃድ ለፈተናዎቹ ሳይንበረከክ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ጥረቱን ቀጥሏል። በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የቤት ልማት ስራውን ለማስፋፋት ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በሱፍቃድ ከሪል እስቴት ልማቱ ዘርፍ በተጨማሪ በ‹‹አኩፋዳ›› ማይክሮፋይናንስ ተቋም ባለድርሻ በመሆን በፋይናንሱ ዘርፍም ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡
ታማኝነት እና የደንበኛን ፍላጎት አክብሮ መስራት ለስኬታማነት አስፈላጊ ግብዓቶች እንደሆኑ የሚናገረው በሱፍቃድ፣ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ እና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማወቅ ያደረጉት ጥረት ለስኬታቸው ትልቅ ሚና እንዳለው ይገልፃል። ‹‹የድርጅታችን ሰራተኞች በ‹‹አቡቀለምሲስ›› የሪል እስቴት ስልጠና ድርጅት ስለዘርፉ ልማት ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ እያንዳንዱን ስራ የምንሰራው ከስልጠና ባገኘነው ትምህርትና ተሞክሮ ነው የአማካሪዎቻችንን ምክርም እንቀበላለን፡፡ ጊዜና ገንዘብን ለታለመለት ዓላማ እናውላለን›› በማለት ስለድርጅቱ አሰራርና የስኬት ምስጢሮች ያስረዳል፡፡
በ12 ሚሊዮን ብር ስራ የጀመረው ‹‹በሱፍቃድ ሪል እስቴት››፣ ዛሬ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለው ተቋም መሆን ችሏል፡፡ ለ23 ዜጎች ቋሚ እና ከ250 እስከ 300 ለሚሆኑ ደግሞ ጊዚያዊ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ በ33 ዓመቱ እዚህ ስኬት ላይ መድረስ የቻለው ወጣት በሱፍቃድ ተስፋዬ፣ በወጣትነቱ የገንዘብ ሀብታም መሆን የቻለ ሰው ብቻ አይደለም፤ ገና በወጣትነቱ ልባምነትንም የታደለ ነው፡፡ ልባም ለመባል ያበቃው ሀብት እንዲያፈራ ያስቻለው አዲስ ነገርን በትጋትና በፅናት የማከናወኑ ተፈጥሮው ብቻ ሳይሆን ያለውን ሀብት ለሌሎች የማካፈል ባህርይውም ነው፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በርካታ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በበረኸት፣ በሀገረ ማርያምና በምንጃር በየዓመቱ ከ200ሺ እስከ 300ሺ ብር በማውጣት ከ100 እስከ 150 ለሚሆኑ ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ደብተርና እስክሪብቶ ያሟላል፡፡ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በማውጣት በአረርቲ ከተማ መንገድ ገንብቷል። የሆስፒታልና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ግንባታም አከናውኗል፡፡ ለአብያተ ክርስቲያናትና ለመስጅዶች በየጊዜው ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ከተማው እንዲለማ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኢንቨስትመንት ፎረም በማዘጋጀት ባለሃብቶችን ለመሳብ ጥረት አድርጓል። ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ‹‹ገናን በምንጃር›› የሚል የቴሌቪዥን ፕሮግራም በማዘጋጀት አካባቢውን የማስተዋወቅ ስራ አከናውኗል፡፡
‹‹አቅማችን በፈቀደ መጠን በአካባቢው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ወረዳውና ከተማው ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ከማኅበረሰቡና ከመንግሥት ጋር በመተባበር በልማትና በጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሳትፎ እናደርጋለን›› በማለት በሱፍቃድ ስለድርጅቱ የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ይገልፃል፡፡
‹‹ሁሉም ሰው ዓላማ ሊኖረው ይገባል፤ የሰው ልጅ ስራ ሳይሰራ መኖር አይችልምና ሁሉም ሰው በሚችለው መስክ መሰማራት አለበት ብዬ አምናለሁ›› የሚለው ስኬታማው ወጣት በሱፍቃድ ተስፋዬ፣ ሰው በተፈጥሮ ያገኘውን ተሰጥዖ ከዓላማና ጥንካሬ ጋር አስተሳስሮ፣ እደርስበታለሁ ብሎ ከሚያስበው ግብ ላይ መድረስ እንዳለበት ይመክራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በጋራ መስራትን መልመድ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ያሏቸውን የተለያዩ ሀብቶች ማገናኘት አስፈላጊ ነው፡፡ እውቀት ያለው እውቀቱን፣ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን እንዲሁም ጉልበት ያለው ጉልበቱን አቀናጅቶ እና ለማኅበረሰቡ ታምኖ ሊሰራ ይገባል›› በማለት ምክሩን ያጋራል፡፡
በሱፍቃድ ተስፋዬ፣
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም