የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ምድር በርካታ የቡና ዝርያዎች ይበቅሉበታል:: የሀገሪቱ የቡና ዝርያዎች በሀገር ውስጥም በውጭው ዓለምም ይታወቃሉ:: እነዚህ ዝርያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን የሀገር የኢኮኖሚ ዋልታነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ:: ስፔሻሊቲ ወይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበርካታ ቡና አምራችና ላኪዎችን ትኩረት መሳቡን ቀጥሏል::
የራሳቸው የሆነ ልዩ ጣዕምና ባህሪ ባላቸው በሀገሪቱ የቡና ዝርያዎች ላይ በስፋት እየተሠራ ነው:: የቡና ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ገበያም ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ሲሆን፤ ገበያው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ትኩረትንም በከፍተኛ መጠን እየሳበ ይገኛል:: ይህ ቡና በበለጠ አሁን ከመቼውም ጊዜ የኢትዮጵያ ቡና ባለ ልዩ ጣዕምና ባህሪ ቡና እየተባለ በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ የሚገኘውም በዚሁ ምክንያት ነው::
በቡና ሥራ ከተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች መካከልም ትኩረታቸውን ልዩ ቡና ላይ አድርገው የሚሠሩት እየተበራከቱ መጥተዋል:: የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም ስፔሻሊቲ ወይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ ቡና ላኪዎች መካከል አንዱ ናቸው::
በቡና ንግድ ብቻ 17 ዓመታትን አሳልፈዋል:: በዚህ ንግድ እነዚህን ያህል አመታትን ቢያሳልፉም፣ ከንግድ ሥራው ጋር የተዋወቁት ግን ገና በልጅነታቸው ተማሪ እያሉ ነበር:: ‹‹የንግድ ሥራ ሀሁን የቆጠርኩት ተወልጄ ባደግኩበት በትግራይ ክልል አዲግራት አካባቢ ነው›› የሚሉት የዕለቱ የስኬት እንግዳችን፤ አቶ ታደሰ ደስታ ይባላሉ:: የታደሰ ደስታ ቢዝነስ ግሩፕ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው::
ልብስ እንዲገዙ ቤተሰብ የሰጣቸውን አንድ መቶ ብር ይዘው ወደ ንግድ ያቀኑት አቶ ታደሰ፤ መነሻቸውም ይኸው አንድ መቶ ብር ብቻ እንደሆነም ያስታውሳሉ:: በወቅቱ በነበራቸው ጥረትና ትጋት እንዲሁም ነግዶ የማትረፍ ከፍተኛ ጉጉት አንድ መቶ ብሯ አምስትና አስር ብር እያተረፈች ንግዱን ይበልጥ እያጣጣሙት እንዲሄዱ አድርጋለች:: ያቺ አንድ መቶ ብር ዛሬ ላይ ብዙ ሚሊዮን ብሮችን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን ማፍራት ችላለች::
ገና ተማሪ እያሉ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በወጣትነት ሙቅ ልባቸው የጀመሩት የእንቁላል እና የቆዳ ንግድ ነበር:: እንቁላልና ቆዳ ከገጠር ወደ አዲግራት ከተማ እያመጡ ነግደዋል:: የእንቁላል ንግድ በባህሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው እንደመሆኑ ሥራውን በዋዛ ፈዛዛ ሳይሆን በብዙ ትጋት፣ በብርቱ ጥረትና በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደከወኑት ይገልጻሉ::
ከእንቁላልና ከቆዳ ንግድ ያተረፉትን ገንዘብ ወደ ሸቀጥ በማዘዋወር ወደ አስመራ ያቀኑት አቶ ታደሰ፤ ከአስመራ ወደ መቀሌና አዲግራት የተለያዩ ሸቀጦችን እያመላለሱ ነግደዋል:: በጥረታቸው ከእንቁላል፣ ከቆዳና ከሸቀጥ ንግድ ያተረፉትን ገንዘብ ይዘው ወደ ቡና ንግድ በመግባት በቡና ላኪነት ውጤታማ የሆኑት አቶ ታደሰ፤ ቡናን የተዋወቁበት አጋጣሚም የቡና ሀገር ከሆነችውና ‹‹አሸማ አሸማ ጅማ የፍቅር ከተማ›› ከተባለላት ጅማ እግር ጥሏቸው በመገኘታቸው ነው::
እሳቸው እንዳሉት፤ ጅማ ላይ የነበራቸው ቆይታ አካባቢው በውስጣቸው የሚንቀለቀለውን የንግድ ፍላጎት ማሟላት የሚችል ምቹ አካባቢ እንደሆነ በመረዳት ዙሪያ ገባውን አጥንተዋል:: ከጅማ አልፈው ቤንች ማጂ ድረስ በመጓዝ ከቡና ጋር ተዋውቀዋል::
በወቅቱ በቀጥታ ቡና ላኪ አልሆኑም:: ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ሁኔታውን ካጠኑ በኋላ ከቡና አምራቹ አርሶ አደር ቡናውን ሰብስበው ለአቅራቢዎች በማስረከብ ነው የቡና ንግዱን የጀመሩት:: ከሰብሳቢነት ከፍ ሲሉ ደግሞ ወደ አቅራቢነት ተሸጋግረው የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ቡና ላኪ መሆን ችለዋል::
የቡና ሥራውም ልክ እንደ እንቁላል ንግዱ እጅግ ፈታኝና በጥንቃቄ መመራት ያለበት ሥራ እንደሆነ ያነሱት አቶ ታደሰ፤ ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ ሲጀምሩ በትንሹ ወደ ዐረብ ሀገራትና ሱዳን እንደነበር ነው ያስታወሱት:: ይሁንና ብዙ ጊዜ ሳይወስድባቸው የገበያ መዳረሻቸውን በማስፋት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና ኤሲያ ሀገሮች ጭምር ቡና በመላክ ተወዳዳሪ ሆነዋል:: ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚገኙና በመቶዎች ከሚቆጠሩ ቡና ላኪዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በደረጃም ቢሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ ቡና ላኪዎች 12ኛ ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል::
‹‹ከትምህርት ይልቅ ነብሴ ለንግድ ታደላ ነበር›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀን እየሠሩ በማታው ክፍለጊዜ አዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት እንደ ተማሩ አጫውተውናል:: በወቅቱ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባቸውን ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ትምህርቱ ከሚሠሩት የቡና ንግድ ጋር አብሮ ሊጓዝ ባለመቻሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባቱን ተወት አድርገው ሙሉ ጊዜያቸውን ለንግዱ ሰጥተዋል:: ያም ቢሆን ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የቋንቋ ትምህርት መከታተላቸውን ቀጥለዋል::
ጅማ ላይ ሆነው የጀመሩት የቡና ሥራ አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ቡናዎችን ሰብስበው ለውጭ ገበያ ማቅረብ አስችሏቸዋል:: ቡና ከሚሰበስቡባቸው አካባቢዎች መካከልም ይርጋ ጨፌ፣ ጉጂ፣ ሲዳማ፣ ነንሰቦ ይገኙበታል:: ይሁንና ይርጋጨፌና በተለይም ጉጂ ሀምበላ በሚባል አካባቢ የሚመረተው የቡና ዓይነት በዓለም ላይ እጅግ ታዋቂና ተወዳጅ በመሆኑ ለባለ ልዩ ጣዕም ቡና ይመርጡታል::
ከእነዚህ አካባቢዎች የሚሰበስቡት ቡና ከፍተኛ መጠን ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ይህም ከሚሰበስቡት ቡና በአማካኝ 80 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ በአካባቢው የሚመረተውን ቡና ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ገዝተው በማሰባሰብ የድርጅቱ ንብረት በሆኑ ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽኖች አማካይነት ቡናው ለውጭ ገበያ ዝግጁ ይደረጋል:: ድርጅታቸው ለዚሁ ሥራ አስፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ አስር የሚደርሱ የቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎችን በአካባቢው ተክሏል:: ወደ ውጭ ከሚልከው አጠቃላይ የቡና መጠን 30 በመቶ ያህሉም በእነዚሁ አስር ጣቢያዎች በራሱ አቅም ይዘጋጃል::
ቀሪው 70 በመቶ ያህሉ ቡና ደግሞ ከሌሎች አምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር በከፊል የተዘጋጀ ቡና በመረከብ ለውጭ ገበያ ዝግጁ ያደርጋል:: ለአብነትም የታጠበ ቡና ከነሸሚዙ ሲመጣ ተፈልፍሎ ለውጭ ገበያ ይዘጋጃል:: ደረቁና የተፈለፈለው ቡናም እንዲሁ በድጋሚ ተፈልፍሎ ለውጭ ገበያ በሚመጥን መልኩ ተዘጋጅቶ ይላካል::
ድርጅቱ በቡና ሥራ ተሰማርቶ ሲሠራ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ አንድ ሁለት እያለ ዛሬ ላይ መድረሱን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት የቡና መጠንና ጥራትም ከዓመት ዓመት እያደገና እየተሻሻለ ስለመምጣቱም ነግረውናል:: ለአብነትም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከ14 እስከ 16 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማምጣት መቻሉን ጠቅሰው፣ ባለፈው ዓመት ብቻ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ያስታውሳሉ::
‹‹በየጊዜው ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የቡና መጠንና ዓይነት ይለያያል›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ድርጅታቸው ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ይናገራሉ፤ በመሆኑም ባለ ልዩ ጣዕም ቡናን በብዛት በሚልኩበት ወቅት የቡናው መጠን ይቀንስና የሚገኘው የገቢ መጠን ይጨምራል:: በተመሳሳይ ለመደበኛ ንግድ የሚላከው ቡና ሲሆን ደግሞ የሚላከው ቡና ከፍተኛ መጠን ይኖረውና የሚገኘው የገቢ መጠን ይቀንሳል ሲሉ ያብራራሉ:: ያም ቢሆን ድርጅታቸው በዓመት በአማካኝ እስከ ሦስት ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው:: በተያዘው በጀት ዓመትም ከ300 እስከ 350 ሜትሪክ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርቦ 27 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው::
ዕቅዱን ለማሳካትም ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ጠቅሰው፣ በተለይም ዘንድሮ ከ80 እስከ 90 በመቶ በስፔሻሊቲ ቡና ላይ ለመሥራት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል:: በዕቅዳቸው ልክ መሥራት ከቻሉ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት::
ትኩረቱን ስፔሻሊቲ ወይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ላይ ያደረገው ታደሰ ደስታ ቢዝነስ ግሩፕ በቀጣይ ሰፋፊ ዕቅዶችን አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: በተለይም ግብርናን በማስፋፋትና በማዘመን ከተልምዷዊ አሠራር በመውጣት በመስኖና በዘመናዊ መንገድ ተጠቅሞ ቡናን የማልማት ሥራ ይሠራል:: ይህም ከድርጅቱ ባለፈ ሀገርን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል ጠቅሰው፣ መንግሥት ለእዚህ ሥራ አስፈላጊውን ትብብር ቢያደርግ መልካም ነው በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::
‹‹በሥራ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ከአርሶ አደሩ ጋር እጅና ጓንት ሆነን እየሠራን ነው›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ቡና የአርሶ አደሩ ሀብት እንደመሆኑ ሀብቱን በአግባቡ እንዲጠቀምና ከሀብቱም ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ድጋፎችን እናደርጋለን ብለዋል:: ከአርሶ አደሩ ጋር ባላቸው ጠንካራ ግንኙነትና ክትትልም እንዲሁ ጥራት ያለው ምርት አግኝተው በተሻለ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን አስታውቀው፣ በዚህም ድርጅታቸውም፣ አርሶ አደሩም ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ሲጀምሩ ለዐረብ ሀገራትና ሱዳን በትንሽ በትንሹ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታደሰ፤ በአሁኑ ወቅት ነባር ገበያዎች ውስጥ መቆየታቸው እንዳለ ሆኖ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እያሰፉ መሆኑንም ይናገራሉ::
አቶ ታደሰ በአብዛኛው አውሮፓ ሀገራት፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሳውዲዐረቢያ፣ ዱባይና ወደ ኤዢያ ሀገራትም እንዲሁ ጃፓን፣ ኮርያ ታይዋን ቡና ይልካሉ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ትልቅ ገበያ ባለበት በሀገረ ቻይና ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና እየላኩ ናቸው:: ድርጅቱ አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለደንበኞቹ በማቅረብና የደንበኞቹን ፍላጎት በማርካት አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትና ተወዳዳሪ መሆን የሁልጊዜም ጥረቱ ነው::
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በተለይም የቡና ባለቤት ለሆነው አርሶ አደር ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል፤ ለአብነትም ችግኝ በማቅረብ ሥልጠና በመስጠትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ድርጅቱ አርሶ አደሩ ቡናውን በተሻለ ዋጋ መሸጥ እንዲችል ዕድል ፈጥሯል:: ከዚህም ባለፈ ድርጅቱ ከአርሶ አደሩ ጋር ውል በማሰር አስቀድሞ ገንዘብ በመክፈል ኢኮኖሚያዊ ችግሩን መቅረፍ እንዲችል ያግዛል:: የቡና ማጠቢያና ማድረቂያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለአብነትም ጉጂ ቢርቢሳ አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማውጣት ማኅበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በአቅራቢያው ማግኘት እንዲችል አድርጓል::
የግብርና ሥራ ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ የሚሠራ ነው የሚሉት አቶ ታደሰ፤ በአካባቢው ለሚገኙ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል:: በቢሮ አገልግሎት ከሚሠሩ ሠራተኞች በተጨማሪ በቋሚነት 154 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ከ150 እስከ 200 ለሚደርሱ ዜጎችም እንዲሁ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል::
ረጅሙን የሕይወት ዘመናቸውን በንግድ ሥራ ካሳለፉት አቶ ታደሰ ጋር የነበረንን ቆይታ ስናበቃ፣ አቶ ታደሰ ዛሬ ለደረሱበት ከፍተኛ ስፍራ ትልቁ ምስጢር የትናንት ትጋትና ጥረታቸው፤ ከዝቅታው ዝቅ ብሎ መነሳት መቻላቸው፤ ጠንክሮ መሥራትና ስኬትን መናፈቃቸው መሆኑን እንገልጻለን:: አበቃን::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም