
አዲስ አበባ፡- የአኩሪ አተር ምርትን እና የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳዳግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የአኩሪ አተር አምራቾች፣ አዘጋጆችና ላኪዎችን አቅም የሚያጎለበት ፕሮጀክት ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡
የማህበሩ የቦርድ አመራር ሊቀመንበር አቶ ሲሳይ አስማረ በፕሮግራም ማስጀመሪያው ወቅት እንደገለጹት፤ የአኩሪ አተር ምርትን በማሳደግ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት ይሠራል፡፡
ኢትዮጵያ ለአኩሪ አተር ምርት የሚሆን ሰፊ መሬት እና ምቹ የአየር ንብረት አላት ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የአምራቾችን፣ የአዘጋጆችን እና የላኪዎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሰንሰለት ውጤታማ በማድረግ ሀገሪቱ ከአኩሪ አተር ምርት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንድትሆን ለባለድርሻ አካላት ቴክኒካል ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ለአኩሪ አተር አምራቾች ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሌሎች ግብአቶች በወቅቱ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከግብአት አቅራቢዎች ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ 60 በመቶ የሚሆነው የምግብ ዘይት የሚገኘው ከአኩሪ አተር ነው ያሉት አቶ ሲሳይ፤ በዚህም በኢትዮጵያ ያለውን የምርት መጠን በመጨመር የሀገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላትና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) በተገኘ የ12 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የአኩሪ አተር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የገበያ ሰንሰለትን ለማስፋፋት የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት እንደሚተገበር ገልጸው፤ የአኩሪ አተር አምራቾችን፣ አዘጋጆችን እና ላኪዎችን አቅም በማሳደግ የምርት መጠንና የገበያ ሰንሰለት ለመጨመር ያግዛል ብለዋል፡፡
ጂአይዜድ የሽንኩርት፣ የአቮካዶ እና አኩሪ አተር ምርቶችን ወደ ወጭ ለመላክ እና የሀገር ውስጥ ገበያውን ለማረጋጋት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር የአኩሪ አተር ምርት ላይ እንዲሰራ የተሰጠው ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን ውጤታማ እና ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ አመላክተዋል፡፡
የጂአይዜድ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሚሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የአኩሪ አተር ምርታማነትን የሚያሳድግ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በቀጣይም ለግሉ ዘርፍ ፋይናንሻልና ቴክኒካል ድጋፍ ከማድረግ ባለፈም የሀገሪቱን የምርት መጠን በማሳደግ እሴት ጨምሮ ወደውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም