ምሥራቅ አፍሪካውያን አርብቶአደሮችን ይበልጥ ያወዳጀው መድረክ

ድንበርም ሆነ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድ መድረክ ተገናኝተው መክረዋል፤ ዘክረዋል። ሁሉም የየሀገሩን ባህል፤ ልምድና ተሞክሮ ለሌላው ለማሳየት በባህላዊ አልባሳቱ አምሮና ደምቆ በመሰየም ጉርብትናውን አጥብቆ አስተሳስሯል፡፡ የመድረኩ አዘጋጅ የሆነችው ኢትዮጵያም በማይነጥፈው ባህሏ በብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ውዝዋዜ እና ጭፍራ ታጅባ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንግዶቿን ተቀብላለች፡፡

አፍሮዎቹ አፋሮች ባገለደሙት ሽርጥ ላይ ጊሌያቸውን እንደሰኩ ክብ ሠርተው ከታች ወደላይ እየዘለሉ ጨፍረዋል፡፡ ከወዲያ ደግሞ የቦረና ኦሮሞ ሴቶች እልልታቸውንና ማራኬ ሀገርኛ ዜማቸውን ለጉድ በሚያሰኝ መልኩ አንቆርቁረውታል፡፡ ዓይናፋሮቹ የሶማሌ ሴት አርብቶአደሮች ደግሞ ግማሽ ጨረቃ በምትመስለው የሳር ጎጇቸው ውስጥ ሆነው ጎብኚውን በሚማርክ አቀራረብ ያመጡትን ባህላዊ ቁሳቁስ እንደ ዕጣን ያሉ ምርቶችን ለዕይታ አቅርበው አስተዋውቀዋል፡፡

ይህ ሁሉ ትዕይንት የቀረበው ታዲያ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ እንዲሁም የመጀመሪያውን ቀጣና አቀፍ የአርብቶአደሮች ቀን ከጥር 17 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀችበት ወቅት ነበር። ለወትሮ የኢትዮጵያ አርብቶአደሮች ብቻ ይሳተፉበት የነበረው የአርብቶአደሮች ቀን በዓል ዘንድሮ በዓይነቱም፤ በዝግጅቱም ለየት ባለ መልኩ ነው የተሰናዳው፡፡

በዝግጅቱም ቁጥራቸው ከ300 የሚልቅ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አርብቶአደሮች፤ የመንግሥት አመራሮች፤ ዲፕሎማቶችና ምሁራን ታድመውበታል። ዝግጅቱን ልዩ ካደረጉት መርሐግብሮች መካከልም በአህጉራዊና ቀጣና አቀፍ የአርብቶአደሮች ጉዳይ ላይ ያጠነጠኑ ውይይቶች፤ የየሀገራቱ አርብቶአደሮች የሚጠቀሙባቸውን ባህላዊ ምግብና መመገቢያዎች፤ የእርሻ ቁሳቁስና አልባሳትን የመሳሰሉትን የሚያሳዩበት ኤክስፖና ባዛር እንዲሁም ጥዕሙ ዜማ፤ ማራኪ ጭፈራ የሚያሳዩባቸው መድረኮች ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

የዩጋንዳዋን ካራሞጃ የአርብቶአደሮች መንደር ማኅበረሰብ ወክለው ከተገኙ ዩጋንዳውያን መካከል ስቴባኒያ ኢማኑኤል አፓ ሎሊናኛ አንዱ ነው፡፡ እሱና የሥራ ባልደረቦቹ በኢጋድ ጋባዥነት ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአርብቶአደሮች በዓል ላይ የመታደም ዕድሉን በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ የፈጠረላቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ በተለይም ደግሞ በኤክስፖው ላይ ከተለያዩ ሀገራት በመጡ አርብቶአደሮች በቀረቡት መሰናዶዎች ትልቅ ትምህርት መውሰዱን፤ ወደ ሀገሩም ሲመለስ የቀሰመውን ልምድና ተሞክሮ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳሳት የፈጠረለት መሆኑን ያስረዳል፡፡

እንደ ዩጋንዳዊው አርብቶአደር ገለፃ፤ እሱ የሚኖርባት ካራሞጃ የተሰኘችው ቆላማ አካባቢ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብት ሀብት ያላት ሲሆን፣ በየአመቱ 20 በመቶ የሚሆነውን የቀንድ ከብት ዩጋንዳ ለገበያ ታቀርባለች፡፡ በተጨማሪም ከ50 በላይ ማዕድናትና በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ ይሁንና ሕዝቡ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ አልሆነም፡፡

ካራሞጃ ለደብቡ ሱዳንና ኬንያ አዋሳኝ በሆነ ሥፍራ ላይ ትገኛለች፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶአደርነት መተዳደሪያ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትና ማረጋገጫና ባህላዊ ሥርዓትም ጭምር እንደሆነ ያነሳል፡፡ በኤክስፖ ላይ የዩጋንዳውያንን አርብቶአደር ባህል የሚሳዩ ቁሳቁስ ይዘው በመገኘት ለቀሪው የቀጣናው አርብቶአደር ማስተዋወቅ የሚያስችሉ መሰናዶዎችን ማቅረባቸውን ይገልፃል፡፡

‹‹በዩጋንዳ አርብቶአደርነት እውቅና አልተሰጠውም፤ ፖሊሲ የለንም›› የሚለው አርብቶአደር ስቴባኒያ፤ ከረጅም አመታት በፊት ሕጉ ቢረቅም የሀገሪቱ ምክር ቤት እንዳላፀደቀው ያስረዳል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሕግ እንዲፀድቅና ሥራ ላይ እንዲውል የአርብቶአደሩ ማኅበረሰብ ሲሞግት መቆየቱን ያመለክታል፡፡ ሕጉ ባለመፅደቁ ምክንያት ማኅበረሰቡ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን፤ ይህም ሁኔታ የመንግሥት አካላትም በቂ ትኩረት ሰጥተው ክትትልና ድጋፍ እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁሟል።

አክሎም ‹‹በካራሞጃ 23 በመቶ የሚሆነው አርብቶአደር ብቻ ነው የትምህርት ዕድል ያገኘው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአካባቢያችን በቂ መሠረተ ልማት ባለመዘርጋቱና እኛም አርብቶአደር እንደመሆናችን ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የምንንቀሳቀስ በመሆኑ ተረጋግተን መማር ስለማንችል ነው›› ሲል ያስረዳል። በበዓሉ ላይ እነሱም ሆነ የሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች መሳተፍ በመቻላቸው መደሰቱን፤ በተለይም ደግሞ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ለመውሰድ ያስቻለው መሆኑን ይገልፃል፡፡

ከዚህ ባሻገር ‹‹የእኛ ሀገር ከፍተኛ የመንግሥት አካላትና ውሳኔ ሰጪዎች ከዚህ በመነሳት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ጫና ለማሳደር ያግዛል›› ይላል፡፡ እሱ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመውሰድ የዩጋንዳን አርብቶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ ይገባቸዋል የሚል እምነት አለው፡፡ በተጨማሪም አርብቶአደር አካባቢዎች ያለውን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በስፋት ሊከናወኑ እንደሚገባ አመልክቶ፤ ይህም የገበያ ትስስሩን በማጠናከር ለቀጣናው ኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና እንደሚኖረው ያስገነዝባል፡፡

በዩጋንዳም ሆነ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ አርብርቶአደሮች አካባቢ ግጭቶች እንደሚከሰቱ አስታውሶ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል አርብቶአደሩን ነውጠኛ አድርጎ የመሳል እሳቤ ፈፅሞ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ያስረዳል። ‹‹ብዙ ጊዜ ግጭት የሚነሳው ከግጦሽና ከውሃ ጋር ተያይዞ ነው፤ ይህ ማለት ግን ሰላም ካለመፈለግ የመነጨ አይደለም፤ እኛ ሰላማዊ ሕዝቦች ነን፤ ይህ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን›› ይላል፡፡ ይልቁንም የውሃና መሰል የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ቢደረግና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ቢከናወኑ ወደ ግጭት የሚሄዱበት ምክንያት አለመኖሩን ነው ያመለከተው፡፡

እንደዩጋንዳዊው አርብቶአደር ገለፃ፤ እንዲህ ያሉ ቀጣና አቀፍ መድረኮች መንግሥታትም ሆነ መላው የዘርፉ ተዋናይ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አንስተው በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ ያግዛል፡፡ መሠረተ ልማቶችን በጋራ በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የዩጋንዳም ሆነ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት አርብቶአደሮች ከከተማ የወጡና ለመንግሥታዊ ሥርዓት፤ ዓለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ ረጂ አካላት ሩቅ በመሆናቸው በብዙ ነገር ተጎጂ ናቸው፤ በመሆኑም መድረኩ ችግራቸውን ለተቀረው ዓለም እንዲያሳውቁ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

የቀጣናው አርብቶአደሮች ኅብረት ማጠናከር እንዳለባቸው ያሳስባል፤ ይህም ደግሞ በየሀጋራቱ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚያስችል ገልፆ፤ ‹‹አርብቶአደሮች ራሳቸውን ማግለል የለባቸውም፤ ለልማታቸውና ለተጠቃሚነታቸው በጋራ መቆም ይገባቸዋል፡፡ እርስ በርስ መወያየት፤ መደጋገፍ አለባቸው›› በማለት ያስገነዝባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ቆይታ አርብቶአደሮች ያላቸውን አንድነትና የሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች በርካታ መሆናቸውን ለመገንዘብ መቻሉን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ሁሉም አርብቶአደር ይህንን አንድነት በመጠቀም በጋራ ለልማቱ መትጋት ይገባዋል ባይ ነው፡፡

ወይዘሮ ኩሻ ጉዮ ደግሞ ሞያሌ ወረዳ ኦብሲሴ ቡላ ቀበሌ ሴት አርብቶአደሮችን ወክለው ነው የተገኙት። እሳቸውም ከተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመጡ አርብቶአደሮች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተሞክሮ ለመካፈል አስችሎኛል ይላሉ፡፡ ‹‹ከሁሉም በላይ ኅብረታችንን ለማጠናከርና በጋራ እንድናድግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ተባብሮ መሥራትና በሰላም መኖር እንዴት እንደምንችል ግንዛቤ አግኝተናል›› በማለት ይገልፃሉ፡፡

ሞያሌ አካባቢ ያለው አርብቶአደር በኢትዮጵያ፤ በሱማሌና ኬንያ አዋሳኝ የሚገኝ እንደመሆኑ በባህልና በአርብቶአደር የአኗኗር ዘይቤ ተመሳሳይነት ያለው ማኅበረሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም ከግጦሽ፤ ውሃ ጋር ተያይዞ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር አስታውሰው፣ ኢጋድ ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ካቋቋመ በኋላ ግጭቶች እንዳይከሰቱ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ያለንን ሀብት በጋራ እየተጠቀምን በሰላም ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ከሰላም ኮሚቴዎች ውስጥ ሴቶችም ይሳተፋሉ፡፡ አዋሳኝ በሆነ ቦታ ላይ ቢሮ አቋቁሞ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ። በተጨማሪም የእሴት ሰንሰለት ፈጥሮ በወተትና ስጋ ምርቶቻችን የላቀ ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑም ያመለክታሉ፡፡

ይሁንና ካለው ሰፊ ሕዝብና፤ የተፈጥሮ ሀብት አንፃር እንደ ትምህርት፤ ውሃ፤ ጤና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች በሚገባ ባለመዘርጋታቸው ማኅበረሰቡ ከድህነት መላቀቅ አለመቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ድርቅ በመጣ ቁጥር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ ቀዬውን ለቆ መሰደድ እንደሚገደድ ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም የሀገራቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደሙ የላቀ ትኩረት ለአካባቢው ሊሰጡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ‹‹በተለይም ሴቶችና ሕፃናት የድርቁ ዋነኛ ተጎጂዎች እንደመሆናቸው እነሱን ማዕከል ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች መስፋት አለበት›› ይላሉ። የሀገራቱ መንግሥታት ቀጣይነት ላለው ልማትና አስተማማኝ ሰላም የቀጣናው ሀገራት በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ኤፔኑ ጁሉ የጋምቤላ ክልል የመስኖና ቆላማ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ክልሉ አርብቶአደርና ከፊል አርብቶአደር ማኅበረሰብ ያለበት እንደመሆኑ የበዓሉ መከበር ለክልላችን ልማት ጠቃሚ እንደሆነ ያምናሉ። በበዓሉ ላይ አርብቶአደሩ ማኅበረሰብ እንዲሳተፍ መደረጉ ራሱን እንዲያስተዋውቅ የላቀ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተለይ በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ አርብቶአደር የሚከተለው የከብቶች አያያዝ ሥርዓት ባህላዊ እንደመሆኑ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ አርብቶአደሮች ልምድ በመቅሰም ሥርዓቱን እንዲያዘምን ያግዘዋል ባይ ናቸው፡፡ እንዲሁም በድንበር ከሚዋሰኑ እንደ ደቡብ ሱዳን ካሉ ሀገራት አርብቶአደሮች ጋር በባህልም ሆነ በቋንቋ የሚዛመዱ እንደመሆናቸው ይህንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ያመለክታሉ፡፡

‹‹በዋናነት ደግሞ በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶችን ከወዲሁ ለማስቀረት፤ ይበልጥ ለመቀራረብ፤ ያሉ ሀብቶችን በጋራ በመጠቀም አብሮ ለማደግ ያስችላል›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው እንደመሆኑ፤ በበዓሉ ላይ የየሀገራቱ ከፍተኛ አመራሮችና ፖሊሲ አውጪዎች፤ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ምሁራን የታደሙ በመሆኑ ድርቅን መቋቋም የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠርና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ ለመምከር የማይናቅ አበርክቶ እንዳለው ያብራራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከምሁራንና ተመራማሪዎች ድርቅን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ረገድ ሚናቸውን ለመወጣት ግንዛቤ ያስጨበጡ ውይይቶች መደረጋቸውን ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ ኤፔኑ እምነት፤ በምሥራቅ አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ፤ ወሳኝ የልማትና የንግድ ኮሪደርና ሰፊ የሰው ሀብት ያለበት ቢሆንም በኢኮኖሚ ወደኋላ የቀረ ቀጣና ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅና የሰላም እጦት ዋነኛ መንስኤ ናቸው፡፡ በመሆኑንም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የመንግሥታቱ ቁርጠኝነትና በትብብር መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ማኅበረሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ በመድረኩ ላይ የተገኙ የየሀገራቱ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚዎች፤ ምሁራንና የኢጋድ አመራሮች ትልቅ ኃላፊነታቸውን ሊውጡ ይገባል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You