ሕብረት ሥራ ማህበራቱ በወረሃ የካቲት

በማኅበረሰቡ ዘንድ ፍትሃዊ የምርትና የሸቀጦች ስርጭት አንዲኖር በማድረግ ቀዳሚ የሆኑት ኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ በተለይም ሰው ተኮር በመሆናቸው ገበያን በማረጋጋት ለሸማቹ እፎይታን በመስጠት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በግብርና ምርቶችና በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚፈጠረውን የገበያ አለመረጋጋትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን በመከላከልና ገበያን በማረጋጋት በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና በማቃላል የላቀ ድርሻ አላቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር የሚካሄደውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ዘንድሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ ‹‹ኅብረት ሥራ ማህበራት ከገበያ በላይ ናቸው›› በሚል መሪ ሃሳብ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ተዘጋጅቷል። ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ከጥር 29 እስከ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተገኝተው የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን ይዘው ለሸማቹ ያቀረቡ አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራትና ሸማች የኅብረት ሥራ ማህበራት በርካታ ናቸው፡፡

ወረሃ የካቲትን በጉጉት የሚጠባበቀው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተገኝቶ ጎብኝቷል፡፡ ጥራት ያላቸውን የአርሶ አደሩን ምርትም በተመጣጣኝ ዋጋ ሲሸምት ሰነባብቷል፡፡ ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ይዘው የቀረቡትን የግብር እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ሲሸምቱ ያገኘናቸው አቶ ሽፈራው አበራ ከሳሪስ አካባቢ ነው የመጡት፡፡ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ በየዓመቱ መዘጋጀቱ መልካምና በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተወሰነ መልኩ ገበያን ማረጋጋት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም አንድ ኪሎ ቡና በመደበኛው ገበያ ማለትም ሱቅ ላይ ከ500 እስከ 550 ብር የሚሸጥ መሆኑን ጠቅሰው በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ጥራት ያለውን ቡና በኪሎ 350 ብር መግዛት ችለዋል፡፡

ሌሎች ምርቶችም እንዲሁ ቅናሽ ያላቸው መሆናቸውን ሲያስረዱ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዱቄት፣ ማርና ሌሎች ምርቶችንም ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፤ በሁሉም የምርት አይነቶች ከመደበኛው ገበያ ቅናሽ መኖሩን አመላክተዋል፡፡ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ምርቶች ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዘይትና የጽዳት ዕቃዎች ላይም መጠነኛ የሆነ ቅናሽ መታየቱን ነው ያመላከቱት፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በየዓመቱ መዘጋጀቱ እጅግ በጣም ጥሩና ገበያውን በማረጋጋት የበኩሉን ድርሻ መወጣት መቻሉን ያነሱት አቶ ሽፈራው፤ የዘንድሮ ባዛርና ኤግዚቢሽን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ሞቅ ያለ አለመሆኑን ነው የታዘቡት፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከዚህ ቀደም በርካታ ቁጥር ያለው ሸማች ተገኝቶ በስፋት ይሸምት ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ምርት አለ የሸማች ቁጥር ግን ቀንሷል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የኑሮ መወደድና የዋጋ ንረቱ እንዲሁም የቦታው ርቀት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ያስረዱት፡፡

ሌላኛዋ ሸማች ወይዘሪት ንጋቷ ቦጋለ ትባላለች። ከየካ ክፍለ ከተማ ከወረዳ አስር የመጣችው ንጋቷ፤ በባዛርና ኤግዚቢሽኑ የቀረቡ ምርቶች በርካታ እንደሆኑ ጠቅሳ፤ ሸማቹ ምርቶቹን በቀጥታ ከገበሬው መሸመት መቻሉ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በከፊል ማረጋጋት የሚችል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እሷ እንዳለችው የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በተለይም ሽንኩርት እጅግ በጣም መወደዱ ይታወቃል። በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ደግሞ ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎች ምርቶችም ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እየቀረቡ ነው፡፡

ሽንኩርት ውጭ ላይ ካለው ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሆነና በኪሎ ከ80 እስከ 90 ብር መግዛቷን ገልጻለች፡፡ ቲማቲምም እንዲሁ ውጭ ካለው ገበያ በብዙ እጥፍ የሚቀንስ መሆኑን ጠቅሳ በኪሎ ስምንት ብር መግዛቷን ተናግራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማር በመደበኛው ገበያ በኪሎ እስከ ስድስት መቶ ብር ሲሆን በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ንጹህ የአርሶ አደሩን ማር በኪሎ ከ300 እስከ 350 ብር እየተሸጠ ስለመሆኑ አስረድታለች፡፡

የኅብረት ሥራ ማህበራት ገበያን በማረጋጋት ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ያነሳችው ንጋቷ፤ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ ዓመት ጠብቆ ከሚዘጋጅ ይልቅ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ መዘጋጀት ቢችል ማኅበረሰቡን አሁን ካለው የኑሮ ጫና ማገዝ እንደሚቻል ስትገልጽ፤ በተለይም ቦታው መሀል ከተማ እንደመሆኑ በከተማ ዳርቻ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚገኘው ሸማች በአቅራቢያው ተደራሽ መሆን እንዲችል ቢደረግ መልካም እንደሆነ በመግለጽ ሀሳቧን ቋጭታለች፡፡

ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራትንና ሸማች የኅብረት ሥራ ማህበራትን ማገናኘት ዋና ዓላማቸው ሲሆን፤ የባዛርና ኤግዚቢሽኑ በተለይም የኅብረት ሥራ ማህበራትን ከተጠቃሚው ጋር በቀጥታ ማገናኘትና ማስተዋወቅ ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ሸማቹ ምርቶቹን መሸመት እንዲችልና አምራቹም ምርቱን መሸጥ የሚችልበት የተሳለጠ መድረክ ነው፡፡ ሌላው መድረኩ ዘላቂ የሆነ ትስስር መፍጠር ያለመ ሲሆን፤ አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራትና ሸማች የኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም ሸማቾች ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በማስቻል የኅብረት ሥራ ማህበራቱ ገጽታቸውን መገንባት የቻሉበት አጋጣሚ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ከ110 ሺ በላይ የሆኑ የኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም ዩኒየኖች መኖራቸውን የጠቀሱት የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ/ር) እንዳሉት እነዚህ ኅብረት ሥራ ማህበራት በአንድ መድረክ ተገናኝተዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒየኖቹ ገጽታቸውን መገንባት ችለዋል፡፡ መድረኩ ዘርፉ በአገር አቀፍ ደረጃ እያበረከተ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ምን እንደሚመስል ማስተዋወቅ የቻለ ነው፡፡

ማኅበራቱ እሳስካሁን ባላቸው አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ 18 በመቶ የገበያ ድርሻ ያላቸው እንደሆኑም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከዚህ የበለጠ የገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈለግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም፤ ኤግዚቢሽንና ባዛር አንዱና ዋናው መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ መድረክ ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለ ነው የተናሩት፡፡ ባዛርና ኤግዚቢሽን በሚካሄድበት ወቅት ሸማቹ ኅብረተሰብ ወይም የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ጊዜ ወስደው ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በመሀል ያለውን ረጅም ሰንሰለት በማሳጠር ደላሎችን በማስወጣት በግብይት ሂደት ውስጥ የሚፈጠረውን ውጣ ውረድ ለማሳጣር እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ አምራቾች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የፖሊሲ አውጪዎችና ምሁራንም ጭምር ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር መገናኘት አለባቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ የኅብረት ሥራ ማህበራት እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና በርካታ ተግባራ የሚከናወኑበት ኤግዚቢሽንና ባዛር መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው የንግድ ስርዓት እጅግ የተወሳሰበና ሰንሰለቱ የረዘመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት በመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት የመፍትሔው አካል መሆን ይችላሉ። አጠቃላይ በግብይት ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ይቀርፋሉ ተብሎ የሚታሰብ ባይሆንም የበኩላቸውን አበርክቶ እየተወጡ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት የገለጹት ኮሚሽነሩ፤

ኅብረት ሥራ ማህበራት ከሌላው የንግዱ ማህበረሰብ ይልቅ ሰው ተኮር እንደሆኑ ገልጸው በተጠቀሰው ጊዜ ለሸማቹ ማህበረሰብ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚዘጋጀውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ክሌሎችም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀውን ባዛርና ኤግዚቢሽን ተከትለው በየደረጃው እንደሚያዘጋጁም አመላክተዋል፡፡ በዚህም ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ገበያን በማረጋጋት የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት፤ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፈ ብዙ አገራዊ ሚና ያላቸው ሕዝባዊ ተቋማት ናቸው፤ ማኅበራቱ ከግብይት ባለፈ የገንዘብ ቁጠባና ብድር፣ የቤቶች የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትና የአምራቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትም አላቸው፡፡ ሁሉም በማህበረሰብ ውስጥ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ዘንድሮ የተካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛርም ‹‹ኅብረት ሥራ ማህበራት ከገበያ በላይ ናቸው›› በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑ በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማህበራት የተደራጀ ማህበረሰብ ያላቸውና በስራቸው 28 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላቸው በመሆናቸው አገልግሎታቸውም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በተለይም አገሪቱ ለምትከተለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አቅጣጫ ትልቅ ድርሻ ያላቸውና ሰፊውን የገጠር ሕዝብ በመድረስ የአገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥም ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኑሮ ጫናን በማቃለል በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ሸማች ማህበረሰብ ከኅብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችልበትን ዕድል መፍጠር የቻሉና በየዓመቱ በወረሃ የካቲት የሚጠበቁ እንደሆኑ በመግለጽ በቀጣይም ተጠናክረው የሚቀጥሉ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኤግዚቢሽንና ባዛሩ መሳካት ወራትን የወሰዱ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ሲያስረዱ፤

አዲስ አበባ የግብርና ምርቶችን የማታመርት በመሆኑ ለባዛሩ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ወደ ባዛርና ኤግዚቢሽኑ እንዲሁም ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ከአምራች ክልሎች ጋር ምርት የማፈላለግና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ትስስር በመፍጠር ምርቶቹ ወደ ከተማዋ መግባት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ከግብርና ምርቶች ባሻገርም ከትላልቅ የፋብሪካ ባለቤቶች ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ እንዲገቡ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም የኅብረት ሥራ ማህበራት ለሸማች ማህበራት ምርቶችን በበቂ ሁኔታ አሰባስቦ ለግብይቱ ማቅረብ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከስምንት ሺ በላይ የኅብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ልዕልቲ፤ ከእነዚህም ውስጥ 154 ሸማች የኅብረት ሥራ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ 1600ዎቹ ደግሞ የቁጠባ ማህበራት እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ሌሎች ማኅበራት እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ125 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ አምራቾችና የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን ለከተማው ነዋሪ ማቅረብ ችለዋል፡፡

ከ88 በላይ የሚሆኑ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን፤ ምርቶቹም እሴት የተጨመረባቸውና ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ በሚፈለገው መጠን የሚቀርብበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ ሸማቹም የሚፈልገውን ምርት በሚፈልገው መጠን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደቻለ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴው በከተማ ላይ ትርጉም ያለው ሥራ መስራቱንና ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው፤ በተለይም በዶሮና በከብት እርባታ ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል። በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት የራሳቸውንና የአካባቢያቸውን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ትላልቅና አገር አቀፍ በሆኑ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች በመሳተፍ ምርቶቻቸውን ለሕዝቡ ይዘው መቅረብ እንደቻሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከስድስት በላይ የሚሆኑ የፋብሪካ ባለቤቶችም እንዲሁ የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን ያነሱት ኮሚሽነሯ፤ ዘይት፣ ፓስታ ማካሮኒና ዱቄት የመሳሰሉ የምግብ ሸቀጦችንና የጽዳት ዕቃዎች ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል፡፡ በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ላይ የተለያዩ የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከመሸጥ ባለፈ በቀጣይነት ምርቶችን ለከተማው ነዋሪ ማቅረብ የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በተለይም ከክልል ከሚመጡ አምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ተጨማሪ የምርትና የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው ኤግዚቢሽንና ባዛር የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ከተማ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ጋር በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ይህ በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ከተካሄዱት ኤግዚቢሽንና ባዛሮች የተለየ እንዲሆን አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016

 

Recommended For You