
አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው ወቅታዊ ምዝገባ ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ የልደት ሰርተፍኬት መሰጠቱን የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው ባለፉት ስድስት ወራት በወቅታዊ ምዝገባ ማለትም ሕፃናት ተወልደው በ90 ቀናት የተመዘገቡት ከ70 ሺህ በላይ ናቸው። ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ብልጫ አለው። አምና በወቅታዊ ምዝገባ 40 ሺህ የሚደረሱ ሕፃናትን መመዝገብ ተችሏል።
በከተማዋ በሚገኙ 73 ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች የልደት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል ያሉት አቶ ዮናስ፤ ምዝገባው በጋንዲ፣ በዘውዲቱ፣ በአበበች ጎበና፣ በአናንያ የግል ሆስፒታል እና በሌሎችም ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ምዝገባው የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎችን እንደሚያጠቃልልም ገልጸዋል።
በቀጣይ ዓመት የከተማውን የልደት ምዝገባ ሽፋን 100% ለማድረስ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ዮናስ፤ በተመድ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው የሲቪል ምዝገባ ውስጥ የልደትና የሞት ምዝገባ ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ሁለቱ ኩነቶች ለመንግሥት የመረጃ ምንጭነት እንደሚያለግሉና ይህም የቀጣዩ ትውልድ መረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈና የጠራ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ዮናስ ገለፃ፤ የልደት ምዝገባው ለህግ፣ ለስታትስቲክስ እና ለአስተዳደር ጉዳዮች ይጠቅማል። ይህም ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል መረጃ እንዲገኝ ያደርጋል። ምዝገባው በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ደግሞ የቀጣይ ትውልድ መረጃ የጠራ እንዲሆን ያደርጋል። መንግሥት ከልደት ጀምሮ የሚያደርገው ምዝገባ ወንጀልን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ከመሆኑም ባሻገር መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትም ይረዳል ብለዋል።
ሕፃናት በተወለዱ በ90 ቀናት የልደት ሰርተፍኬት የሚሰጣቸው መሆኑ ደግሞ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የልደት ምዝገባ ሥርዓት የተከተለች ከተማ እንድትሆን ያደርጋታልም ብለዋል።
የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የሕፃናት ጥበቃ ኃላፊ በሆኑት ጆላንዳ ቫን ዌስተሪንግ እና የዩኒሴፍ ዓለም አቀፍ የልደት ምዝገባ ስፔሻሊስት በሆኑት ባኸካር ሚሽራ የተመራ ልዑክ የአዲስ አበባን የወቅታዊ ምዝገባን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ልዑኩ አዲስ አበባ በወቅታዊ ልደት ምዝገባ ሽፋን እና ጥራት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የዘረጋችው ሥርዓት ትልቅ እምርታ እያሳየ ያለና በሀገር አቀፍ የምዝገባ ሥርዓት ላይ በጎ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒሴፍ በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያደርገው የወቅታዊ ልደት ምዝገባ አፈፃፀም በኢትዮጵያ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ያነሱት የሕፃናት ጥበቃ ኃላፊ ጆላንዳ ቫን፤ አዲስ አበባ ለክልል እና ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ መሆን የምትችል መሆኗን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የልደት ምዝገባ ሽፋን ላይ ምልከታ ያደረጉት የዩኒሴፍ ዓለም አቀፍ የልደት ምዝገባ ስፔሻሊስት ባኸካር ሚሽራ የከተማው አመራር ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በሌሎች ሀገራት ከተሞች ያልተለመደ መሆኑን ገልጸው የምዝገባ ሥርዓቱ በጤና ተቋም መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም