የ‹‹ሼካ ፓስታ›› – አባት አቶ መሐመድ አብዱረህማን

ስለ ድሬዳዋ ሲነሳ ሞቃታማነትዋ፣ ነዋሪዎችዋ በቀላሉ ከሰው የሚግባቡ እና ነገሮችን ቀለል አድርገው የሚያዩ የፍቅር ሰዎች እንደሆኑ ማስታወስን ያስገድዳል። ድሬዳዋ ከኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ጋርም የሚያስተሳስራት ታሪክ በመኖሩም ስሟ ተለይቶ ይነሳል። በንግድም የምትታወቅ ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ ስለመሆኗም ይነገርላታል። በእነዚህና በተለያዩ መገለጫዎችዋ ድሬ ብለው በአጭሩ የሚጠሯት ብዙ ናቸው። እኛም እንዲህ ወደ ሚነገርላት ድሬ በጥር ወር ማብቂያ ላይ ተገኝተናል።

በከተማዋ ውስጥ ለሥራ ጉዳይ ስንቀሳቀስ ስሙ ስለናኘው ሼካ ፓስታ ታሪክ ሰማን። የአካባቢው ሰዎች ስለታሪኩ ሲነግሩን ሼካ ፓስታ የሚገኝበትን ስፍራ ለማወቅ ጉጉታችን ጨመረ። ስናጠያይቅ ሰዎች በከተማዋ ኮኔል በሚባል አካባቢ እንደሚገኝ አቅጣጫውን አመላከቱን። በከተማው ታዋቂ በመሆኑ ለማግኘት አልከበደንም። የድሬ መኖሪያ ቤቶችም ሆኑ የንግድ ሱቆች ጥንታዊ መሆናቸው የተገነቡበት ግብአትና ዲዛይናቸው ምስክር ነው። ሼካ ፓስታም የሚገኘው ከእነዚህ ውስጥ በአንደኛው መሆኑን አወቅን።

ሼካ ፓስታ ዝና ያለው በመሆኑ፤ የጠበቅነው ትልቅ የሥራ ድርጅት ይሆናል ብለን ነበር። ቀረብ ስንል፤ ለእይታ ብዙ ግልጽ ባልሆነ በአነስተኛ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ‹‹የሁላችን ምግብ ቤት››፤ ከስሩ ደግሞ ሼካ ፓስታ የሚል መለያ ተሰቅሏል። ከአስፓልት ዳር ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ ሰፊ የሚባል ቤት አይደለም። አናታቸው ላይ የሙስሊም ኮፍያ ያደረጉ አዛውንት ከፊታቸው ላይ ሰፋ ባለ የከሰል ምድጃ ወደ አራት የሚሆኑ ፉልና እንቁላል ማብሰያ ጥደው ያለእረፍት የጣዱትን ምግብ እያማሰሉ ለደንበኞች እያዘጋጁ ሲያቀርቡ ከስፍራው ደረስን። በሌላ ወገን ደግሞ ፓስታ መካሮኒ፣ እንጀራም ደንበኛው እንደፍላጎቱ እያዘዘ ተመግቦ ይወጣል። ደግሞ ሌላው ይተካል። ሁሉም ተመግቦ በፍጥነት ይወጣል።

አዛውንቱ ፉልና እንቁላል የሚያበስሉበት ከሰል፣ ከውስጥ ደግሞ ሌላው ምግብ የሚዘጋጅበት እሳት ከተመጋቢው ጋር ተደማምሮ የቤቱን የሙቀት መጠን ከፍ አድርጎታል። አየሩን ለማቀዝቀዝ ቬንትሌተር ባይጠቀሙ ከአካባቢው ሙቀት ጋር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ተመጋቢው በዚህች ጠባብ ቤት ውስጥ እንደፍላጎቱ ተስተናግዶ የሚወጣው እንዲህ ባለው ሁኔታ ነው። ከጠዋት ከቁርስ ሰአት ጀምሮ እስከ ቀኑ ስምንት ሰአት ባለው ጊዜ ተመጋቢን ማስተናገድ ‹‹በሁላችን ምግብ ቤት›› የዘወትር ተግባር ነው።

የገንዘብ አቅም ያለውም የሌለውም የቤቱ ደንበኛ ነው። የራበው ሰው ገንዘብ ስሌለው አይመለስም። ‹‹ምስኪን ሰው አይገፋም›› ይላሉ ባለቤቱ መሐመድ አብዱርሐማን። ሁኔታውን አይተው ገንዘብ አይቀበሉትም። ምን ማለታቸው ነው? ንግድና ሰብአዊነት እንዴት ይሆናል? ብለን ነበር። ይህንን እና ስለንግድ ቤታቸው ስያሜ፣ ስለእርሳቸው የኑሮ ውጣ ውረድ፣ ስለቤተሰባቸው ስለሚኖሩባት ድሬዳዋና ሌሎችንም አንስተን ተጨዋውተናል።

አቶ መሐመድ፤ ትሁትና አዛኝ ሰው እንደሆኑ ከአንደበታቸውም እና ከገጽታቸውም ለመረዳት አዳጋች አይደለም። እኛን ለመቀበልም በፍጥነት ከሥራ ገበታቸው ተነስተው አክብሮታቸውን አሳዩን። ጥንካሬያቸው በሥራ ታታሪ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አንደበተ ርቱእነታቸው፣ ቅልጥፍናቸው እና የአካል ብቃታቸው ስማቸውን ከፍ ያደርገዋል። ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸው ሰው አይመስሉም።

የትውልድ አካባቢና የአስተዳደጋቸው ሁኔታ

አቶ መሐመድ እንዳጫወቱን የተወለዱት ሐረር ሐማሬሳ ሼክ ፊኒን አወዳይ አካባቢ ሲሆን፤ ዘመኑ ደግሞ 1940 ዓ.ም ላይ ነበር። ለእናታቸውም ሆነ ለአባታቸው ብቸኛ ልጅ ናቸው። አባታቸው የሃይማኖት ትምህርት ያስተምሩ ስለነበር የእርሳቸውን እናት ያገቧቸው ከተማሪዎቻቸው አንዷ የሆነችውን ልጅ መርጠው ነበር። በወቅቱም ለራሳቸው የመረጧቸው ‹‹ያልተማረ ሰው አያገባትም›› በሚል ነበር።

አቶ መሐመድ እናታቸው በሞት የተለዩዋቸው ህጻን ሆነው ጣዕማቸውን ሳያውቁ ነበር። ከእናታቸው ህልፈት በኋላ አባታቸው ሁለተኛ ሴት አገቡ። አባታቸው ሁለተኛዋ ሴት ለልጃቸው ለአቶ መሐመድ ጥሩ ሆና አላገኟትም። በደንብ ባለመንከባከቧ ፈትተው ልጆቻቸውን ይዘው ኑሯቸውን በሐረር ከተማ ውስጥ አደረጉ። አባታቸውም በህይወት ብዙ አብረዋቸው አልቆዩም። አቶ መሐመድ የ12 አመት ታዳጊ ሆነው አባታቸውም በሞት ተለዩዋቸው።

የአቶ መሐመድ የኑሮ ውጣ ውረድ የጀመረው ከዚህ እድሜ ጀምሮ ነበር። የጎዳናን አስከፊ ህይወት ለመኖር ተገደዱ። ከጎዳና ላይ ኑሮ ለመውጣት በአቅማቸው ሥራ ሲያፈላልጉ በሚኖሩበት ሐረር ከተማ ውስጥ የእስራኤልና የግብጽ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ምግብ ቤት ውስጥ እቃ አጣቢነት ሥራ አግኝተው ተቀጠሩ። አባታቻው በህይወት እያሉ ታማኝ መሆን፣ አለመስረቅ፣ ውሸት አለመናገር እንደሚያስከብር ደጋግመው ይነግሯቸው ስለነበር፤ ይህ በልባቸው ውስጥ ተቀርጿልና በዚሁ መልክ ከሰዎች ጋር መኖር ጀመሩ። በሆቴል ቤቱ ይህንኑ ታማኝነት ይዘው ነበር የተቀጠሩት። ለሆቴል ቤቱ ባለቤቶች ወላጅ እንደሌላቸው አስቀድመው ተናግረው ነበር። በሥራቸው ላይ የአባታቸውን ቃል አክብረው ትጉህ ሆነው ቆዩ። በባህሪያቸውና በሥራቸውም በሆቴል ቤቶቹ ባለቤቶች ተወደው አብረው ዘለቁ።

በቀን አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም እየተከፈላቸው ለተወሰኑ ዓመታት ከሰሩ በኋላ ሌላ አማራጭ ፈለጉ። አቶ መሐመድ ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን ሞክረዋል። ከተቀጠሩበት የሆቴል ቤት ወጥተው ‹‹ድምጽ›› በሚል ለህትመት ትበቃ የነበረች ጋዜጣን አዙረው መሸጣቸውንም ያስታውሳሉ። ጋዜጣውን ሲሸጡም አንባቢዎችን ለመሳብ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ ከጽሁፉ ውስጥ የተወሰኑትን ወይም ርእሱን ለደንበኞቻቸው ያነቡላቸዋል። በዚህም‹‹ እስኪ አንብብልን‹‹ ብለው የሚጠይቋቸው ደንበኞች እንደነበሯቸውም ያስታውሳሉ።

‹‹ድምጽ ጋዜጣ ዜናሽ እስኪወጣ ትናፍቂናለሽ›› ሲሉም በድምጻቸው አንጎራጉረውልናል። በሙዚቃው በድምጽም ሞክረው ቢሆን ድምጻዊነትም ያዋጣቸው ነበር። ድምጻቸው ለሙዚቃ የሚሆን ቃና ያለው ነው። ወይም የሬዲዮ ጋዜጠኛ ቢሆኑ ድምጻቸው አስደሳች ነው ተባባልን። ‹‹ኑሮ የትም ይከታል›› የሚሉት አቶ መሐመድ፤ አንድ ሰው ሥራ ካልሰራ በጎረቤቱም ቢሆን አክብሮት አያገኝም የሚል እምነት አላቸው። ኑሮን ለማሸነፍ ሥራ ሳይመርጡ ሁለገብ የሆኑት ለዚህ ነው ።

ኑሮ ከሐረር ወደ ድሬዳዋ

ዕድሜቸውም ወደ 18 ሲደርስ፤ ጓደኞች አፍርተው ወጣ ወጣ ማለት ሲጀምሩ የጓደኞቻቸው ባህሪ የተለየ ሆኖ አገኙት። ከጓደኞቻቸው ጋር ለመዝናናት በአንዱ ቀን ሲወጡ ጠጅ ቤት ይዘዋቸው ይሄዳሉ። እንዲህ ያለው ለእርሳቸው አዲስ ነገር ነበር። መጠጥም ሆነ ጫትና ሌላ ነገር ተጠቅመው አያውቁም። አባታቸው በህይወት በነበሩ ጊዜ የሚወስዷቸው መስጊድ ነበር። የሚያውቁትም ስብእናን የሚገነባ፣ መንፈስንም የሚያድስ ወደ ሃይማኖት ተቋም ወይም ወደ ፀሎት ስፍራ ቦታ መሄድን ነበር። ጓደኞቻቸው የወሰዷቸው ቦታው ግን ከዚህ ጋር የሚቃረን ሆኖ አገኙት።

ዳግመኛ ላለመሄድና ጓደኞቻቸውም እንዳይቀ የሟቸው ለመሸሽ አካባቢ መቀየር እንዳለባቸው ከራሳቸው ጋር መከሩ። ድሬዳዋን የጤና እክል ገጥሟቸው በ1953 ዓ.ም የማየት እድሉን አግኝተዋል። እንዳይዋት የወደዷት ድሬዳዋ ምርጫቸው ሆነች። ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ድሬዳዋ እና አቶ ሞሐመድ አልተፋቱም።

በዚህ ጊዜም አንድ ገጠመኛቸውንም አጫወቱን፤ ለህክምና ተኝተው በነበረበት ሆስፒታል ውስጥ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አፄ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታማሚዎችን ይጎበኛሉ። ለታማሚዎችም ለእያንዳንዳቸው አምስት አምስት ብር እየሰጡ ይጎበኙ ነበር። አቶ መሐመድ በተኙበት ክፍል ውስጥ አምስት ብር ከወሰዱ በኋላ ሌላ መኝታ ክፍል ቀይረው ድጋሚ አምስት ብር ይቀበላሉ። በድምሩ 10 ብር መሆኑ ነው። በዚያን ጊዜ ይህን ያህል ብር በማግኘታቸው ደስታቸው ወደር አልነበረውም። በወቅቱ 10 ብር ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ብዙ ነገርም ይገዛል። ከደስታቸውም ብዛት በሽታው ለቀቃቸው። በ10 ብሩ አንሶላ፣ ሸሚዝና ሌላም የሚያስፈልጋቸውን ገዝተው ወደ ሐረር ሲመለሱ ለትራንስፖርት ተጠቅመው፣ ለምሳም አስር ሳንቲም ከፍለው ገንዘብ ተርፏቸው እንደነበር አጫወቱን።

አቶ መሐመድ ድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ሳይሆኑ በዚህ መልኩ ጥሩ እንደተቀበለቻቸው ትውስታቸውን በማንሳት ኑሮአቸውን ድሬዳዋ ካደረጉ በኋላ ስላለው ሁኔታ ደግሞ አጫወቱን። ድሬዳዋ እንደገቡም ትልቁ መስጅድ በሚባለው ውስጥ በጽዳት ሥራ ተቀጠሩ። በወቅቱ ድሬዳዋ ውስጥ አረቦች፣ ግሪኮች፣ አርመኖች፣ ጣሊያኖች፣ ፈረሳዮች፣ ህንዶች፣ የባንያን ዜጎች በብዛት ይኖሩ ነበር። ከእነዚህ ዜጎች በአንዱ ሥራ የመቀጠር እድል አገኙ። አረብኛ ቋንቋ ይናገሩ ስለነበር አረቦች ጋር ለሥራ ተቀጠሩ። አቶ መሐመድ ‹‹ድሬዳዋ በመምጣቴ ለሥራ እንጂ ለደባል ሱስ ተገዥ አልሆንኩም። ››ይላሉ።

እነዛ ጓደኞቻቸው በህይወት አለመኖራ ቸውንም አስታውሰው፤ ያኔ ጓደኞቻቸው መጠጥ ቤት እንደወሰዷቸው በዚያው ቀጥለው ቢሆን ብለው አሁን ላይ ሲያስቡት፤ በአዕምሮም በአካልም ጤናማ እንደማይሆኑና በህይወትም ሊኖሩ እንደማይችሉ ይናገራሉ። እርሳቸው አሁን ምንም አይነት ሱስ እንደሌለባቸውና የሱስ ተገዥ ለሆኑትም እንደሚያዝኑ አጫወቱን። አቶ መሐመድ ሱስ የብዙ ነገር እንቅፋት ነው ይላሉ።

በአንድ ወቅት ላይ ጫት ይቅሙ እንደበርና ሲጋራም ያጨሱ እንደነበር አልሸሸጉም፤ ግን አልቀጠሉበትም። ከጫትና ከሲጋራ የተላቀቁበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱ ደግሞ አንዲት የሚያውቋት ልጅ ሳምባ በሽታ ታማ ህክምና እንድታገኝ ይረዷታል። ባለቤታቸው ከዚህች ልጅ ጋር በሌላ ነገር ይጠረጥሯቸዋል። በመካከላቸውም አለመግባባት ተፈጠረ። የባለቤታቸው ጥርጣሬ አግባብነት ስላልነበረው በንዴት ይመቷቸዋል። በዚህ የተነሳም በፖሊስ ተይዘው ይታሰራሉ። ያቺ ህክምና እንድታገኝ ይረዷት የነበረችው ሴት ውለታዋን ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይዛ ስትጠይቃቸው ጫትና ሲጋራም ይዛላቸው ትሄድ ነበር። የልጅቷ አሳቢነት ስለተሰማቸው ለእርስዋ ሲሉ ጫትም፣ ሲጋራም ይተዋሉ። ይህ የሆነው ከ40 ዓመት በፊት ነው።

ድሬዳዋ ከተማ በመጡበት ዘመን የከተማዋ ጽዳትና ውበት ለሥራ የሚያነሳሳ እንደነበርም ያስታውሳሉ። በተለይም ቀፊራ የሚባለው አካባቢ በብዛት ነጮች ይኖሩ እንደነበርና በአካባቢውም የተለያዩ የአትክልት አይነቶች ይሸጥ እንደነበር አስታወሱን። አብዛኞቹ ነጮችም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደነበሩ ነው የገለጹልን። ዛሬ በከተማዋ ታይዋን ተብሎ የሚጠራው የንግድ ቦታ ያኔ የቄራ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበርም ያስታሳሉ፤ የነዋሪው ብዛትም አሁን ያለውን ያህል እንዳልነበር ነው የገለጹት።

አቶ መሐመድ የሚሰሩበትን ቤት ቢቀያይሩም ሥራቸው ግን ተመሳሳይ ነበር። የግል ሥራቸውን ለመጀመር ምክንያት የሆናቸውንም እንዲህ አጫወቱን፤ ሸዋ ቡና ቤት ተቀጥረው ሲሰሩ፤ ሻይ ተፈልቶ በፔርሙዝ ይሰጣቸዋል። በየመንደሩ እየዞሩ ሸጠው ለባለቤቱ ገቢ ያስገባሉ። ለእርሳቸው በቀን አንድ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ይከፈላቸዋል። በተጨማሪ በቀን አንድ ብርጭቆ እርጎ ይሰጣቸዋል።

በግለሰብ ቤት እስከመቼ የሚለው ነገር ጥያቄ ፈጠረባቸው። እራስን መቻል የሚለው ፍላጎት እየጨመረ መጣ። ሀሳቡም ሻይ መሸጥ ስለነበር ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ገዝተው በማሟላት ወደ ግል ሥራቸው ገቡ። ሻዩን እያዞሩ መሸጥ ጀመሩ። አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው ደግሞ ልብስ ሰፊዎች ናቸው። ቁርስ እንቁላል እያቀረቡላቸው ጥሩ ተቀባይነትን እያገኙ ገቢ ማግኘት ጀመሩ። ሰዎቹ ተጠቅመው የሚከፍሏቸው በሳምንት በመሆኑ ለእርሳቸው ለገንዘብ አጠቃቀም ጥሩ ሆነላቸው።

በሸክም እያዞሩ መሸጡ ስለከበዳቸው ቤት ተከራይተው አንድ ቦታ ሆነው መሥራቱን መረጡ። በወቅቱ የቤት ኪራይ ከአምስትና ከስድስት ብር የበለጠ አልነበረም። ሥራቸውም ጥሩ ገቢ እያስገኘላቸው በሚያገኙት ገቢም ትዳር መሥርተው ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ጥሩ ኑሮ መምራት ጀመሩ። በሻይ ንግድ የተጀመረው ሥራ ወደ የሁላችንም ምግቤት ሼካ ፓስታ አደገ።

የሼካ ፓስታ መነሻ ታሪክ

የሼካ ፓስታ መነሻውን አቶ መሐመድ እንደነገሩን፤ በወቅቱ ስሙ ኮከብ የሚባል ቁመቱ ደግሞ ረጅም ፓስታ በገበያ ላይ ነበር። ይህን ፓስታ ገዝተው በቤታቸው ለምግብነት ይጠቀማሉ። የፓስታው ዋጋ ሁለት ብር ነው። ‹‹ፓስታው በልተንም በተደጋጋሚ ይተርፋል። ለምን ሽጬ የተረፈውን ደግሞ አንበላም›› የሚለው ሀሳብ መጣላቸው። ከሻይ ጋር ፓስታ ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ጀመሩ፤ ተወደደላቸው። ፓስታ የሚለው ደንበኛ በዛ። አንድ ሰሐን ሙሉ ፓስታ በአንድ ብር ይሸጡ ነበር። በወቅቱ አንድ ሊትር ዘይት በ60 ሳንቲም ገዝተው ከመስራት በተጨማሪ፤ የአትክልቱም ዋጋ እንዲሁ አነስተኛ ነበር።

አካባቢው ላይ በምግብ ቤት የፓስታ ምግብ በማቅረብ የቀደማቸው እንደሌለ የሚናገሩት አቶ መሐመድ፤ የፓስታ ተመጋቢው ቁጥር ሲጨምር የሚያቀርቡትን የፓስታ አይነት መምረጥ እንደጀመሩ ገለጹልን። እርሳቸው እንዳሉት በወቅቱ፤ ከጣሊያን ሀገር የሚገቡ ማግዳ ሳንታሉቻ፣ ሚና ቺርኮ የሚባሉ የፓስታ አይነቶችን መጠቀም ጀመሩ። ከጣፋጭ ስጎ ጋር በማቅረብ ተፈላጊነታቸውን ጨመሩ። ምግባቸውን ፈልጎ ወደ እርሳቸው የሚሄደው ደንበኛ ሼካ ፓስታ ብሎ ስም አወጣላቸው። እርሳቸው የሁላችን ምግብ ቤት ብለው ከሰየሙት ጋር ይጠራ ጀመር።

አቶ መሐመድ፤ በትጋታቸው እንዲህ እውቅናን ያግኙበት እንጂ ለገንዘብ ብለው ደንበኛ አለዩበትም። በአጋጣሚ ገንዘብ ባይኖረው እንኳን መብላት የፈለገ ሰው ሲመጣ ‹‹ምስኪን ነው ይብላ›› ይላሉ። አንድ ጊዜ ነው። የአንድ ሰሃን ሙሉ ፓስታ ዋጋ ከአንድ ብር ሶስት ብር ገብቷል። ደንበኛቸው ወጣት ነው። ዋጋው ተወዶበታል። መብላት ስለፈለገ እየተጨነቀ አዞ በሰሃን የያዘው ፓስታ ተደፋበት። ‹‹ አንተ ልጅ አትደንግጥ ኢንሹራንስ አለው›› ብለው ድጋሚ በመስጠት ልጁን ገንዘብ ከመጠየቅ ይልቅ ከድንጋጤው የመለሰቡበት መንገድ ለእርሳቸው የመንፈስ እርካታ ሰጥቷቸዋል። ስለምግባቸው ሲጠየቁ መልሳቸው ‹‹ያለው ይከፍላል። ያጣም ይበላል›› የሚል ነው።

ይሄ ባህሪያቸው ዛሬም በኑሮ ውድነት አልተለወጠም። በአንድ ብር ሲሆን ሙሉ ይቀርብ የነበረው ፓስታ ዋጋ ወደ 70 ብር ከፍ ብሏል። ደግ በማድረጋቸው እንደውለታ ቆጥረው ከጊዜ በኋላ አስታውሰው፣ የገንዘብ ስጦታ ያደረጉላቸውም አልጠፉም። እርሳቸው ያደረጉላቸውን በገንዘብ እንኳን የማይመልሱት እንደሆነ የሚያመሰግኗቸውም ብዙ ናቸው። እንዲህ ያለው ለእርሳቸው ከገንዘብ በላይ ነው።

አቶ መሐመድ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የፓስታ ምግብ እያቀረቡ ቢሆንም፣ በሂደት ግን እንደፉል ያሉ ቀለል ያሉ ምግቦች፣ እንጀራም በደንበኛው ፍላጎት በተጨማሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። ሌሎች አጋዥ ሰራተኞችም አሏቸው። በአቅርቦቱ ላይ በተለይም ፓስታ የሚገዙት እራሳቸው ናቸው። በሥራ ልምድ ጣዕም ያላቸውን የፓስታ አይነቶችን ስለሚያውቁ የሚያቀርቡት እራሳቸው ናቸው። አሁን ላይ እንደቀድሞ አይነት ጣዕም ያላቸውን የፓስታ አይነቶች ለማግኘት ዋጋው የሚቀመስ ባለመሆኑ ገበያው ላይ የተሻለ ነው የሚሉትን እንደሚገዙ ገለጹልን። ለፓስታው ማባያ የሚሆነውን ስጎም እንዴት መቀመም እንዳለበት ለሰራተኞቻቸው ያሳዩዋቸዋል።

አቶ መሐመድ፤ በምግባቸው ታዋቂና በደንበኞ ቻቸውም ተመራጭ ቢሆኑም ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ አላለፈም። በኪራይ የሚኖሩበትን የቀበሌ ቤት አለወጡም። የንግድ ቤታቸውም እንዲሁ አነስተኛ ነው። ጠንካራ ሰራተኛ ሆነው የተሻለ ኑሮ ለምን መኖር እንዳልቻሉም ጠይቀናቸው ። እርሳቸው እንዳሉት ለኑሮአቸው አለመሻሻል አንዱና ዋና ምክንያት ብለው ያነሱት፤ የቤተሰብ መብዛት ነው።

የትዳርና የቤተሰብ ሁኔታ

በተለያየ ምክንያት ትዳራቸው አልጸና ብሏቸው፤ 13 ከሚሆኑ ሴቶች ጋር ጋብቻ ፈጽመዋል። ከሁለም ወደ 26 ልጆች አፍርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ በህይወት የሉም። 19ኙ ግን አሉ። 22 የልጅ ልጆችም አይተዋል። በኑሮ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰው በትንሹም ቢሆን፣ የሚረዷቸው ልጆቻቸው ግን የብዛታቸውን ያህል እንዳልሆኑ ነገሩን። አሁን አብረዋቸው ካሉት ባለቤታቸው ከወለዷቸው ሶስት ልጆቻቸው ጋር እንደሚኖሩና ከእርሳቸው ውጭ በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ግን ድጋፋቸውን የሚፈልጉ ልጆች መኖራቸውን አጫወቱን።

አቶ መሐመድ፤ የልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው መብዛት በስምም በመልክም ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራቸው እንደሆነም ጠይቀናቸው የልጆቼን ስም እንዴት አጣለሁ በሚል አይነት ነበር በፈገግታ የመለሱልን። የልጅ ልጆቻቸውን ግን የሁሉንም ስም ለማወቅ እንደሚቸገሩ አልሸሸጉም። ከጊዜ በኋላ የኑሮ ለውጥ አለማምጣታቸው ቁጭት ውስጥ ቢከታቸውም የኑሮ ጫናው ደግሞ ሌላው ፈተና ሆኖባቸው ከአቅም በላይ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። የእለት ኑሮአቸውን ለመሸፈን ግን ‹‹እጅ አልሰጠሁም›› ይላሉ።

አቶ መሐመድ፤ በአጋጣሚ ትዳራቸው አልሳካ ብሏቸው ከተለያዩ ሴቶች ጋር ጋብቻ ቢፈጽሙም ከንግግራቸው እንደተረዳነው ግን ለትዳር ያላቸው አመለካከት በአንድ ጣሪያ ሥር የሚኖሩ ሊተገብሩት የሚገባ ነው። እርሳቸው እንዳሉት ሚስት ፍቅር፣ ልጅ የምትሰጥ፣ ምግብ አብስላ የምታቀርብ፣ ቤቷን በንጽህና ይዛ ደስታ የምትሰጥ በመሆኗ ክብርና አክብሮት ይገባታል። በተለይም በመደባደብ የሚያምኑ ጥንዶች ጥሩ መንገድ እንዳልሆነ ይመክራሉ። የፍች አንዱ መንስኤ አለመቻቻል እንደሆነም ያምናሉ።

እኛም ብርቱነታቸውን በአንደበታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሥራ ቦታቸውም ተገኝተን የዓይን እማኝ ሆነናል። ትኩረታቸው ሥራቸው ላይ ነው። በአንድ ጊዜ ወደ አራት ማብሰያዎችን ጥደው ያለማቋረጥ እያዘጋጁ ከከሰሉ ሙቀት ጋር ሲሰሩ ላያቸው ያስደንቃሉ። መንፈሳዊ ቅናትም ያሳድራሉ። በተጨማሪ ገበያ ወጥተው ለማብሰያ የሚውል ከሰል በጆንያ ሙሉ በትከሻቸው ተሸክመው ለምግብ ቤቱ የሚያስፈልግ መሶብ ሙሉ እንጀራም እንዲሁ በአንድ እጃቸው ይዘው በብስክሌት በፍጥነት እየነዱ ከንግድ ሱቃቸው ያደርሳሉ።

አቶ መሐመድ፤ እንዲህ በሥራው፣ በመልካም ነታቸው በከተማዋ ይታወቃሉ። በዚህ የረጅም ሥራ ጊዜና በእድሜያቸውም ከከተማ አስተዳደሩ ወይም ከተለያዩ አካላት ሽልማት እንደሚያገኙ ገምተን ነበር። እስካሁን ግን የሚያበረታታቸውን የምሥጋና እውቅና አላገኙም። አቶ መሐመድ ሰርቼ አተርፋለሁ፣ እለወጣለሁ አድጋለሁ የሚሉበት እድሜ ላይ ባይሆኑም ተስፋ መቁረጥ ግን አይፈልጉም። አቅማቸው እስከሚፈቅድ ድረስ የሚሰሩት ሥራ መተዳደሪያቸውም በመሆኑ በመቀጠል የእለት ኑሮን ለማሸነፍ ይተጋሉ።

በዚህ የረጅም ጊዜ የሥራ ቆይታቸው የገንዘብ ትርፍ ባያገኙም ‹‹ሰው አትርፌበታለሁ›› የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ዛሬ ለህክምና ወደ ተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት ሲሄዱ የሚሰጣቸው አክብሮትና ፍቅር፣ በመንገድ ላይም ‹‹ሼካ ፓስታ›› እያሉ ሲጠሯቸው የሚሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ቃላት እንደሚያጥረቸው ነው የገለጹልን።

አቶ መሐመድ ያለወላጅ እና ዘመድ ድጋፍ በራሳቸው ጥረት በአቅማቸው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው አንዱ የህይወት ገጽታቸው የሆነውን ሌሎች በተለይም ወጣቶች ሊማሩበት እንደሚችሉ በመግለጽ፤ በኑሯቸው ላይ ለውጥ ሊያመጡ ያልቻሉበትም ቢሆን ትምህርት እንደሚሆን ነው የተናገሩት። ከአቅም ጋር ያልተገናዘበ ቤተሰብ ማፍራት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው የገለጹት።

አሁን ዘመኑ እርሳቸው ከኖሩበት በተሻለ ሰዎች ኑሮ ዘይቤያቸውን መምራት የሚያስችላቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለየ ሁኔታ ለወጣቱ ምክር የሰጡት ሱስ ከሚያስይዙ ነገሮች እራሱን እንዲቆጥብ ነው። ሱሰኛ መሆን ከማህበራዊ ነገር እንደሚያርቅና በእድገትም ወደኋላ እንደሚያስቀር ነው የተናገሩት።

ስለሚኖሩባት ድሬዳዋም የመቻቻል ተምሳሌት እንደሆነች ይገልጻሉ። ይህ በመልካም የሚገለጸው ስሟ እንዲቀጥል ነዋሪዎችዋ በአንድነት፣ በመተሳሰብና በፍቅር ለሥራ መትጋት እንዳለባቸው ይመክራሉ። የአሁኑ ከንቲባም ለለውጥ፣ ለእድገትና ለሰላም የሚተጉ እንደሆኑ መስክረውላቸዋል። እኛም ለአቶ መሐመድ እድሜና ጤና ተመኘንላቸው።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You