የሀገራችን አብሮ የመልማት እሳቤ ለአፍሪካውያን ቀጣይ የኅብረት ጉዞ ወሳኝ ነው!

ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሠረት የጣለችው ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ ነው:: የጦርነቱ ውጤት ጥቁር ሕዝብ በጎራዴ ተዋግቶ ነፃነትን፣ ክብርን ማስመለስ፣ የራስ የሆነውን ሀብትንና መኖሪያ ሀገርን ማስከበር ይቻላል የሚለው መንፈስ እንዲሠራጭ አድርጓል:: ቢጫውም፣ ነጩም፣ ጥቁሩም የሰው ልጅ እኩል ነው የሚለውን አስተሳሰብ አምጥቷል:: የአፍሪካ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሄ ነገር ይቻላል ማለት ነው ብለው እንዲነቁ አድርጓቸዋል::

የዓድዋ ጦርነት ድል፤ ቀደም ባለው ጊዜ በምዕራብ አውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በካረቢያን የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች በተናጠል ያደርጉት የነበረው የነፃነት ንቅናቄ፤ ከፍ ወዳለ የነፃነት እሳቤ (የፓን አፍሪካኒዝም አድጎ ወደ ተቋማዊ) ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊያድግ የቻለበትን መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል::

ሀገራችን ለፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ትልቅ አቅም የሆነውን የዓድዋን ድል በብዙ መስዋዕትነት እውን ከማድረግ ባለፈ፤ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይም የማይተካ ሚና እንደተጫወተች የታሪክ መዛግብት በደማቅ ቀለማት ያሰፈሩት እውነታ ነው።

በወቅቱ ኅብረቱን ለመመስረት በተሰባሰቡ 32 ነፃ ሀገራት መካከል የነበሩ የአተያይ ልዩነቶች የሚጠቡበትና ወደ መስማማት የሚመጣባቸውን መንገዶች በጥበብ በማጥበብ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት (የቀድሞውን አፍሪካ አንድነት ድርጅት) እንዲመሠረት ረጅም ርቀት ተጉዛለች።

ከዚህም ባለፈ፤ በቅኝ ግዛት ውስጥ ለነበሩ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ፤ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን እና የሎጂስቲክ ድጋፎችን ከማቅረብ ጀምሮ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን አድርጋለች። በዚህም የብዙ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ባለውለታ ነች።

አፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ሂደት ውስጥ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፣ የሀገራቱን መሪዎች እዚሁ አዲስ አበባ መሰባሰብን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ‹‹የአፍሪካን አንድነት የሚመሠረትበትን ቻርተር ሳናጸድቅ ልንበተን አይገባም:: አንድ የአፍሪካ ድርጅት እንዲቋቋም ሳናደርግ ልንለያይ አይገባም:: ይህን ሳናደርግ ብንቀር ኃላፊነት ለሰጡን ፣ እምነታቸውን ለጣሉብን ሕዝቦቻችን ያለብንን አደራ እንዳልፈፀምን የሚያስቆጥር ይሆናል›› በሚል በወቅቱ ያደረጉት ንግግር የፈጠረው ጫና ለኅብረቱ መመስረት ታሪካዊ ተደርጎ የሚወሰድ ነው::

በቀደመው ዘመን /በነፃነት ትግሉ ወቅት አፍሪካውያን ማንነታቸው ተከብሮ በዓለም አደባባይ ቀና ብለው መራመድ እንዲችሉ በጋራ ተንቀሳቅሰዋል:: በዚህም በኅብረት መንቀሳቀስ ምን ያህል አቅም እንደሚሆን በተጨባጭ ማየት ችለዋል። በሂደትም የጋለውን የአንድነት መንፈስ በማስቀጠል በኩል የኢትዮጵያ ስም በትልቁ ተፅፎ ይገኛል::

ለዚህ ነው ዛሬም ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሆነ በኅብረቱ ውስጥ ከፍ ያለ ስምና ቦታ ያላት:: ለዚህም ነው በአፍሪካ ነባራዊ እና ታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ተጨምሮ ፣ የሰላም ማዕከል መሆኗ፣ ከተለያዩ ኃያላን ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነትና ተሰሚነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራት ቦታ ታሳቢ ተደርጎ የኅብረቱ መቀመጫ እንድትሆን የተመረጠችው::

የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ ላይ 55 ሀገራትን በአባልነት አቅፎ፤ መቀመጫውንም እዚሁ መዲናችን አድርጎ አመታትን አስቆጥሯል:: በጉዞው ታዲያ አንድ የሆነች አፍሪካን እውን ለማድረግ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል:: በዚህ ውስጥ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እስከ ንግዱ ዓለም የዘለቁ የጋራ ትብብሮች በሀገራቱ መካከል እንዲፈጠሩ ሲያደርግ ቆይቷል:: ይህ አንጋፋ ድርጅት ዛሬ ስድስት አስርት አመታትን አስቆጥሯል::

በቅርቡም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ ይካሄዳል:: ጉባኤው በአመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ነው:: አንደኛው ከአዲስ አበባ ውጪ የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው በጥር ወር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ነው:: ከጥር ውጪ የሚካሄደውን ጉባኤ አንዳንድ ጊዜ ሀገራት ማስተናገድ ሲያቅታቸው ኢትዮጵያ ያንንም ጭምር ተቀብላ በአመት ሁለት ጊዜ ጉባኤውን ታስተናግዳለች::

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግቦቹንና ዓላማዎቹን አሳክቶ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የመሆን ህልማቸውንም እውን አድርጎ ዱላውን ለአፍሪካ ኅብረት አቀብሏል:: የዱላ ቅብብሉ ተረኛ የአፍሪካ ኅብረት ታዲያ በሚፈለገው ፍጥነትና በሚፈለገው ጊዜ ዓላማዎቹን ከግቡ ለማድረስ ሩጫውን ቀጥሏል፤ ምንም እንኳ በርከት ያሉ መሰናክሎች ቢኖሩበትም::

እርግጥ ነው ኅብረቱ ባለፉት አመታት በርከት ያሉ ሥራዎችን ለመከወን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል:: የሠራቸውም፣ ያልተሳኩም፣ በሚቀጥሉት አመታት ሊሳኩ የሚችሉ ትልሞች ይዞ ወደፊት እየሄደ ነው:: አፍሪካ ዛሬ ብዙ ፈተናዎች አሉባት:: እነዚህን ፈተናዎች ለመሻገር ደግሞ በአህጉሪቱ ልጆች የተመሠረቱ ተቋማት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ::

አፍሪካ ኅብረትም እኤአ 2063 ለማሳካት ያሰባቸውን ግቦች መወያያ አጀንዳ እያደረገ ቀጥሏል:: ኅብረቱ በየአመቱ በሚያደርገው የመሪዎች ጉባኤ ላይም የአፍሪካውያንን ኑሮ ለማሻሻል፣ የጤና ዘርፉን ለማሳደግ፣ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን፣ ኢኮኖሚን ለማሻሻልና በትምህርቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አጀንዳዎችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው::

ብዙዎቹ በጉባኤ የሚነሱ አጀንዳዎች ውጤታማነታቸው ለጥያቄ የሚቀርብ ስለመሆኑ፤ አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች በርካቶች ናቸው:: በኅብረቱ የሚቀርብ አጀንዳ ከአጀንዳነት አልፎ ሲተገበር አለመታየቱ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው ።ይህም ሆኖ ግን አፍሪካውያኑ የተወያዩባቸውን ጉዳዮችና አጀንዳዎች ባፀደቋቸው የድርጊት መርሐ ግብሮች ላይ ጠንካራ አቋምና አፈፃፀም ማሳየት እንደሚኖርባቸው ይጠበቃል::

ከዚህም ቀዳሚው ጉዳይ አህጉሪቱ በኢኮኖሚ ራሷን ማጠናከር የምትችልባቸውን መንገዶች ማበጀት ነው:: ኅብረቱ ከዚህ ቀደም አጀንዳ አድርጎ ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የጋራ የንግድ ቀጣናዎችን ማጠናከር ነው:: ሌላው የአህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ ነው:: በአፍሪካ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች፣ ጦርነቶችና የመፈንቅለ መንግሥት ተግባራት አህጉሪቱን ዛሬም አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እንድትራመድ አድርጓታል::

አፍሪካ በኑሮ፣ በኢኮኖሚ፣ በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዛሬም ትፈተናለች:: እነዚህን ጉዳዮች በአጀንዳ ይዞ ከግቡ የማድረሻው ጊዜ እኤአ 2063 እየተቃረበ ነው:: እስካሁን ኅብረቱ ከሄደበት ርቀት ሁለትና ሦስት እጥፍ በፈጠነ መንገድ አጀንዳዎቹን ለማሳካት መራመድ አለበት:: አፈፃፀሞችን መገምገምና ማስተካከል ይጠበቅበታል::

በዚህኛው አመት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ትምህርትን አጀንዳ ያደረገ ነው:: በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጉባኤ ከዚህ በፊት በተነሱ አጀንዳዎችና ከዚህ በኋላም አህጉሪቱ ማሳካት የምትችላቸውን ግቦች እውን ለማድረግ ከፍ ያለ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል:: ኅብረቱ አሁን ባለው ተጨባጭ ግምገማ ከዚህ በፊት ከሄደው ይልቅ ከዚህ በኋላ የሚጓዘው ሩቅ እንደሚሆን ይታመናል::

ለኅብረቱ ጉዞ ስኬት አሁንም የኢትዮጵያ አስተዋፅኦና አበርክቶ ላቅ ያለ ነው:: በአህጉሪቱም ሆነ በቀጣናዋ ሰላም፣ እድገት፣ ..ወዘተ ትልቅ ሸክም አለባት:: ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጀመረችው ሰጥቶ የመቀበል መርህን መሠረት ያደረገ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ያስቀደመ አካሄዷ አህጉሪቱ ከኢኮኖሚ መተሳሰር ወደ ኢኮኖሚ ውሕደት ለመድረስ የሚያስችላትን አቅጣጫ እንድትከተል ጥቁምታ ይሰጣል::

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚና ከፍተኛ ነው:: በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት እያደረገች ነው:: የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች:: ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ትገኛለች::

በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኛትን የባቡር መስመር ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል:: ከኬንያ ጋር የሚያገናኘውን የመንገድ ግንባታ ሥራ ወደ ሥራ ለማስገባት ቅድመ ሁኔዎች እየተከናወኑ ነው:: ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረግ በተጨማሪ ኬንያንና ታንዛኒያን በተመሳሳይ ሁኔታ በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው:: ይህ ሁኔታም ወደ ፊት የቀጣናውን ሀገራት ወደ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ እገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ጥርጥር የለውም::

በተለይም ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከኢኮኖሚ መተሳሰር ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመድረስ የሚያስችላቸውን አቅጣጫ ተከትለው እየሄዱ እንዳሉ ከአንዳንድ ሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል:: ከኢኮኖሚ ትስስሩ በተጨማሪ በመንገድ ትራንስፖርትና በትልቁ የባቡር መንገድም ተሳስሯል:: አሁን ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝን በቧንቧ ከኦጋዴን ወደ ጅቡቲ ለማጓጓዝ ወደ ሥራው ለመግባት እየተዘጋጁም ይገኛሉ:: ይህ ጅቡቲ ወደብንና የታጁራን ወደብ የፈጠረው ሁለንተናዊ ትስስርን ሳይጨምር ነው::

ይህን የኢኮኖሚ ውሕደት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በቀጣይ የፖለቲካዊ ውሕደትን ሊያመጣ እንደሚችል ይታመናል:: ይህም ለኢኮኖሚያዊ ውህደት መነሻ ሆኖ ቀስ በቀስ አፍሪካ ለያዘችው ለ2063 አጀንዳ መሳካት ትልቅ ተሞክሮና አቅም እንደሚሆንም ከወዲሁ ለመገመት የሚከብድ አይሆንም:: ይህ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው አብሮ የመልማት እሳቤ ከዚህም ባለፈ ለአፍሪካውያን ቀጣይ የኅብረት ጉዞ ወሳኝ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You