ያደጉ እና የአፍሪካ አገሮች የመሪዎች ስብሰባ እና ዲፕሎማሲ

አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ያደጉ አገሮች ከአፍሪካ አገራት ጋር የመሪዎች ስብሰባ ለማድረግ 55 የአፍሪካ አገር መሪዎችን ወደ አገራቸው የመጥራት አሰራር እየተካሄደ ይገኛል:: ለአብነት ያክል የቻይናና የአፍሪካ መሪዎች፣ የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች፣ የሩስያና የአፍሪካ መሪዎች ፣የጣልያንና የአፍሪካ መሪዎች፣ የህንድና የአፍሪካ መሪዎች እና የሳውዲ አረቢያና የአፍሪካ መሪዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ያደጉ አገራት በሚጠሩት ኮንፈረንስ አንዳንዴ እገሌ እና እገሌ የሚባሉ የአፍሪካ መሪዎች እንዳይመጡብኝ ይላሉ ወይም የስብሰባ ግብዣ አይደረግላቸውም:: ለአብነት ያክል አሜሪካ የአፍሪካ አገራትን መሪዎች ስብሰባ ስትጠራ የአንዳንድ አገራት መሪዎችን እንዳይሳተፉ አድርጋለች::

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ አንድ በኢኮኖሚ ያደገ አገር 55 የአፍሪካ አገሮችን ወደ አገሩ በመጥራት እንወያይ ማለቱ ተገቢ ነው? ወይስ የበላይና የበታች መገለጫ ነው? ይህ አይነት ስብሰባ የመሪና የተመሪ ስብሰባ አያስመስለውም ወይ? የሚለው ሀሳብ ላይ ለማጠንጠን ነው:: በእርግጥ ያደጉ አገራት ሀብት ስላላቸው ብቻ የሚፈልጉትን አገር መሪዎች ተሰብስባችሁ ኑ እና እንወያይ ማለት ሁለቱን ወገን በእኩል ደረጃ የማያስቀምጥ (Not Equal footing) መሆኑን ያሳያል:: አፍሪካ አህጉር እንጂ አንድ አገር አይደለም::

የፌዴራል መንግስት አወቃቀር ያለው አገር የክልል መንግስታት መሪዎችን ጠርቶ በዋና ከተማው የሚያደርገው ስብሰባ ዓይነት እነዚህ ያደጉ አገሮች የአፍሪካ አገራትን እንደ ክልል መንግስታቸው እየቆጠሩ የሚያደርጉት ስብሰባ ይመስላል:: በእርግጥ እነዚህ ያደጉ አገራት የአፍሪካ መሪዎችን ጠርተው ስብሰባ የሚያደርጉትና የገንዘብ ድጋፍ ቃል የሚገቡት ለጽድቅ ሳይሆን የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም በአፍሪካ ለማስጠበቅ ነው:: የአፍሪካ አገር መሪዎችም ከሚያገኙት የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ ጠሪ አገር በጋበዘው ስብሰባ አለመገኘት የሚያመጣባቸውን የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ጫና መቋቋም ስለሚከብዳቸው “ጠሪ አክባሪ” እያሉ ይሄዳሉ::

ሁለቱም ወገን በሚያደርጉት ውይይት የሚፈታ ችግር እንደሚኖር የሚጠበቅ ቢሆንም የሚፈጠር ችግርም ሊኖር ይችላል:: ለምሳሌ ሩስያ የአፍሪካ አገሮችን ጠርታ አቋም የሚያዝበት አጀንዳ ስታቀርብ ውሳኔው አሜሪካንን ላያስደስት ይችላል:: በተመሳሳይ አሜሪካ የአፍሪካ መሪዎችን ጠርታ የምታወጣው ውሳኔ ቻይናን እና ሩስያን ሊያስከፋ ይችላል:: በዚህ መሀል ሁሉም የአፍሪካ አገራት በትልልቅ ዝሆኖች መሀከል አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ:: የዓለም የፖለቲካ ውዝግብ ካለባቸው የዩክሬን እና የሩስያ፣የእስራኤልና ፍልስጤም፣ የታይዋን፣የሰሜን ኮርያ እና የመሳሰሉት አገራት አጀንዳ ጋር የተያያዙ ሲሆኑ የሚፈጥረው የዲፕሎማሲ ቀውስ ከባድ ሊሆን ይችላል::

እንደ አሜሪካ ያሉ ሃያላን አገራት ወሳኝ የሆኑ አጀንዳዎች ላይ ከእኛ ጋር ወይስ ከእኛ ተቃራኒ (You are either with us, or against us) የሚል አቋም ያራምዳሉ:: ይህን መሰል አጀንዳ የአፍሪካ አገራትንም ሊከፋፍል ይችላል:: አፍሪካ በአንግሎፎን እና ፍራንኮፎን በሚል በቋንቋ የመከፋፈል፤ የአረብ ሊግ አባል የሆነና ያልሆነ፡ የቆዳ ቀለማቸው ነጭ የሆነ እና ጥቁር የሆነ የአፍሪካ አገሮች እና የመሳሰሉ አርቴፊሻል ክፍፍል በመፍጠርም አፍሪካ በአንድነት እንዳትቆም ያደርጋሉ::

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ይህ አይነት ጥሪ በሌሎች ያደጉ አገሮችም በተከታታይ ሊጠራ እንደሚችል መገመት ይቻላል:: በመሆኑም ጣልያን ሁሉንም የአፍሪካ መሪዎች እንደጠራችው ሁሉ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት፣ የእስያ አገራት፣ አረብ አገራት ወዘተ የአፍሪካ መሪዎችን በሙሉ ኑ እና እንወያይ ማለታቸው እንደሚቀጥል መጠበቅ ያስፈልጋል:: ይህ አይነት አቻ ያልሆነ የመሪዎች ስብሰባ ጥሪ ሲቀጥል ሃያና ሰላሳ የሚሆኑ የአደጉ አገራት ሁሉም የአፍሪካ መሪዎችን ኑ ወደ መዲናዬ ማለታቸው አይቀርም::

የአፍሪካ መሪዎች የራሳቸውን በርካታ ስራ ትተው የአደጉ አገሮችን ብሄራዊ ጥቅም ሲያሳኩ የሚኖሩበት ሁኔታ ይፈጥራል:: እንዴት ነው አንድ አገር ከአንድ አህጉር ጋር በአቻ እንዲወያይ የሚፈቀደው? ይወያይ ከተባለም አንድ ያደገ አገር ወደ 55 አገራት የያዘችው አፍሪካ ይመጣል እንጂ እንዴት ተሰብስባችሁ ኑ ይላሉ:: ይህንን ለማካካስ ይመስል አንዳንድ የመሪዎች ስብሰባ በአፍሪካ አገር በተራ ሲከናወን ይታያል::

ይህንን አሰራር ኢትዮጵያን በዓለም ሁለተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ አዲስ ትርክት(Narrative) መፍጠር ያስፈልጋል:: ይህ አዲስ ትርክት ያደጉ አገሮች የአፍሪካ አገሮች ጋር የመሪዎች ስብሰባ ማድረግ ከፈለጉ እነርሱ ወደ አፍሪካ ይምጡ፤ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ደግሞ አዲስ አበባ ስለሆነ ከዚህ በኋላ 55 አገሮች ወደ አንድ አገር የሚሄዱበት ሳይሆን አንድ የበለጸገ አገር ወደ በርካታ አገሮች የያዘችው አፍሪካ ይምጣ ማለት ያስፈልጋል::

ይህ አቋም የአፍሪካ ሕብረት አቋም እንዲሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይጠይቃል:: ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል በመሆኗ የመሪዎችን ስብሰባ ተራዋ ሲደርስ በአዲስ አበባ ማከናወኗ የማይቀር ነው:: እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የጂ 20 (G20) አባል በመሆኑ ተራው ሲደርስ ሕብረቱ ስብሰባውን ማድረጉ አይቀርም:: ሆኖም የሕብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ስለሆነ የጂሀያ (G20) በመዲናችን እንዲከናወን የዲፕሎማሲ ስራ ቀድሞ መስራት ያስፈልጋል::

የዲፕሎማሲው ስራ አካል ውስጥ አንዱ የአፍሪካ ሕብረት የራሱ የሆነ የውጭ ፖሊሲ ሰነድ እንዲኖረው መስራት ወይም አጀንዳ ማራመድ:: ከዚያም 55 የአፍሪካ አገራት በጋራ ለሚያከናውኗቸው የመሪዎች ስብሰባ ከተቻለ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ አልያም በአንዱ የአፍሪካ አገር ውስጥ እንዲሆን ውሳኔ እንዲተላለፍ መስራት ያስፈልጋል:: ይህንን ሀሳብ ማራመድ አንድ ያደገ አገር ከ55 የአፍሪካ አገራት ጋር አቻ አለመሆኑን ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር “ከፈለጋችሁን እኛ ጋር ኑ” የሚል መልዕክት ያለው ነው::

ያደጉ አገራት ሁሉንም የአፍሪካ መሪዎች ወደ አገራቸው የሚጠሩበት ዋና ጉዳይ የብሄራዊ ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ ባሻገር ወደ 55 አገራት ልዑካን እየላኩ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት የገንዘብና የጊዜ ብክነትን እንዲቆጥብላቸውም ነው:: በተቃራኒው የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ አደጉ አገሮች ሲሄዱ ከጉዞ ጋር በተያያዘ የጊዜና የወጪ ጫና ይኖርባቸዋል:: ለአደጉት አገራት ደግሞ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲያከናውኑና ገቢ እንዲያገኙ እድል ይሰጣቸዋል::

አሁን አንድ በኢኮኖሚ የየተሻለ የአፍሪካ አገር ሁሉም የአውሮፓ አገር ጋር ፎረም መስርቼ የመሪዎች ስብሰባ አደርጋለሁ ብሎ ወደ ዋና ከተማው ቢጠራቸው መሳለቂያ ከመሆን ባሻገር አንዱም ዝር አይልም:: ይህ ታዲያ ተገቢ ነው? በአፍሪካ ላይ የተደረገው የባሪያ ንግድ ፣ የቅኝ ግዛት ሰቆቃ፣ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ሳይበቃን በመሪዎች ስብሰባ ስም ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚደረገው ስራ ዙሪያ አዲስ ትግል ያስፈልጋል::

ከአደጉት አገራት የሚገኝ የገንዘብና ሌሎች ጥቅሞች ሳይቋረጡ የአሰራር ሂደቱ እንዲስተካከል ማድረግ ያስፈልጋል:: ከላይ እንደተጠቀሰው መሆን ካለበት ያደጉ አገራት ወደ አፍሪካ መዲና ይምጡ አልያ አቻ የሆነ አሰራር አለመሆኑን ማሳወቅ የአፍሪካ ሕብረት ተግባር ሊሆን ይገባል::

የአውሮፓ ሕብረት የአህጉሩ የውጭ ፖሊሲ አለው:: ሁሉም የሕብረቱ አባል አገራት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ከሌላ ወገን ጋር ይደራደራሉ:: የአፍሪካ ሕብረት ግን ይህንን መሰል የአህጉር ፖሊሲ ስለሌለው ሁሉም እየተነሳ ስብሰባ ጠርቻለሁ ተሰብስባችሁ ኑ ይሏቸዋል:: ፖሊሲ መኖር አሰራር ወጥ እንዲሆን ያግዛል፤ የጋራ አቋም ለመያዝ ከመርዳቱ በተጨማሪ በመሪዎች ስብሰባ አንዱ አስተማሪ ሌላው ተማሪ የሚሆንበት አሰራር አይኖርም::

አፍሪካን በዚህ ደረጃ የሚፈልጓት ከሆነ ለምንድነው በተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የማይፈቅዱት? በተለያዩ መድረኮች ላይ ይህንን መቀመጫ መስጠት እንደሚገባ ይናገራሉ እንጂ መፈፀም አይፈልጉም:: በተመሳሳይም እነሱ የሚመሩት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማለትም የዓለም ባንክ፤ አይኤምኤፍ እና ወዘተ ተቋማት በአፍሪካ ላይ የሚፈጥሩት ጫናና ጣልቃ ገብነት (structural adjustment) የመሪዎችን ነጻነት የሚጋፉበት ሁኔታ ከፍተኛ ነው::

ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች ለስብሰባ ሲሄዱ በጋባዥ አገር የሚደረግላቸው እንክብካቤ ለአንድ መሪ የሚመጥን ነው ወይ? ብለን መጠየቅም ተገቢ ነው:: በእንግሊዟ ንግስት ቀብር ለመሳተፍ ወደሎንዶን የሄዱ የአፍሪካ መሪዎች በአውቶቡስ ገብተው እንዲሄዱ መደረጉና የእኛ ክብርት ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ግን በዚህ መልኩ አልጓዝም የአንድ ሉአላዊ አገር መሪ ነኝ በማለት ተቃውሞ ገልጸው እርሳቸው በፈቀዱት የክብር መኪና እንደተጓዙ የሚያሳይ ዜና በስፋት ሲሰራጭ ነበር::

ይህ ቀላል መልዕክት አይደለም:: የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ከሆነው “ክብርና አቻነት” ጋር በጣም የተያያዘ ነው:: አፍሪካ የብዙ ደሀ አገሮች የሚገኙባት አህጉር ብትሆንም እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር መሰጠት ያለበት ክብር ለአገሮች መኖር ተገቢ ነው:: የሉዓላዊነት መለኪያው ድህነት ወይም ሃብት አይደለም::

የአደጉ አገራት ከአፍሪካ ጋር በጋራ እንስራ ሲሉ የፎረም ስያሜ በማውጣት ነው:: የአንድ ፎረም ስያሜ ሲወጣ አገርን ነው ወይስ አህጉርን ማስቀደም ያለበት:: ለምሳሌ “ጣልያን – አፍሪካ” የመሪዎች ስብሰባ ነው መባል ያለበት ወይስ “አፍሪካ – ጣልያን” የመሪዎች ስብሰባ መሆን ያለበት:: ሁለተኛው አማራጭን መጠቀም ተገቢ ነው:: ምክንያቱም አፍሪካ አህጉርና 55 አገሮች የያዘች እንጂ አንድ አገር የያዘች አይደለችም:: በመሆኑም የመሪዎች የስብሰባ ፎረም ላይ የአፍሪካ ስም ቀድሞ እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል::

ያደጉ አገሮች የአፍሪካ መሪዎችን ለስብሰባ ሲጠሩ አንዳንድ አገሮች ላይ የሚያከናውኑት የማግለል ተግባር ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምንም ካላሉ ተቀብለውታል ወይም አጽድቀውታል ማለት ነው:: ለምሳሌ አሜሪካ ከእነዚህና ከእነዚያ አገራት በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተጋብዛችኋል ይላሉ:: የተጠሩት መሪዎች ተሰባስበው ሲሄዱ እንዳትመጡብኝ የተባሉ አገር መሪዎች ስሜታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ብዙም አያስቸግርም::

ከአፍሪካ ጋር የሚደረጉ የመሪዎች ስብሰባ በተዘዋዋሪም ቢሆን አንዱ የአፍሪካ አገር እንዲገለል ሌሎች የአፍሪካ አገራት ትብብር አሳይተዋል ማለት ያስችላል:: ለምንድነው ሁሉም የአፍሪካ አገር ለኮንፍረንስ ሲጠራ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ላይ የዲፕሎማሲ ጫና የሚፈጠረው? የአፍሪካ መሪዎች እንደ አህጉር ማሰብ ትተው እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር መሪ ብቻ ሆነው ማሰብ ስለቻሉ ይመስላል:: ይህ አይነት አሰራር ያደጉት አገራት አፍሪካዎችን አንድ እንዳይሆኑ የሚከፋፍሉበት ስውር እጅ ከመሆኑ ባሻገር የሁለቱም ወገን አቻ ያለመሆንና የዲፕሎማሲ ዝንፈት ነው:: ይህንን ዝንፈት ማቃናትና ማሻሻል የአፍሪካ መሪዎችና የአፍሪካ ሕብረት ስራ ነው::

ለማጠቃለል ያህል ያደጉ አገራት ከ55 የአፍሪካ አገራት ጋር ፎረም በመመስረት “የጋራ” ኮንፍረንስ ማከናወናቸው ላይ አፈጻጸሙ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ለማሳየት ተሞክሯል:: ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የፎረሙ ስያሜ አፍሪካን በሁለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ መሆኑ፣ በርካታ አገራት ወደ ያዘችው አፍሪካ ከመምጣት ይልቅ ወደ አገራቸው የመጥራት አሰራር መኖር፣ የማይፈልጓቸውን አፍሪካ አገሮችና መሪዎች የሚያገሉበት መሆን፣የራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ፣ እነርሱ በአፍሪካ መሪዎች ተሰብስበው ወደ አንድ አፍሪካ አገር እንዲመጡ ቢጠሩ የማያደርጉትን በአፍሪካ አገሮች ላይ እያደረጉት መሆን፣ የመሪዎችን ክብር በጠበቀ መልኩ ያለማከናወን አብነቶች መኖርና ወዘተ ጉዳዮች ይገኛሉ::

ለዚህ መፍትሄው የአፍሪካ አገራት በጋራ ጥቅሞቻቸው ላይ በጋራ በመቆም የሚከፋፍሉ ጉዳዮችን ማስወገድ፣ የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ እንዲኖረው በማድረግ በመርህ መመራት፣ ሁሉንም የአፍሪካ አገራትን የሚጠቅም አጀንዳ እና ፕሮግራም አለኝ የሚል አገር በአፍሪካ ሕብረት በተቀመጠው አጀንዳ 2063 ውስጥ ሚና እንዲጫወት ከሕብረቱ ጋር እንዲሰራ ማድረግ ተገቢ ነው::

መላኩ ሙሉዓለም ቀ.

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዪት የሥልጠና ዳይሬክተር ጀነራል

melakumulu¬@yahoo.com

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

 

Recommended For You