
አዲስ አበባ፡- አውደርእዩ ኢትዮጵያ የራሷን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሄደችበትን ርቀት ያሳየ መሆኑን ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ገለጹ፡፡
ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርእይ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ይገኛል፡፡
አውደ ርእዩን ሲጎበኙ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የሕፃናት የምግብ መብት ተሟጋች ፣የንግድ ሥራ ፈጣሪ፣ የማህበራዊ ሥርዓቶች ስትራቴጂስት እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩት ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ አውደ ርእዩ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካንም የዲፕሎማሲ ታሪክ ማሳየት የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓለም የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በተለይ ደግሞ የጥቁር ሕዝብ ጥያቄ ይዛ ከፊት በመሰለፍ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች እንዲሁም የአፍሪካን ታሪክ ከዓለም ሕዝቦች ጋር ለማገናኘት መሠረት የጣለች ሀገር ነች ብለዋል፡፡
በዲፕሎማሲ ሳምንት የፎቶ ግራፍ አውደ ርእይም የተካተቱ ታሪኮች የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለበርካታ አፍሪካ ሀገራት ነጻነት የተጋ እንዲሁም አፍሪካዊ የሆኑ ተቋማት እንዲመሰረቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑ የሚታይበትና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ተጽእኖ ፈጣሪነትን ያስገነዘበ ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ፍሬአለም ተቋም ባልነበረበት ጊዜ አፍሪካን ወደ አንድ የሚያመጣ ተቋም ለመመስረት ማሰብ ፣ መታገል ብሎም መፈጸም መቻል እጅግ የሚደነቅና ቀደምት አባቶች የጣሉት መሠረት ምንያህል ጠንካራ መሆኑን ከዓለም ጋርም ከሚባለው በላይ የሆነ ግንኙነት የመሠረቱ መሆናቸው በአውድ ርእዩ መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ታሪክን ማወቅ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት ወይዘሮ ፍሬዓለም፤ እንደነዚህ ያሉ አውደ ርእዮችም ትውልድ ትክክለኛ የሀገሩን ታሪክ የሚያውቅበት ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍበት እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ትውልድ ሁሉ የሚኮራበት እንደመሆኑ ይህንን ለማስተዋወቅ ብሎም ሁሉም ዜጋ የሀገሩን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት መሄድንና በአንድነት መቆምን እንደሚጠይቅ በአውደ ርእዩ ላይ ከተካተቱት ታሪኮች ትውልዱ መማር ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ከውጭ ሀገራት ተጽዕኖ በብዙ ትግል መልክ እንዲይዝ የተደረገ ሲሆን፤ ወደፊትም ብዙ ትግሎች እንደሚጠብቋት በመገንዘብ ጊዜውንና ወቅቱን የሚመጥን የዲፕሎማሲ ሥራ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም