የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ  የግጭት አፈታት ላይ ያተኮሩ 7 የጥናት ሥራዎችን ለህትመት ሊያበቃ ነው

አዲስ አበባ፡- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግጭት አፈታት ላይ ያተኮሩ 7 የጥናት ሥራዎችን ለህትመት ሊያበቃ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለህትመት ለማብቃት እየሠራቸው ያሉ የጥናት ሥራዎች በከተማና በገጠር የግጭት አፈታት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን በዩኒቨርሲቲው የሕግና አስተዳደር ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን፣ ዶ/ር አዲስወርቅ ጥላሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስታውቀዋል፡፡

ከብሪትሽ ካውንስል ጋር በመተባበር ዩኒቨርሲቲው እያሠራቸው የሚገኙ የጥናት ሥራዎች በአጠቃላይ 8 ሲሆኑ፤ በግጭት አፈታት ዘዴ ላይ ያተኮሩት 7ቱ ናቸው፡፡ አጥኚዎቹ በብሪትሽ ካውንስል የጥናትና ምርምር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ፣ የጥናት ሥራዎቻቸውን የመጀመሪያው ረቂቅ አቅርበዋል፡፡

የሰላም ጉዳይ ላይ ካተኮሩት ጥናቶች መካከል ሁለቱ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ላይ የተሰሩ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ምርምሮች ደግሞ ትኩረታቸውን በሲዳማ ክልል በከተማና በገጠር የግጭት አፈታት ላይ አድርገው የተሠሩ ናቸው፡፡

ብዙውን ጊዜ መሰል ምርምሮች ሲሠሩ በብዛት ትኩረት የሚያደርጉት የገጠሩ ማኅበረሰብ ግጭቶችን በምን መንገድ ይፈታል በሚለው ላይ ነው ያሉት ዶ/ር አዲስወርቅ፣ በእነዚህ ምርምሮች ግን በከተማ ያለው የግጭት አፈታት ዘዴም ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

የጥናት ሥራዎቹ በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተመደቡላቸው አማካሪዎች አማካኝነት ምላሽ እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ አጥኚ ጥናቱን ካበለጸገ በኋላም ወርክሾፕ ተዘጋጅቶ ለህትመት የሚላክ ይሆናል ብለዋል፡፡

ማንኛውም የምርምር ሥራ ሲሠራ ችግሮችን መነሻ በማድረግ እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር አዲስወርቅ፤ ጥናቶቹ ችግርን መነሻ አድርገው፣ ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለው የደረሱበትን ሂደታቸውን ሲያጠናቅቁ የሚያመላክቱ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ጎን ለጎንም የምርምር ሂደታቸው የማይታወቁ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ፣ መልካም የሆኑ ልምዶችን ለሌሎች ለማካፈልም ፋይዳ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

የጥናት ሥራዎቹ ሂደታቸውን ሲያጠናቅቁ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባላቸው ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ የሚደረግ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቀው ስኮፐስ ዳታ ቤዝ ላይ እንዲታተም የሚደረግ ይሆናል፡፡

ዶ/ር አዲስወርቅ እንዳሉት፤ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የሚያሠራቸው የምርምር ሥራዎች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ አልፈው ለማኅበረሰብ ችግር መፍትሔ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

 

አዲስ ዘመን  የካቲት 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You