ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች ናት። በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ይገኛሉ። ወርቅና የመሳሰሉት የከበሩ ማዕድናት፣ ፖታሽ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ሊቲየም፣ ታንታለም፣ ብረትና ብረትነክ ማዕድናትና ሌሎች ለኢንዱስትሪ እና ለኮንስትራክሽን ግብዓቶች የሚውሉ በርካታ ማዕድናት ይገኙባታል፡፡
ሀገሪቷ የእነዚህ ሁሉ ማዕድናት ባለቤት ትሁን እንጂ ማዕድናቱን አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተሠሩ ሥራዎች እዚህ ግባ የማይባሉና ብዙ መሰናክሎች መሻገር ያልቻሉ እንደሆነም ይነገራል። በተለይ ከሕገወጥነት እና ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ዘርፉን በእጅጉ እየፈተኑት መሆኑ ይስተዋላል።
ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰፊ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ተደርጎ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩበት ቢሆንም፤ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት እንዳልተቻለ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአሁኑ ወቅት በማዕድን ዘርፉ 70 ፈቃድ የወሰዱና 134 በፍለጋ ላይ የተሠማሩ ባለፈቃዶች አሉ። ለ3286 የክልል ባሕላዊ ወርቅ አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ ለሁለት የውጭ ባለሀብት እና ለሦስት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ተሠማርተዋል፡፡
በዘርፉ በኩባንያዎችና በኢንዱስትሪዎች አማካኝነት ለ145 ዜጎች እንዲሁም በባሕላዊ ወርቅ አምራች ኢንተርፕራይዞች ለ94 ሺህ 997 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። እንደ ድንጋይ ከሰል ባሉ የማዕድን ልማት ጥሩ አፈጻጸም እየታየ ሲሆን፤ በዚህም ሀገሪቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያወጣች ከውጭ ታስመጣ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በዚህ ልማት ማስቀረት ችላለች።
በማዕድን ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ አምራቾች ያሉ ቢሆንም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ከዘርፉ ለማግኘት የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዳልቻለም ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡት የማዕድን ምርቶች የታሰበውን ያህል ገቢ ማግኘት እንዳልተቻለ ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ በስድስት ወራት ለውጪ ገበያ ከቀረቡ የማዕድን ምርቶች 243 ነጥብ 24 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ 142 ነጥብ 978 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። አፈጻጸሙም የእቅዱን 58 ነጥብ 7 በመቶ ነው። ለውጭ ገበያ የተላኩት ማዕድናት የወርቅ፣ የታንታለም፣ የሊቲየም ኦር፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ 10 ክልሎች የወርቅ ማዕድን ሥራዎች በባሕላዊ መንገድ ይመረታሉ። ስድስት ወራት በኩባንያዎች ደረጃ ተመርቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት የታቀደው የወርቅ ምርት መጠን 2499 ነጥብ ዘጠኝ ኪሎግራም ሲሆን፤ 1445 ኪሎግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት ተችሏል። በተመሳሳይ በባሕላዊ የወርቅ አምራቾች 1288 ኪሎግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ፤ 431 ኪሎግራም የወርቅ ምርት ነው ለብሔራዊ ባንክ የገባው።
በባለፉት ስድስት ወራት ከወርቅ ምርት 227 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ 134 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህ አፈጻጸም ከባለፉት ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዚህ ስድስት ወራት አፈጻጸም ብልጫ አሳይቷል፡፡
ባሕላዊ የወርቅ አምራቾች ያመረቱት የወርቅ ምርት የኩባንያ የወርቅ ምርት ድርሻ አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ 77 በመቶ ያህሉ ወርቅ በኩባንያ ደረጃ እንዲሁም 23 በመቶ ያህሉ በባሕላዊ አምራቾች የተመረተ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሚኒስትሩ፤ በስድስት ወራት በወርቅ ምርት ለማግኘት የታቀደውን ገቢ ለማግኘት ያልተቻለበት ዋንኛ ምክንያት በክልል ደረጃ ያሉ አነስተኛ ፈቃድ ባላቸው አምራቾች በኩል ክፍተት መኖሩን አንስተዋል። ወርቅ ማምረት ላይ ምርት ችግር ሳይኖር ምርቱ እያለ ዋንኛ ችግር የሆነው ምርቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ የማስገባት ችግር እንደሆነ አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በፖታሽ ማዕድንም ኢትዮጵያ በደናክል ተፋሰስ ከ26 ቢሊዮን ቶን በላይ የፖታሽ ሃብት (resource) እና 540 ሚሊዮን ቶን የሚገመት የፖታሽ ክምችት (reserve) ከዓለም ግዙፉ ያልለማ የፖታሽ ክምችት ያላት አገር ናት ። ይህ ፖታሽ ለማዳበሪያና ለውጭ ገበያ (ለኤክስፖርት) የሚውል ነው። ይህን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ ፡፡
በድንጋይ ከሰል ማዕድንም ከ600 ሚሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ሃብት መኖሩን የሚናገሩት ሚኒስትሩ፤ አሁናዊ የሀገር ውስጥ ፍላጎት በዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን እንደሚጠጋ ያመላክታሉ። ከውጭ የሚገባው የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ120 በላይ ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ ማዳን መቻሉን አመላክተዋል።
በድንጋይ ከሰል ምርት ለሀገር ውስጥ ምርት አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችል ብዙ ክምችት አለ። ሆኖም ግን የድንጋይ ከሰል የራሱ የሆነ የጥራት መለኪያ ስላለው ከአመራረቱ ጋር ተያይዞ የጥራቱ ችግሮች ይነሳሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚፈልጓቸውን የጥራት መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ስለሚፈልጉ ይህንን የሚያሟላ ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ምርት ማምረት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
የድንጋይ ከሰል ጥራትን ለመጨመር የድንጋይ ከሰሉን የማጠብ ሥራ የሚሠራ ፋብሪካ እንደሚፈልግ ገልጸው፤ እንደ ሀገር እስካሁን ባለው ሁኔታ እሴት ጨምሮ የድንጋይ ከሰልን እያጠበ እያቀረበ ያለው አንድ ፋብሪካ ብቻ መሆኑን ይጠቁማሉ። በመሆኑም በሁሉም አቅጣጫ ያለው የሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትም በሚገባ በማወቅ ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ማምረት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በተጨማሪም እነዚህ እሴት ጨምረው የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችንና ኢንቨስተሮችን ማበረታታት ይገባል። አሁን ላይ የድንጋይ ከሰል የሚያመርቱ አካላት እሴት እየጨመሩ ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት የአቅርቦት ሠንሠለት ማስተሳሰር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከተቋማት፣ ከማኅበራት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የሚገልጹት፡፡
አሁን በሀገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል እሴት በመጨመር ጥራቱ በጠበቀ መንገድ ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን በቅርብ በማሳካት የድንጋይ ከሰል ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻል መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም እሴት በመጨመር የሚያመርቱ (ፕሮሰስ) የሚያደርጉ ኢንቪስተሮች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የሲሚንቶ ክምችት ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሲሚንቶ ምርት ባለፋት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የምርት እጥረት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህ ዋንኛ ምክንያት በአገሪቱ ላይ ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች ሥራ በማቆማቸው እንደሆነ አመላክተዋል።
‹‹አሁን ላይ ግን ቀደም ሲል ማምረት ያቆሙ ፋብሪካዎች ወደ ምርት እየመጡ፤ አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት እየገቡ መሆናቸው ሲሚንቶ ምርት ተስፋ ያለው መሆኑን ያሳያል። አዳዲሶቹ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ደግሞ የተሻለ ማምረት ይቻላል። ለእነዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያስፈልገውን የድንጋይ ከሰል በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ የመተካቱ ሥራ መጠናከር ይኖርበታል።
በተያዘው በጀት ዓመት ሥራ ላይ ያሉት 11 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ፋብሪካዎች በዓመት 14 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል። ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ሲሚንቶ ፍላጎት 36 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ሦስት ነጥብ 51 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ተመርቷል። በዚህም የእቅዱን 83 በመቶ መፈጸም ተችሏል›› ነው ያሉት፡፡
በአገሪቱ አስተማማኝ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት ዋንኛው አስፈላጊ የሆነው ብረት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ የሚያስፈልገው የብረት ማዕድን ሀብት እንዳለም ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት ‹‹አሁን ላይ የለሙት የብረት ምርቶች ብዙ አይደሉም፤ ገና ብዙ የሚቀራቸው ነገር በመኖሩ አልተጀመረም። አሁንም ብረት ላይ ትኩረት ተደርጐ እየተሠራ ሲሆን፤ ብረት ለተወሰነ ጊዜ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱ አይቀርም›› ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የማዕድን ኢንዱስትሪ ምርትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ 143 ሺህ 458 ቶን ብረት፣ 273 ሺህ የድንጋይ ከሰል መገኘቱን አስታውቀዋል። የግንባታ ግብዓት እጥረቶችን ለመፍታት ምርት ያቆሙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግራናይትና በማርብል ማዕድናት ምርት ጋር ተያይዞ ተስፋ ያለው ነገር እንዳለ ጠቅሰው፤ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ሲስተካከል ምርት ማምረት እንደሚቻል አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ማዕድን ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም ያሉት ሚኒስትሩ ፤ ሕገ-ወጥ ንግድ፣ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እንዲሁም ስለማዕድን ሃብት ያለው የግንዛቤ ማነስ፣ በቂ የሰው ኃይል እጥረት፣ በቂ የልማት በጀትና ቴክኖሎጂ አለመኖሩ ከማዕድን ሀብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳትችል አድርጓታል ሲሉ አስረድተዋል።
‹‹ማዕድን ሀብቱ በራሱ የሚያመጣቸው ተግዳሮቶች አሉ። የፀጥታ ችግር በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ያለው ይሄ ሀብት ባለበት አካባቢ ነው። የማዕድን ሀብት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀብት በመሆኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በጋራ ተጠቃሚ በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚን መገንባት ያስፈልጋል። ይህ ሀብት በሕገወጥ መንገድ ለሕገወጦች ሲሳይ መሆን የሌለበት ነውና ጥንቃቄ ያስፈልጋል›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ አንዳንድ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ለማዕድን ሥራ አዳጋች ቢሆንም በተቻለ አቅም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢንቪስተሮች መጥተው በኢንቨስትመንቱ ላይ እንዲሠማሩ ሠላም መኖር እንዳለበት ሲያስረዱ፤ የማዕድን ኢንሸስትመንት ረጅም ጊዜን የሚፈልግ ሲሆን፤ ለአብነትም ወርቅ ለመፈለግ ብቻ አስር ዓመታት ሊፈጅ ይችላል። ለማምረት ደግሞ እንዲሁ ሌላ ሃያ እና ሠላሳ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። ሲሚንቶ እና ነዳጅ ለማግኘትም ሆነ ለማምረት እንደዚሁ ረጅም ጊዜ ያስፈልጋል በዚሁ ሁሉ ጊዜም ሠላም ሊኖር ይገባል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ እንደሀገር የማዕድን ዘርፉን የሚመራ ካውንስል ተቋቁሟል። ካውንሱሉ ብዙ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት፣ የአካባቢን ፀጥታ ሁኔታ የሚከታተል እና ዘርፉ የሚመራበት ሁኔታ የሚቆጣጠር ነው። ሕገወጥነት ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የማዕድን ካውንስሉ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ሲሆን፤ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች እየፈተሸ ይሠራል።
‹‹ማዕድን ሲባል በተለምዶ የሚታወቀው ከወርቅ ያለፈ አይደለም። ማዕድን ወርቅ ብቻ አይደለም በርካታ ማዕድናት አሉ። ወርቅም ቢሆን አሁን ላይ እየተመረተ ያለው በባሕላዊ መንገድ ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በባሕላዊ መንገድ ወርቅ የአመራረት ሂደት በራሱ ጤነኛ ስላልሆነ ከፈቃድ አሰጣጡ ጀምሮ ለብዙ ሕገወጥ ነገሮች ተጋላጭ መሆኑን ይናገራሉ። ብዙ ሕገወጥ አካላት ያሉበት በመሆኑ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጣ በማድረግ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በወርቅ ምርት ለመሠማራት የሚፈልጉ ፋብሪካዎች ስላሉ እነዚህን በመደገፍ የሚጠበቀውን የወርቅ ምርት ማግኘት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ በየደረጃው ያሉ ፍቃድ የሚሰጡ አካላት ኃላፊነት ስላለባቸው ተጠያቂነት የሚያሰፈን ሥርዓትን መከተል ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዘርፉ ሙያዊ ሥነምግባር፣ ልምምድ፣ ኢንቨስትመንት እና ተከታታይነት ያለው ሥራን የሚፈልግ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አሁንም የማዕድን ምርቶች በተለያዩ ደረጃዎች ቢመረትም ምርት ወደሚፈለገው አገልግሎት እየዋለ የታለመለትን ግብ እየመታ አይደለም ይላሉ። ባለፈው ዓመት በማዕድን ሕገወጥነት የተሳተፉ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ መሻሻሎችና ለውጦች መኖራቸውን አመላክተዋል። ዘርፉ የአቅም ግንባታና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ትብብር የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል ።
‹‹ኮንትሮባንድ በሁሉም ዘርፍ ያለ የሀገር ችግር ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ወርቅ እና ማንኛውንም አይነት ማዕድናትን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ማውጣት ብዙ ከባድ አለመሆኑን አንስተዋል። ኮንትሮባንድ በመከላከል ሕገወጥነት የመቀነስ ሥራ በማዕድን ሚኒስቴር ብቻ የሚሠራ ሳይሆን እንደሀገር ብዙ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም