ከዳተኛው ገዳይ

እናት እና ልጅ በአንድ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጠሩ። ልጅ ምንም እንኳ ፊደል ቆጥሮ፤ ሥራ ይዞ፤ ኑሮ መስርቶ ከእናቱ ቤት ወጥቶ ቤተሰብ መመሥረት ቢኖርበትም፤ ያ አልሆነም፡፡ አዲስ አስራት ለ34 ዓመታት በእናቱ ቤት ከእናቱ ጋር ኖሯል፡፡

አዲስ ዕድሜው እየገፋ ሲሔድ፤ እናቱ ወይዘሮ ከበቡሽ እንግሊዝን ደግሞ እርጅናው እየተጫናቸው መጣ፡፡ እርጅናቸውን ተከትሎ ጤና ማጣት ጀመሩ። ራሳቸውን ችለው አብስለው መመገብ ተስኗቸው፤ ልጃቸው አዲስ እጅ ላይ ወደቁ፡፡ ሌሊት ተነስቶ ያያቸዋል፤ ቀን ምግብ እያበሰለ ይመግባቸዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እየጠጣ አምሽቶ ይማረርባቸዋል፡፡ ሰድቦ ያስቀይማቸዋል፤ መልሶ አቅፎ እየሳመ እያባበለ ይቅርታ ይጠይቃቸዋል፡፡ አዲስ በተለይ ጠጥቶ ሞቅ ካለው ምን እንደሚያደርግ አያውቅም፡፡ በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ ከሁሉም የተለየ የከፋ ድርጊት ፈፀመ፡፡

የአዲስ ውሎ

በጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ የሚሠራውን ምግብ አበሳስሎ ለታማሚ እናቱ ቁርስ ሲሰጥ ሰዓቱ ረፋፍዶ ነበር፡፡ አዲስ ለመርማሪ ፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እንደተናገረው፤ ‹‹በግምት ከጠዋቱ 4 ከ30 ደቂቃ አካባቢ፤ ለእናቴ ቁርስ ከሰጠሁ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያን ሔድኩኝ፡፡ ተሳልሜ ፀሎት አደረስኩ፡፡ በኋላ ግን በሰፈራችን ካለ አንድ አረቄ ቤት ጎራ አልኩ፡፡›› ይላል፡፡

አዲስ ‹‹አረቄ ቤት አንድ ሁለት ብዬ እወጣለሁ›› ያለው ሰው ቀኑን ሙሉ ሲጠጣ ውሎ ፀሐይ ጠለቀች፤ መሸ፡፡ ሰዓቱ ሁለት ሰዓት አልፎ ምሽት ሦስት ሰዓት ሊሞላ ደቂቃዎች ሲቀሩት ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ቤት ሲደርስ እናቱን በረንዳ ላይ ሲጠብቁት አገኛቸው። ይዟቸው ወደ ቤት አስገብቶ፤ ደግፏቸው የሳሎን ሶፋ ላይ አስቀመጣቸው፡፡ ሶፋው ላይ ከጎናቸው ሲቀመጥ አንገታቸውን አንቆ አጥብቆ አቅፏቸው ነበር። ሲዝለፈለፉ እዚያው ሶፋ ላይ አስተኝቷቸው እርሱ መኝታ ቤት ገብቶ ተኛ፡፡

አዲስ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ከእንቅልፉ ሲነቃ፤ እናቱ ወይዘሮ ከበቡሽ እንግሊዝ ተነስተው በድጋሚ ወጥተው በረንዳ ላይ ቆመዋል። እንደገና እንዲገቡ አድርጎ በድጋሚ ሶፋ ላይ አስተኛቸው። አዲስ በድጋሚ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲነቃ እናቱ ከእንቅልፍ አልተነሱም፡፡ ቁጭ ብሎ ብዙ ጠበቃቸው አልነቁም፡፡ ሁኔታው ስላላማረው ሐኪም ቤት ሊወስዳቸው አሰበ። መኪና አስመጥቶ ይዟቸው ከቤት ሲወጣ ከበዱት። ስላልቻላቸው አዲስ ከእናቱ ወይዘሮ ከበቡሽ ጋር አብረው መሬት ወደቁ፡፡ እንደምንም ተሸክሞ በመኪና ጭኖ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አደረሳቸው፡፡

ሆስፒታል ደርሰው ምርመራ ከመደረጉ በፊት የሕክምና ባለሙያዎቹ፤ ‹‹ወይዘሮ ከበቡሽ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይዘህ የመጣኸው የሞተ ሰው ነው፡፡›› አሉት፡፡ አዲስ ግን በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ላይ እናቱን ሐኪም ቤት ሲወስዳቸው መሞታቸውን አላወቀም፡፡ ይልቁኑ እንዲድኑለት አስቦ ነበር፡፡

የሐኪሞቹ ጥርጣሬ

የእናቱ ሕይወት ማለፉን የሰማው አዲስ ልጃቸው መሆኑን እርሱ ለብዙ ጊዜ ሲንከባከባቸው እንደነበር ጠቅሶ፤ ለሐኪሞቹ ብቻውን እንደመጣ ተናገረ፡፡ ማንም እንደሌለው በማሳመን፤ አስክሬኑን እንዲሰጡት ጠየቀ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፤ ግለሰቧ መሞታቸው ስለተረጋገጠ የሕክምና ባለሙያዎች አስክሬኑን ገንዘው እንደሚሰጡት ገለፁ፡፡ ሐኪሞቹ የተለመደ ሥራቸውን ሊያከናውኑ ሲሉ አጠራጣሪ ነገር ተመለከቱ፡፡ ግለሰቧ አንገታቸው አካባቢ ቀልቶ ጠቁሯል፡፡ ታንቀው እንደነበር የሚያመላክት ፍንጭ አገኙ፡፡

የሕክምና ባለሙያዎቹ ለአዲስ ያገኙትን ምልክት ሲነግሩት ተርበተበተ፡፡ ወድቀውበት ሊያነሳቸው ሲሞክር በጨርቅ አንገታቸውን እንደጎተተ እና ሳያስበውም በዚያ አጋጣሚ ተጎድተው ሊሆን እንደሚችል ተናገረ።

‹‹እባካችሁ ለማንም እንዳትናገሩብኝ›› አለ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹ ግን ወደ ውጭ እንዲወጣ አዘዙት፡፡ ወዲያው እንዳያመልጥ በማሰብ ፖሊስ ጣቢያ ደወሉ። አዲስ በበኩሉ፤ ከሆስፒታሉ ወጥቶ በተለምዶ ሃጂ ቱሬ ወደሚባል አካባቢ ሔደ፡፡ ከሱቅ በረኪና ገዝቶ እዛው ሱቁ ደጃፍ ላይ በረኪናውን ጠጣ፡ ፡ ይህንን ሲያደርግ የተመለከቱ ሰዎች ተጯጩኸው በረኪናውን ከአፉ ላይ ነጠቁት፡፡ ሆኖም ብዙ በመጠጣቱ መሬት ወድቆ ራሱን ሳተ፡፡ የማያውቁት ነገር ግን በረኪናውን ጠጥቶ ያገኙት ሰዎች ተረባርበው ወተት መጋት ጀመሩ፡፡ አዲስን ለማዳን ሲታገሉ፤ ስልኩ ጠራ፡፡ የተሰባሰቡት ሰዎች ስልኩን በማንሳት አዲስ ራሱን ስቶ መውደቁን እና የት አካባቢ እንዳለ ተናገሩ፡፡

የፖሊስ ምርመራ

ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ30 አካባቢ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ፓስተር ፖሊስ ጣቢያ ከጳውሎስ ድንገተኛ ክፍል አንድ የሞተ ሰው መኖሩን እና ሞት የተከሰተውም በተፈፀመ ወንጀል ነው የሚል ጥርጣሬ ላይ መድረሳቸውን በስልክ ጥቆማ ተሰጠ፡፡ የዕለቱ ተረኛ መርማሪ ፖሊስ ዋና ሣጂን ዳኛቸው ደሳለኝ በፍጥነት ሆስፒታል ደረሰ፡፡

የዕለቱን ተረኛ የጤና ባለሙያ መርማሪው ማነጋገር ጀመረ፡፡ የጤና ረዳት ነርስ የሆነው ሰው ጥርጣሬውን በዝርዝር አስረዳ፡፡ ሟች ሆስፒታል ከመምጣታቸው በፊት እንዳረፉ እና የ78 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ወይዘሮ ከበቡሽን ይዞ ለመጣው ግለሰብ መሞታቸውን ሲነግሩት እንዳለቀሰ የጤና ረዳቱ አስረዳ፡፡

በኋላም ሟችን ያመጣው አዲስ ‹‹አስክሬኑን ይዤ ልሔድ››፤ ብሎ ጠይቆ እንደነበር እና በቅድሚያ አስክሬኑ መገነዝ አለበት ሲባል አዲስ እንዳልተስማማ የጤና ባለሙያው አስታውሶ፤ ለመርማሪው ተናገረ። በኋላም የጤና ባለሙያዎቹ ተሰባስበው አስክሬኑን ለመገነዝ ሲያሰናዱ፤ ሟች ወይዘሮ ከበቡሽ አንገታቸው አካባቢ መቅላቱን ሲመለከቱ ተጠራጥረው ውጭ የወጣውን አዲስን በመጥራት የመታነቅ ምልክት እንዳለባቸው ሲነግሩት አዲስ መደንገጡን የጤና ባለሙያው አስታውሶ፤ ለመርማሪ ፖሊሱ ሁኔታውን አስረዳ።

እንደጤና ባለሙያው ገለፃ፤ አዲስ እናቱ ወይዘሮ ከበቡሽ ሕይወታቸው ያለፈው በጨርቅ ታንቀው ሊሆን ይችላል የሚለውን ዜና ሲሰማ እጅግ ተረብሾ ነበር፡፡ ‹‹ወድቃብኝ ለማንሳት ሲከብደኝ አንገቷን በጨርቅ ይዤ በመጎተት ለማንሳት ሞክሬያለሁ። ያንን ያደረግኩት ትሞታለች ብዬ አይደለም፡፡ እባካችሁ ለማንም እንዳትነገሩብኝ›› ሲል የሕክምና ባለሙያዎቹን ተማፅኗል፡፡

የሕክምና ባለሙያዎቹ የሙያ ሥነምግባራቸው እንደማይፈቅድ ገልፀው እደጅ እንዲጠብቃቸው ከነገሩት በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደውለው ጥቆማ መስጠታቸውን የጤና ባለሙያው አብራራ፡፡

መርማሪ ፖሊሱ አስክሬኑን ተመልክቶ የሕክምና ባለሙያዎቹን ምስክርነት አዳምጦ፤ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ሆኖም ተጠርጣሪው አዲስ፣ ጊቢ ውስጥ አልነበረም። ከአዲስ ጋር አብሮ የመጣው የታክሲ ሹፌር ተጠርጣሪ አዲስ፣ ወደ ሆስፒታሉ ጀርባ መሔዱን ጠቆመ፡፡

መርማሪ ፖሊሱ ከሆስፒታሉ የአዲስን ስልክ ቁጥር ተቀብሎ ሲደውል፤ አዲስ ከሆስፒታሉ ጀርባ ሃጂ ቱሬ አካባቢ በረኪና ጠጥቶ ራሱን መሳቱን ሰዎች ነገሩት፡፡ የመርማሪ ፖሊሱ ወደ ቦታው በማቅናት አዲስን አገኘው፡፡

አዲስ ሲነቃ እያለቀሰ፤ ‹‹መሞት አለብኝ፤ እናቴን ገድዬ መኖር አይገባኝም፡፡›› እያለ ሲያለቅስ፤ መርማሪ ፖሊሱ ተጠጋው፡፡ ሰዎች ገለል አሉ፡፡ ተጠርጣሪ አዲስን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ አደረገ፡፡

መርማሪ ፖሊሱ ባደረገው ማጣራት ዕድሜው 34 ዓመት የሆነው ተጠርጣሪ አዲስ ዓለም፤ በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ደብረሰላም ትምህርት ቤት አካባቢ ካለው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሌሊት በግምት 11፡00 ሰዓት አካባቢ 78 ዓመት የሆናቸውን ወላጅ እናቱን ሟች ከበቡሽ እንግሊዝን በእጁ አንገታቸውን አንቆ በመያዝ የአየር እጥረት እንዲከሰት በማድረግ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉን የሚያሳይ መረጃ አሰባሰበ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 የቤት ቁጥር 540 የተፈፀመው ይህ ወንጀል፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 540 ስር የተመለከተውን መተላለፍን እንደሚያሳይ አረጋገጠ፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ምርመራ የተገኘ ደብዳቤን፣ የሟች የአሟሟት ሁኔታ፣ ተከሳሽ ለመርማሪ ፖሊሱ ቃል ሲሰጥ የተቀረፀ ቪዲዮን በማደራጀት ተራ የግድያ ወንጀል በመፈፀሙ አዲስ ተጠያቂ እንዲሆን ለዓቃቤ ሕግ አደራጅቶ መረጃውን አቀረበ፡፡

የዓቃቤ ሕግ ክስ

ዓቃቤ ሕግ በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን ማስረጃ ገላጭ ፎቶ ግራፎችን እና የተቀረፁ ቪዲዮዎችን እንዲሁም በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 27(2) መሠረት ለፖሊስ የሰጠውን የተከሳሽ የሟች የወይዘሮ ከበቡሽ ልጅ አዲስ የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤትን እና የሰው ምስክርነት አካቶ ክስ መሠረተ፡፡

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 የቤት ቁጥር 540 በጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ደብረሰላም ትምህርት ቤት አካባቢ ባለው መኖሪያ ቤታቸው የ78 ዓመት እናት ወይዘሮ ከበቡሽ ሞተዋል፡፡ አሟሟታቸው በተካሔደው የማጣራት ሥራ ዕድሜው 34 ዓመት የሆነው ልጃቸው ተጠርጣሪ አዲስ፤ ሌሊት በግምት 11፡00 ሰዓት አካባቢ ወላጅ እናቱን ሟች ከበቡሽ እንግሊዝን በእጁ አንገታቸውን አንቆ በመያዝ የአየር እጥረት እንዲከሰት በማድረግ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉ ታውቋል፤ ይላል፡፡

የተፈፀመው ይህ ወንጀል፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 540 ስር የተመለከተውን መተላለፍን እንደሚያሳይ አረጋግጦ፤ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ምርመራ የተገኘው ደብዳቤን፣ የሟች የአሟሟት ሁኔታ፣ ተከሳሽ ለመርማሪ ፖሊስ ቃል ሲሰጥ የተቀረፀ ቪዲዮን አካቶ ተራ የግድያ ወንጀል በመፈፀሙ ተጠያቂ እንዲሆን ሲል አቃቤ ሕግ ክስ አቀረበ፡፡

ዐቃቤ ሕግ በክሱ ሒደት የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የሰነድ፣ ኤግዚቢት እና ገላጭ ማስረጃዎችን እንዲሁም የሰው ምስክሮችን ቃል፣ በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም፤ የአቃቤ ሕግን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሙን ያረጋገጠ በመሆኑ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።

 

ውሳኔ

በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በክርክሩ መሠረት ተከሳሽ አዲስ አስራት ይመር፣ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት፤ ወንጀሉ ሆን ብሎ ያልፈፀመው መሆኑ እንደቅጣት ማቅለያነት ተይዞለት በጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ አዲስ እናቱ ወይዘሮ ከበቡሽን በመግደሉ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You