የማለዳ ሀሳቦች የሰው ልጅ የዘመን ድሮች..የጊዜ ዘሮች ናቸው፡፡ በእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ አቆንጉለው በትዝታ ረመጥ የሚፋጁ፡፡ ትላንትን ከዛሬ፣ አምናን ከዘንድሮ እያደሩ የሚቋጩ የናፍቆት ሸማኔዎች፡፡ እነኚህ የልጅነቴ መልከኛ ሀሳቦች ከወንድነቴ ገዝፈው፣ ከወጣትነቴ ልቀው ልጅነቴን ያስመኙኛል፡፡ በረገጥኩት የእግሬ ዳና ላይ ማለዳዬን ስለው፣ ማምሻዬን ኩለው ይከተሉኛል፡፡ በመዳፌ እርቃን በአይበሉባዬ ላይ አርፈው አሁን እንደሆኑ ያክል የትም አያቸዋለሁ…የማለዳ ሀሳቦቼን፡፡
ጠዋት ጀምበር ምሥራቅ አድማስ ላይ ስታቅላላ…ምሽት ምዕራብ ራስጌ ላይ ስትንፏቀቅ በነዚህ ሁሉ ውስጥ ልጅነቴ ይታወሰኛል፡፡ ዛሬም ድረስ የድሮዋ ፀሐይ፣ የልጅነቴ ጀምበር የምታበራ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከቤቴ አቅራቢያ ካለው የግራር ዛፍ ላይ የሚያንቃርሩት አሞራዎች፣ የሚያፏጩት አእዋፍት የልጅነቴ አድባሮች ሆነው ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ መኪና መንገዱን ተሻግሮ ካለው ካቴድራል የሚሰማኝ የካህኑ ዜማ፣ የአጥቢያው እግዚኦታ፣ የደጀ ሰላሙ ቡራኬ እኚህ ሁሉ…አበባ ለመቅሰም የሚያጠዘጥዙ ንቦች፣ አፈር ጭራ ያገኘቻትን አንዲት ትል ልጆቿን ለማብላት የምታንቃርር ሴት ዶሮ፣ ጫጩት ለመያዝ የምታደባ ጭልፊት እነኚህ ሁሉ…
ከሁሉም በኋላ አይ ጊዜ እላለሁ…የጊዜ እውነት ያስደንቀኛል፡፡ የጊዜ ፍርድ፣ የጊዜ ሚዛን ያስገርመኛል። ሕይወት ምንድነው ላለኝ ጊዜ ነው እለዋለሁ፣ ጊዜ ምንድነው ላለኝ ሕይወት ነው ስል እመልስለታለሁ። የጊዜ ሽርፍራፊዎች የሕይወትን ሙላት ያጎላሉ፡፡ የሕይወት ሙላት በጊዜ ሽርፍራፊ የሚጎል ነው። በትካዜ ስንባክን፣ በሀሳብ ስንባዝን ከሕይወት እየጎደልን ነው። ቀጠሮ ስናረፍድ፣ በማይጠቅሙን ነገሮች ስንጠመድ እየደበዘዝን ነው፡፡ የሕይወት ሙላት የደስታ ባሕር ነው፡፡ የፍስሐ ውቅያኖስ፣ የፈንጠዝያ ደሴት ነው፡፡ መከራዎቻችን ሁሉ ከሸራረፍናቸው የግዜ ሽራፊ ውስጥ የወጡ ናቸው…ይሄን ሳስብ የሸራረፍኩት የሕይወት ጠባሳ ይታወሰኛል፡፡ ይሄን ሳስብ በልጅነቴ ውስጥ፣ በወጣትነቴ ውስጥ የሸረፍኳቸው የጊዜ ሽራፊዎች ይመጡብኛል፡፡ ሁሉም ሰው የሕይወት ጠባሳ አለው። በጎደለ ቀን፣ ባልሞላ ጊዜ የተገጠበው የሕይወት ትውስታ፡፡
ሕይወት በጊዜ የተሸመነች የፈጣሪ ድርና ማግ ናት፡፡ የሕይወት ነጠላ የለውም…እግዜር ሲሸምነን በአንድ አይነት ድርና ማግ ነው፡፡ ባለጁ በጊዜ ውስጥ እንድናብብ፣ በጊዜ ውስጥ እንድንጠወልግ አድርጎ አበጅቶናል፡፡ ደውሮናል….
ልጅነት የሕይወት ቀለም ነው….ወጣትነትን ያስናቀ፣ ጉልምስና የማይደርስበት ባለቀለም የላመ መልክ፡፡ እኚህ የሕይወት ቀለም እስከ እድሜያችን አፋፍ ድረስ የሚዘልቁ የሰውነት አውራ ናቸው፡፡ ቢሸራረፉም፣ ቢገማመሱም ከነእድፍና ኩነኔያቸው ጋር ፀዐዳ ናቸው፡፡
የማለዳ ሀሳቦቼ ከወጣትነቴ አንሰው አያውቁም…ከወደፊቴ የተለቁ የሕይወቴ ራስ ናቸው፡፡ በትላንት ውስጥ የሚያኖሩኝ፣ የልጅነቴን ማምሻና ንጋት የሚያስቃኙኝ መስታወቴ ናቸው፡፡ በተለይ እማዬና አባዬ ያሉበትን የልጅነት ጠዋቴን አረሳውም፡፡
ከማለዳ ሃሳቦቼ አንዱ…
ጠዋት ከእንቅልፌ የሚያነቃኝ አባቴ ነው…ከሰፈራችን ከአቶ ታከለ አውራ ዶሮ ጩኸት እኩል ከእንቅልፉ ይነቃል፡፡ ከእናቴና ከአባቴ መሐል ነው የምተኛው እንዳይቀሰቅሰኝ ቀስ ብሎ ይነሳና ዛሬም ድረስ በሚገርመኝ አባታዊ ጥንቃቄ በሩን ይከፍትና ነጭ ሀጫ ጋቢውን እስከ ቁርጭምጭሚቱ ድረስ ለብሶ ወደ ውጪ ይወጣል፡፡ የእናቴን አላውቅም እኔ ግን እነቃለሁ…አልጋዬ ላይ ትንፋሼን ውጬ ዝም እላለሁ። ወዲያው እናቴ እግሩን ተከትላ ከአባቴ ባልተናነሰ ጥንቃቄ እንዳትቀሰቅሰኝ እየተሳበች ከአልጋው ትወርድና ወደ ማዕድ ቤት ትሄዳለች፡፡ ሰፊው አልጋ ላይ ብቻዬን ሆኜ የአባቴን እግዚአብሔራዊ ወንድነት፣ የእናቴን አምላካዊ ሴትነት በማይገባኝ ልጅነታዊ ሀሳብ አስባለሁ። የአባቴ ዳዊት መድገሚያ ከመኝታ ክፍላችን መስኮት አጠገብ ስለነበር የአባቴን የማለዳ ፀሎት መስማት ግዴታዬ ነበር፡፡ በተኛሁበት የአባቴን የሰርክ ፀሎት አዳምጣለሁ፡፡ የሚለው አይገባኝም…ግን እመሰጣለሁ። ግን እደመማለሁ፡፡ ልጅ ሆኜ አባቴ የእግዚአብሔር ወንድሙ አሊያም ደግሞ አጎቱ አሊያም ደግሞ ጓደኛው ነበር የሚመስለኝ፡፡
ምንም እንኳን ከእንቅልፌ ተነስቼ እንደ አባቴ ባልደግምም ፈጣሪ ግን ከአባቴ እኩል የሚያጸድቀኝ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ሌሊት የአባቴን ዳዊት እየሰማሁ እናቴ ለቁርስ እስከምትቀሰቅሰኝ ድረስ እጋደማለሁ፡፡
ከማለዳ ሀሳቦች ሌላ..
እናቴ ለእኔ ምን አይነት እናት፣ ለአባቴ ምን አይነት ሚስት እንደሆነች ብጠይቁኝ አላውቀውም። የእናቴ ሴትነት፣ የእናቴ እናትነት፣ የእናቴ ሚስትነት ዛሬም ድረስ ያልደረስኩበት ተፈጥሮ ነው፡፡ እናቴ ሴት ብቻ አይደለችም፡፡ እናቴ እናት ብቻ አይደለችም። ሚስትም ብቻ አልነበረችም፡፡ እናቴ ለአባዬ ሚስቱ ብቻ አልነበረችም…ምንም ነገር ፈልጎ የማያጣበት የፀጋ አድባሩ ናት፡፡ አንድ ሴት በአንድ ወንድ ልብ ውስጥ የትም ቦታ ስትገኝ እናቴን ነው ያየሁት፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ሴቶችን አውቃለሁ እንደ እናቴ በባላቸው ልብ ውስጥ ሁሉም ቦታ ላይ ሲገኙ አላየሁም፡፡ ልጅ ሆኜ እናቴ አንድ ስለመሆኗ ብዙ ጊዜ የተጠራጠርኩበት ጊዜ ነበር፡፡ እማ ስላት ሳሎን ወይ ብላኝ ወዲያው እጇ መኝታ ቤት ራሴን ሲዳብሰኝ አገኘዋለሁ፡፡ የት ነሽ ስላት ኩሽና ነኝ ብላኝ በማላውቀው ፍጥነት ፊቴ ቆማ አያታለሁ፡፡ ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ እቃ ቤት በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ እናቴ አለች፡፡ ሩቅ ናት ስል ቅርቤ ናት፡፡ የለችም ስል አጠገቤ አገኛታለሁ፡፡ እዚህ ዓለም ላይ የእናቴን አይነት ሴት በማግባቱ እንደ አባቴ እድለኛ ወንድ ያለ አይመስለኝም፡፡ አባቴ በእናቴ የተባረከውን ያክል በምንም አልተባረከም፡፡ ለካ ወንድ በሴት ነው የሚባረከው፣ ለካ ባል በሚስቱ ነው ቀን የሚወጣው፡፡
እማዬና አባዬ ያሉበት የልጅነት ጠዋቴ የሕይወቴ ምርጡ ጠዋት ነው፡፡ የአባዬ ሚስት እማዬ የአብረሃም ሚስት ሣራን ትመስለኛለች፡፡ አባዬ ደግሞ አብረሃምን..እኔ ደግሞ ይስሐቅን..በዚህ ሁሉ ውስጥ ካራ አሲዞ ወደ ሞርያ ተራራ ወስዶ ልሰዋህ ቢለኝ እንቢ የምለው አይመስለኝም፡፡ የሕይወቴ ትልቁ ኩራቴ የእናቴ ልጅ መሆኔ ነው፡፡ የአባቴን ነፍስ ነጋ ጠባ አነባታለሁ..እንደ እማዬ ደስታ በምድር የላትም፡፡ የእናቴ ደስታ ምን እንደሆነ ግን ዛሬም ድረስ አልደረስኩበትም…እኔና አባዬ እንደሆንን ግን ይሰማኛል፡፡ አንዳንድ ነፍሶች በዝምታ ውስጥ የሚስቁ ናቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ በጩኸት ውስጥ፡፡ የእማዬ ደስታ እንደ ሣራ ደስታ በዝምታ ውስጥ የሚገለጥ ነው፡፡ በዝምታ ትወደናለች፣ በዝምታ ታፈቅረናለች፡፡ እዚህ ዓለም ላይ የዝምታን ፍቅር እማዬ ብቻ ነው ምታውቀው፡፡
ካደኩ በኋላ እንደ እማዬ አይነት ሴት ለማግኘት ያልገባሁበት አልነበረም፡፡ ልባም ሴት በፍለጋ እንደማትገኝ ሳላወቅ በመልካም ሴት ልብ ውስጥ ልቤን ላሳርፍ ብዙ ደክሜ ነበር፡፡ መልካም ሴት በፍለጋ እንደማትገኝ ያወኩት ግን ሣራ ሚስቴ ሆና ወደ ሕይወቴ ከገባች በኋላ ነበር፡፡ ሣራና እማዬ የተለያዩ ሴቶች ናቸው፡፡ መላዕክትና አጋንንት፡፡
ለካ እማዬ ለዚህ ምድር አንድ ሴት ነበረች…ከእማዬ በኋላ ምድር ላይ ሌላ መልካም ሴት ዳግመኛ አልተፈጠረም፡፡ የእሷ ልጅ በመሆኔ እኮራለሁ..አባዬ ሌሊት ከጋሽ ታከለ ዶሮ ጩኸት ጋር ከእንቅልፉ እየተነሳ ለፈጣሪ ፀሎት የሚያደርሰው እማዬን ስለሰጠሁ ይሆን እያልኩ ልክ ባልሆንም አስባለው.. ይሆን እንዴ እያልኩ ዛሬ ላይ እንደ ቂል የማለዳ ሀሳቦቼን እመዛለሁ፡፡
ካደኩ በኋላ ሁሉም ገባኝ…ፈጣሪ ከአባቴ እኩል እንዳላጸደቀኝ ያወኩት ሣራን ሳገባ ነው፡፡ ሣራና እማዬ የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው፡፡
በተለይ እማዬና አባዬ ያሉበትን የልጅነት ጠዋቴን፡፡ ካደኩ በኋላ ደግሞ ልጅነቴ በጣም ይናፍቀኛል፡፡ የአባዬ ሚስት እማዬ የእኔ እናት እማዬ ትመስለኛለች፡፡ እንደ እማዬ አይነት ሚስት ብትኖረኝ እላለው…በልጅነቴ ውስጥ እንደ እማዬ አይነት ሚስት ስመኝ ነው ያደኩት እዚህ ምድር ላይ እንደ አባዬ አይነት እድለኛ ወንድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሰፈሩ ውስጥ በእማዬ የማይቀና የለም። ፈጣሪ እማዬን ለአባዬ በመስጠቱ …
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016