
አዲስ አበባ፦ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በዓለም ሊኖራት የሚገባውን ቦታ እንደሚያሳይ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የአውደ ርዕዩ እያንዳንዱ ክፍል ታሪካዊ መሠረት አለው። በዚህም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ ለመዳሰስ ተሞክሯል። አምስት በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአንድ አውደ ርዕይ መሸፈን አይቻልም። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ክፍል በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችና መፋጠጦች አሉ።
አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የነበራትን ሚና፣ የገጠማትን ፈተናዎችና የታሪክ መሠረቶችን ዳሷል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ሊኖራት የሚገባውን ቦታ የሚያሳይ ነው ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ የአዲሱ ዘመን ዲፕሎማሲ ወጣቶችን የሚያሳትፍና በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር አውደ ርዕዩ ለቀጣዩ ትውልድ የዲፕሎማሲ ሥራ መሠረት የጣለ ነው ብለዋል።
ዲፕሎማሲ የማይነካው መስክ እንደሌለ ከአውደ ርዕዩ መረዳት ይቻላል። ሌላው የዲፕሎማሲ ሥራ በአንድ ወገን ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ከሌሎች ጋር በትብብርና በአጋርነት የሚሠራ ነው ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ በአውደ ርዕዩ የቀረቡ እያንዳንዱ ሥራዎችን የሚጋሩ ሀገራት አሉ። ይህንን የተመለከቱ አምባሳደሮች አውደ ርዕዩ ድንቅ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደር እሸቴ ገለፃ፤ ዲፕሎማሲ ማለት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር መሥራት ማለት ነው። በዓለም ላይ ሁሉም የድርሻው የሆነውን እና ያልሆነውን ለመውሰድ እንደሚጥር መረዳትና ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በተፈጥሮ፣ በሃይማኖት፣ በሀብት ቅርምት እንዲሁም በታላላቅ ኃይሎች ትርምስ ምክንያት ብዙ ፍላጎት ያለበት ነው።
በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። አውደ ርዕዩ ደግሞ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዴት ማስከበር እንደሚገባና ከሌሎች ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት ለምን እንደሚያስፈልግ የመነሻ ሃሳብ ይሆናል። በርካታ ሰዎችንም የሚያነሳሳ እና ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል አምባሳደር እሸቴ።
አውደ ርዕዩ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ መነሻ፣ የአሁኑን ዘመን ተግዳሮትና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን እና በቀጣይ የዲፕሎማሲ ዘመን የሚያጋጥመውን ፈተና የሚያሳይ ነው ያሉት አምባሳደር እሸቴ፤ አውደ ርዕዩን የሚጎበኙ ዜጎች በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።
አውደ ርዕዩ ወጣቶች እንዲነሳሱ እና በመጪው ዘመን ለሀገራቸው ጥቅም፣ ነፃነትና እኩልነት እንዲሰሩ ያደርጋል። ለዚህም ጠንካራ ዲፕሎማሲና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም