ዓለማችን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተመለከተቻቸው እጅግ ተፅዕኗቸው ጎልቶ ከሚታይ የከተማ ፕላነሮችና አንዱ ለመሆኑም በርካቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ አሜሪካዊ ነው፡፡ ሮበርት ሞሰስ ይባላል፡፡ ‹‹ዘ ማስተር ቢልደር /Master Builder›› በሚል ቅፅል ስሙ ይበልጥ ይታወቃል፡፡
እኤአ በ1888 የተወለደው ይህ ሰው አንድ ከተማ በርካታ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ከመደርደር ይልቅ በዛፍ የተከበቡ ምቹ ጎዳናዎች፣ ፓርኮችንና ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የከተማ ልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች ሊኖራት እንደሚገባ በማመንና በማሳመን የአሜሪካዋን ኒውዮርክ ከተማ በሃሳብና በራዕዩ ልክ ገልብጦ እንደሠራት ብሎም ለክቶ እንደሰፋት ይታመናል፡፡
ሞሰስ ኒውዮርክ ከተማን የግል ሃሳቡንና ፍልስፍናውን በሚያንፀባርቅ መንገድ መገንባት ሲያስብ አንስቶ በግንባታ ሂደት ላይ እያለም የበርካቶች የቅሬታ አስተያየት ተለይቶት አያውቅም። ፓርክ ‹‹ምን ያደርጋል›› የሚሉም በርካቶች ነበሩ። ሰውየው ግን ሠርቶ ማሳየትን ብቻ ምርጫው በማድረግ የሚወረወርበትን ድንጋይ እንደጡብ በመደርደር ኒውዮርክ ከተማን በሃሳብና በራዕዩ ልክ እውን ከማድረግ ያስቆመው አልነበረም፡፡
ከትናንት እስከ ዛሬ በከተማ መሃል የሚገኙ መናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች ከሚሸፍኑት መሬት አንፃር በተለይ የመሬት ጥበብ ባለባቸው ሀገራት ‹‹መተግበር የሌለበትና ቅንጦት ነው›› በሚል የሚነሱ ጥያቄዎች ብሎም ቅሬታዎች እዚህም እዚያም ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡
የዘርፉ ምሁራን እንደሚገልፁት ከሆነ ግን፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም ጥግግቱ ከፍ ያለ ወደ ጎን ከማስፋት ይልቅ ወደ ላይ የሚሰፋ ከተማን በማዋቀር በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሕዝብ ማስፈርን አማራጭ አድርጋለች፡ ይህ አማራጭ ደግሞ ከተሞች ለመናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ቦታዎች ሰፊ ቦታ ቢሰጡም እንዳይጨናነቁ አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ደግሞ ከኒውዮርክ በላይ አይገኝም፡፡ ዓለም ላይ ኒውዮርክ ከተማ በጥግግት ከሚታወቁ ከተሞች ግንባር ቀደም ሆና ትጠቀሳለች፣ ይሁንና በዓለማችን ትልቁ ሴንትራል ፓርክና 341 ሄክታር የሚሆን ክፍት ስፍራ የሚገኘው በዚህች ከተማ ነው፡፡
‹‹የፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎችን ፋይዳ ከሚሸፍኑት መሬት አንፃር መመልከት ከባድ ስህተት ነው›› የሚሉት የዘርፉ ምሁራን፣ ይህን በቅጡ መረዳት የሴንትራል ፓርኩን አመታዊ ጉብኚዎችና ገቢ ማወቅ በቂ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ፡፡ Central Park. Com በሚል ገፅ ላይ እንደተመላከተውም፣ ሴንትራል ፓርክ እኤአ በ2023 ከዓለማችን ድንቅ 50 መዳረሻዎች መካከል በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በአመቱም 37 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጎብኚዎችን አስተናግዷል፡፡
በእርግጥም መናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች ጨምሮ አንድን ከተማ ትራንስፎርም የሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ትርጉም እጅጉን ግዙፍ ነው፡፡ ከማኅበራዊ መስተጋብር አንፃር በተለይ በአሁኑ ወቅት ግላዊነት የጎላበትን የማኅበራዊ ግንኙነት ፈር በማስያዝ የጋራ ማኅበራዊ እሴትን ለማጠናከር የሚኖራቸው ፋይዳ በቀላሉ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ ከሕፃን እስከ አዛውንት ለሁሉም ክፍት እንደመሆናቸውም በአጠቃላይ ጤናማና ደስተኛ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሁነኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡
የከተማ መናፈሻና ክፍት ስፍራዎች የመዝናኛ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ የሁለንተናዊ ሃሳብ መነሾ ስለመሆናቸውም በርካቶችን የሚያስማማ ሃቅ ነው። ‹‹ግሪካውያን ለዓለም ያበረከቷቸውን በርካታ የፍልስፍናና ሌሎች እውቀቶች የፈለቁት በአረንጓዴ ክፍት ስፍራና መናፈሻዎች ተሰባስበው በመወያየት በመማማራቸው እንደሆነ የሚመሰክሩም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከኢኮኖሚ አንፃር በተለይ ከመስህብነት አንፃር የበርካታ ቱሪስቶች መናኸሪያ በመሆን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መነቃቃት ብሎም እድገት፣ ለቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተደራጀ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጨምሮ ለሁለንተናዊ እድገት ፋይዳቸው ጉልህ ነው፡፡ ከፖለቲካ መስተጋብር አንፃርም ‹‹ለኑሮ የምትመች ከተማ›› የሚል ስምና ዝናን ከፍ በማድረግ ተፅእኖ ፈጣሪነትን የማግዘፍ አቅማቸው እጅጉን ከፍተኛ ስለ መሆኑም የማይካድ ነው፡፡
ባለፉት አመታት በርካታ የዓለማችን ከተሞች እድገት ሕንፃ መደርደር አለመሆኑን ከሮበርት ሞሰስ ራዕይና አላማ እንዲሁም ስኬት በመረዳት እድገትና ፕላናቸውን ከፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች መስተጋብር ጋር አስተሳስረው ለመሄድ ብዙ ሠርተዋል፡፡ የተቀናጀ የከተማ ክልል ልማትን እውን ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል፡፡ በጥረታቸው ልክ የተሳካላቸውም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። አንዳንዶች በተለይ በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በአንፃሩ መሰል ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ካለው የከተማ ልማት ትግበራ ጋር በአግባቡ ለመተዋወቅ አመታትን መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጨርሶ አልተዋወቁም፡፡
የአፍሪካ መዲና የሆነችውና በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የምታስተናግደው መዲናችን አዲሰ አበባም ስሟን፣ ዝናዋንና የዕድሜ ርዝማኔዋ በሚመጥን መልኩ መናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች ጨምሮ አንድን ከተማ ትራንስፎርም የሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች አላት ከማለት የላትም ለማለት ቀላል ሆኖ አመታት አስቆጥራለች፡፡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ሆነ እንግዶች ውስጣዊ ስሜታቸውን የሚያዳምጥበትና አዕምሯዊ ዕረፍት የሚያገኝበት ብሎም የሚዝናኑበት ውብና ንፁሕ መናፈሻዎችና አረንጓዴ ስፍራዎችን ማግኘት ተቸግረው ረጅም አመታት ለማሳለፍ ተገደው ቆይተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በአንፃሩ ስሟ ብቻ አዲስ ሆኖ መቶ ዓመታትን የዘለቀችን አዲስ አበባ፣ ስሟን በሚመጥን መልኩ ተወዳዳሪና ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ ለጎብኚዎች አማላይ ከተማ ለማድረግም የተለያዩ ፕሮጀክት እውን አድርጓል፡፡ እውን ከሆኑት ባሻገር በሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም ከተማዋን ዳግም የሚወልዱ ናቸው፡፡
በመዲናዋ እውን የሆኑ ፕሮጀክቶች፣ አሁን ላይ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ አውድ ጉልህ አስተዋፅኦ ማምጣት እንደሚችሉ በተጨባጭ እያስመሰከሩ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ረገድ በአግባቡ ከተሠራባቸው የገቢ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም አያጠያይቅም፡፡ በሥራ ፈጠራው ወቅታዊውን የሀገሪቱ ራስ ምታት እያቃለሉም ናቸው፡፡
ሜጋ ፕሮጀክቶቹ የሀገሪቷንና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ ገጽታ ለውጠዋል፡፡ ሁሌም እነዚህን ሥፍራዎች የሚያይ ዓይን (Eyes on the Street) አለና ለመዲናዋና ለእንግዶቿ ቀዳሚ አማራጭና መዳረሻ ከመሆን ባለፈ ባለፈ ቱሪዝምን ከማጐልበት አኳያ በገሃድ የሚታይ ትሩፋት አምጥተዋል፡፡
ከኢኮኖሚ አበርክቶ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት በቱሪዝሙ ዘርፍ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ቱሪስቶች በተለያዩ መንገዶች ከ55 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከቀናት በፊት ‹‹አወቁልኝ›› ብሎናል፡፡
ሜጋ ፕሮጀክቶቹ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ምርጫና መዳረሻ በመሆን የከተማነት ሁለንተናዊ እድገት የሚያሳልጡ ብሎም የሚያደምቁ ሆነው እያየናቸው ነው፡፡ በተለይ ማታ ላይ እንቅስቃሴ የምታቆመውንና ወደ ጭለማ የምትቀየረውን ከተማ፣ 24 ሰዓት የደመቀች እንድትሆን አስችለዋታል፡፡ የተለያዩ ጥበባዊ የሆኑ አውደ ራእዮችን ኮንሰርቶችና የቲያትሮች ዝግጅቶች የሠርግ ፕሮግራሞችን ለማካሄድ የከተማዋ ቀዳሚ ተመራጭ ስፍራ ሲሆኑ እያየን ነው፡፡
ስመጥር የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልና የሚያድግ ኢኮኖሚ የመገንባት ተስፋ በተጨባጭና በእጅ ባለ እምቅ ሀብት ላይ መመስረት ይኖርበታል። በእጅ የሌለ የማይጨበጥ ነገር የሀገርን ኢኮኖሚ ለመመስረት መሞከር ባሕር በሌለበት ዓሣ ለማጥመድ ከመመኘት አይለይም።
ይህ በአምራች ዘርፉ ካየነው የአግሮ ፕሮሰሲንግስ ወይንም የግብርና ምርቶች በማቀነባበር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚሹ ሀገራት በግብርና ዘርፍ በእንስሳትም ሆነ በአትክትልና ፍራፍሬው በተጨባጭ እጅ ያለ ዕምቅ በተለይም ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት፣ ብቁ ሙያተኛና ፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና የውሃ ሀብት ሊኖራቸው ግድ ይላል እንደ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከግብርናው ባሻገር በተጨባጭ እጅዋ ላይ ያሉ የብልፅግናዋ መሠረት የሆኑ ሀብቶች አላት፡፡ ከእነዚህ አንዱም ቱሪዝም ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ከግብርናው የሚለየው ሊለማ በሚችልበት ልክ ያልለማና ዘርፉ ሊሸከመው በሚችለው ልክ ዜጎች ተሰማረተው እየኖሩበት ያለመሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንደዘርፍ ትኩረት ስቦ በተቋም መመራት ከጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም ገና ያልተነካና በእምቅነት ደረጃ ያለ ነው ማለት ይቻላል። አጠቃላይ ኢኮኖሚውንም ትራንስፎርም የማድረግ አቅም ግዙፍ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው በርካታ ሀገራት በተፈጥሮ የታደሉ ከሆኑ፣ ለዓለም የሚያሳዩት እጅግም ሰፊ ታሪክ አይኖራቸውም፡፡ አንዳንድ የድንቅ ታሪክ ባለቤት የሆኑ ሀገራት ደግሞ፣ እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሀብትና ውበት ባለቤቶች ሆነው አይገኙም፡፡ ኢትዮጵያችን ግን በዓለማችን ድንቅ ታሪክን፣ ተፈጥሯዊ ውበትንና ባህላዊ ፀጋዎችን በገፍ ታድለው ከተጎናፀፉ ውሱን ሀገራት መካከል የምትመደብ ናት፡፡
ኢትዮጵያ ውበት ተመልካች አጥቶ ገረጣ እንጂ አልሞተም፡፡ አቧራ ተጭኖት ደበዘዘ እንጂ ከነጭራሹ አልጠፋም፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ሊወጡ የሚችሉ ብዙ አስደማሚ የውበት ፀጋዎችን ታድላለች፡፡ ሀገራችን ጥበበኞች በአድናቆት የሰላ ብዕራቸውን ቀለም የሚያንቆረቁሩባት፣ ተአምራትን መፍጠር የሚያስችል እምቅ ውበት ባለቤት ናት፡፡
ሀገሪቱ ወደ ሀብት ሊቀየሩ የሚችሉው በርካታ ሀብቶች ቢኖራትም፣ ሀብቶቿን ከተደበቁበት የሚያወጣላት ግን ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ‹‹ይህን መቀየርና ኅብረተሰቡንም ሀገርንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል›› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) ከሸገር ፕሮጀክት፣ የአንድነት ፓርክንና የእንጦጦ ፓርክን እውን ለማድረግ ቀጥለው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስተዋውቀዋል፡፡
የሸገር ፕሮጀክቶችን ወደ ክልሎች ለማስፋፋት፣ ሁሉም ከኢትዮጵያ ሀብቶች ተቋዳሽ የሚሆንበትን ዕድል ለማመቻቸት ያለመና ‹‹ገበታ ለሀገር›› የተሰኘ ፕሮጀክት በሀገሪቱ በተለያዩ ሥፍራዎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ ተግባራዊ አድርገዋል። በመልክአ ምድር አቀማመጡና በተፈጥሯዊ ውበቱ፣ መንፈስን በሚያድሰው ምቹ አየሩ እና አፍን በእጅ የሚያስይዝ ምትሃታዊ የውበት ጥግነቱ የሚታወቀው የወንጪ ሐይቅ፣ በመንግሥት የገበታ ለሀገር ከለሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሚገኙ መስሕቦች ሁሉ በመልከዓ ምድራዊ ውበቱ፣ ልብን በሐሴት በሚሞላው አስገራሚ የተፈጥሮ ፀጋና ሀብቱ በቀዳሚነት የሚቀመጠውና ‹‹የአፍሪካ ስዊዘርላንድ» በሚል ቅፅል ስሙ በጎብኚዎች ዘንድ የሚታወቀው የወንጪ ሐይቅ፣ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መሥጠት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
የእነዚህና ሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ታዲያ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አቅም ይበልጥ በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውንም ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሁለንተናዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም። ይሁንና የቱሪዝም ተስፋ እንዲሰምር የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመፍጠር ባሻገር መሰል ድንቅ ሀብቶችን ከተደበቁበት እንደማውጣት ሁሉ ከሀብቱ በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ ስለመሆን መጨነቅም የግድ ነው፡፡
ቀጣዩን የሀገሪቱ የቱሪዝም ኢኮኖሚ የተሸከመው ባቡር እጅጉን ግዙፍ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ እንደ መነሻው ሁሉ መድረሻው ከፍ ያለ ስፍራ ስለመሆኑን ከወዲሁ እያስመለከተ ይገኛል፡፡ ይህ እስከሆነም በትንሹ ሳይሆን በትልቁ ማሰብና ማቀድ እንዲሁም መሥራት የግድ ይላል፡፡
በእነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች ምክንያት የባህልና የቱሪዝም ቁሳቁሶችን ለገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ፣ ጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች ከፊታቸው ትልቅ መና እየጠበቃቸው ነው፡፡ ስለሆነም ይህን መና በአግባቡ ስለመቋደስ ከወዲሁ ዝግጅታቸው ጨርሰው ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ የሀገርም ሆነ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እነዚህን መዳረሻዎች ቀዳሚ ምርጫ ከማድረግ ባለፈ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ተግቶ መሥራት ይገባል፡፡ ይህ ግን ቀላል ሥራ አይደለም። መስጠትን አቅዶ ማልማትን ይጠይቃል።
የክልልና የከተማ አስተዳደሮችና በተለይ የቱሪዝምና የኢንቨስትመን፣ የመሠረተልማትና ሌሎችም ተቋማት ይህን ግዙፍ ኢኮኖሚ ተሸክሞ የመጣ ባቡር በአግባቡ ስለመጠቀም በፅኑ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የቤት ሥራም ከነገ ሳይሆን ከዛሬ የሚጀምር መሆኑም ጠንቅቀው መረዳት ግድ ይላቸዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትም ዘርፉ እንደ ቀድሞው በልምድ ሳይሆን በእውቀት የሚመራበትን መንገድ መቀየስ እና የሰለጠኑ ሙያተኞች ዘርፉን የሚቀላቀሉበት ብሎም ለሁለንተናዊ ለውጥና አበርክቶቱ አጋዥ የሚሆኑበትን ድልድይ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡
ጉዳዩ ከብሔራዊ ጥቅም National Interest ጋር የሚቆራኝ እንደመሆኑ ከፖሊሲ ማዕቀፍ እስከ ትግበራ እነዚህን የቱሪዝም አቅሞች የበለጠ ለመጠቀምና ሀገርን ለተቀረው ዓለም ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት ብሎም የግልም ሆነ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መዘንጋት አይኖርባቸውም፡፡
በመንግሥት በኩል ሰላምን ማረጋገጥ ጨምሮ የመሠረተ ልማት፣ የተፈጥሮና የባህል ቅርሶችን መንከባከብና ማልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የላቀ ማድረግ፣ የባህልና የቱሪዝም የመረጃ ሥርዓትን ማሻሻልን ጨምሮ የልማት አጋሮችን በማቀናጀት የተለያዩ ተግባራት መከወን ሊዘነጋ አይገባም፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ የግል ባለሀብቶች የመንግሥትም ይሁኑ የግል ባንኮች ብድር የሚያመቻቹበት ሁኔታም ሊፈጠር ይገባል፡፡ ከከተማ እስከ ሀገር በሚዘልቀው ቀጣዩ ግዙፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባቡር ለመሳፈርና ከምንሻው እድገት ለመድረስም፣ ሁሉም አካላት ከወዲሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ በቅንጅት ሊሠሩ የግድ ይላል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም