በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚኖረው ዝናብ የበልግ ምርቶችን አስቀድሞ ለመዝራት ያግዛል

አዲስ አበባ፡– በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚኖረው ዝናባማ የአየር ንብረት በበልግ ወቅት የሚለሙ ምርቶችን አስቀድሞ ለመዝራት የሚያመች መሆኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

እስከ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አብዛኛዎቹ የበልግ ሰብል አብቃይ እንዲሁም የአርብቶ አደርና የከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከቀላል እስከ መጠነኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

በአየር ትንበያው መሠረት የበልግ ሰብል አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች በተለይም በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናቶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

እርጥበቱ የተለያዩ ሰብሎችን አስቀድሞ ለመዝራት የሚያስችል በመሆኑ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት የዘር ግብዓት በማዘጋጀት የግብርና ሥራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አመላክቷል።

በተጨማሪም የሚገኘው ዝናብ ለግጦሽ ሳርና የውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁሞ፤ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪም ለገጸ ምድርና ለከርሰ ምድር ውሃ ሀብት መሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

በኦሞ ጊቤ ፣ የላይኛውና የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ፣ በአዋሽ አፋር ደናክል ፣የላይኛው ባሮ አኮቦ ፣ የላይኛውና የመካከለኛው ምሥራቃዊ ዓባይ ፣በጥቂት የላይኛው ተከዜ አካባቢዎች ፣በገናሌ ዳዋ እንዲሁም በዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እርጥበት እስከ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ሲል ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በተጨማሪ ከየካቲት 13-21 ቀን 2016 ዓ.ም የተሻለ የደመና ሽፋንና የተስፋፋ ዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ አመላክቶ፤ በደቡብ ምሥራቅ ፣ በምሥራቅ ፣ በሰሜን ምሥራቅ እንዲሁም በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።

ባለፉት አስር ቀናት በደቡብ ፣ደቡብ ምእራብ እንዲሁም በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ዝናብ ማግኘታቸውን አመላክቶ፤ የእርጥበት ሁኔታው ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላትና ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል አዎንታዊ ሚና እንደነበረው ኢንስቲትዩቱ አስታውሷል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን  የካቲት 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You