ዓድዋ… ሰው፣ ነጻነትና እኩልነት

የካቲት 23 1888 የዛሬ መቶ ሀያ ስምንት ዓመት በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን ላይ አንድ ታሪክ ተመዘገበ፣ አድዋ የሚል የስሞች ሁሉ፣ የክብሮች ሁሉ፣ የነጻነቶች ሁሉ በኩር፡፡ ሁለት በታሪክ፣ በባህል፣ በስልጣኔ፣ በአይዶሎጂ የተራራቁ ሀገራት ኢትዮጵያና ጣሊያን አንዱ በራስ ወዳድነት አንዱ ደግሞ በነጻነት ስም ጽንፍ ቆሙ፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተ ሰሜን አቅጣጫ በ1065 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የኢትዮጵያውያን የከፍታ ምኩራብ አድዋ ለህልውናቸው በተጉና በእብሪት በታጠቁ ሁለት ተቃራኒ ነፍሶች ታመሰች፡፡

እውነት፣ ጽናትና፣ አንድነት ሕብረት ፈጥረው፣ ጀግንነት፣ አትንኩኝ ባይነትና የሀገር ፍቅር ስሜት አብረው ራስ ወዳዱንና እብሪተኛውን የፋሺስት ወራሪ ኃይል ለሕልውናቸው የቆሙ ጥቁር ነፍሶች አሸነፉት፡፡ በዚህ የጥቁርነት ተጋድሎ ውስጥ እኔና እናንተ ተፈጠርን፡፡ በዚህ የአንድነት መንፈስ ውስጥ ጥቁርነት ለመለመ፡፡ አፍሪካ ቀና አለች፡፡ በነዚያ ስለክብራቸው ሞትን በደፈሩ፣ ስለ ነጻነታቸው መከራን በናቁ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ዛሬን አየን። ይሄ የታሪክና የሰው መሆን ልኬት በአንድ ቃል እና በአንድ እውነት ቢታሰር ‹ሰው፣ ነጻነትና እኩልነት› የሚል ስም ይወጣዋል፡፡

ሰው ነጻነትና እኩልነት ከወደ አፍሪካ በኩል ዓለምን ተዋወቁ፡፡ አዲስ ታሪክ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ እውነት በጥቋቁሮቹ ኢትዮጵያውያን በኩል ስፍራ ያዙ፡፡ ዓለም አይታው የማታውቀውን የጀግንነት ወኔ ከወደ አፍሪካ በኩል አየች። ይህ የኢትዮጵያ የአንድነት መንፈስ በመላው አፍሪካ ተቀጣጥሎ አፍሪካን ነጻ አወጣ፡፡ ዓለም ደግሞ የተዛባውን የነጮች የበላይነት አስተሳሰብ እንድታስተካክል ተገደደች፡፡ ዛሬም ድረስ አፍሪካና ዓለም የአድዋን ፍሬ እየበሉ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁሮች ቀና ያደረጋቸውን አድዋን ያከብራሉ፡፡

አድዋ እኔና እናንተን በገዘፈ ታሪክ ላይ ያቆመ የአባቶቻችን የተጋድሎ ውጤት ነው፡፡ ይህ ስም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዘላለማዊ ክብር፣ ለነጮቹ ደግሞ ዘላለማዊ ውርደት ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ አድዋ ከብዙሀን ለብዙሀን የተንጸባረቀ የጥቁርነት አክሊል ነው፡፡ ስለሌሎች የፈሰሰ ደም፣ የደቀቀ አጥንት፣ ያላበ ላብ የፈጠሩት እውነታ ነው፡፡ ዓለም ሳትፈልግ በግድ እያነቃትም ቢሆን የዋጠችውና በደማቅ ብዕር የከተበችው የውርደት ታሪኳ ነው፡፡

ከአድዋ ድል ቀደም ብሎ በ1880ዎቹ አካባቢ ላይ በጀርመን በርሊን አውሮፓውያን አንድ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡ የስብሰባው አንኳር ዓላማ አፍሪካን በመቀራመት አንጡራ ሀብቷን የመመዝበር የራስወዳድነት ምክክር ነበር፡፡ በዚህ የቀኝ ግዛት ምክክር ላይ አፍሪካውያንን ያዋረዱና ክብር የነኩ በርካታ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ነበር፡፡ ጥቁርነት ባርነት ነው፣ ነጭ የኃይል፣ ጥቁርነት ደግሞ የደካማነት ምልክት እንደሆነ በሰፊው ሲወራ ነበር፡፡ በዚህ አስተሳሰብ በኩል በኃይልና በበላይነት መንፈስ ድንበር የመሻገር ዓላማቸውን እውን የማድረግ እርምጃቸውን ቀጠሉ፡፡

እንዳሉትም ሰራዊታቸውንና የጦር መሳሪያቸውን ተማምነው አይረባም ወዳሉት አፍሪካ ዘመቱ፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያን እንድትወር እድል ያገኘችው የወቅቱ ስልጡን ሀገር ጣሊያን ነበረች፡፡ ጣሊያኖች በጀነራል አልቤርቶኒና በጦር አዛዣቸው ጄነራል ባራቴሪ እየተመሩ የተስፋችን ምድር ወዳሏት ኢትዮጵያ ደረሱ…ግን እንዳሰቡት የሆነ አንድም ነገር አልነበረም፡፡ በዓለም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊ የጦር መሳሪያ እየተመራች ዘመናዊውን የጣሊያን ወታደር ድባቅ መታችው፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠር የኢትዮጵያ ገበሬ ሰራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በጦር ሰራዊቱ አስፈሪ የሆነውንና በወታደራዊ አካዳሚ የሰለጠነውን የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ኃይል ተቆጣጠረው፡፡ እኚህ ከላይና ከታች በሁለት አረፍተ ነገር የተገለጹት እውነት የማይመስሉ አድዋዊ ጀብዶች እንዴት? ለምን? የሚሉ አመራማሪ ጥያቄዎችን በማስነሳት ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል፡፡

በአድዋ ትንሳኤ በአፍሪካ ሰማይ ስር የነጻነት ጮራ ፈነጠቀ፡፡ እኩልነት ነገሰ፡፡ የበላይነት ተገረሰሰ። ይሄ ታሪክ ሕብረት የወለደው የእኔና የእናንተ ታሪክ ነው፡፡ ይሄ ታሪክ አፍሪካን የፈጠረ፣ ጥቁርነትን ያገነነ የአባቶቻችን የሀገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ የሀገር ፍቅር በተግባር ሲገለጽ አድዋን ይመስላል፡፡ አንድነትና ኅብረት ሚዛን ላይ ሲያርፉ ኢትዮጵያዊነትን ይመዝናሉ፡፡ አባቶቻችን ይቺን ሀገር ሲተውልን በብዙ መስዋዕት ውስጥ አልፈው ነው…፡፡

አድዋ በሀገራቸው ቀልድ በማያውቁ ኢትዮጵያዊ አርበኞች ሞትና እንግልት የመጣ የጥቁሮች ድል ነው፡ ይህ ድል በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ስር ላሉ አፍሪካውያን መታደስን ፈጥሯል፡፡ በባርነት ቀንበር ለተያዙ፣ ፍትህና እኩልነት ለተነፈጋቸው ጭቁን ነፍሶች ድህነት ሆኗል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ታላቁ የአድዋ ድል የዓለምን የፖለቲካ መልክና ርዕዮተ ዓለም ከቀየሩ ኩነቶች ውስጥ አንዱም ሆኖ አልፏል፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች በፊት ገጻቸው ላይ በአፍሪካ ድል ማግስት የመጣውን አፍሪካዊ ማዕበል በመመልከት ‹የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፣ ታላቅ የትውልድ ማዕበል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ ብርታኒካ የነጻነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ ላይ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አባት እየተባሉ የሚጠሩት ዳግማዊ አጤ ሚኒሊክ በሌሉበት የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ መሪ ሲል መርጧቸዋል፡፡

ከአድዋ የድል ዜና በኋላ በአፍሪካ ምድር በርካታ ተዐምራቶች ተፈጥረዋል፡፡ የአድዋ የድል ብስራት ለእኛ ለአፍሪካውያን የክብር ጮራን ሲፈነጥቅ ለነጮቹ ደግሞ የውርደት ማቅን አከናንቧል፡፡የነጮች የበላይነት፣ የምዕራባውያን ፊታውራሪነት እክል የገጠመው ነጭ በጥቁር የተሸነፈ እለት ነው፡፡  አድዋ ስም ብቻ አይደለም፣ አድዋ ተራራ ብቻ አይደለም…አድዋ ታሪክ ነው፣ አድዋ የጭቁን ሕዝቦች የነጻነት ዓርማ ነው፡፡ ሰው ነጻነትና እኩልነት ከአፈር የተነሱበት ማግስት ነው። ከሁሉ በላይ በደም የተሰመረ የሰብአዊነት ድንበር ነው፡፡

ከዚህ ታሪክ ቀጥለው ሀገርና ሕዝብ ባለታሪክም የሆኑ በርካታ ጭቁኖች አሉ፡፡ ይሄን ታሪክ ተደግፈው የቆሙ፣ ተማምነው የጸኑ፣ በዚህ ታሪክ ስር የሳቁ እልፍ ነፍሶች በየምኩራቡ አሉ፡፡ ከዓለም መፈጠር ቀጥሎ ዓለምን እንደ አዲስ የፈጠረ በተለይ የሰው ልጆችን ስር የሰደደ ራስወዳድነት ወደፍትህና ወደሚዛናዊነት የመለሰ የጥቂት ሀገሮች ድፍረትና ወኔ ግን ደግሞ የብዙሀን ነጻ መውጣት የተንጸባረቀበት አድዋ እንሆ ዛሬም በደመቀ መንፈስ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ ጣሊያን እንደነበረች አልቀጠለችም፡፡ ጣሊያን ብቻ አይደለችም አፍሪካና ዓለምም እንደነበሩ አልቀጠሉም። በፖለቲካቸው ላይ፣ በታሪካቸው ላይ፣ በስነልቦናቸው ላይ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ነጮች ያልመለሱት አንድ ጥያቄ ቢኖር የአድዋን የድል ሚስጢር ነው፡፡ አድዋ ለነጮች ሁሌም ውርደት ሁሌም ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን አይደሉም ሲሉ ለሽንፈታቸው ማስተባበያ ያቀርባሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ኢትዮጵያውያንን እንደ መለኮታዊ ኃይል ቆጥረው ለሽንፈታቸው የእምነታቸውን ኃይል ተጠያቂ ሲያደርጉ ይደመጣል፡፡

ኢትዮጵያዊነትን እንደ ሚስጥር ቆጥረው ዛሬም ድረስ ከነ ጥያቄያቸው የተቀመጡ ሀገራት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እውነት ነው ኢትዮጵያዊነት በአንድነት ሲታጀብ ሚስጥር ነው፡፡ በፍቅርና በወንድማማችነት ሲቋጠር መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ አድዋ ለነጮቹ ጥያቄ..ለእኛ ደግሞ መልስ..እንሆ ዘላለማዊ ክብር፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ በጣሊያን ምድር ብዙ ነገር ሆኗል፡፡ የወቅቱ የጣሊያን ንጉስ አማኑኤል ኡምቤርቶ የልደት ቀን በመላ ሀገሪቱ የሀዘን ቀን እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ዋና ከተማዋን ሮምን ጨምሮ ፍሎሬንስ፣ ሚላንና ቬነስ የመሳሰሉ ከተሞች ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር› በሚሉ ቁጣ በወለዳቸው ሕዝባዊ መፈክሮች ተጥለቅልቀው እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡ እዛም እዚም በነጮች መሸነፍ የተንገበገቡ እፍረት ወለድ የምዕራባውያንና የአውሮፓውያን የዝምታ ጉርምርምታ ሲደመጥ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በአንድነት በመቆማችን ነው። የአንድነታችን ዋጋ አድዋ ላይ ሀገርና ሕዝብ፣ ታሪክና ነጻነት ፈጥሮልናል…፡፡

ጥቁሮች በታሪካቸው የአድዋን ያክል ክብርና ሞገስ አግኝተው አያውቁም፡፡ ይሄ ስም፣ ይሄ ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ የአንድነት መንፈስ በምን ይገለጻል? ኢትዮጵያ አዲስ አፍሪካዊ አህጉር እና አስተሳሰብ ፈጠረች በሚል ሊገለጥ የሚችል ይመስለኛል። እውነቱም ይሄ ነው፡፡ ይሄን እውነት ለማረጋገጥ ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ያለችውን ዓለም ማየቱ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓለምን የተዛባ አስተሳሰብ ወደእኩልነት ሚዛን ያወረደች የፍትህ ውሀ ልክ ናት፡፡ ይሄ ክብር እንዴት እንደመጣ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ አድዋ የተፈጠረው በኢትዮጵያውያን አንድነት ነው፡፡ እንዴትም ቢታሰብ ከዚህ ውጪ መልስ የለውም፡፡ በወቅቱ ከመኳንቱ ጋር ያልተስማሙ፣ የንጉሱን አስተዳደር የሚተቹ መሳፍንቶች የነበሩ ቢሆንም ጣሊያን ሀገራችንን ሊወር ሲመጣ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅራኔና ቅሬታውን ወደ ጎን ብሎ ጣሊያንን ሊፋለም አድዋ ከትሟል፡፡

የአባቶቻችንን ነፍስና ስጋ? የአባቶቻችንን አእምሮና ልብ? ይሀው ነበር፤ ዛሬ ላይ እየራቀን የመጣው እውነት ይሄ ነው። አባቶቻችን ከነልዩነታቸው ወደ አድዋ አልሄዱም፣ ቅሬታና ቅያሜያቸውን ይዘው አልዘመቱም፣ ምን አገባኝ ሲሉም በዝምታ አልተቀመጡም። ሁሉም ነገር ከሀገር በኋላ እንደሚደርስ ስለሚያውቁ ቅድሚያ ለሀገራችን ሲሉ በአንድነት ተቧድነዋል፡፡ አባቶቻችን ከነቅሬታቸው ዘምተው ቢሆን፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልዩነታቸው ከሀገር ፍቅር ስሜታቸው በላይ ገዝፎ ቢሆን ዛሬ ላይ በዚህ ክብርና ሞገስ ባልቆምን ነበር። የተፈጠርነው በአባቶቻችን አንድነት ነው። ዛሬን ያየነው በአርበኞቻችን የሀገር ፍቅር መንፈስ ነው፡፡ ለነገው አድዋ እነሱን እንምሰል።

የሀገር ጉዳይ ሁሌም ከፊት ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ከግለሰብ ጉዳይ በልጦ አያውቅም፡፡ ከፖለቲካና ከብሄር ቡዳኔ ቀድሞ አያውቅም። አባቶቻችን በመሀከላቸው ቅራኔ ነበር ግን በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድነት ቆመው አድዋን ፈጥረዋል፡፡ በዚህም ትውልዶችን የባለ ጥልቅ ታሪክ ባለቤት አድርገዋል። እኛም ዛሬ ልዩነታችንን ወደ ጎን ብለን የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የጀመርነውን ጉዞ ወደ ስኬት እንዲመጣ መትጋት ይጠበቅብናል። ልጆቻችን የሚኮሩበትን፣ መጪው ትውልድ የሚደነቅበትን የአባቶቻችንን አይነት አድዋ መፍጠር ግድ ይለናል፡፡ በፊታችን የእኛን አንድነት የሚሹ በርካታ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጎዳዮች አሉ፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ሕይወታችን ለራሳችንም ሆነ ለትውልድ ልንሰራው የሚገባ አድዋ አለ፡፡

ስለሰላም፣ ስለአንድነት ያልፈታናቸው ብዙ ንትርኮች አሉ፡፡ ጀምረን ያልጨረስናቸው፣ ተነጋግረን ያልተግባባንባቸው ብዙ ሀገራዊ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ የእኛ አድዋ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ የዚህ ትውልድ ጀብድ ከእርቅና ከምክክር የሚጀምር ነው፡፡ ሳንታረቅና ሳንግባባ፣ ሳንመካከርና አንድነት ሳናበጅ ታሪክ ከማበላሸት ባለፈ ታሪክ መስራት አይቻለንም። የእኛ አድዋ ከፍቅር ነው የሚጀምረው፡፡ ከወንድማማችነት ነው የሚቀጥለው፡፡

አሸናፊነት ያለው በቅደም ተከተል ውስጥ ነው፡፡ ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀ ሁነት ሁሉ አሳፋሪ ነው፡፡ የአባቶቻችን አድዋ ክብር ያገኘው በአባቶቻችን ለሀገር ቅድሚያ በሰጠ እሳቤ ነው። የእኛም አድዋ ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት የሚጀምር ነው፡፡ ሀገር ያልቀደመችበት፣ ሕዝብ ያልተሰለፈበት አድዋ የለም፡፡ ግለሰብ ወይም ደግሞ ብሄር የጀገነበት ሕዝባዊ ክብር ታይቶ አይታወቅም፡፡ የእኛ አድዋ ከፍቅር ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ክብር የሚቋጭ ነው፡፡ አድዋ የታላቅ አስተሳሰብ ነጸብራቅ ነው፡፡ በአድዋ ድል ውስጥ ሞትና ክሽፈት፣ ማሸነፍና መሸነፍ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ አንድነት ጸንሶ የወለደው የሚደንቅ የጦር አመራርነት፣ መጨረሻ ከሌለው መታመን ጋር መሳ ለመሳ የቆመበት ነው፡፡ ከሁሉም የሚልቀው እውነት ደግሞ ኢትዮጵያ የቀደመችበት፣ ሰው መሆን ከነጻነትና ከክብር ጋር ያበሩበት መሆኑ ነው። በአጭር ቃል የድንቅ ጥበብ፣ የድንቅ አስተውሎት ውጤት ነው፡፡

ዛሬ ላይ እኔና እናንተ በግልም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወታችን እየባከንን ያለነው ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ባለመስጠታችን ነው። ሀገራቸውን ከፊት ያደረጉ ሕዝቦች ሁሌም አሸናፊዎች ናቸው፡፡ የለያዩንን ነገሮች ወደ ጎን ብለን ወደ ትልቅ ሀገራዊ የቤት ስራችን እናማትር። የአባቶቻችን የማሸነፍ ጥበብ ለሀገራቸው ቅድሚያ መስጠታቸው እንደነበር መቼም ልንረሳው አይገባም፡፡ እኔና እናንተም ለማሸነፍ ለሀገራችን ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡ ለመግባባት፣ ለመስማማት ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡ እያቀያየሙን ያሉ ነገሮች ብንተዋቸው፣ ብናዘገያቸው የማይጎዱን ነገሮች ናቸው፡፡ እየጣሉን፣ ኋላ እያስቀሩን ያሉት እነዚህ ነገሮች እንደሆኑ ገና አልገባንም። ለረጅም ዘመናት በነዚህ ነገሮች ስንገፋፋ ኖረናል፡፡ ለምን? ስንል ራሳችንን እንጠይቅ..

ከአድዋ መማር አለብን፣ ከአባቶቻችን መማር አለብን..እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግስት፣ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ አድዋና አርበኞቻችን የሚያስተምሩን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አድዋ የኅብረ ብሄራዊነት፣ የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ ነው። ለሀገርና ሕዝብ ቅድሚያ የመስጠት ዋጋ ነው። የእምነት፣ የጽናት፣ የአልበገሬነት ንቅናቄ ነው። እንደ ሀገር ከታሪካችን የምንማረው ብዙ ነገር አለ…ዓመት በመጣ ቁጥር ማክበር ሳይሆን እኛ የዚህ ትውልድ አብራኮች በአባቶቻችን መንፈስ ውስጥ መውደቅ አለብን፡፡ እነሱን መምሰል ይጠበቅብናል.. ማየት ብንችል፣ ወደሚያግባባን መራመድ ብንችል እስከዛሬ ድረስ ሲያገፋፉን የነበሩ ነገሮች ሁሉ እዚህ ግባ የማይባሉ እንደሆኑ እንደርስባቸው ነበር፡፡ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ምረቃ ማግስት እንቃ እላለው..አባቶቻችን በዘመናዊ ጦርና፣ በዘመናዊ መሳሪያ ነቅቶና በቅቶ የመጣውን ጣሊያንን በንቃት የበለጡት ለሀገራቸው ቅድሚያ በመስጠት ነው። ለሀገር ቅድሚያ መስጠት መንቃት ነው። ከዛሬ አርቆ ነገን ማየት የዚህኛው ትውልድ የቤት ስራ ነው፡፡

ተማሪ ብንሆን አባቶቻችን አስተማሪዎቻችን ነበሩ፡፡ ቀናኢ ብንሆን አድዋ ቃል ኪዳናችን መሆን ይችል ነበር፡፡ ለለውጥ ብንዘጋጅ ታሪኮቻችን እኛን ለማስተሳሰር በቂዎች ነበሩ፡፡ ከአድዋና ከአርበኞቻችን ሀገር የማቆየት ተጋድሎ እንማር። ለጥቁርነት ጌጥ ከሆነው፣ ነጮችን ካስጎነበሰው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እንማር፡፡

በአድዋ ላይ ቆመን መለያየት አይታሰብም። አድዋ ቋጠሮ ነው..እኔን ካንተ አንተን ከሌላው የቋጠረ የኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ ነው፡፡ አድዋ የኢትዮጵያውያን እጆች በአንድነት የሳሉት የጋራ ስዕላቸው ነው፡፡ እጆቻችን ለታሪክ ብርቅ አይደሉም፣ ክንዶቻችን ለድል ሩቅ አይደሉም… የአባቶቻችንን የአንድነት መንፈስ መውረስ ከቻልን በዳግም አድዋ ስም ዳግማዊ አፍሪካን መፍጠር እንችላለን፡፡ ዛሬም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እንደ ቀደመው ዘመን ከኛ የሚጠብቁት አለ፤ ዛሬም የአፍሪካ አይኖች ወደ እኛ ለአዲስ እውነታ እንደማተሩ ነው፡፡ የምዕራባውያን ዘመነኛ ቅኝ ግዛት መልኩን ቀይሮ በዘመናዊው ዓለም በአፍሪካ ላይ ዳግም አገርሽቷል፡፡ ይሄ ግርሻ፣ ይሄ መልከ ልውጥ ባርነት የሚቆመው ደግሞ እንደያኔው የአባቶቻችን ወኔ እኔና እናንተ በአንድነት መቆም ስንችል ነው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016

 

Recommended For You