የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚደረጉ ጥረቶች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል

 

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚያደርጓቸው ጥረቶች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሊቀርብ እንደሚገባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተር ናሲም ኦልማን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በቂ ድጋፍ መቅረቡ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

ዶክተር ናሲም አክለውም፤ የበለጸጉ ሀገራት ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በሚጥሩት የአፍሪካ ሀገራት ላይ የተለያዩ ተግባራትን ወደሥራ ለማስገባት እንቅፋት ይፈጥራል ብለዋል።

እ.ኤ.አ በ2009 በኮፐንአገን እንዲሁም ፓሪስ ስብሰባ ላይ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል መገባቱን አስታውሰው፤ በCOP28 ስብሰባ በርካታ አበረታች ተስፋዎችና ፕሮጀክቶች ይፋ ቢሆኑም ተፈጻሚነታቸው እምብዛም እንደሆነ ጠቁመዋል።

እ.አ.አ. በ2030 በየሀገራቱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አምስት ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ናሲም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም በየዓመቱ ከ215 እስከ 387 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ለታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት አራት ነጥብ ሶስት ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ተግባራዊ ለማድረግና የሚፈለገውን የፋይናንስ ክፍተት ለመቅረፍ አዲስ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠርና በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ በበለጠ ሁኔታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እየሠራ ነው ያሉት ዶክተር ናሲም፤ በቀጣይም የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግና ውጤቱን በመገምገም ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዶክተር ናሲም ገለጻ፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴው አሻራ መርሀ- ግብር በተለይም በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ላይ የድርቅ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚረዳ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ ኃይል የመጠቀም አማራጮች ለማስፋት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተፈጥሮን መሠረት ባደረገው የአረንጓዴ ሌጋሲ መርሀ ግብር ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቷን ማለትም ተፋሰሶችን እና ደኖችን በመጠቀም የመቋቋም አቅምን ለመገንባትና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

የአረንጓዴው ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ በተለይም በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ያሉ የድርቅ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እንደ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ሀገሪቱ የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ያተኮሩ ተጨማሪ ሥራዎችን እንድትጀምር ንፁህ የማብሰያ ምድጃዎችን በማዘጋጀት እና በማሰራጨት የቤት ውስጥ ብክለት ተጋላጭነትን የሚቀንስ መሆኑንም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ሌጋሲ ፕሮግራም የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋትና ዘላቂ ልማትን በማጎልበት ላይ ላበረከቱት በጎ አስተዋፅኦም እውቅና ተሰጥቷል ብለዋል።

የፓሪሱን ስምምነት ለማስማማት ዓለም አቀፍ ግብ ላይ ለሚሰሩ አፍሪካውያን ባለሙያዎች ECA ድጋፉን እንደሚቀጥል እና ግስጋሴውን ለመለካት መለኪያዎችን እንደሚያዘጋጅም ጠቅሰዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You