የጥበብ ቤት እንደ ድንጋይና እንጨት የሚፈርስ፤ የሚናድ አይደለም። ጥበብ ቤቷን ሥትሰራ ቢችል አናጢ ባይችል መዶሻና ሚስማር ላቀበለ ሁሉ ዋጋዋ ትልቅ ነው። ባሳለፍነው ዓርብ ወርሃ የካቲት አሀዱ ብሎ በጀመረበት ቀን በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ትልቅ እንድምታ ያላቸው ሁለት አበይት ጉዳዮች ተከናውነው አልፈዋል። እነዚህ ሁለት ነገሮች በዕለቱ አሊያም በዓመቱ ብቻም ሳይሆን በዘመን ሁሉ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
አንደኛውን ጉዳይ ስናነሳ፤ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ለመሥራት ስለታቀደው የ”ፈረጃ” ፊልም ይሆናል። በዕውቁ ተዋናይ ሔኖክ ወንድሙ የተጸነሰው የዚህ የሕዝብ ፊልም ሀሳብ ከአንድ ደረጃ ላይ ደርሷልና የት ደርሶ ይሆን በሚል የፊልሙ ዋና አዘጋጅ በሆነው በዚሁ ተዋናይና በሌሎችም የፊልም ባለሙያዎች የደረሰበትን ደረጃ ለሕዝቡ አሰሙልን ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተውበታል። ከዚሁ መግለጫ ጋር የዚህን ታሪካዊ ፊልም ውጫዊ ዳሰሳ በቀጣዩ የሳምንት አምዳችን እንቃኛለን። ዛሬን በሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ መሰንበቻ እናድርግ።
ጉዳዩ በቀጥታ ወደ ደራሲያኑ መንደር ያመራል። በአንጋፋው የደራሲያን ማኅበር ቤት ውስጥ ብሩህ ሰማይ ከብርሃን ጸዳል ጋር ታይታለች። ሁለተኛው የዕለተ ዓርብ ጦማር ሲፈታ መልካም ብስራት ለደራሲያኑ እንዲሁም ለማህበሩ ይለናል። ባደጉት ሀገራት ብቻም ሳይሆን በብዙዎቹ ዘንድ አስከብሮና አንደላቆ የሚያኖረው የደራሲያኑ ዓለም ለኛ ሀገር ግን ያለመታደል ሆኖ የችግር መሰንቆ ነው። ማኅበሩም በችንካር ቆሞ ስለመክረሙ ለማንም ነጋሪ አያሻውም። የ60 ዓመታት የዕድሜ ባለጸጋ ሆኖ ሳለ፤ ዛሬም ግን በሁለት እግሩ ቆሞ ለመሔድ ሳይችል ቀርቶ እንደ ሕጻን ልጅ በእጁ ሲድህ ማየት አጥንት የሚሰብር ነው።
ብስራቱም ይህ ነው፤ ወድቆ ላለመሞት ከሚፍጨረጨርበት የሞት ሽረት ትግል ወጥቶ እራሱንም ችሎ ለሌላውም መትረፍ የሚችልበትን ትልቁን የ3 ሺህ ካሬ ሜትር የሕንጻ ግንባታ ለማድረግ የተነሳበትን የመጀመሪያውን እውን እርምጃ ለማሳየት ቻለ። በየካቲት 1 ቀን፤ ከአንድ የግንባታ ድርጅት ጋር በመፈራረም ጉዞውን አብስሯል።
ጥበብ ቤቷን ሠራች ማለታችን በምክንያት ነው። ስንልም ደግሞ በአይን የሚታየውን ቁሳዊውን ቤት ብቻም ለማለት አይደለም። ከዚህ ቁሳዊ ቤት በስተጀርባ የሚመጣ ጥበባዊ ትንሳኤም በመኖሩ ነው። እንደሚታወቀው የደራሲያን ማኅበሩ እጅግ እግሩ ጠፍሮ ለራሱም ለሌላውም እንዳይሆን ያደረገው ትልቁ ነገር ገንዘብ ነው። ገንዘብ የሚለውን ችንካር በዚህ ነቅሎ ለማውጣት ያስችለዋል። ከእግሩ እሾህ ለገባ፤ መጀመሪያ የሚያስፈልገው ነገር መርፌ አሊያም እሾህ ነው። ማኅበሩ የዚህ ሕንጻ ባለቤት ከሆነ በኋላ ያለበትን መርዛማ እሾህ ነቅሎ በማውጣት በደንብ ወደፊት ለመራመድ የሚያስፈልገው ብልሀት ብቻ ነው።
በደራሲያን ቤት ውስጥ ደራሲያን አሉ፤ ብዕራቸው የነተበ ትጉህ ብዕረኞች ድሮም ዛሬም ድረስ፤ ከዚሁ ችግር የተነሳ ቤቱ የነዚህን ደራሲያን ሥራዎች በባለቤትነት ለመምራትና ለሚያስፈልጋቸው ወሳኝ ነገሮች መድረስ ሳይችል ቀርቷል። እንደብዙ ሀገራት ተሞክሮ የደራሲያኑ ማኅበር አባላት ሥራዎችን መሥራት እስከቻሉ ድረስ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም። የኛ ሀገርስ ለምን? ብለን እንዳንል፤ እንኳንስ ለማህበሩ አባላትና ለራሱም ያጣ የነጣ ሆኖ ጉስቁልቁል ያለ ፊቱ ነው የሚታየን። በዚህ ሁሉ ዘመናት አንጀቱ ተበጥሶ ላለመውደቁም፤ ከአባላቱ ከሚሰበሰብ ጥቂት ገንዘብና ከአንዳንድ የውጭ ድጋፎች ነው። እንጂማ፤ የሀገር ባለውለታ ሆኖ ሳለ እንደመረሳቱ ቢሆንማ ኖሮ፤ ለማስታወሻነት የምትሆን ጨርቁን እንኳን ባላየን ነበር። ምስጋና ለእነዚህ የጥበብ ልጆች ይግባና ለአይን በማይታይ ዱር ገደሉ ሁሉ ሲታገሉና በጫንቃቸው ተሸክመው ወንዙን እያሻገሩ ዛሬ ላይ እንዲደርስ ሆኗል።
የተባለው ቤት ሲሰራ፤ ጥበብም የራሷን ቤት ከውስጡ ትሰራለች። ስንቱን ከሞት ሊቀሰቅስ የሚችለውን የጥበብ ሥራዎቻቸውን፤ በገንዘብ እጦት ምክንያት እንደታቀፉት አብረው ለሚያልፉት አባላቱ ትልቅ የምስራች በር ነው። ምናልባትም ከዚያን ወዲያ የሚጨነቁት ምንና እንዴት ልሥራ በሚል ይሆናል፤ ምክንያቱም እንዳይንቀሳቀሱ ከሆዳቸው ሰትሮ የያዛቸው የገንዘብ ችንካር በማህበሩ ተነቅሏልና። እንደ አንድ ደራሲ ብቻም ሳይሆን እንደተቋሙ የሚኖረው ኪነ ጥበባዊ እንቅስቃሴም ከወትሮው ለወጥና ለየት ያለ ይሆናል። ታዲያ፤ ከማኅበሩ ቡስካ በስተጀርባ፤ ቤቷን የሠራችው ጥበብ ናት ብንል ዋሾ ሊያስብለን የሚችል ምንስ አለና።
ስለ ቤቱና ዕለቱ ደግሞ ጥቂት እንበል። ለዚህ ዕለት ስኬት ለመድረስ የማህበሩ አባላት የከፈሉት ዋጋና የላይ ታች ውጣውረድ ቀላል የሚባል አነበረም። በተለይ ደግሞ ጉዳዩን ከግብ ለማድረስ ወዲያና ወዲህ ሲሉ በአንድ ወቅት የመኪና አደጋ ሁሉ ደርሶባቸው የነበሩት የማኅበሩ ሊቀመንበር የዝና ወርቁ ከብዙዎች ምስጋና ተችሯቸዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር እስትንፋሱ ሳይቋረጥ ዛሬም ድረስ መኖሩ በእንደነዚህ አይነቱ የግል መስዋዕትነትና እንደርሷ ባሉ መንፈሰ ብሩሃን ነው። በእያንዳንዱ ስድሳ ዓመታት መካከል፤ እሾሃማውን ቀንበር ተሸክመው በቅብብሎሽ ያመጡ እጅግ በርካታ ናቸው። ለማኅበሩ ብቻም ሳይሆን፤ እንደ ሀገር ለሀገር ባለውለታ ሆነው፤ የማኅበሩ አንድ አካል የነበሩ ብዙ ደራሲያን የሞቱት በስጋዊ ብቻም ሳይሆን በምስጋና እጦትም ጭምር ነው።
“ምስጋና ትልቅ ነገር ነው። አንጥንትና መንፈስንም ያለመልማል። ከምንም በላይ፤ የቤት ግንባታውን ለማከናወን እኔ አለሁ ሲል የመጣውን የግንባታ ድርጅትም ሊመሰገን ይገባል። የሚያገኘውን ትርፍ ሳያሰላ በመልካምነት በመምጣቱ፤ ኢትዮጵያዊ የሆነውን የመረዳዳት ባሕል አሳይቶናል። በዚህ ሥራ ውስጥ፤ የኛ የደራሲያን ማኅበርም ሆነ ድርጅቱ፤ ሁለቱም የቆሙት በአንድ ዓላማ በመሆኑ ደስ ብሎኛል” ሲሉ የዝና ወርቁ ንግግራቸውን አደረጉ።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ከተመሰረተበት ዕለት አንስቶ በተጓዘባቸው 60 የድክርትና የመፍገምገም ዓመታት ውስጥ በጥበብ ወጭቱ እውቀትን፤ በማድጋው የመንፈስን መና እየሞላ ኢትዮጵያን ገንብቷል፤ የገነቡትንም ወልዶ አሳድጓል። በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያኖረው የብርሃን ላንባ፤ በነበልባሉ ውስጥ መልክና ታሪኩን ያሳያል። በሀገራችን በተካሄዱ የፖለቲካ ለውጥና ሥርዓቶች ውስጥ ከማንም በላይ ደራሲያኑ፤ ከፊተኛው ረድፍ ላይ ነበሩ። በብዕራቸው ሳይቆሙ፤ አሳልፈው ደረታቸውን ለጥይት የሰጡ ጥቂት አይደሉም።
ኢትዮጵያን የመቀየርና ከሰቆቃው ድኅነት የማውጣት ሕልማቸው ታላቅ ነበር። ሁሉም የማኅበሩ አምሳል፤ እጅና እግር ነበሩ። እነዚህ የንጋት ክዋክብት በችግር ማቀው፤ እንደ ጠዋት ጤዛ ሲረግፉ ነገር ግን ያ “ሀገር ማለት ሰው ነው” ነው የተባለው አምሳለ ሀገሩ ሰው ግን ሳይደርስላቸው፤ ለስጋም ሆነ ለመንፈስ የሚሆን አዱኛ ሳይሰጣቸው አምልጠውት ሄደዋል። ወደኋላ ተመልሰን፤ የብዙ ደራሲያንን ሕይወት ለማየት ብንሞክር የምናገኘው አንድ አይነት ሕይወት፤ አንድ አይነት መረሳትና መገፋት ነው። ባለውለታ ሲታለፍ በዝምታ፤ ብርቃችን አይደለም። ይህ ጥቁር ጥላሸት፤ ዛሬም ድረስ ለምልክት በደራሲያን ማኅበር ፊት ላይ እንደማዲያት ሆኖ ይታያል።
የነገሩን ጫፍ ወዲህ ስንመዘው፤ ይህ ማኅበር በአሁኑ ሰዓት የጀመረው የሕንጻ ግንባታ፤ ያለፈ እንባውን ባይጠርግለትም በተስፋ እየተጽናና ወደ አዲስ ማንነት እንዲገባ ያደርገዋል። ቀደም ሲል ከመንግሥት ያገኛት የ3 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ስጦታ ምናልባትም ለትውልድ ሁሉ የሚሆን፤ የዘለዓለም ሕይወቱ የሚተክልበት ይሆናል። ማኅበሩ ከአፈሩ፤ ጥበብ ደግሞ ከአየሩ ላይ ቤታቸውን ይሠሩበታል።
ይህን ለመሥራት ታዲያ ማኅበሩ አሁንም የገንዘብ ችግር አለበት፤ ሳንቲም እንኳን ወድቃ ቅጭል የምትለው ከመንደሩ ርቃ ነው። በአንድ ወቅት የዚሁ ማኅበር አባል ከሆነ ሰው ጋር ተገናኝተን ስናወራ ያለኝ ነገር ትዝ አለኝ። ድንገት በጨዋታ መሀል ስለ አንድ ጉዳይ ልጠይቀው ፈለኩና ነገርየውን ማኅበሩ ያከናውነው እንደሆን በማለት ብጠይቀው ጊዜ “አይ…ወዳጄ እኛ ለራሳችን ጡረተኞች ነን” ሲል ቁጭት በታከለበት ስሜት ውስጥ ሆኖ መለሰልኝ። በርግጥም አላጋነነውም፤ የ60 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነ ማኅበር ምንም የገቢ ምንጭ ሳይኖረው ከዚህም ከዚያም እያለ ለመሰንበት ታህል ብቻ ሲኖር ቆይቷል። በዚህ መልኩ ለቆየው የደራሲያን ማኅበር የሕንጻ ግንባታውን ለማካሄድ ምናልባትም ተአምር ያስፈልገው ነበር፤ ያውም የ40 ሚሊየን ብር ተአምር። ለዚህ ገንዘብ፤ አለሁልህ በማለት ከጎኑ የሚቆምለትና የሚደግፈው አካል የግድ ነበር። ለዚህ በጎነትም ዲቢ የተገጣጣሚ ቤቶች እራሱን አቅርቧል። በተገጣጣሚ ቤቶች፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለመብት የሆነው የዲቢ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት፤ መሀንዲስ ብርሃኑ ካሳ የካቲት አንድ በነበረው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ተፈራርመዋል።
ይህ በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው ስምምነት እከክልኝ ልከክልህ የሚመስል ቢሆንም፤ ነገር ግን ከመጠቃቀም ይልቅ መጥቀምን መሰረት ያደረገ የበጎነት ነጸብራቅ ነው። ጥበብ ቤቷን ለመሥራት የግድ ካላት፤ በየትኛውም አስቸጋሪ ዘመናት መሃከል ሰው አጥታ አታውቅምና ዛሬም የሆነው ይሄው ነው። ያን ያህሉን ገንዘብ ቆጥሮ ለማሰራት ለማይችለው የደራሲያን ማኅበር፤ ድርጅቱ በራሱ ወጪ ለመገንባት ተስማምቷል። ታዲያ በምትኩ፤ ከግንባታው መልስ ለአምስት ዓመታት ያህል በጊዜያዊነት ተረክቦ በኪራይና በመሰል አገልግሎቶች ወጪውን ለማካካስ ይሞክራል።
በእኚህ 5 ዓመታት ያወጣውን ይመልስለት ይሆን? ብንል፤ ለምላሹ በሂሳባዊ ቀመር ብዙ ለመጠበብ አያሻንም፤ የዝና ወርቁ እንዳሉትም “በእርግጠኝነት አይመልስለትም”። ይህንኑ ጥያቄ ለግንባታ ድርጅቱ ባለቤት፤ ለብርሃኑ ካሳ በማቅረብ፤ እንዴትስ ይህን ለማድረግ እንደፈለጉ በተጠየቁ ጊዜ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “እኛ የምንሰራው ድንጋይ ነው፤ ደራሲያኑ ግን የሚሰሩት ሰውን ነው። እኛ ሁላችንም የእነዚህ ደራሲያን ውጤቶች ነን፤ ያሉትም የሞቱትም። ይህን ለመስራት ስወስን አተርፍበታለሁ በማለት አይደለም። ስራው እንደ ሀገር ምናልባትም ትንሽ ነገር ሊሆን ይችላል፤ እንደኛ ድርጅት ግን ለሀገራችን ባለውለታዎች መስራት በመቻላችን እድለኞች ነን። ትልቁ ታሪካችንም ነው። በእነዚያ አምስት ዓመታት፤ ምናልባትም ያወጣነውን ግማሽ ያህሉን ብቻ ይሆናል የምናገኘው፤ ግን በጣም ደስተኞች ነን። ለደራሲያን ማኅበር መስራት ማለት ለሀገር መስራት ማለት ነው።
በሚሠራው በዚህ የጥበብ መንደር ውስጥ ከቤቶቹ ከፊሉ ለመጽሐፍት መሸጫና አዳዲስ የሕትመትና የጥበብ ውጤቶች የሚሰፍሩበት ይሆናል። እንዲሁም የአባላቱ የጥበብ ሥራዎችም ከመጀመሪያው፤ ከሕትመትና ስርጭቱ ጀምሮ በኃላፊነት የደራሲያን ማኅበር የሚረከበው ስለመሆኑ የማኅበሩ ሊቀመንበር፤ አበረ አዳሙ አንስተውታል። ከበስተጀርባ ጥበብ ቤቷን ሠራች፤ ትሠራለች ስንል አንድም ለዚህ ነው። ከምንም ነገር በላይ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ጥበብ የምትፈልገው ሰውን ነው። ሌላው ቀርቶ የማኅበሩን የእውቅና ደረጃ ከፍ በማድረግ ጎልቶ እንዲወጣ ለማስቻል እንኳን ሰው የሚያስፈልግ ቢሆንም ግን የለም ለማለት ያስደፍራል።
በደራሲያን ማኅበር የታሪክ ማኅደር ውስጥ፤ እስከዛሬ ድረስ እንደ ግለሰብ በክብር አባላትነት የተመዘገቡ ብቸኛው ሰው፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ብቻ ናቸው። እንደ ተቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የብሔራዊ ቤተ መጽሃፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ይገኙበታል። እንደኛ ሀገር እምብዛም ስለማንጠቀምበት ነገሩ ቀላል ቢመስለንም፤ እንዲህ እንደ ደራሲያን ማኅበር ላሉት፤ እውቅ ተቋማትንና ዝነኛ ግለሰቦችን አስጠግቶ ከሥሩ ማድረግ ያለው ሚና ዳጎስ ያለ ነው።
“አንድ አሜሪካዊ ጠቢብ ባለጸጋ ነበር። ይህም ሰው በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሊባል የሚችል ዘመናዊና ቅንጡ ቤት ለመስራት ፈለገና ዕቅድ ነድፎ፤ በቆንጆ ዲዛይን ሰርቶ አዘጋጀው። መሰረቱንም ጣለ። ከዚያም ሥራውን በንድፉ መሰረት ለመስራት እንደጀመረ ሕይወቱ አለፈ። ባለቤትየውም የባለ ራዕይውን ራዕይ ተሸክመው፤ ከውስጣቸው የሀዘን ማቅ ሳይለብሱ ሥራውን አስቀጠሉት። ቤቱም ተገነባና የታሰበው ተቋም እንደታሰበው ተሰራ። እናም ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በመጨረሻው ቀን የዓለም መሪዎችና ታላላቅ ጋዜጠኞች የተገኙበት ዝግጅት ተደረገ። ጋዜጠኞቹም ወደ ሴትየዋ በመሄድ “እንዲያው ባለቤቶት በሕይወት ኖረው ይህን ቢያዩ እንዴት ደስተኛ በሆኑ ነበር፤ ለማንኛውም በመካከላችን ባለመገኘታቸው በጣም እናዝናለን! እና ምን ይሰማዎታል?’ አሏቸው።
ሴትየዋም ፈገግ በማለት እንዲህ ብለው መለሱ “የኔ ወንድም ተሳስተሃል፤ ባለቤቴ እኮ ይህንን አይቶና ጨርሶ ነው የሞተው፤ እንጂ ጀምሮ አይደለም የሞተው፤ ሲሉ መለሱለት” አሉ፤ የቀድሞው የማኅበሩ ሊቀመንበር፤ አንጋፋው አርቲስት ጌትነት እንየው፤ ከመጸሐፋቸው በቀነጨቧት ታሪክ። ጥበብም እንዲሁ ናት፤ ምነው ይህን አይተው በሞቱ ኖሮ አትልም። ዛሬ ለምትሠራው ቤት መሠረቱን የጣሉትና አስቀድመው ያዩት፤ እነዚያ የሔዱቱ ስለመሆናቸው ታውቃለችና ለዘነጋናቸውም ሁሉ የዋጋቸውን ትከፍላለች።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016