ኢትዮጵያውያን  የደመቁበት የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ደረጃ የተሰጣቸው የዓመቱ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በነዚህ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች ከማሸነፍ ባለፈ በአስደናቂ ብቃት በርካታ ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ ደምቀዋል።

ከትናንት በስቲያ በቤልግሬድ በተካሄደው ውድድር የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ያፈራት አትሌት ጽጌ ዱጉማ በ800 ሜትር የቦታውን ፈጣን ሰዓት እና ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፋለች። አትሌቷ ርቀቱን በ1 ደቂቃ 59 ሰክንድ ከ66 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ነው የቦታውን ፈጣን ሰዓት እና ክብረወሰን በማሻሻል ያሸነፈችው። በዚሁ ርቅት አትሌት ትግስት ግርማ 2 ደቂቃ ከ21 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት 2ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።

ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ ውድድሮችም በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአስደናቂ ብቃት ፈጣን ሰዓቶችን ማስመዝገባቸው ይታወቃል። ከነዚህም መካከል የዓለምና የኦሊምፒክ የ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በ2ሺ ሜትር ፈረንሳይ ሌቪን ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃትና ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት ተጠቃሽ ነው።

ለሜቻ በዚህ ውድድር ለረጅም ዓመታት በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል ከፍተኛ ዝግጅትና ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። 4:51:17 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ማሸነፍ ቢችልም ያስመዘገበው ሰዓት በታሪክ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሆነ እንጂ ክብረወሰኑን በእጁ ለማስገባት አላስቻለውም። ቀነኒሳ ይህን ክብረወሰን ከዓመታት በፊት 4:49:99 በሆነ ሰዓት ማስመዝገቡ ይታወሳል። ለሜቻ ይህን ክብረወሰን ለማሻሻል ጥቂት ሰከንዶች ቢዘገይም ሌቪን ላይ ያሳየው አስደናቂ አቋም ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።

በተመሳሳይ ውድድር ሌቪን ላይ የዓለም የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮኗ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ያሳየችው ብቃትም አስደናቂ ነበር። ጉዳፍ በ3ሺ ሜትር ውድድር የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል የተቃረበች ቢሆንም በሽርፍራፊ ሰከንዶች ሳይሳካላት ቀርቷል። ያም ሆኖ ያስመዘገበችው 8:17:11 ሰዓት የርቀቱ ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። የርቀቱ ክብረወሰን 2014 ላይ ስቶክሆልም ላይ በገንዘቤ ዲባባ የተመዘገበ ሲሆን ሰዓቱም 8:16:60 ነው። በዚህ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሂሩት መሸሻ በ8፡29፡71 የራሷን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላው የተመዘገበ ድል በቶረን አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ 1500 ሜትር 3:57.24 በሆነ ሰዓት የገባችበት ነው። እሷን ተከትለውም ድሪቤ ወልተጂና ሂሩት መሸሻ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ ወጣቱን አትሌት ቢኒያም መሐሪንና ጌትነት ዋለን በ3ሺ ሜትር አስከትሎ የገባበት ድንቅ ፉክክርም የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የቤት ውስጥ ውድድር የበላይነት ያጎላ ሆናል።

እነዚህ ውጤቶች ከሁለት ሳምንት በኋላ በስኮትላንድ ግላስጎ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያውያንን ስብስብ ከወዲሁ አስፈሪ አድርገውታል። በተለይም በ3ሺ እና 1500 ሜትር የምትወዳደረዋ ጉዳፍ እንዲሁም ለሜቻ ግርማን የመሳሰሉ አትሌቶች በጥሩ ብቃት ላይ ከመገኘታቸው ባሻገር አዳዲስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እያሳዩ የሚገኙት ድንቅ ብቃት በውጤት መታጀባቸው በዓለም ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ልታስመዘግብ የምትችለውን ውጤት ከወዲሁ እንዲጠበቅ ያደረገ ነው።

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ባለፉት 18 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በ17ቱ በመሳተፍ በሜዳልያ ስብስብ ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ሆና ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ታሪክ 59 ሜዳሊያዎችንን (31 ወርቅ 13 ብርና 15 ነሐስ) ተገኝተዋል። ባለፉት 18 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በወንዶች ምድብ 23 ሜዳልያዎች (12 ወርቅ 3 ብርና 8 ነሐስ) እንዲሁም በሴቶች ምድብ 30 ሜዳሊያዎች (15 ወርቅ 8 ብርና 7 ነሐስ) ተመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም ከዓለም አንደኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። ይህ የኢትዮጵያ የበላይነት ዘንድሮም በግላስጎ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብርቅዬዎቹ አትሌቶች ሰሞኑን እያስመዘገቡ የሚገኙት ፈጣን ሰዓትና የውጤት የበላይነት አንድ ማሳያ ሆኗል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016

 

 

Recommended For You